Saturday, 06 June 2015 14:35

የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ጦራቸው በተጠንቀቅ እንዲቆም አሳሰቡ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ሩስያ መጠነ ሰፊ ወረራ ልታደርግብን ትችላለች ብለዋል

   በሩስያ በሚደገፉት የዩክሬን አማጽያን እና በመንግስት ጦር መካከል ባለፈው ረቡዕ የከፋ ግጭት መከሰቱን ተከትሎ፣ ፕሬዚደንት ፔትሮ ፖሮሼንኮ የጦር ሃይላቸው ከሩስያ ሊቃጣ ከሚችል የተደራጀ መጠነ ሰፊ ወረራ አገሪቱን ለመከላከል በተጠንቀቅ እንዲቆም ማሳሰባቸውን ሮይተርስ ዘገበ።
የሩስያ ወታደሮች ከዩክሬን አማጽያን ጋር በመተባበር በምስራቃዊ የአገሪቱ ክፍል ጥቃት እየፈጸሙ ነው ሲሉ ከትናንት በስቲያ ለአገሪቱ የፓርላማ አባላት የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ ጦራቸው ከአማጽያኑ የሚቃጣበትን ጥቃትና ከሩስያ ጋር በሚያዋስኗት ሁሉም የድንበር አካባቢዎች ሊፈጸምበት ከሚችለው ሰፊ ወረራ አገሪቱን ለመከላከል በበቂ ሁኔታ መዘጋጀት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
የዩክሬን አማጽያን ባለፈው ረቡዕ ማሪንካ ከተማን ለመቆጣጠር ባደረጉት ሙከራ፣ ከመንግስት ጦር ጋር በከባድ የጦር መሳሪያዎች የታገዘ አስከፊ ግጭት መደረጉን የጠቆመው ዘገባው፣ ፕሬዚዳንቱም ግጭቱ ሩስያና አማጽያኑ በአገሪቱ ላይ ቀጣይ የተደራጀ ወታደራዊ ጥቃት እንደሚሰነዘር የሚያሳይ ነው ማለታቸውን ገልጧል፡፡
ዩክሬንና የኔቶ አባል አገራት የሆኑ አጋሮቿ፣ በአገሪቱ ምስራቃዊ አካባቢዎች የሚገኙ ሁለት ግዛቶችን ከፊል አካባቢዎች ይዘው ለሚገኙት አማጽያን የጦር መሳሪያዎችንና ወታደሮችን በመላክ ጥቃት እየፈጸመች ነው ሲሉ ሩስያን በተደጋጋሚ ሲከሱ መቆየታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ባለፈው የካቲት ወር ላይ የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረስም፣ መጠነኛ ግጭቶች ሲከሰቱ መቆየታቸውንና፣ ባለፈው ረቡዕም አስከፊ የተባለው ግጭት መከሰቱን ገልጧል፡፡ ምዕራባውያን አገራት ሩስያ በሰላም ስምምነቱ ውስጥ የተካተቱ ሃላፊነቶቿን አልተወጣችም ሲሉ የተቹ ሲሆን፣ ወታደሮቿን ከዩክሬን ግዛት ማስወጣትና ለአማጽያኑ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ማድረጓን ማቆም አለባት ማለታቸውን ዘገባው አስረድቷል፡፡
ሩስያ በበኩሏ፤ ግጭቱን እንደገና የቆሰቆሰችው ዩክሬን ናት፣ ይህንንም ያደረገችው በቅርቡ በሩስያ ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ይጣል አይጣል የሚለውን ይወስናል ተብሎ በሚጠበቀው የአውሮፓ ህብረት ላይ ጫና ለማሳደር በማሰብ ነው ብላለች፡፡
ፕሬዚዳንት ፖሮሼንኮ በአሁኑ ወቅት 9ሺህ ያህል የሩስያ ወታደሮች ድንበር ጥሰው ገብተው በግዛታችን ወታደራዊ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው ቢሉም፣ ሩስያ በበኩሏ መሰረተቢስ ውንጀላ ነው ስትል የፕሬዚዳንቱን ንግግር ማጣጣሏን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከአጠቃላይ አገራዊ ምርቷ 5 በመቶውን ለወታደራዊ በጀት የመደበችው ዩክሬን፣ በቀጣዩ አመትም በወታደራዊ በጀቷ ላይ ጭማሪ ልታደርግ እንደምትችል ፕሬዚዳንት ፖሮሼንኮ ለፓርላማ አባላቱ ባደረጉት ንግግር መግለጻቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Read 2607 times