Saturday, 20 June 2015 12:36

ዘመናዊው ሃኪም ባህላዊ መድሃኒት ላይ አተኩረዋል

Written by 
Rate this item
(36 votes)

 ለ11 ዓይነት በሽታዎች ፍቱን መድሃኒት አለኝ ይላሉ
     በዕፅዋትና የባህል መድሃኒት ዘርፍ ለ25 ዓመታት ምርምር አድርገዋል
     ከጫት ወይን የሚሰራበትን መንገድ በምርምር ማግኘታቸውን ይናገራሉ
           ለዓመታት በተማሩበትና በሰለጠኑበት የማህፀንና ፅንስ ህክምና ሙያ በተለያዩ የመንግስትና የግል ሆስፒታሎች ረዘም ላለ ጊዜያት አገልግለዋል፡፡ ከዘመናዊው የህክምና ሙያ ጐን ለጐን በባህላዊ መድሃኒትና በዕፅዋት ዙሪያ የተሰሩ ጥናቶችንና ጽሑፎችን ይከታተሉ ነበር፡፡ በመከታተል ብቻ ግን አልተገደቡም፡፡ ከ25 ዓመታት በላይ በዕፅዋት ምርምር ላይ መስራታቸውንም ይናገራሉ፡፡ በምርመራቸውም ከአስራ አንድ ለሚበልጡ የተለያዩ ህመሞች ፈዋሽ የባህል መድሃኒቶችን እንዳገኙና በዚህም ወገኖቻቸውን ለመርዳት ፅኑ ፍላጐት እንዳላቸው ይገልፃሉ፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሳዬ ከእኚህ የባህል መድሃኒት አዋቂ ከዶክተር ኢያሱ ኃ/ስላሴ ጋር በዕፅዋቶች ላይ ስለአደረጓቸው ምርምሮች፣ ስለባህል ህክምናቸውና የወደፊት ዕቅዳቸው ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡

   እንዴት ነው ወደ ዕፅዋት ምርምር ዘርፍ የተሳቡትና ወደ ሙያው የገቡት?
ስለዕፅዋት የተፃፉ ጽሑፎችንና የምርምር ሥራዎችን የማንበብ ፍላጐትና ዝንባሌ ነበረኝ። ይህ ነገር ወደ ዕፅዋት ምርምር እንድሣብ፣ ስለ ‹0ፅዋቶች ዝርያ፣ አመጣጥና ጠቀሜታ ለማወቅ ፍላጐት እንዲያድርብኝ አድርጐኛል፡፡ ናይጀሪያ እየሰራሁ በነጀረበት ወቅት ፕሮፌሰር ላምቦ ከሚባል የታወቀ ሣይካትሪስት ሐኪም ጋር አብሮ የመሥራት ዕድል አግኝቻለሁ፡፡ ይህ ፕሮፌሰር ብዙውን ጊዜ በዕፅዋቶች ላይ ምርምር ሲያደርግና ሲጠቀም አየው ነበር፡፡
ይህ ሁኔታ እኔ ውስጥ ፍላጐት አሳደረብኝና ከእሱ ጋር እየዋልኩ ሁኔታውን ማጥናት ጀመርኩ። ናይጀሪያዎች በአንጐል መናወፅና ከሚጥል በሽታ ጋር በተያያዘ ብዙ ችግሮች ነበሩባቸው፡፡ በዚህ ፕሮፌሰር አማካኝነት ስለ እነዚህ በሽታዎች ብዙ ትምህርት አገኘሁ፡፡ እንግሊዝ አገር በነበርኩበት ጊዜም ለሪሰርች አንድ ትልቅ ላይብረሪ ስገባ የኢትዮጵያ ኸርባል ጥናቶች መጽሐፍ አገኘሁ፡፡ በአፄ ቴዎድሮስ ጊዜ እንግሊዞች ወስደውት እዛው ያስቀሩትና በብራና የተፃፈው “መፅሐፈ መድሃኒት” የተባለውን በዚህ ላይብረሪ ውስጥ አግኝቼ ፎቶ ኮፒ በማድረግ ወሰድኩት፡፡ እነዚህን መጽሐፎች ሳነብ፣ በአገራችን በዕፅዋት ላይ የተደረጉ ምርምሮች እምብዛም አለመኖራቸውን ስመለከት ወደሙያው የበለጠ እንድሣብና እንዳጠና ተገፋፋሁ፡፡ ወደ አገሬ ከተመለስኩም በኋላ በዚሁ ዘርፍ ላይ የበለጠ መመራመርና የተፃፉ ነገሮችን ማንበብ ማዘውተሬ ወደ ሙያው እንድገባ የተገፋፋሁበት ምክንያቶች ናቸው፡፡
በአገራችን ያለው የባህል ህክምና ዕድገት ምን ይመስላል? በዘርፉ በቂ ጥናትና ምርምር ተደርጓል ብለው ያስባሉ?
