Saturday, 20 June 2015 11:03

“Game of Thrones 5”፣ መታየት ያለበት ተከታታይ የቲቪ ድራማ

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(5 votes)

ባለፈው እሁድ የተጠናቀቀው የጌም ኦፍ ትሮንስ 5ኛ ሲዝን፣ ካለፉት አመታት የላቀና መታየት የሚገባው ምርጥ የቴሌቪዥን ድራማ ነው - በተለይ ለዘመናችን፣ በተለይ ለአገራችን ቁልፍ በሆኑ ዋና ዋና ጥያቄዎች ዙሪያ ያጠነጠነ ድራማ መሆኑ አስደንቆኛል። የድራማው ዋና ዋና የታሪክ ሰንሰለቶችንና ዋና ባለታሪኮቹን እየጠቃቀስኩ ለማስቃኘት ልሞክር።

1. ጉልበትንና እምነትን፣ ሃይማኖትንና ቤተመንግስትን ማደባለቅ።  
ሰርሲ ላኒስተር፣ ንግስት ናት። ልጇ በቅርቡ ዘውድ ቢጭንም ገና ላቅመአዳም ስላልደረሰ፣ እቴጌ ሰርሲ የንጉሡ ሞግዚት፣ አማካሪና እንደራሴ ሆናለች። በዚህ ትልቅ ስልጣን ዙሪያ፣ በርካታ የስጋት፣ የጥርጣሬና የጥላቻ ጦሮች የከበቧት ይመስላታል። አምርራ ከምትጠላቸውና እንደ ደመኛዋ ከምታያቸው ሰዎች መካከል፣ ወንድሟ ቲርዮን ላኒስተር ነው። ቲርዮን፣ ድንክ በመሆኑ የንግሥና ተስፋ እንደሌለው እርግጠኛ ናት። ግን፣ እንደፈለገች የሚሽከረከርላትና የሚታዘዝላት አይነት ሰው አይደለም። ብልህነቱና የንግግር ችሎታው ያስጠላታል። የንጉሡ ዋና አማካሪ መሆን እንደማያቅተው ስለምታውቅም፣ እንደ ተቀናቃኝ ነው የምታየው።
“ደግነቱ” እንከን የለሽ አይደለም። አለቅጥ የመጠጣትና የመስከር፣ እናም በዘፈቀደ ሕይወቱን የማባከን ዝንባሌ አለበት። እንደለመደው ሴቶችን እያንጋጋ “ሲንዘላዘል”፣ በአጋጣሚ ከአንዲት ሴት ጋር ከተዋወቀ በኋላ ግን በፍቅር ባነነ። በትሹም ቢሆን፣ ሕይወቱን ስርዓት የማስያዝ ጉልበት አገኘ - በፍቅር ሃይል።
ግን፣ የንጉሥ ቤተሰብ ነው። የቱንም ያህል በፍቅር ሕይወቱ ቢታደስ፣ ከተራ ሴት ጋር ተጋብቶ አብሮ እንዲኖር አይፈቀድለትም። የቤተሰብን ክብር ይነካል። ይሄ ለሰርሲ ጥሩ ሰበብ ነው - ወንድሟን ክፉኛ ለማቁሰል ይጠቅማታል። “ለቤተሰቡ ክብር ሲል ከሚያፈቅራት ሴት መለየትና መሥዋዕት መክፈል አለበት” በማለት የወንድሟን ሕይወት ለማናጋት አልከበዳትም። ደግሞም ተሳክቶላታል።
