Saturday, 20 June 2015 11:40

ዕጣ ፈንታ!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(7 votes)

እሣት እንደናፈቀው ምድጃ ፊቱ ቀዝቃዛ ነው። አይኖቹ እሣት አይወረውሩም፡፡ ይልቅ በረዶ ይረጭባቸዋል፡፡ ጥርሶቹ ብዙ ጊዜ ባይገለጡም አንዳንዴ ለቀቅ ሲያደርጋቸው፣ ክርክም ብለው የተደረደሩ ናቸው፡፡ ግን የትምባሆ ጢስ ፈርሞባቸው ያን ያህል ትኩረት አይስቡም፡፡
መርመራ ዳንሣሞን ያለ መጥረቢያ ማየት ይናፍቃል፡፡ ጧት ሻይ ቤት፣ ቀን ሥራ ቦታ፣ ምሽት አረቄ ቤት ሲቆይ ወይም ወደ ቤቱ ሲገባ ትከሻው ላይ ጣል አድርጐት ነው፡፡ መጥረቢያው እንጀራው፤ የሕይወቱ ዋልታና ማገር ነው፡፡
ልጁ ቢላሎም አንዳንዴ ከርሱ ጋር አብሮ ይወጣና ሽንብራ ከሱቅ ገዝቶ ወደ ቤት ይልከዋል፡፡ ሌላም ጊዜ “ቢጤ” የሚባለውን ለምግብነት የተዘጋጀ ቆጮ ወደ እናቱ የሚያደርሰው ያው ልጁ ቢላሎ ነው።
ቁመናው ዘለግ ያለ፣ እግሩ ጫማ ያለመደ፣ ልብሱ ላብ የጠገበ፣ አቧራ የቃመ ነው፡፡ በዚያ ላይ የቀናው ዕለት ግሥላ ሲጋራ፣ ያጣ ቀን ደግሞ ትምባሆ በወረቀት ጠቅልሎ ስለሚያጨስ ጠረኑን ተጋርቷል። ኑሮ ኑሮ የሚመሥለውም ግሥላ ያጤሰ ቀንና አረቄ መጠጫ ያገኘ ጊዜ ነው፡፡ ያኔ ሠላምታው ሁሉ ሞቅ ያለ ነው፡፡
ጧት ለሥራ ሲወጣ አፉ ላይ የሚያደርጋት ቂጣ እንኳ ባይኖር፣ በምራቁ አጥፍቶ ጆሮው ላይ በቁጠባ የሰካትን ትምባሆ ምጎ ቀኑን አሃዱ ይላል፡፡
ባለቤቱ ታደለችም ከእሱ የባሰች ናት፡፡ ቤተሰቦችዋ አልቀው፤ ሰው ቤት እየዞረች ሥራ ስትሰራ አግኝቶ ነው ያገባት፡፡ የመጀመሪያ ልጅዋን ቢላሎን ስትወልድ፣ ደጓ ጐረቤታቸው ወይዘሮ አስካለ ባይኖሩ ጉድ ፈልቶ ነበር፡፡ እንጀራ እየፈተፈቱ፣ ቡና እያፈሉ “እኔን የማርያም አራስ!” በማለት ከርህራሄ ጋር አርሰዋት ነበር፡፡ አሁን ግን እሣቸውም ደኸዩ፡፡ ባላቸው ከሞቱ በኋላ ቤታቸው መቅኖ ራቀው፡፡ ከመርመራ ቤት ለዓመል ያህል ይሻላል እንጂ እንደ ድሮ ብዙ ትሩፋት የለውም፡፡ እንዲያም ሆኖ ወይዘሮ አስካለ አሁንም ደግ ናቸው፡፡ ዛሬም ለሰው ይራራሉ፡፡ ያለቻቸውን ቆርሰው ያካፍላሉ፡፡ መሃን ስለሆኑ ወደ ቤተክርስቲያን ባያደሉ ኖሮ ጠጅ መጣል ይዋጣላቸው ነበር፡፡ ግን ባላቸው ሲሞቱ “የታባቱ ለዚህ ከንቱ ዓለም” ብለው ፊታቸውን ወደ ቤተስኪያን አዞሩ፡፡
መርመራ ማታ ሲገባ ተበሳጭቶ እንደነበር ሚስቱ አስታውሳ፤ “አይዞህ የታባቱ ፈጣሪ ያለው ይሆናል!...ዛሬ ብታጣ ነገ ታገኛለህ፡፡ ጤና ብቻ ይስጠን” ብላ አረጋግተው ነበር፡፡ እንጨት የሚያስፈልጠው ሰው እንዳላገኘ ገብቷታል፡፡ አንዳንዴ እንዲህ እንደሚሆን ሁለቱም ያውቁታል፡፡ የቀናው ዕለት ያም ያም… ናልኝ… ናልኝ ይለዋል፡፡ ዕድል ስትጠምበት ደግሞ ሁሉም ፊቱን ያዞርበታል፡፡ ያኔ ኩርምት ይላል። በተለይ ትምባሆዋን ሲያጣ ሞት ያስመኘዋል፡፡ ደግነቱ የሱስን ነገር የሚያውቅ ሰው አያልፈውም፡፡
