Saturday, 28 January 2012 13:12

”ካዛንቺስ ቶታሉ ጋር ጠብቂኝ”

Written by  ዮናስ ኪዳኔ
Rate this item
(0 votes)

ትላንተና ነው፡፡

ጓደኛዬ፣ እኔና ሁለታችን ከሰዓቱን የት ማሳለፍ እንዳለብን እየተከራከርን ነበር፡፡ ከእልህ አስጨራሽ ውይይት አዘል ንትርክ በኋላ ስምምነት ላይ ደረስን፡፡ ፊልም እያየን ለማሳለፍ፡፡ ፊልም በማየት ሙሉ ከሰአቱን ማሳለፍ ስለማይቻል ከሲኒማ ቤት ያመለጡ ሰአታት ካሉን ሁለታችንም መፅሀፍት ስለያዝን በማንበብ ለማሳለፍ አቀድን፡፡ጓደኛዬ ጥበቡ ሁለት መፅሀፍቶችን ይዟል፡፡ ‘ዘ ሲክሬት’ እና አሁን የማላስታውሰውን ነገር ‘የማድረግ ጥበብ’ የምትል መፅሃፍ፡፡ ምን የማድረግ ጥበብ ነበር የምትለው? ብቻ ‘ከሰአትን ሳይደበሩ የማሳለፍ ጥበብ’ እንዳልሆነ እርግጠኛ ነኝ፡፡

እኔና ጓደኛዬ አንዳንዴ ካልሆነ በቀር በመጽሐፍት ምርጫ አንመሳሰልም፡፡ እኔ በርዕሳቸው ላይ “ጥበብ”፣ “ሚስጥር” የሚሉ ቃላት ያሏቸው መጽሐፍት ምርጫዎቼ አይደሉም፡፡ ጓደኛዬ ግን “ጥበብ” ተኮር መፅሐፍትን በማንበብ ነው ጊዜውን የሚያጣብበው፡፡ እኔ በበኩሌ creative non – Fiction ወይም በፈጠራ የተዋዙ ኢ - ልቦለድ ጽሑፎች ምርጫዎቼ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው “ፒያሳ ማህሙድ ጋ ጠብቂኝ” የተሰኘችውን የጊዜው ተወዳጅ መጽሐፍ የያዝኩት፡፡ ይቺን መጽሐፍ ካነበብኩ በኋላ “ካዛንቺስ ቶታሉ ጋ ጠብቂኝ” በሚል ርዕስ መጽሐፍ የማሳተም አስደናቂ ሀሳብ ተከሰተልኝ፡፡ ሃሳቤን ለጥበቡና ለሌሎችም ጓደኞቼና ጓደኛ መሰል ጀለሶቼ/ምቀኞቼን ሳማክራቸው “ርዕሱ የተሰረቀ ነው” በማለት ወሽመጤን፣ ቅስሜንና ሌሎች በስም እንጂ በአድራሻ የማላውቃቸውን የሰውነት አካሎቼን የሚቆረጡትን ቆርጠው፣ የሚሰበሩትን ሰበሯቸው፡፡ እስከመቼ ይሆን ሀገራችን ውስጥ የፈጠራ ሰዎችን የማናበረታታው? እስቲ እናንተው ፍረዱኝ፡፡ “ፒያሳ ማህሙድ ጋ” እና “ካዛንቺስ ቶታሉ ጋ” ምን አገናኛቸው? ሌላው ቀርቶ ከፒያሳ ማህሙድ ጋ ተነስተን ካዛንቺስ ቶታሉ ጋ ለመድረስ 2 ብር ከ80 ለታክሲ መክፈል እንዳለብን ዘንግተነው ነውን? ጓደኞቼ ግን ቢያንስ 2 ከ 80 ለሚያወጣው የፈጠራ ስራዬ የ80 ሳንቲም ዋጋ እንኳን አልሰጡትም፡፡ ይልቁንስ “ርዕስ ሰብሳቢ” ብለው ቅጽል ስም አወጡልኝ፡፡ ልብ በሉ እንግዲህ ይቺን ቅጽል ስም የሰጡኝ ርዕስ ኮርጀሃል ብለው ስላሰቡ ነው፡፡ እኔ ግን “ርዕስ ሰብሳቢ” ብላችሁ ቅጽል ስም የሰጣችሁኝ ከገናናዋ “ኪራይ ሰብሳቢ” ኮርጃችሁ ነው ብዬ አልሞገትኳቸውም፡፡ ምክንያቱም “ርዕስ” እና “ኪራይ” በጣም የተራራቁ ቃላት ናቸውና፡፡ ይልቁንስ ይበል የሚያሰኝ የፈጠራ ቅጽል ስም ነው ብዬ አበረታታኋቸው፡፡