ምን ዋጋ አለው? በጥላቻ የተመረዘ ነፍስ፣ አንድ ሁለቴ በማጥቃት አይረካም። ባለቅኔው ፀጋዬ ገብረመድህን ይህንን አይነት ባሕርይ የሚገልፅ ግጥም አለው - “የተወጋ ቢረሳ፣ የወጋ አይረሳ” የሚል መልዕክት ያዘለ ግጥም ነው። በጥላቻ የተወረወረው ወጥመድ እየሰፋና እየተወሳሰበ ይቀጥላል። ወይም ደግሞ፣ ጥቃት፣ አፀፋ፣ የአፀፋ መልስ... እያለ፣ እየከረረና እየመረረ ይሄዳል። እቴጌ ሰርሲ፣ በዚህ በዚህ የሚስተካከላት የለም።
ታዲያ፣ እለት በእለት የምትዘረጋው ወጥመድና መረብ፣ ወንድሟን ዝም ለማሰኘት ብቻ አይደለም። ቅስሙን ሰብራ ለማንኮታኮትና አዋርዳ ለማሽቀንጠር ነው። ይህም አይበቃም። እስር፣ የግድያ ሴራ፣ የሞት ፍርድ... እየተከተለ ይመጣል።
እቴጌ ሰርሲ፣ እንደጠላትና ተቀናቃኝ የምታየው ወንድሟን ብቻ ሳይሆን፣ ነባር የንጉሥ አማካሪዎችንም ነው። ሌላም ይጨመርባታል። ልጇ ዘውድ በጫነ ማግስት፣ በለጋነቱ እድሜ ከምትበልጠው ሴት ጋር ተጋብቷል። ከተቀናቃኝ የመሳፍንት ቤተሰብ የተወለደችው ሚስት፣ ንጉሱን እንዳሻት ለማሾር ብላ ነው ያገባችው። ሃሳቧን ለማሳካትም ጊዜ አልወሰደባትም።
በዚህ የበገነችው እቴጌ ሰርሲ ላኒስተር፣  ተቀናቃኞቿን ሁሉ ለማጥፋት ዘዴ ስታውጠነጥን ነው የምትውለው፤ የምታድረው። እንደሌላው ጊዜ፣ ሁነኛ ዘዴ አገኘች። ከሌላው ጊዜም ይበልጣል እንጂ። ተቀናብሮ የተዘጋጀና ያለቀለት ዘዴ ነው ያገኘቸው። ከሷ የሚጠበቀው፣ የመወጠሪያ ገመድ አንድ ሁለቴ ሳብ ሳብ ማድረግ ብቻ ነው። መወጠሪያው ገመድ፣ የአጎቷ ልጅ ነው። ሁሌም ታዛዧ ነው፤ ... ሁሌም ታዛዧ ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን፣ አይታው አታውቅም።
የአጎቷ ልጅ፣ የሃይማኖት ቡድን ውስጥ በአባል እንደገባ መች አወቀች? ስታየው፣ ሌላ ሰው ሆኗል። እንደባህታዊ ነው የለበሰው። አነጋገሩም እንደድሮው አይደለም። ሁለመናው ተለውጧል። በጭፍን የሃይማኖት እምነት ተነክሯል። ከዚያም አልፏል እንጂ። ጭፍንነትን የሚያስተጋባ ሰባኪ ሆኗል (አክራሪ)። እሱና መሰሎቹ፣ “አገሬው ዌስትሮስ በሙሉ፣ በተለይም ዋና ከተማዋ ኪንግስ ላንዲንግ፣ በሃጥያተኞች ረክሳለች” በማለት ዘመቻ ጀምረዋል። ታዲያ ስብከት ብቻ አይደለም።
ሰው ሁሉ ስብከታቸውን ሰምቶ በጭፍን ቢያምንላቸውና ተከታይ ቢሆንላቸው እንኳ አያረካቸውም። የእያንዳንዱን ሰው አኗኗር ለመቆጣጠር ነው የሚመኙት - ለማዘዝ፣ ለማስፈራራትና ለማስገደድ። ሃብታምም ይሁን ድሃ፣ ገበሬም ይሁን ምሁር፣ ግንበኛም ይሁን ይሁን የመሳፍንት ዘር፣ የሃይማኖት ትዕዛዛትን የሚጥስ አንድም ሰው መኖር እንደሌለበት ይሰብካሉ። ሁሉም ሰው፣ ወደደም ጠላም፣ የሃይማኖት ትዕዛዛትን መፈፀም አለበት። በሌላ አነጋገር አመፀኛ አክራሪ ሆነዋል - ጉልበትንና ሃይማኖትን በማቀላቀል።
