Saturday, 20 June 2015 11:26

ዓለማችን ባለፈው አመት ለጦርነት 14 ትሪሊዮን ዶላር አውጥታለች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

- በቀን ከ42 ሺህ በላይ ሰዎች ይሰደዳሉ
- ባለፈው አመት 60 ሚ. ያህል ሰዎች ተሰደዋል፤ ግማሽ ያህሉ ህጻናት ናቸው
- በግጭት ሳቢያ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በ350 በመቶ አድጓል
- አይስላንድ የአለማችን ሰላማዊ አገር ናት

       ባለፈው የፈረንጆች አመት 2014 ብቻ በዓለማችን የተለያዩ አገራት ለተደረጉ ጦርነቶችና የእርስ በርስ ግጭቶች ከ14 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ወጪ መደረጉን ዘ ቴሌግራፍ ዘገበ፡፡
ኢንስቲትዩት ፎር ኢኮኖሚክስ ኤንድ ፒስ የተባለው አለማቀፍ ተቋም ያወጣውን ሪፖርት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ባለፈው አመት ለጦርነትና ለእርስ በርስ ግጭት የወጣው አጠቃላይ ወጪ፣ ከዓለማችን አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት 13 በመቶ እንደሚሆንና የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የካናዳ፣ የስፔንና የብራዚል ኢኮኖሚ በአንድ ላይ ተደምሮ አይደርስበትም፡፡
አለማችን ግጭትን በ10 በመቶ መቀነስ ከቻለች ለጦርነትና ለእርስ በርስ ግጭት ከሚወጣው ገንዘብ 1.43 ትሪሊዮን  ዶላር ማዳን ትችላለች ብለዋል የኢንስቲትዩቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ስቲቭ ኪሌላ፡፡ ሰሞኑን ይፋ የተደረገው አለማቀፍ የሰላም ሁኔታ አመልካች ሪፖርት በበኩሉ፣ በ2015 የግጭት መናኸሪያ በመሆንና በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ በመገኘት ረገድ የአለማችን ግንባር ቀደም አገር ሶሪያ መሆኗንና ኢራቅና አፍጋኒስታን እንደሚከተሏት አስታውቋል፡፡
በአመቱ የሰላም ሁኔታዋ በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰባት አገር ሊቢያ ናት ያለው ሪፖርቱ፣ የእርስበርስ ግጭት ከተነሳበት ጊዜ አንስቶ 6ሺ ያህል ዜጎች የሞቱባትንና 1 ሚሊዮን ህዝብ የተፈናቀለባትን ዩክሬን በሁለተኛነት አስቀምጧታል፡፡ በአለማችን በግጭቶች ሳቢያ ለህልፈተ ህይወት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር ባለፉት አራት አመታት ከ350 በመቶ በላይ አድጓል ያለው ሪፖርቱ፣  በ2010 ብቻ 49 ሺህ ሰዎች መሞታቸውንና ይህ ቁጥር በ2014 ወደ 180 ሺህ ከፍ ማለቱን ጠቁሟል፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው በ2013 ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ ለሞት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር 61 በመቶ በማደጉ ነው ያለው ሪፖርቱ፤ በአመቱ ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 18ሺህ እንደነበርና አብዛኞቹ ሟቾችም በአፍጋኒስታን፣ ኢራቅ፣ ናይጀሪያ፣ ፓኪስታንና ሶሪያ የተገደሉ እንደሆኑ አስታውቋል፡፡
በአንጻሩ ደግሞ ሰላማዊ ሆና በመዝለቅ ቀዳሚዋ አህጉር ናት በተባለችው አውሮፓ የሚገኙት አይስላንድ እና ዴንማርክ የዓለማችን ሰላማዊ አገራት ተብለዋል በሪፖርቱ፡፡ ቢቢሲ በበኩሉ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን መረጃ ጠቅሶ ከትናንት በስቲያ እንደዘገበው፣ በጦርነትና በእርስ በእርስ ግጭት  ሳቢያ የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር ታይቶ በማይታወቅበት ደረጃ ከፍ በማለት በ2014 60 ሚሊዮን ያህል ደርሷል፡፡ በየዕለቱ አገራቸውን ጥለው የሚሰደዱ ዜጎች ቁጥርም 42 ሺህ 500 ደርሷል፡፡
የተመድ የስደተኞች ኮሚሽን ያወጣው ሪፖርት እንደሚለው፣ የስደተኞች ቁጥር በ2013 ከነበረበት በ8.3 ሚሊዮን ያደገ ሲሆን ለስደተተኞች ቁጥር መጨመር ዋነኛ ምክንያት የተደረገውም ተባብሶ የቀጠለው የሶርያ ግጭት እንደሆነ ተረጋግጧል፡፡ ባለፉት አምስት አመታት 15 ያህል ግጭቶች መከሰታቸውን ወይም እንደገና ማገርሸታቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ከእነዚህ መካከልም ስምንቱ በአፍሪካ፣ ሶስቱ ደግሞ በመካከለኛው ምስራቅ አገራት የተከሰቱ እንደሆኑ በመግለጽ፣ በዚህም እስከ 2014 መጨረሻ 59.5 ሚሊዮን ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ለስደት መዳረጋቸውንና ከእነዚህም ግማሽ ያህሉ ህጸናት መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
ስደተኞቹ የአንድ ሃገር ህዝብ ቢሆኑ፣ አገሪቷ በአለማችን በህዝብ ቁጥር ብዛት 24ኛ ደረጃ ልትይዝ እንደምትችል አስታውቆ፤ 19.5 ሚሊዮን የሚሆኑ የተለያዩ አገራት ዜጎችም በስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች አስከፊ ኑሮ እንደሚገፉም አክሎ ገልጧል፡፡
በርካታ ዜጎች ከሚሰደዱባቸው የዓለማችን አገራት መካከል ቀዳሚዋ 4 ሚሊዮን ሰዎች የተሰደዱባት ሶርያ ስትሆን. አፍጋኒስታን በ3 ሚሊዮን፣ ሶማሊያ በሁለት ሚሊዮን ይከተላሉ፡፡ በሜዲትራንያን ባህር በኩል ወደተለያዩ የአውሮፓ አገራት የገቡ 1.8 ሚሊዮን ስደተኞች ጥገኝነት ለማግኘት ያቀረቡትን ጥያቄ ምላሽ እየተጠባበቁ እንደሚገኙና፣ ከእነዚህም መካከል ብዙዎቹ በጀርመንና በስዊድን እንደሚገኙም ሪፖርቱ ጠቁሟል፡

Read 1261 times