ዛሬ ጧት ሲወጣ ግን የማይደፈር ነገር ሊደፍር ወስኗል፡፡ የማሕበረሰቡን ሕግ ሊጥስ ቆርጧል። እርሱ እየተራበ፣ አራስ ሚስቱ ሆድዋ እየጮኸ፣ ለአንድ ሀብታም የተለቀሰበት እንጨት በቁሙ ሲበሰብስ ቆሞ አይመለከትም፡፡ ዛሬ ይለይለታል፤ ብሏል ለራሱ፡፡ በሲዳማ ብሔር ለትልቅ ሰው ልቅሶ ተተክሎ የተለቀሰበት እንጨት ለማገዶ አይውልም፣ ሃራም ነው፤  እንደ ነውር ይቆጠራል፡፡ መርመራ ይህንን ከልጅነቱ ጀምሮ ያውቃል፡፡ ያደገበት ነው፡፡ ተወልዶ ያደገው ተፈሪ ኬላ ባለወልድ ቤተክርስቲያን አካባቢ ነው፡፡ ከትንሿ ከተማ ወጣ ብሎ ነው ዕድሜውን የገፋው፡፡
ረፈድፈድ ሲል ወይዘሮ አስካለ ሁለት ስኒ ቡና በሕፃናት ወተት መያዣ ቆርቆሮ እንዲሁም፣ ትንሽ ቁራሽ ቂጣ አፏ ላይ ጣል አድርገው ለአራስዋ አመጡላት፡፡
አራስዋ ሌላ የምትቀምሰው ነገር አልነበራትም፡፡ ልጅ ቢላሎ ለእናቱ ብሎ እንጂ ሻይ ቤት ሄዶ ቢላላክ፣ ዳቦና ሻይ አያጣም ነበር፡፡ ግን አራስ እናቱን መጋኛ እንዳይመታት ብሎ ፈራ፡፡ እናቱን ከሚያጣ ደግሞ ረሃብ ቢያኝከው ሺ ጊዜ ይመርጣል፡፡ ሁሌም ለእናቱ ይሳሳላታል፡፡
ወይዘሮ አስካለ ቡና ሲያመጡላት ለእሱ የመጣለት ያህል ነበር የተደሰተው፡፡ የእሳቸውን እግር መውጣት ተከትሎ እናቱ ጠራችው፡፡ ገብቶታል፤ ለምን እንደጠራችው፡፡ በሌላ ስኒ ቡና አድርጋ ከቂጣው ላይ ቆርሣ ሰጠችው፡፡
“በቃኝ ታዱ…አንቺ ብዪ እኔ አልራበኝም” አላት እየተግደረደረ፡፡
“ለምን አይርብህም? ማታም ጦም አይደል ያደርከው?”
ከቁራሹ ላይ ቆርሶ ጐረሰና መለሰላት፡፡
ዛሬ ማታ ግን መርመራ ባዶ እጁን አይመጣም። የዕድል ቀኑ እንደሆነ ጠዋት ሲወጣ ነግሯታል፡፡ ቀኑን በምጥ አሣልፈው መርመራን መጠባበቅ ያዙ። ወይዘሮ አስካለም ያለወትሯቸው ብቅ ሳይሉ ቀሩ፡፡
ቢላሎ ተንቆራጠጠ፡፡ ቢቸግረው አብዝቶ አረቄ ወደሚቀማምስባት ቤት ሄዶ አንዣበበ፡፡ አባቱ ግን አልነበረም፡፡ ከተማዋ ውስጥ ሞቅ ያለውን መጠጥ ቤት ሁሉ  አሰሰ፤ የለም፡፡ መርመራን የበላ ጅብ አልጮህ አለ፡፡ ወረድ ብሎ ወደ አበበ አድማሴ ግንብ ቤት ሲደርስ ግርግር አየ፡፡ የሆነ ሰው ወድቆ በመኪና እያፋፈሱ ያስገቡት ነበር፡፡
ቢላሎ ግን እርሱ አልታየውም፤ መኪናው ሲነሳ ቀልቡ ያረፈው መሬት ላይ የተበተነ ሽንብራ ላይ ነበር፤ እያፈሰ በሹራቡ ያዘው፡፡ ተስገብግቦ ሰበሰበው፡፡ በሞትና ሕይወት መካከል ያለን ሰው ሽምብራ በማፈሱ የተናደደው ሰውዬ “የማን አባቱ ባለጌ ነው!” ሲል አምባረቀበት፡፡
 “እንዴ…የራሱ የመርመራ ልጅ አይደል!” ሌላ ሰው በምፀት ተናገረ፡፡
እሱ ግን ሽንብራውን እንደያዘ በድን ሆኖ ቀረ፡፡
“አንተ አባትህ እኮ ነው የተገጨው፣ አንድ ሰውዬ ሲያባርረው የጎማ እራት ሆነ፤ አይተርፍም!”
