Saturday, 13 June 2015 14:38

የባቡር ፕሮጀክቶቹ ሰነድ ከቻይንኛ ወደ እንግሊዝኛ አለመተርጎሙ ችግር ፈጥሯል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(10 votes)

በሜኤሶ ደዋሌ የባቡር መስመር የእሳተ ጐሞራ ሥጋት አለ

   በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን እየተተገበሩ ያሉት የሃዲድ መስመር ዝርጋታዎች በውሉ መሰረት እየተከናወኑ መሆናቸውን ለማረጋገጥና የጥራት ደረጃቸውን ለመከታተል የሚያስፈልጉ ሰነዶችን ተቋራጮቹ ከቻይንኛ ወደ እንግሊዝኛ አስተርጉመው ለማቅረብ ባለመፈለጋቸው በሥራው ላይ እንቅፋት መፍጠሩ ተገለፀ፡፡ የፌደራል ዋናው ኦዲተር ባቀረበው ሪፖርት ላይ እንደተገለፀው፤ ሁሉም የባቡር ፕሮጀክቶች :-
የአዲስ አበባ ከተማ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት፣ የአዲስ አበባ ሰበታ ሜኤሶና የሜኤሶ ደዋሌ ፕሮጀክቶች የባቡር ግንባታዎች በቻይና የሃዲድ ግንባታ ደረጃ 2 እየተሰሩ መሆናቸው ቢገለጽም ተቋራጮቹ የጥራት ማረጋገጫ ማኑዋል፣ የላብራቶሪ ቁሳቁስ ማኑዋልና የዋና ዲዛይኑን ሰነድ የእንግሊዝኛ ትርጉም ለማቅረብ ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ኮርፖሬሽኑ አገራዊ የባቡር ምህንድስና እና የዲዛይን ኮዶች አዘጋጅቶ ተግባራዊ ማድረግ ሲገባው የተለያዩ የውጭ አገር የባቡር ስታንዳርዶችን የተከተሉ የዲዛይንና ግንባታ ስምምነቶችን መፈረሙም በሪፖርቱ ላይ ተጠቁሟል፡፡ በኮርፖሬሽኑ እየተተገበሩ ያሉት የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በ1999 ዓ.ም በትራንስፖርት ሚኒስቴር መሪነት አጥኚ ግብረሃይል ተቋቁሞ፣ አማራጭ የየብስ ትራንስፖርትን አስመልክቶ ያደረገው ጥናት እንጂ እያንዳንዱን ፕሮጀክት አስመልክቶ የተሰራ የፕሮጀክት ጥናት ሰነድ እንደሌለም ተገልጿል፡፡ በሜኤሶ ደዋሌ የባቡር መስመር ግንባታ ላይ ያለውን የእሳተ ገሞራ መከሰት ሁኔታ ሊገመግም የሚችል ጥናት አለመደረጉን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ኮርፖሬሽን እ.ኤ.አ በ2011 ከቻይናው ተቋራጭ (CCECC) ጋር ባደረገው ውል፣ ተቋራጩ ባቀረበው የቴክኒክ ፕሮፖዛል ውስጥ በምስራቅ አፍሪካ ያለው የእሳተ ጐሞራ በዓመት 0.5 ሳ.ሜ እንደሚሰነጠቅ ጠቁሞ ይህ ትልቅ ስምጥ ሸለቆ አሁንም
እየተሰነጠቀ መሆኑንና በዚህ ምክንያትም በላይኛው የምድር አካባቢ ያለው ክፍል ላይ ከፍተኛ እንቅስቃሴ መኖሩን፣ በተደጋጋሚ ፍንዳታዎችና የመሬት መሰንጠቆች እየተከሰቱ እንደሆነና ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ በዝርዝር የተጠናና የሚታወቅ ነገር ባለመኖሩ የእሳተ ጐሞራ መከሰት ሁኔታን አስተማማኝ ለማድረግ አለመቻሉን ኦዲት ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል፡፡ በኮርፖሬሽኑ እየተተገበሩ ባሉ ፕሮጀክቶች፣ የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ ተግባራዊ እየተደረገ አይደለም ያለው ሪፖርቱ፤ በአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ በርካታ የቱሪስት መተላለፊያ መንገዶችን ሳያስፈቅዱ መዝጋት፣ የፓርኩን ንፅህና አለመጠበቅ ያለፈቃድ መንገዶችን በፓርኩ ውስጥ እየቀደዱ ማውጣት የመሳሰሉ ችግሮች እንደሚከሰቱ ጠቁሞ በፕሮጀክቶቹ ላይ የሚሰሩ የውጪ አገር
ባለሙያዎች የዱር እንስሳትን ያለፈቃድ እያደኑ ለምግብነት እንደሚያውሉም ገልጿል፡፡  

Read 5481 times