ይህንን ሁሉ የሚያደርገው ማን እንደሆነ አላጣሁትም፡፡ ጥበቡ ነው፡፡ ትክክለኛ ስሙ አይደለም፡፡ የተለያዩ ነገሮችን የማድረግ ጥበብን ማዕከል አድርገው የሚንቀሳቀሱ መጽሐፍትን በተደጋጋሚ የማንበብ ጥበቡን አይቼ ያወጣሁለት ስም እንጂ፡፡

ለምሳሌ ባለፈው ሳምንት “ህይወትን በስኬት የመምራት ጥበብ” የሚል ርዕስ ያለውን መጽሐፍ ጥበብ በጐደለው ሁኔታ ሲያነብ አየሁት፡፡ ለሃያ ስንተኛ ጊዜ መሰላችሁ ያነበበው! እኔም በጣም አዘንኩ፡፡ ጓደኛዬ መጽሐፉን እንደ ውዳሴ ማርያም ቢደጋግመውም አንድም ቀን ህይወቱና ስኬቱ ተገናኝተው አያውቁም፡፡ ይሄን የጓደኛዬን ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት አንድ መጽሐፍ ለማሳተም ቆርጬ ተነሳሁ፡፡ ርዕሱም “ህይወትን በስኬት የመምራት ጥበብ የተሰኘውን መጽሐፍ በተሳካ ሁናቴ በህይወታችን ውስጥ ተግባራዊ የማድረግ ጥበብ” ይሰኛል፡፡ ርዕሱ ትንሽ እንደረዘመ ይገባኛል ነገር ግን ጓደኛዬ ስኬታማ ለመሆን ከፈጃቸው ጊዜያት አይረዝምም፡፡ ሀሳቤን ሳማክረው አሁንም “ርዕስ ኮርጀሃል” አለኝ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ጥምድ አድርጐ ያዘኝ - ጓደኛዬ ጥበቡ፡፡

እኔና ጓደኛዬ ጥበቡ ለፊልምና ለመጽሐፍት ጥልቅ ፍቅር እንዳለን ልታስቡ ትችላላችሁ፡፡ እውነቱ ግን እንደሱ አይደለም፡፡ ለኔና ለጥበቡ ፊልምና መጽሐፍት ምሽጐቻችን ናቸው፡፡ የኑሮ ውድነቱ ሊያደርስብን ከሚችለው ፈርጀ ብዙ ጥቃቶች ራሳችንን የምንከላከልባቸው ከቢሮክራሲ የፀዱ መሳሪያዎቻችን፡፡