በእርግጥ፣ የተወሰኑ ሚስኪን ሰዎችንና አለኝታ ቢስ ሴተኛ አዳሪዎችን ከማሸማቀቅና ከመረበሽ ያለፈ ነገር ለማድረግ አቅም የላቸውም። ገና ብዙ ተከታይ አላገኙም። እንደተለመደው፣ “የምር ሃይማኖተኛ ናቸው” በሚል ብዙ ሰው ያደንቃቸዋል። በተግባር ግን፣ ዓለማዊ ኑሮውን ትቶ በማያፈናፍኑ ጭፍን የሃይማኖት ትዕዛዛት ለመታፈን የሚፈልግና እነሱን ለመቀላቀል የሚጎርፍ ብዙ ሰው የለም።
አብዛኛው ሰው “ሃይማኖተኞቹ”ን ቢያደንቅም፤ ‘በሆታ’ እየደገፈ አይቀላቀላቸውም። ሕዝቡን በሙሉ በጉልበት ለማስገደድ ቢሞክሩስ? አያዋጣቸውም። መንግስት ያለበት አገር ነው። መንግስትን ለመፈታተን ደግሞ፣ አቅማቸው አይፈቅድም። በአንዳች ተዓምር አቅም ማግኘት አይችሉም። አቅም የሚያገኙበት እድል የለም ማለት ግን አይደለም። ለዚያውም፣ ሳይወጡ ሳይወርዱ በቀላሉ አቅም የሚያገኙበት እድል ቢፈጠርላቸውስ? ለዚያውም፣ ራሱ መንግስት እድል ቢፈጥርላቸውስ? ለዚያውም ራሷ ንግስቲቱ!
እቴጌ ሰርሲ ላኒስተር፣ ተቀናቃኞቿን ለማጥፋት የሚጠቅማት ከሆነ፣ ለዓመፀኞቹ አክራሪዎች የተወሰነ ስልጣን ልትሰጣቸው ትችላለች። ብዙ ስልጣን አትሰጣቸውም። ትንሽ ብቻ። ከጎን በኩል ሚጢጢ መንግስታዊ ሃይማኖት እንደመፍጠር ማለት ነው - ከመንግስት ድጋፍ የሚያገኝ ሃይማኖት። “ያኛውን ወይም ይሄኛውን የሃይማኖት ትዕዛዝ ጥሰሃል” እያሉ የማሰርና የመፍረድ ስልጣን እንዲኖራቸው ማድረግ አያቅታትም። ተቀናቃኞቿ፣ “ዝሙት ፈፅማችኋል”፣ “ሃጥያትን በዝምታ አልፋችኋል” ተብለው ሲወነጀሉ፣ ሲታሰሩ፣ ሲዋረዱ... እየታያት በምኞት ብታሰላስል አልተሳሳተችም።
“ሃይማኖተኞቹ እኔ ላይ ቢዞሩብኝስ?” ብላ የምታስብበት ምክንያት ለጊዜው አልታያትም። ንግስት ናት። የንጉሡ እናትና ቀኝ እጅ ናት። ማን ይነካታል? በእርግጥ፣ ተቀናቃኞቿም ‘ማንም አይነካንም’ ብለው የሚያስቡ አውራ ሰዎች ናቸው። ሃይማኖተኞቹ የሰርሲን ተቀናቃኞች የማጥቃት ስልጣን ካገኙ፣ በዚያው ያቆማሉ? እንዲያም ሆኖ፣ ሰርሲ ፈፅሞ ስጋት አልገባትም።
አንደኛ፣ ለሃይማኖተኞቹ ባለውለታቸው ናት፤ ስልጣን እንዲያገኙ አድርጋለች። ... ግን፣ “የሰጠችንን ስልጣን መልሳ ልትነጥቀን ትችላለች” በሚል፣ እንደዋና ጠላት ቢያዩዋትስ? ከመንግስታዊ ሃይማኖት ወደ ሃይማኖታዊ መንግስት መሻገር ቢያምራቸውስ? የማይሆን ነገር ነው! ይሆናል?