በአገራችን በባህል መድሃኒቶች ምርምር ላይ የተሰማሩ ሰዎች እምብዛም የሉም፡፡ ሙያውን በዘመናዊ መንገድ ለማሳደግና ባለሙያዎችም ሙያቸውን ለትውልድ እንዲያስተላልፉ ለማድረግ የሚሰራ ሥራ የለም፡፡ “ኢትዮጵያን ኸርባል ሂስትሪ ውስጥ ተፅፎ እንዳገኘሁት፣ በአገራችን እስከዛሬ ከ80ሺ በላይ የሚሆኑ የባህል መድሃኒት አዋቂዎች አሉ፡፡ እነዚህ የባህል መድሃኒት አዋቂዎች ሙያውን የሚተገብሩበት ሁኔታ ግን አሳዛኝ ነው፡፡ ባለሙያዎቹ በአብዛኛው መድሃኒቱን የሚሰሩት ከሰው ተደብቀው ነው፡፡ ጓሮ ገብተው ተደብቀው ሰርተው ነው ለሰው የሚሰጡት፡፡ ይህ ደግሞ የመድሃኒቱን ንፅህና በማሳጣት ህመምተኛውን ለከፋ ችግርና አደጋ የሚያጋልጥ ይሆናል፡፡
ከዚህ ሌላ ደግሞ ባለሙያዎቹ ሙያውን ለሰዎች ለማሳየት አይፈልጉም፡፡ ምኑ ከምኑ ጋር ተዋህዶ መድሃኒት እንደሚሆን ማሳወቅ ፈጽሞ አይፈልጉም፡፡ ልጅ ካላቸው ለልጃቸው አሊያም በጣም ለሚወዱት ሰው ነው ሙያውን የሚያወርሱት፡፡ ያለበለዚያ ሲሞቱ ሙያው አብሮአቸው ይሞታል፡፡ ይህ ደግሞ ሙያው እንዳያድግና የተሻለ ደረጃ ላይ እንዳይደርስ አድርጐታል፡፡ በየገዳማቱ፣ በየቤተክርስቲያናቱና በየመስጊዱ ውስጥ ተፅፈው የተቀመጡ የባህል ህክምናዎች አሉ፡፡ እነዚያን አውጥቶና አጥንቶ በግልጽ ህብረተሰቡ አንዲጠቀምበት የሚያደርግም ሆነ የሚያስተምር የለም፡፡
የኢትዮጵያ ምግብ ጥናት ድርጅት በዚህ ጉዳይ ላይ ሊያስመሰግነው የሚችል ተግባር አከናውኗል። በዚህ ጉዳይ ላይ በርካታ ጥናቶችን በማድረግ መጽሐፍም አሳትመዋል፡፡ ይህ ድርጅቱ ለህብረተሰቡ ያበረከተውን እጅግ ጠቃሚ የሆነ ነገር ነው፡፡ እዚያ መፅሐፍ ውስጥ የሌለ ነገር የለም፡፡ እኔ መጽሐፉን እንደማጣቀሻ ዋቢ (reference) ነው የምጠቀምበት። ኢትዮጵያ ውስጥ በየትኛውም አቅጣጫ ያሉ ብዙ ዓይነት ቅጠሎች ከፍተኛ የመፈወስ አቅም ያላቸው ናቸው፡፡ ይህንን ማጥናትና ማወቅ፣ ህብረተሰቡ የሚጠቀምበትን መንገድ ማመቻቸት… ለዘርፉ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብዬ አምናለሁ፡፡
የባህል ህክምና ከዘመናዊው ህክምና እኩል መሰጠት አለበት ብለው ያስባሉ? በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነትስ እንዴት ይገልፁታል?
