Print this page
Saturday, 13 June 2015 15:01

ትኩረት የሚሻው የመድሃኒት አጠቃቀማችን

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(5 votes)

      የዓለም ጤና ድርጅት ለመድሃኒት በሰጠው ትርጓሜ መሰረት፤ መድሃኒቶች ለህመምተኞች በሚስማማ መልኩ ተዘጋጅተው በሽታዎችን ለማከም፣ ለማስወገድና ለመከላከል የምንጠቀምባቸውና በፋብሪካ ተመርተው የሚወጡ ኬሚካሎች ናቸው፡፡ መድሃኒቶች በተፈጥሮአዊ ባህርያቸው የጐንዮሽ ጉዳትን የሚያስከትሉ ሲሆን ይህ የጐንዮሽ ጉዳታቸው እንደ መድሃኒቶቹ ዓይነትና የአወሳሰድ መጠን ሊለያይ እንደሚችል ያመለክታል። በዚህ ምክንያትም መድሃኒቶችን ለህመምተኞች የሚያዙ ሃኪሞችም ሆኑ መድሃኒቶችን ለተጠቃሚው የሚያድሉ ሙያተኞች (ፋርማሲስቶች)፤ መድሃኒቶቹ በህመምተኛው ላይ የሚያስከትሉትን አላስፈላጊ ውጤትና የጐንዮሽ ጉዳቶቹን ለህመምተኛው በግልጽ ማሣወቅና፣ ህመምተኛው መድሃኒቱን ተገቢውን የአወሳሰድ ሥርዓት ተከትሎ መውሰድ እንደሚገባው በግልጽ መንገር ይኖርባቸዋል፡፡
በአገራችን ያለው የመድሃኒት አጠቃቀም በአብዛኛው ትክክለኛ ሥርዓትን ያልተከተለና ጤናማ አለመሆኑ ከመድሃኒቶቹ የጐንዮሽ ጉዳቶች ጋር ተዳምሮ በርካቶችን ለከፋ የጤና ችግር እንደሚያጋልጣቸው የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ሃኪም ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው ስለዚህ ጉዳይ ሲያስረዱ፤ “ህብረተሰቡ መድሃኒትን በአግባቡ የመጠቀም ልምድ የለውም፤ በአግባቡና በሥርዓቱ ያልተወሰዱ መድሃኒቶች የሚያስከትሉትን የከፋ የጤና ችግር በሚገባ ተረድቷል ማለትም አይቻልም፡፡ በመንግስትም ሆነ በግል የጤና ተቋማት ውስጥ ያሉ የጤና ባለሙያዎችም ሆኑ በመድሃኒት እደላ (ሽያጭ) ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ስለትክክለኛ የመድሃኒት አጠቃቀምና መድሃኒቶች ስለሚያስከትሉት የጐንዮሽ ጉዳት ለህመምተኞቹ በግልጽና በአግባቡ የማስረዳቱ ጉዳይ እጅግ ብዙ ይቀረዋል፡፡ አንዳንዴም በባለሙያዎቹ የጊዜ ማጣት ወይም በቂ ዕውቀት ካለመኖር የተነሳ ሊሆን ይችላል። ግን አንድ ህመምተኛ ስለሚወሰደው መድሃኒት ምንነት፣ መድሃኒቱ ስለሚያስከትለው የጐንዮሽ ጉዳት፣ አንዳንዴም ስለመድሃኒቱ ኬሚካላዊ ይዘት በባለሙያ በደንብ ሊነገረው ይገባል፡፡ መድሃኒቱን በተገቢው ሰዓትና መጠን መውሰዱ ከምን ሊያድነው እንደሚችል ማስረዳትም ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡
“አግባብ ያልሆነ የመድሃኒት አጠቃቀም ህይወትን ለአደጋ የሚያጋልጥና የከፋ የጤና ችግር የሚያስከትል መሆኑንም እንዲያውቅ መደረግ ይገባዋል” ብለዋል ሃኪሙ፡፡
መድሃኒቶች በተለያዩ አገራት ተሠርተው የተለያዩ ስምና ብራንዶች እየተሰጣቸው ወደ አገር ውስጥ እንደሚገቡ የሚናገሩት ዶክተሩ፤ በእነዚህ መድሃኒቶች የመፈወስ አቅም ላይ ተጠቃሚዎች በየጊዜው የሚያነሷቸው ጉዳዮች እንዳሉና በአብዛኞቹ እንደማይስማሙባቸው ጠቁመዋል፡፡