ሁለተኛ፤ ታዛዧ የነበረው የአጎቷ ልጅ በሃይማኖተኞቹ ቡድን ውስጥ ቁልፍ ቦታ መያዙ፣ ሊጠቅማት ይችላል። የቅርብ ዘመዷና በቅርብ የምታውቀው የአጎቷ ልጅ፣ ለጥቃት አጋልጦ አይሰጣትም። አይደለም? ...ግን፣ የቅርበቱ ያህል፣ ሃጥያተኛ ተብላ እንድትወገዝ የሚያደርጉ ብዙ ሚስጥሮቿን ያውቃል። በዚያ ላይ፣ በዝምድና የመቧደን ዘረኝነት፣ ገለጥ ተደርጎ ሲታይ ባዶ ነው። ዘረኝነት፣ ኦና ሰብዕናን ለመሙላት የሚያገለግል ባዶ ውሸት መሆኑን እንዴት ዘነጋችው? ዙሪያውንና ራሷን ብትመለከት በቂ ነው። ተቀናቃኞቿን የምታሳድዳቸው፣ የሩቅ ሰዎች ስለሆኑ አይደለም። ወንድሟን ጭምር ለማጥፋት የምታሴረው፣ በዘርና በዝምድና ስለተራራቁ ነው እንዴ? እና በዝምድና ትስስርና በአጎቷ ልጅ ብትተማመን ያዋጣታል? ... ቢሆኖም አላሳሰባትም።
ሦስተኛ፣ ከተቀናቃኞቿ ከተገላገለች በኋላ፣ አመፀኞቹ አክራሪዎች ከልክ እንዳያልፉና ጭፍን እምነታቸውን እንዲያለዝቡ በምክንያታዊ ውይይት ልታሳምናቸው ትችል ይሆናል። ...ግን ደግሞ፣ ከመነሻው ተቀናቃኞቿን እንዲያጠፉላት የመረጠቻቸው ለምን ሆነና? ከጭፍን እምነት የማይነቃነቁና ለምክንያታዊ ውይይት ቅንጣት ቦታ የማይሰጡ በመሆናቸው አይደል? ቢሆንም... አላስጨነቃትም።
“What goes around comes around” የሚለውን የብልሆች አባባል አታውቀውም፤ ወይም ደንታ አልሰጣትም። ወደ ሌሎች አቅጣጫ “ጃስ” ብላ የለቀቀችው አውሬ፣ ወደራሷ አቅጣጫ እየተንደረደረ ቢመጣ... ማስቆሚያ ዘዴ አላት? አሁን የሚያሳስባት፣ ይሄ ሳይሆን፣ የስልጣንና የፖለቲካ ቁማር ነው። በዚሁ ቁማር ውስጥ፣ የሃይማኖት አክራሪነት የመጫወቻ ካርድ እንዲሆንላት ትፈልጋለች። ብዙም ሳይቆይ መልሶ መጫወቻ እንዳያደርጋት አስተማማኝ መከላከያ ይኖራት ይሆን? ለቁጥር የሚታክቱ የአለማችን አሳዛኝ ታሪካዊ ጥፋቶች የተለኮሱት፣ እንደ እቴጌ ሰርሲ በምኞት የሰከሩ ሰዎች በሚፈፅሙት ስህተት ሰበብ ነው። እያንዳንዱ ሰበብ የራሱን መዘዝ ጎትቶ ያመጣልና።
ይሄ የታሪክ ሰንሰለት፣ በዘንድሮው የጌም ኦፍ ትሮንስ ተከታታይ ድራማ ውስጥ ጎልተው ከሚታዩ የታሪክ ትልሞች አንዱ ነው - በዌስትሮስ ምድር፣ የዋና ከተማዋ የኪንግስ ላንዲንግ ትልም ልንለው እንችላለን።

2. የመስዋዕት አምልኮ (የሰው ሕይወት=የማገዶ እንጨት)