እኔና የስራ አጥነት ባልደረባዬ ጥበቡ ሰሞኑን የጋራ ችግራችን የሆነውን ከሰዓት በኋላ የሚፈጠር ድብርት ከስሩ ለመንቀል ከተመድ እውቅና ውጪ የሆነ ጉባኤ አካሂደን ነበር፡፡ ጉባኤው በአመዛኙ ውጤታማ ነበር፡፡ ምክንያቱም የጋራ ችግራችንን ለመቅረፍ የሚያስችሉ የመፍትሔ ሃሳቦችን አመላካች ነበር፡፡ ጉባኤው ከዚህ በተጨማሪም የተጠቀሰውን ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ ፊልም መመልከትን፣ መጽሐፍት ማንበብን፣ እርስ በእርሳችን መነበብን፣ ሀሜትን፣ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ተከራክሮ የጋራ አቋም መያዝን፣ ፊትን ወደ ፈጣሪ መመለስንና ሌሎችንም ተዛማጅ ሀሳቦች በአማራጭነት አቅርቦ ተወያይቷል፡፡ በመጨረሻም ፊልም መመልከትና መጽሐፍት ማንበብ አማራጭ የሌላቸው መፍትሔዎች መሆናቸው ተደርሶበት ጉባኤያችን ተጠናቋል፡፡ ሀሳቦቹን ተግባራዊ ለማድረግም የሁለታችንን ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ የጋራ መግባባት ላይ ደርሰን እንደነበረም ሳልጠቅስ አላልፍም፡፡ ቤተሰባዊ የበጀት ድጐማ እንዳለ ሆኖ፡፡

ምን ይሄ ብቻ! ከዩኒቨርስቲ አንድ ላይ መመረቅና በስራ ማጣት መመሳሰላችን ረጅም እድሜ ያስቆጠረ የሁለትዮሽ ጓደኝነታችንን ያጠናከረልን ጓደኛሞቹ እኔና ጥበቡ ለኑሮ ውድነቱ ፍቱን መድሀኒትም ፈልስመናል፡፡ ለመድሀኒቱ መፈልሰም በመነሻነት የምንጠቅሰው በሁለታችንም ላይ ያስተዋልነውን ስለ ኑሮ ውድነቱ  አብዝቶ የማሰብ አባዜን ነው፡፡ እንዲህም አልን “ደስ የማይልን ነገር ስለምን በአእምሯችን እንዲመላለስ ፈቀድን?”

ይህቺን የጥልቅ ሳይንሳዊ እውቀት ማሳያ የሆነች አረፍተ ነገር በተናገርንባት ቅጽበት የኑሮ ውድነት ማስወገጃ መፍትሔው ተገለጠልን፡፡ መፍትሔውም የኑሮ ውድነትን መርሳት ይሰኛል - እስከነመፈጠሩ መርሳት!

የኑሮ ውድነትን እስከነመፈጠሩ (ፈጣሪ እንዳልፈጠረው ተስፋ እናደርጋለን) ከረሳነው በህይወታችን ጣልቃ እየገባ ሰላም ሊነሳን እንዴት ይቻለዋል? ህልውናው የተካደበት ነገር “ኧረ አለሁ” ብሎ የለመደውን ሰውን ሰላም የመንሳት ተግባሩን አጠናክሮ ሊቀጥል አይችልም፡፡ ቢልስ ማን ይሰማዋል? የለማ በቃ የለም!

ህገመንግስታችን በአንቀጽ 39 የሰጠንን መብት ለመጀመሪያ ጊዜ ለመጠቀም ያህል ከጓደኛዬ ጥበቡ ጋር መለስተኛ የሆነች መገንጠል በማድረግ፣ “የኑሮ ውድነትን የለህም ብሎ የመካድ ጥበብ” የተሰኘች አነስ ያለች ባለ 300 ገጽ መጽሐፍ ስለማሳትም ዝርዝር ሀሳቦችን ከዛ ማየት ይቻላል፡፡ የመጽሐፌን ርዕስ ጓደኛዬ በጣም ወዶልኛል፡፡ እናንተስ?