ቢላሎ እየተንቀጠቀጠ ሽምብራውን ይዞ በረረ። ቤት ሲደርስ ግን ለእናቱ ምንም ትንፍሽ አላለም፡፡ ወዲያው ምጣድ ጥዶ በበቆሎ አገዳ ቆላና ሰጣት። በጣሳ የተቀመጠችውን ቡና ሞቅ አድርጐ አቀረበላት፡፡
አራስዋ እሷን ቀማምሣ ሕፃንዋን ማጥባት ያዘች።
አሁን ቢላሎ ልቡ አላርፍ አለ፤ ነፍሱ ባተተች። ዐይኑን እንባ ጋረደው፡፡ አባቱ ለእነርሱ ሆድ ሲባትል መኪና እንደገጨው ያውቃል፡፡ ሊወጣ ፈለገ፣ ደግሞ እናቱስ? ለማን ጥሏት ይሂድ? በዚህ ምሽት ይህን ጭራሮ ግርግዳ ጥሶ ጅብ ቢበላበትስ?
በዚህ መሀል ወይዘሮ አስካለ ከተፍ አሉ፡፡ “ቤቶች!” ከሌላው ቀን በተለየ ዘው ብለው ገቡ፡፡
“እሜት፤ እትዬ አስካለች” አለች ታደለች፡፡
“ሠላም ናችሁ?”
“ሠላም ነን!”
ምንም አዲስ ወሬ እንደሌለ ገባቸውና ቢላሎን ለብቻው ጠሩት፡፡ ፊቱ ኦና መስሏል፡፡
“የተሠማ ወሬ አለ እንዴ?”
“እናቴ እንዳትሠማ!” አለ ቢላሎ በፍርሃት እየተርበደበደ፡፡
“የአባትህን አደጋ ሠምተሀል?...ይርጋለም ሆስፒታል ተወስዷል፡፡”
አንገቱን አቀርቅሮ ዝም አለ፡፡
“ምን ይሻላል ታዲያ … እናትህ ደሞ ኋላ ለምን አልነገራችሁኝም ትለን ይሆን?”
“አሁን አይንገሯት!” አሮጊቷን ተማፀናቸው፡፡
ወይዘሮ አስካለ ቢላሎን ውጭ ትተውት ወደ ቤት ገቡ፡፡
ምሽቱን በሙሉ ልጅንም አባቱንም ጠበቁ፡፡ ሊነጋጋ ሲል አንድ መኪና መጥቶ ደጅ ላይ ሲቆም ታደለች ደነገጠች፡፡
“እትዬ አስካለ መርመራ አንድ ነገር ሆኗል?!” ስትል ሊያረጓጓት ሞከሩ፡፡ በርግጥ መርመራ ምንም አልሆነም። ድንጋጤ እንጂ ብዙ ጉዳት የለበትም ተብሎ የመጀመሪያ እርዳታ ተደርጎለት ነበር የመጣው፡፡
“እንኳን እግዜር አተረፈህ!” ብለው ተቀበሉት። መኪናዋም አጓርታ እንደ አመጣጧ ጠፋች፡፡  አሁን ቤት ውስጥ የጎደለው ቢላሎ ነው፡፡ የሄደበትን ለማንም አልተናገረም፡፡ ወ/ሮ አስካለ የአባቱ ነገር አልሆንለት ብሎት ሃኪም ቤት የሄደ መስሏቸው ነበር፡፡ እነታደለችን ተሰናብተው ወደ ቤታቸው ሊሄዱ ሲሉ ግን እውነቱን በዓይናቸው በብሌኑ አዩት። አንድ ጊዜ እሪታቸውን ሲያቀልጡት መርመራ ከቤቱ ተስፈንጥሮ ወጣ፡፡ ቢላሎ ጓሮ ያለው ዛፍ ላይ ተንጠልጥሏል፡፡ መርመራ ዛፉን ትክ ብሎ አየው፡፡ “ዛሬ ለመሸጥ የቆረጥኩት የለቅሶ ዛፍ ጣጣ ይሆን?” ብሎ አሰበ፡፡ ይህንን ግን ሌላም ጊዜ አድርጐታል። ዓይኑን ከዛፉና ከቢላሎ ላይ ሳይነቅል ግሥላውን አውጥቶ ለኮሰ፡፡

Read 3893 times