ከወደ ሰሜን በምትገኘው በዊንተርፌል ዙሪያ ሁለት ጎራዎች የሚያካሂዱት ትንቅንቅ ላይ ያጠነጠነ ሌላ ታሪክ አለ። ስልጣን ለመያዝ ወደ መዲናዋ ለመዝመት ያቀዱት ሁለቱ ጎራዎች፣ በቅድሚያ አንዱ ሌላውን በማጥፋት ሰፊውን የሰሜን ግዛት ለመቆጣጠር ይጨፋጨፋሉ።
በአንድ በኩል፣ የጭካኔ ባህርይ የተጠናወተው የሩስ ቦልተን ጎራ አለ። “ሰው ሰጥ ለጥ ብሎ ስርዓት የሚይዘው፣ መቀጣጫ ሲያይ ነው” በሚል ሰበብ የጭካኔ ባሕርይ ተላብሰዋል። እንደ ክፉ አውሬ ያደርጋቸዋል ቢባል ይቀላል። የአባትዬው ከሩሶ ቦልተን ጭካኔ ያነሰ ይመስል፣ የልጅዬው የራምሰስ ይብሳል።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ የመስዋዕትነት አምልኮ የተጠናወተው፣ የስታነስ ባራቲያን ጎራ አለ። “አገሬውን በስርዓት የማስተዳደር ታሪካዊ ሃላፊነት ተጭኖብኛል” ብሎ የሚያስበው ስታነስ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ፣ የእያንዳንዱ ሰው ሕይወት ከስንጥር የበለጠ ዋጋ እንደሌለው ያምናል። “ሕይወትህ፣ ከማገዶ እንጨት የተሻለ ዋጋ የለውም” በሚል እምነት እንደመመራት ነው። እናም እያንዳንዱ ሰው ራሱን ለመስዋዕትነት ማቅረብ ግዴታው ነው። የአገራችን የ60ዎቹ ዓ.ም ሶሻሊስቶች ሲያስተጋቡት ከነበረው መዝሙር ብዙም አይለይም።
“ይህ ነው ምኞቴ እኔ በሕይወቴ
ከራሴ በፊት ለኢትዮጵያ እናቴ”
ታዲያ፣ አዳሜ እንዲህ በመስዋዕትነት የሚያምን ቢሆንም፣ ራሱን እንደ በግ ለእርድ እንደ እንጨት ለማገዶ በፈቃደኝነት የሚሰጥ ቂላቂልና እብድ ሰው ብዙ አይገኝም። “መስዋዕት ማለት የራስህን አላማ ለማሳካትና ሕይወትህን ለማሻሻል፣ ከባባድ ችግሮችንም ተቋቁመህ የአቅምህን ሁሉ መጣር ማለት ነው” ብሎ ነገሩን ለማለሳለስና ራሱን ለማታለል የሚሞክር አይጠፋም። ግን ዋጋ የለውም።
በስታነስ አገር፣ መስዋዕት ማለት መስዋዕት ነው። “የራስህ አላማ ገደል ይግባ፤ ሕይወትህ ነድዶ ይጥፋ” ... በቃ፣ እንደ ማገዶ እንጨት። ይሄ ነው መስዋዕትነት። ነገርዮው፣ እንዲህ የሕይወትና የሞት ጉዳይ ቢሆንም፣ አዳሜ ቆም ብሎ የመስዋዕትነት አምልኮውን በቅጡ ለመመርመርና ክፉ እምነት መሆኑን ለመገንዘብ አይፈልግም። መስዋዕትን እያዳነቀ በሕይወት ለመቀጠል ይመኛል (የስቃይ አምልኮ፤ ከጤናማ ሰው የሚጠበቅ ባይሆንም)።