የትላንትናውን ውሏችንን መተረክ ልቀጥልና ቤተሰብ በመመስረቻችን በዚህ ጊዜ ከቤተሰብ ባገኘነው ድጐማ ተማምነን ከሰዓቱን በሲኒማ ቤት ለማሳለፍ ከመግባባት ላይ ደርሰን ስናበቃ “የት ሲኒማ ቤት” የሚለው ቀጣይ የውይይት አጀንዳችን ሆነ፡፡ በከተማችን ያሉ ሲኒማ ቤቶች ላይ ሀሳባዊ ዳሰሳ አደረግን፡፡ ሲኒማ ቤት ምርጫችን መሠረት ያደረገው አንድ ነገር ነበር፡፡ ይኸውም ሲኒማ ቤቱ ከኑሮ ውድነት ያለው ርቀት ነው፡፡ የኑሮ ውድነትን በምንም አይነት መንገድ ሊያስታውሱን ከሚችሉ ሁኔታዎች የፀዳ ሲኒማ ቤትን ለመምረጥ የኑሮ ውድነት መልክአ ምድራዊ አቀማመጡን ባዘለው አእምሯችን ኳተንን፡፡

ለምን ፒያሳ አንሄድም በማለት ድንቅ ሀሳቤን ለጥበቡ ነገርኩት፡፡ ከተራራማው እና ከፒያሳማው (አዲስ መልክአምድራዊ አቀማመጥ ነው) የአእምሮዬ ክፍል የመነጨ ሃሳብ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ጓደኛዬ ጥበቡ ግን “የፒያሳን ነባራዊና ታሪካዊ ሁኔታ ጠንቅቆ ካለማወቅ የመነጨ ተራ ሀሳብ” በማለት ሀሳቤን አጣጣለብኝ፡፡

ምክንያቱን ስጠይቀውም “ምክንያቱም ፒያሳ የአፄ ምኒሊክ ሀውልት አለ” አለኝ፡፡

“እሱማ ብቻቸውን አይደሉም፤ ፈረሳቸውም አለ” አልኩት ግራ ገብቶኝ፡፡ “የምኒልክን ሀውልት ካየን ደግሞ በዛ ዘመን ኑሮ ምን ያህል ርካሽ እንደነበር ማሰላሰላችን አይቀሬ ነው” አለኝ፡፡ ለማለት የፈለገው ገባኝ፡፡ በጓደኛዬ ሃሳብ በጣም ተመሰጥኩ፡፡ ለ30 ደቂቃ ያህል በአግራሞት ጭንቅላቴን አወዛወዝኩላት፡፡

በእውነቱ ይሄን የመሰለ ምጡቅ አእምሮ ማሰላሰል የነበረበት “ከሰዓቱን የት ሲኒማ ቤት ፊልም በማየት እናሳልፍ” አይነት ተራ ሀሳቦችን ሳይሆን “አባይ በረሃ ላይ ከተገነባው እጅግ ዘመናዊው የኢትዮጵያ የሳተላይት ማምጠቅያ ጣቢያ (ኢሳ) ለማምጠቅ ያሰብናት መንኮራኩር ሰው አልባ ትሁን ወይስ ከሰው ጋር መጣቂ” አይነት ምጡቅ ሀሳቦችን ነበር፡፡ ምን ዋጋ አለው፡፡

ጓደኛዬ የእምዬ ምኒልክን (አብዬ ለምን እንደማይባሉ አልገባኝም) ሀውልት ከኑሮ ውድነት ጋር ያዛመደበትን

መንገድ ስለወደድኩለት ለ30 ደቂቃ ያህል በተለያዩ ቃላት ያለኝን አድናቆት ገለጽኩለት፡፡ እሱም በበኩሉ ለአድናቆቴ ያለውን አድናቆት ከ50 ደቂቃ ላልበለጠ ጊዜ ውስጥ በአጭሩ ገለፀልኝ፡፡

አንዳችን ለአንዳችን ያለንን አድናቆት በዚህ መልኩ ከተገላለጽን በኋላ የምክክር አቅጣጫቻችንን ከሲኒማ ቤት ወደተገኘው ወደ ሌላ ቤት ስንቀይር የተሻለ እንደሆነ አሰብን፡፡ ይሄም የሆነው ህልውናውን የካድንበትን የኑሮ ውድነት በየሲኒማ ቤቶች ቅርንጫፍ መ/ቤቱን የከፈተ ይመስል ከሲኒማ ቤቶቹ ያለው ርቀት አጭር ሆኖ በማግኘታችን ነው፡፡