የባህል መድሃኒት አሠራሩና ሁኔታው ከዘመናዊው ጋር ይመሳሰላል፡፡ ልዩነቱ የሚወስደው መድሃኒት መጠንና መድሃኒቱ የሚቀመምበት ሁኔታ ነው፡፡ የባህል መድሃኒቶች ክብራቸውን ይፈልጋሉ፡፡ ዕፅዋቶቹ የየራሳቸው ተፈጥሮአዊ ባህርይ ስላላቸው መድሃኒቶቹ የሚወዱትና የሚጠሉት ነገር አለ። መድሃኒቱን ስትወስድ፤ “ይህንን አታድርግ” ይህንን አድርግ ሊባል ይችላል፡፡ በዘመናዊም ይህ ነገር ያለ ነው፡፡ መድሃኒቶቹን ያረክሳል እየተባሉ የሚገልፁ ነገሮች አሉ፡፡ ዘመናዊ መድሃኒቶች በፋብሪካ ተዘጋጅተው የሚወጡ ስለሆነ ንፅህናቸው አስተማማኝ ነው፡፡ የባህል መድሃኒቶች ቅድም እንዳልኩሽ ተደብቀው የሚሰሩ በመሆናቸው የንፅህናቸው ጉዳይ አስተማማኝ የማይሆንበት ጊዜ ይኖራል፤ ሌላው የባህል መድሃኒቶች እንደ ዘመናዊዎቹ ሁሉ ከነርቭ ጋር ለተያያዙ ህመሞች በማሸትና በማሞቅ መፍትሔ ሊያስገኙ ይችላሉ። ለምሳሌ እኛ በማግኔቲክ ሲስተም፣ በሙቀትና ከዕፅዋት በተገኙ መድሃኒቶች በማሸት ብቻ ለወገብ ህመም መፍትሔ እያስገኘን ነው፡፡ ሴሎቹ እንዲከፈቱ እንዲፍታቱና ሥራቸውን በአግባቡ እንዲሰሩ ለማድረግ የሚያስችል ህክምና እየሰጠን ነው፡፡
ህክምናውን ለህመምተኞች ለመስጠት የሞከሩበት ሁኔታ የለም?
የመጀመሪያ ጥናትና ምርምር ያደረግሁት በወገብና በእግር ነርቮችና በአስም በሽታ ላይ ነበር፡፡ ይህንን አጥንቼ እንደጨረስኩ “ክርስቲና” በሚባለው የማህፀንና ፅንስ ህክምና ክሊኒኬ ውስጥ ህክምናውን መስጠት ጀመርኩ፡፡ ህክምናው የሚሰጠው በመቀባት ብቻ ነበር፡፡ የሚጠጣም ሆነ ሌላ ነገር አልነበረንም። የአስም ህሙማን መድኀኒቱን በአፍንጫቸው በመሳብ ብቻ ከህመማቸው የሚፈወሱበት መንገድ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት የታካሚው ቁጥር እየጨመረ መጣ፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ በማህፀንና ፅንስ ክሊኒኩ ውስጥ መጨናነቅን ፈጠረ፡፡ ህክምናውን በተለየ ክሊኒክ ውስጥ መስጠት እንደምንችል የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ቢነግረንም በወቅቱ ይህንን ማድረግ ባለመቻላችን፣ ክሊኒኩ ለተወሰነ ጊዜ እንዲዘጋ ተደረገ፡፡ ከዚያ በኋላ የማህፀንና ፅንስ ክሊኒኩ በድጋሚ ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የባህል ህክምናውን ለጊዜው አቆምነው፡፡
እስከዛሬ ለምን ያህል ሰዎች ህክምናውን ሰጣችሁ? ለምን ያህል ህሙማን የፈውስ መፍትሄ አስገኝተናል ብላችሁ ታስባላችሁ?
