Saturday, 06 June 2015 14:35

የብሩንዲ ምርጫ በድጋሚ ተራዘመ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የብሩንዲው ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ ህገመንግስቱ ከሚፈቅድላቸው ውጪ ለሶስተኛ ዙር በምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸውን ተከትሎ በአገሪቱ የተቀሰቀሰው ግጭት በዚህ ሳምንትም ያገረሸበት ሲሆን  የአገሪቱ የፓርላማና ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለሶስተኛ ጊዜ ዳግም መራዘሙን ቢቢሲ ዘገበ፡፡ በአገሪቱ ያለው ሁኔታ ሰላማዊ ምርጫን ለማከናወን አያስችልም በሚል ምርጫውን እንዲያራዝሙ ከአፍሪካውያንና ምእራባውያን መንግስታት ጫና ሲደረግባቸው የቆዩት ፕሬዚዳንቱ፣ ምርጫው እንዲራዘምና በመጪው ነሃሴ ወር መጨረሻ እንዲካሄድ መወሰናቸውን ከትናንት በስቲያ አስታውቀዋል፡፡
ከአገሪቱ ዋነኛ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች አንዱ የሆኑት አጋቶን ሩዋሳ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፣ ፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ አምባገነን መሪ ስለሆኑ ከስልጣናቸው መውረድ አለባቸው ያሉ ሲሆን፣ የጸጥታ ሁኔታው ሳይሻሻል፣ ገለልተኛ የምርጫ ኮሚሽን ሳይመረጥና የግል ሚዲያው ላይ የሚደረገው ጫና ሳያበቃ በአገሪቱ ምርጫ ሊከናወን አይችልም ብለዋል፡፡ የብሩንዲ ምርጫ ከዚህ ቀደም እንዲራዘም በተወሰነው መሰረት፣ የፓርላማ ምርጫው ትናንት፣ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ደግሞ በሰኔ ወር መጨረሻ ሊካሄድ ቀን ተቆርጦ ነበር፡፡
ፕሬዚዳንቱ በምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸውን ማስታወቃቸውን ተከትሎ ያልተሳካ መፈንቅለ መንግስት መካሄዱና በአገሪቱ በተቀሰቀሰው ግጭት ከ20 በላይ ዜጎች መሞታቸውን፣ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ብሩንዲያውያንም ወደ ጎረቤት አገራት መሰደዳቸውን ባለፈው ሳምንት መዘገባችን ይታወሳል፡፡

Read 1633 times