የምናውቃቸውን ቤቶች ሁሉ ዘረዘርን፡፡ መቃሚያ ቤት፣ መጠጥ ቤት፣ ጆተኒ ቤት፣ ፑል ቤት፣ የእግዜር ቤት፣ ምግብ ቤት፣ ጓደኛችን ቤት ዝርዝሩን ተመለከትነው፡፡ ከዝርዝሩ ውስጥ መስሪያ ቤት ባለመኖሩ ክፉኛ አዘንን፡፡ ስራ የምናገኘው መቼ ይሆን በማለትም አማረርን፡፡ አማርረን ስናበቃ ላለማረር የገባነውን ቃል በማፍረሳችን ለደቂቃዎች ተፀፀትን፡፡

የዘረዘርናቸውን ቤቶች መገምገም ጀመርን፡፡ መቃሚያ ቤት መሄድን ሁለታችንም በሙሉ ድምጽ ውድቅ አደረግን፡፡ ጫት አረንጓዴ ነው፡፡ አረንጓዴ እጽዋትን ማውደም ደግሞ የአየር ብክለትን ማባባስ መስሎ ስለታየን መቃሚያ ቤትን ከዝርዝሩ አወጣነው፡፡ በነፃ የምናገኛትን ብቸኛዋ ’ኦክስጅን ነፍሴን’ እንጣ እንዴ?

መጠጥ ቤት የስራ ችግርን የሚቀርፍ ቢሆን ኑሮ በሄድን ነበር፡፡ ነገር ግን መጠጥ ቤት የስሪያ ችግርን እንጂ የስራ ችግርን አያስወግድም፡፡ ታድያ ለምን እንሄዳለን፡፡ በዚያ ላይ ገንዘቡስ ከየት ይመጣል? ለካ አያቴ “ሆ” የምትለው ወዳ አይደም፡፡

በዚህ ከቀጠልን ሁሉንም ቤቶችን ሰርዘን ባዶ እጃችንን እንዳንቀር ስጋት ገባን፡፡ ግን ለምንድነው ከንፁህ አየር በቀር ዓለም ላይ ያሉ ነገሮች ሁሉ የሚከፈልባቸው?

አንድ የተባረከ ሃሳብ መጣልን፡፡ ለውሳኔ እንዲመቸን ከዘረዘርናቸው ቤቶች መሀል የማይከፍልባቸውን ለይተን አወጣናቸው፡፡ የእግዜር ቤት/ቤተክርስትያንና ጓደኛችን ቤት፡፡ ወደ ቤተክርስትያን ለመሄድ አልፈለግንም፡፡ ምክንያቱም ፈጣሪ “ሸክማችሁ የከበደ ወደ እኔ ኑ” አለ እንጂ “አማራጭ ያጣችሁ ወደ እኔ ኑ” አላለምና! ለነገሩ የሸክሙ አይነት ነው እንጂ እኛም “ጓደኛችን ቤት እንሂዳ” አልኩት ጥበቡን፡፡ 4 ኪሎ ፓርላማ ጋ ካለው ሰዓት ትንሽ አነስ የሚል ሰዓቱን ፊቴ ላይ ደቀነብኝ፡፡ 11፡20 ሆኗል፡፡

ተመስገን ነው፡፡ ያሰብነው ተሳክቷል፡፡ እንደሁልጊዜው፡፡ ከሰዓቱን ሳይደበሩ ለማሳለፍ “ከሰዓቱን የት እናሳልፍ” ለሚል ወሬ ራስን ከመጥመድ የተሻለ አማራጭ ከወዴት ይገኛል? በየቀኑ የምናደርገው ይህንኑ ነው፡፡ እኔ፣ ጓደኛዬ ጥበቡና ሁለታችን፡፡

 

 

 

 

Read 3444 times Last modified on Saturday, 28 January 2012 13:29