አንድ መድሃኒት የቤተሙከራ ዘመኑን ጨርሶ ጥቅም ላይ እንዲውል እስከሚደረግበት ጊዜ ድረስ ቢያንስ ከ10-15 ዓመታት እንደሚፈጅበት የሚናገሩት ሃኪሙ፤ የመድሃኒቱ ፈጣሪ ኩባንያ መድሃኒቶቹ ተመርተው ገበያ ላይ ከዋሉበት ጊዜ ጀምሮ ቢያንስ ለ15 ዓመታት የሚቆይ የባለቤትነት ማረጋገጫ ይሰጠዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥም ኩባንያው ከሌሎች የመድሃኒት አምራች ኩባንያዎች ጋር ተስማምቶ፣ መድሃኒቱን በራሳቸው የቅመማ ሂደት ደረጃውን ጠብቀው እንዲያመርቱ ፈቃድ ይሰጣቸዋል፡፡ በዚህ ፈቃድ መሰረትም ኩባንያዎቹ  የመድሃኒቱ ፈጣሪ ኩባንያ ከሚሰራው መድሃኒት ጋር ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን መድሃኒቶች እያመረቱ የራሳቸውን ስምና ብራንድ በመስጠት ገበያ ላይ ያውሉታል፡፡ በፈዋሽነታቸውም ሆነ በይዘታቸው ተመሳሳይ የሆኑ መድሃኒቶች በተለያዩ ስምና ብራንዶች ለተጠቃሚው ይደርሳሉ ማለት ነው፡፡ የእነዚህ መድሃኒቶች የፈውስ አቅም ታዲያ አንድ አይነት ነው፡፡ የመድሃኒቶቹ ዋጋ ከፍና ዝቅ ማለት ጋር ከመድሃኒቶቹን ጥራትና የመፈወስ አቅም ጋር ማያያዙ ተገቢ የሆነ አመለካከት አይደለም፡፡
መድሃኒቶቹ እንደሚመረቱበት አገር የታክስና የማምረቻ ቁሳቁስ ዋጋ እንዲሁም የሠራተኛ ክፍያ ዋጋቸው ከፍና ዝቅ ሊል ይችላል፡፡                 
መድኀኒቶች ወደ አገር ውስጥ ከመግባታቸው በፊትም ሆነ በአገር ውስጥ ገብተው ለተጠቃሚው ከመድረሳቸው በፊት በመድኀኒቶቹ ጥራትና በመጠቀሚያ ጊዜያቸው ላይ የሚደረጉ ቁጥጥሮችን አስመልክተው ሲናገሩም በአገራችን የመድኀኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን እንደዚህ አይነት ጉዳዮችን የመቆጣጠር ኃላፊነት እንዳለበት ጠቁመው መድኀኒቶች ወደ አገር ውስጥ ከመግባታቸው በፊትም ሆነ ገበያ ላይ ከማዋላቸው በፊት የመድኀኒቶቹን ጥራትና ፈዋሽነት ለማረጋገጥ በቤተ ሙከራ ፍተሻ ያደርጋሉ፡፡ መድኀኒቶች የህንን አሰራር ተከትለው ካልሆነ በስተቀር ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ አይፈቀድም፡፡ ይሁን እንጂ መድኀኒቶች ወደ አገር ውስጥ ገብተው በተለያዩ መንገዶች ለህብረተሰቡ እንዲዳረሱ ሲደረግ የሚደረግ ክትትልና ቁጥጥር የለም፡፡ መድኀኒቶቹ ከተሰራጩ በኋላ በድንገት ገበያ ውስጥ በመግባትና ሳምፕሎችን (ናሙናዎችን) በመውሰድ ተገቢ ምርመራና ቁጥጥር ማድረግ እምብዛም የተለመደና እየተሰራበት ያለ ጉዳይ አይደለም፡፡ በችርቻሮ ስራ ላይ የተሰማሩ መድኀኒት ሻጮችና አከፋፋዮች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን መድኀኒቶች ከገበያ ለማስወገድ ጥረት ሲያደርጉ አይታዩም። ይህ ታዲያ ህብረተሰቡን ለከፍተኛ አደጋ የሚያጋልጥና በመድኀኒት አጠቃቀም ሥርዓት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን የሚያስከትል ነው፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ይህን መሰሉን ለአገርና ለህዝብ አደጋ የሆነ ችግር በጋራ ለማስወገድ ጥረት ማድረግ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መድኀኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የመድኀኒት