ሁሉም ሰው፣ ሙሉ ለሙሉ ጤና አጥቷል ማለት ግን አይደለም። እምነቱን ተከትሎ በቁሙ ከእንጨት መሃል ገብቶ መቃጠልን አይፈልግም - እንደማንኛውም ጤናማ ሰው። መቼም ቢሆን፣ የመስዋዕት ፅዋ የኔ ተራ ይሆናል ብሎ አያስብም። ሌሎች በመስዋዕት እሳት ሲቃጠሉ ግን፣ ተመልካችና አዳናቂ ይሆናል።
በእርግጥም፣ መነሻው ላይ የእሳት እራት የሚሆኑት፣ በጠላትነት ወይም በተቀናቃኝነት የተፈረጁ ሰዎች ናቸው - እንዲህ አይነት ሰበብ ተገኝቶማ ማን ይምራቸዋል? ግን በነሱ አያበቃም። የመስዋዕት ቃጠሎን ሁልጊዜ  እያዳነቁ፣ ሁልጊዜ ከእሳት ማምለጥ እንዴት ይቻላል?
ቢሆንም፣ ስታነስ ባራትያን ከሌላው ሰው የተለየ ያን ያህል “ክፉት” አይታይበትም። ሰዎችን አቃጥሎ የመጨረስ ምኞት የለውም። አዎ፣ ብዙ ወንጀል፣ ብዙ ጥፋት ሰርቷል። የአገርንና የትውልድን ሃላፊነት መሸከም እጣ ፋንታዬ ነው በሚል ሰበብ የሰራቸውን ጥፋቶች፣ እንደገና ወደ ነበሩት መመለስ ቢችል የሚመኝበት ጊዜ አለ።
ሌላ ሌላውን ነገር ሁሉ ትቶ፣ ከሚስቱና ከአንዲት ልጁ ጋርበሰላም የቤተሰብ ሕይወቱን በፍቅር የመኖር ምኞትም ያብሰለስለዋል። ቅሬታ የለውም ማለት አይደለም። እንደሌሎቹ የመሣፍንት ቤተሰቦች፣ ወንድ ልጅ አለመውለዱ ያንገበግበዋል። አንዳንዴም፣ ሚስቱን ጥፋተኛ አድርጎ እያየ የጥላቻ ስሜት ሽው ይልበታል።
ሴት ልጁ እንደሌሎች ልዕልቶች አለመሆኗም ያሳርረዋል። የግራ ፊቷ፣ በበሽታ ምክንያት የዝሆን ቆዳ መስሏል። እንዲያም ሆኖ፣ ነፍሷ ንፁህ ነው። ገና ሕፃን ብትሆንም፣ ከቅንነትዋ ጋር ብሩህ አእምሮዋ የደስ ደስ ገፅታን ሰጥቷታል። የምትወደድ ልጅ ናት። ከሁሉም በላይ ደግሞ አባቷ ስታነስ ባራትያን ይወዳታል። እንዲያውም ከሷ በላይ በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሌላ ነገር እንደሌለ ይሰማዋል - ብዙውን ጊዜ (ሁሌ ባይሆንም)።
ከዚህ ውጪ፣ ሌላው ሌላው ሁሉ ሸክም ነው። ይሄ አገርን የመምራት ጉዳይ፣ በራሱ ፈቃድ መርጦ የተቀበለው ነገር ሳይሆን፣ እጣፈንታው ሆኖ በግድ የተጫነበት ሃላፊነት ነው - ከአባት፣ ከአያት የተወረሰ። አጠገቡ የሚገኙ የሰሜን ተቀናቃኞቹን የማንበርከክ፣ ከዚያም ወደ ዋና ከተማዋ ወደ ኪንግስ ላንዲንግ ዘምቶ ስልጣን የመያዝና አገሬውን የማስተዳደር ሃላፊነት ተጥሎበታል። ለዚህ ነው፣ በርካታ የቃጠሎ መስዋዕቶችን መገበር ግዴታ የሆነበት...
