Saturday, 28 January 2012 13:31

ሆሊውድ ለሴትና ለጥቁር ባለሙያዎች አልተመቸም

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

በሆሊውድ ከሚሰሩ የፊልም ዳይሬክተሮች የሴቶች ቁጥር አምስት በመቶ ብቻ መሆኑን አንድ ጥናት ሲጠቁም ሆሊውድ ለጥቁር የፊልም ባለሙያዎችም የመስራት እድል ነፍጓል፡፡ ባለስልጣናትና የፊልም ኩባንያዎች ከንቀታቸው የተነሳ ስለ ጥቁር ህዝብ ምንም የሚያውቁት ነገር የለም ሲል ጥቁር አሜሪካዊው የፊልም ባለሙያ ስፓይክ ሊ ተናግሯል፡፡ስፓይክ ሊ ባለፈው እሁድ በተጀመረው የሱንዳኔ ፊልም ፌስቲቫል ላይ “ሬድ ሁክ ሰመር” የተባለ አዲስ ፊልሙን ያስመረቀ ሲሆን፤ ፊልሙን ለመስራት የትኛውንም የሆሊውድ ስቱዲዮ  ደጅ አለመጥናቱን ጠቁሞ ሆሊውድና የፊልም ኩባንያዎች ለጥቁር ባለሙያዎች ምንም እገዛ አያደርጉም ሲል ነቅፏቸዋል፡፡

ፊልሞቹን በገዛ ገንዘቡ እንደሚሰራ የሚናገረው ባለሙያው፤ የሆሊውድ የፊልም ኩባንያዎች ለአዳዲስ ፊልሞች የፋይናንስ ድጋፍ ከማድረግ ይልቅ በተከታታይ እና በቴክኖሎጂ ቅንብር ለሚሰሩ ፊልሞች ላይ ማድላታቸው ያሳዝናል ብሏል፡፡በሌላ በኩል ባለፉት በሆሊውድ የፊልም ኢንዱስትሪ ባለፉት 13 ዓመታት የሴት ዲያሬክተሮች ተሳትፎ በግማሽ እንደቀነሰ “ሴንተር ፎር ዘ ስተዲ ኦፍ ውመን ኢን ቴሌቭዥን ኤንድ ፊልም” የተሰኘው ተቋም ያወጣውን ሪፖርት ጠቅሶ የዘገበው ሎስ አንጀለስ ታይምስ፤ ሴት ባለሙያዎች የዶክመንታሪ፣ ድራማ እና የኮሜዲ ጭብጥ ባላቸው ፊልሞች ላይ መጠነኛ ተሳትፎ ቢኖራቸውም በሆረር፣ አክሽንና አኒሜሽን ፊልሞች ላይ የመስራት እድላቸው ዝቅተኛ እንደሆነ አመልክቷል፡፡ አምና ከታዩ ፊልሞች 94 በመቶ ያህሉ በወንድ ዲያሬክተሮች መሰራታቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በሆሊውድ  የፊልም ስራ መስኮች ሴቶች ያላቸው ድርሻ ዝቅተኛ ነው ብሏል፡፡ የሆሊውድ ፊልም ኩባንያዎች፤ በሴቶች የሚሰሩ ፊልሞች የገበያ ስኬት ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው የገለፀው ሪፖርቱ፤ ሴቶች ከፊልም ፀሃፊዎች 14 በመቶ፤ ከከፍተኛ ፕሮዲውሰሮች 18 በመቶ፤ ከፕሮዲውሰሮች 25 በመቶ፤ ከኤዲተሮች 20 በመቶ እንዲሁም ከሲኒማቶግራፈሮች አራት በመቶ ድርሻ አላቸው ብሏል፡፡

 

 

 

 

 

Read 2496 times Last modified on Saturday, 28 January 2012 13:38