አቅርት፣ አግባብ ያልሆኑ የመድኀኒት አጠቃቀሞችንና የሚያስከትሉትን የጤና ችግሮች አስመልክቶ በአዳማ ከተማ ሰሞኑን ለጋዜጠኞች አንድ የግንዛቤ ማስጨበጫ አውደጥናት አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዚህ አውደ ጥናት ላይ የኤጀንሲው የግዥ ትንበያና አቅም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ይገዙ እንደተናገሩት፤ አግባባዊ ባልሆኑ የመድኀኒት አጠቃቀም ችግሮች ሳቢያ በተጠቃሚዎች ላይ የሚደርሱ ከፍተኛ የጤና ችግሮች አሉ፡፡ ኤጀንሲው በአገሪቱ ዋና ዋና የጤና ችግሮች ላይ ያተኮሩ፣ ጥራታቸው የተረጋገጠ መሰረታዊ መድኀኒቶችን በበቂ መጠን፣ በተመጣጣኝ ዋጋና ቀጣይነት ባለው መልኩ እያቀረበ ለመንግስትና የግል የጤና ተቋማት የሚያሰራጭ መሆኑን ጠቁመው እነዚህን መድኀኒቶች በተገቢው መንገድ፣ በተፈላጊው መጠንና ሁኔታ በመውሰድ አግባብ ባልሆነ መንገድ በመውሰድ ከሚከሰቱ የጤና ችግሮች ህብረተሰቡ ራሱን ሊጠብቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡በዚሁ አውደ ጥናት ላይ ጥናታዊ ፅሁፋቸውን ያቀረቡት የኤጀንሲው የግዢ ትንበያና አቅም ግባታ ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሲራጅ አደም በበኩላቸው፤ ኤጀንሲው መድኀኒቶችን እየገዛ በአገሪቱ ባሉት የተለያዩ ቅርንጫፎቹ አማካኝት የሚያከፋፍል መሆኑን ጠቁመው የመንግስትም ሆነ የግል የጤና ተቋማት መድኀኒቶች በተገቢው ጊዜ እንዲደርሳቸው በማድረጉ ረገድ ኤጀንሲው ከፍተኛ ስራ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡ በአገሪቱ የሚገኙ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች መድኀኒቶችን ይዘው ለማቆየት የሚችሉባቸው ጊዜያት ውስን መሆኑን የጠቆሙት እኚሁ ፅሁፍ አቅራቢ ከሁለት እስከ አራት ወር በሚደርሱ ጊዜያት መድኀኒቶች በጤና ተቋማት ውስጥ መቆየት እንደሚችሉና ከዚህ ጊዜ በላይ መድኀኒቶችን በየጤና ተቋማቱ ማቆየቱ ለብልሽት ሊዳርግ እንደሚችልም ገልፀዋል። ኤጀንሲው በአዳማ ከተማ ውስጥ የሚገኘውን ቅርንጫፍ የመድኀኒት ማከማቻና ማከፋፈያ መጋዘኑንም ለጋዜጠኞቹ አስጎብኝቷል፡፡ ይህ ቅርንጫፍ መጋዘን በቅርቡ የቃጠሎ አደጋ ደርሶበት እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸውና እስከአሁን በገንዘብ ሊተመኑ ያልቻሉ መድኀኒቶችና የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶችን በቃጠሎው አጥቷል፡፡ የቅርንጫፍ መ/ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ አየለ ታደሰ በቃጠሎው አደጋ ምክንያት በመጋዘኑ ላይ የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ ዝርዝር ማብራሪያ ለመስጠት አልቻሉም፡፡ ምርመራው ተጠናቆ እንዳልደረሳቸውና የተቃጠለውን የመድኀኒት መጠንም ለማወቅ ጊዜው ገና መሆኑን በዚሁ የጉብኝት ወቅት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡                        

Read 4858 times