ስታነስ ባራትያን ይህን ሁሉ የሚያወራው፣ ራሱን ለማታለል እንጂ፣ በግዴታ ሸክም የጫነበት ሰው የለም። ሰዎችን ለቃጠሎ መስዋዕት እንዲማግድ ያስገደደው ሃይል የለም። “ሃላፊነት እጣፈንታዬ ነው። መስዋዕት የግድ ነው። ሰዎች ሳይማገዱ፣ ያለ መስዋዕትነት ጥሩ ውጤት አይገኝም” ብሎ የሚያምነው በራሱ ምርጫ ነው።
ቢሆንም፣ ሰዎች በእሳት ሲነዱ ማየት ያስደስተዋል ማለት አይደለም። እንደ ሩስ ቦልተንና እንደ ራምሰስ የጭካኔ አባዜ አልተጠናወተውም - ስታነስ።
እንዲያውም፣ ስለ ቃጠሎ መስዋዕት የማያስብበት ጊዜ ቶሎ እንዲመጣ ይመኛል። የእስከዛሬው ይበቃል። የሰሜን ተቀናቃኞቹ ላይ ለመዝመት ተዘጋጅቷል። በአንድ ውጊያ ያሸንፍና ወደ ዋና ከተማይቱ ይገሰግሳል። በቃ። ግን፣ የጦርነት ዘመቻ እንደ አፍ አይቀልም። የሽምቅ ጥቃት ያጋጥማል። ጋራ ሸንተረሩ ሁሉ በበረዶ ግግር ተሸፍኖ አላንቀሳቅ ይላል። ቀን አልፎ ቀን ሲተካ፣ ስንቅ የተመናመነበት ጦር፣ በቆፈን እየተኮራመተ በበሽታ ይዳከማል...።
ይሄኛውን ችግር ለመፍታት፣ ያኛውን ውጥን ለማቃናት፣ ለዚህኛውም ለዚያኛውም፣ ቁልፉ መላ የመስዋዕት ቃጠሎ ብቻ ነው። የማይወደዱ፣ የተናቁና ከንቱ ሰዎችን በማቃጠል የተጀመረው የመስዋዕት አምልኮ፣ ትንሽ ቆይቶ ዜማው ይቀየራል። “ይሄ ምኑ እንደመስዋዕት ይቆጠራል? የመስዋዕት ዋጋ ከፍ የሚለው፣ የሚወደዱ፣ የሚከበሩና ደህና ሰዎች ላይ ሲሆን ነው” ወደሚል ማምራቱ ይቀራል? በዚህ ከቀጠለስ መጨረሻው የት ነው? “እጅግ የምትወዳት አንድያ ልጅህን ለመስዋዕት ካላቀረብካት ድል አይቀናህም” ወደ ሚል ደረጃ ባይደርስ እንኳ፣ የመስዋእት ጥሪ ወደ ስታነስን ቤት አምርቶ በር ባያንኳኳ እንኳ፣ የእሳቱ ነበልባል ዙሪያውን መለብለቡ ይቀራል?
