Saturday, 06 June 2015 14:33

የአለማችን ሮቦቶች ውድድር በአሜሪካ እየተካሄደ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 አሸናፊው ሮቦት 3.5 ሚሊዮን ዶላር ይሸለማል

    በሮቦቲክስ መስክ የተሰማሩ 24 የአለማችን ኩባንያዎችና የምርምር ቡድኖች ያመረቷቸው ሮቦቶች የተሳተፉበትና 3.5 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት የሚያስገኘው የዳርፓ የሮቦቶች ውድድር ትናንትና ዛሬ በአሜሪካ እየተካሄደ እንደሚገኝ ቢቢሲ ዘገበ፡፡
በአሜሪካው መከላከያ ቢሮ ፔንታጎን ድጋፍ በሎሳንጀለስ አቅራቢያ በመከናወን ላይ በሚገኘው በዚህ ውድድር የሚሳተፉ ሮቦቶች አደጋን የመቋቋም ብቃታቸውን የሚያሳዩ አስቸጋሪ ተግባራትን እንዲፈጽሙ በማድረግ አሸናፊው ይለያል ተብሏል፡፡
ሮቦቶቹ እንዲያከናውኗቸው ከተመደቡላቸው ስምንት ተግባራት መካከል፡- መኪና መንዳት፣ በር መክፈትና ማለፍ፣ ግድግዳ መብሳት፣ በደረጃዎች ላይ መወጣጣት የሚገኙበት ሲሆን፣ በውድድሩ ላይ የሚገለጽ ሌላ ለየት ያለ ተልዕኮም እንዲፈጽሙ ይደረጋል፡፡
እያንዳንዱ ሮቦት እነዚህን ስምንት ተግባራት ለማከናወን ሁለት ሙከራዎች የሚሰጡት ሲሆን ፈጥኖ ተግባራቱን በተሳካ ሁኔታ ማከናወንም ለአሸናፊነት በመስፈርትነት ከተቀመጡት ነጥቦች አንዱ እንደሆነ ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የውድድሩ አዘጋጅ የሆኑት ዶክተር ጊል ፕራት እንዳሉት፣ የዘንድሮው ውድድር ከአምናው ጋር ሲነጻጸር በአስር እጥፍ አስቸጋሪ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የተለያዩ የአለም አገራት የሮቦቲክስ ዘርፍ ኩባንያዎችና የምርምር ቡድኖች ለውድድሩ የቀረቡ ቢሆንም፣ የመጀመሪያውን ማጣሪያ አልፈው ለፍጻሜ የደረሱት፣ 24 መሆናቸውንና ከእነዚህም መካከል የአሜሪካ፣ የደቡብ ኮርያ፣ የጃፓን፣ የጀርመንና የጣሊያን ኩባንያዎች እንደሚገኙበት ዘገባው አመልክቷል፡፡  

Read 1906 times