Saturday, 20 June 2015 11:30

ሰሜን ኮርያ በክፍለ ዘመኑ የከፋ በተባለው ድርቅ ተመታች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አምና የተመዘገበው ዝናብ በ30 አመታት ዝቅተኛው ነው
   ሰሜን ኮርያ ባለፉት መቶ አመታት ገጥሟት በማያውቅና የከፋ የምግብ እጥረቷን በከፍተኛ ሁኔታ በማማባስ ወደ ቀውስ ያስገባታል ተብሎ በተሰጋለት ድርቅ መመታቷን ስካይ ኒውስ ዘገበ፡፡ የአገሪቱን የዜና ወኪል ኬሲኤንኤን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፤ ህዋንጌና ፓዮንጋን የተባሉትን ዋነኞቹ የሰሜን ኮርያ ሩዝ አብቃይ ግዛቶች ጨምሮ በመላ አገሪቱ የሚገኙ የሩዝ ሰብሎች በዝናብ እጥረት ሳቢያ በቡቃያው አርረዋል፡፡ አገሪቱ በክፍለ ዘመኑ የከፋ ባለችው ድርቅ መመታቷንና በግብርና እንቅስቃሴዋ ላይ ከፍተኛ ጥፋት መድረሱን ያስታወቀች ሲሆን፣ ድርቁ ተመድ ከአምስት አመት ዕድሜ በታች ከሚገኙ ሶስት ህጻናት አንዱ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ የመቀጨጭ ችግር ተጠቂ እንደሆነ ባረጋገጠባት ሰሜን ኮርያ ላይ የከፋ ጥፋት ያስከትላል ተብሎ እንደሚሰጋ ጠቁሟል፡፡  
ባለፉት 30 አመታት የአገሪቱ ታሪክ ዝቅተኛ የተባለው የዝናብ መጠን ባለፈው አመት መመዝገቡ፣ ለድርቁ መከሰት በምክንያትነት የተጠቀሰ ሲሆን፣ ሩዝ በቂ ውሃ ካላገኘ በአግባቡ ማደግ አለመቻሉና የዝናብ እጥረቱ መቀጠሉ አደጋውን የከፋ እንደሚያደርገው ይጠበቃል ተብሏል፡፡ የአገሪቱ አርሶ አደሮች የውሃ ፓምፖችን በመጠቀም ሰብሎቻቸውን ውሃ እንዲያጠጡና ከጥፋት እንዲታደጉ የሚያበረታታ አገር አቀፍ ዘመቻ መጀመሩም ታውቋል፡፡

Read 1336 times