የጌም ኦፍ ትሮንስ ሁለተኛው የታሪክ ትልም በዚህ አቅጣጫ ነው እየከረረና እየመረረ የሚጓዘው። “እያንዳንዷ መንስኤ የራሷ ውጤት፣ እያንዳንዷ ሰበብ የራሳ መዘዝ አላት” የምንል ከሆነ፤ “ድራማው አይምሬ ነው” ልንለው እንችላለን።

3. በተወላጅነት እየተቧደኑ፣ ወደ እልቂት!
ሦስተኛው የታሪክ ትልም፣ የመጨረሻው ጠረፍ የዌስትሮስ ድንበር ላይ የሚካሄደው ግብግብ ነው። እንደ ተራራ ከገዘፈው የበረዶ ግንብ ባሻገር፣ ጦረኛነትና አረመኔነት የገነነባቸው መዓት ጎሳዎች አሉ። wildling ይሏቸዋል።
በርካታዎቹ የጎሳ መሪዎችና ጦረኞች፣ የበረዶ ግንቡን የማለፍ እድል ቢያገኙ፣ የዌስትሮስ ግዛቶችን ከላይ እስከ ታች ለመዝረፍና የቀረውን ለማውደም፣ ህዝቡን ሁሉ ለመግደል የሚመኙ ናቸው። ትንሽ እግራቸውን ለማስገባት በቻሉበት አጋጣሚ ሁሉ፣ በድንበር አካባቢ በደም የማይጨቀይ የዌስትሮስ ከተማና መንደር የለም።
“ሕፃን ሽማግሌ ሳይሉ የሚገድሉ አውሬዎች ናቸው። ዌስትሮስን ለመዝረፍና ለማጥፋት የሚፈልጉ አረመኔዎች!” በቃ፣ ከበረዶው ግንብ ባሻገር የሚኖር ሰው በሙሉ፣ (መዝረፍና መግደል የሚመኝም ሆነ የማይመኝ)በጅምላ “የአረመኔዎች ወገን” ተብሎ ይፈረጃል። እንደ ጆን ስኖው፣ “ሰዎችን በጅምላ ሳይሆን እንደየድርጊታቸውና ባሕርያቸው እንደመዝናቸው” የሚል አዝማሚያ የሚያሳይ ሰው ካለ፣ “ከሃዲ” ተብሎ ይፈረጃል። ዘረኝነት እንዲህ ነው።
ከድንበሩ ባሻገርም ተመሳሳይ የዘረኝነት ባህል ነግሷል - “የዌስትሮስ ሰው ሁሉ ክፉ ጠላታችን ነው” በሚል ፍረጃ።

የዌስትሮስን መጨረሻ - “ከሰበብ ወደ መዘዝ”።
የዌስትሮስ ምድር፣ እንዲህ በሦስቱም አቅጣጫዎች፣ በጥፋት አፋፍ ላይ የደረሰች አገር ናት። ከወዲያ ጫፍ፣ የሃይማኖት አክራሪነት ይቆሰቆሳል። ከመሃል የመስዋዕት መዝሙር ይስተጋባል። ከወዲህኛው ጫፍ የዘረኝነት ጥላቻ ይግለበለባል። የሞት መንጋ እየተግተለተለ፣ እልፍና እልፍ ሆኖ እየተመመ እየመጣ እንደሆነ ሲያዩ፣ አብዛኞቹ ሊጋፈጡት ይፈልጋሉ? ወይስ አይተው እንዳላዩ በመሆን፣ በጭፍን እምነት፣ በመስዋዕትነትና በዘረኝነት እብደት መጓዝን ይመርጣሉ?
የዘንድሮው የጌም ኦፍ ትሮንስ ተከታታይ ድራማ፣ ከእስከዛሬዎቹ ይበልጣል የምለው ከላይ ያቀረብኳቸው የታሪክ ትልሞች፣ ጥልቀት ባላቸው ቁልፍ ጭብጦች (ሃሳቦች) የተቃኙና በጥራት ነጥረው የተቀረፁ የታሪክ ሰንሰሎች ሆነው በመቅረባቸው ነው።

Read 3757 times