 በወገብ፣ በሪህ፣ በአስምና ተጓዳኝ ህመሞች ተይዘው ይሰቃዩ ለነበሩ ከ800 በላይ ለሚሆኑ ህሙማን ህክምናውን ሰጥተን ፈውስ አስገኝተናል፡፡ በእኛ የባህል መድኀኒት ታክመው ለዓመታት የቆየና ነቀርሳ የሆነ በአንገት ላይ የነበረ ከፍተኛ ቁስለት ሙሉ በሙሉ እንዲድንና ታማሚው ከችግሩ እንዲፈወስ አድርገናል፡፡ ይህ በህይወቴ ውስጥ ትልቅ ደስታን የሚሰጠኝና ሙያውን የበለጠ እንድወደው የሚያደርገኝ ጉዳይ ነው፡፡
አሁንስ ለምን ያህል በሽታዎች ፈውስ የሚሰጡ መድኀኒቶች አሏችሁ? መድኀኒቶቹ የሚወሰዱት በምን መልኩ ነው? የመድኀኒቶቹ አስተማማኝነትስ ምን ያህል ነው?
አስራ አንድ ለሚሆኑ የተለያዩ በሽታዎች መድኀኒቶች አሉን፡፡ መድኀኒቶቹ የሚወሰዱት ራስን ለችግር በማያጋልጥና በቀላል መንገድ ነው። እኛ የምንሰጠው መድኀኒት የሚበላ፣ የሚጠጣ፣ በሰውነት ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡ በአንገት .ላይ የሚደረጉ መድኀኒቶችም አሉን፡፡ ይህ እንግዲህ የሥነ ፍጥረት ምስጢር ነው፡፡ ዘመናዊ ሳይንስ ሊመልሰው የማይችል ነው፡፡ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ በመቀባት፣ በማሸት የሚሰጥ ህክምናም አለን፡፡ ከወይራ ዘይት ጋር እየተቀላቀሉ የሚሰሩ መድኀኒቶች አሉ፡፡ መድኀኒቶቻችን በሙሉ ግን የሚበሉ፣ የሚጠጡ አይደሉም፡፡ ወደሰውነት ውስጥ የሚገቡ መድኀኒቶች የሉንም፡፡
ይህንን ህክምና ለመስጠት የሚያስችል ፍቃድስ አግኝታችኋል?
አዎን! በማህበራዊና የግል አገልግሎት ዘርፍ ህክምናውን ለመስጠት የሚያስችለን ፈቃድ አግኝተናል፡፡ ለህክምናው መስጫ የሚሆን ክፍልም አዘጋጅተን ለህሙማን መድኀኒት እየሰጠን እንገኛለን፡፡
ለአገልግሎታችሁ የምትጠይቁት ክፍያ እንዴት ነው?
እኛ ቀድሞውኑ አላማ አድርገን የተነሳነው ከህሙማን ገንዘብ መሰብሰብን አይደለም። በዘመናዊ ህክምና መፍትሄ ያላገኙ ህሙማን በባህላዊ መድኀኒት መፈወስ የሚችሉበትን መንገድ ለማመቻቸት ነው፡፡ ለምንሰጠው ህክምና የምንጠይቀው ክፍያ እጅግ አነስተኛና ማንም ሰው በቀላሉ ሊከፍለው የሚችለውን ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በርካታ ህሙማንን ያለምንም ክፍያ በነፃ ስናክም የቆየንበት ሁኔታ ሁሉ ነበር፡፡ የእኛ ዓላማ ህብረተሰቡ በባህላዊ መድኀኒት በቀላሉ ጤናውን ማግኘት እንደሚችል ማሳየት፣ ስለባህል መድኀኒት በሚገባ እንዲያውቅና መድኀኒቱን በራሱ መጠቀም እንደሚችል ማሳወቅ፣ ስለዕፅዋቱ ምንነት፣ ጠቀሜታቸውና አሰራሩ፣ የሚያስከትሏቸውን የጎንዮሽ ጉዳቶች ሁሉ በዝርዝር ለህብረተሰቡ ማሳወቅ ነው፡፡
በዕፅዋትና ባህላዊ መድሃኒቶች ላይ ያደረጓቸውን ጥናትና ምርምሮች አስመልክተው ያዘጋጁት ፅሁፍ አለ?
አዎ፡፡ በዘርፉ ያደረግሁትን ምርምርና ጥናት ሁሉ በፅሁፍ የማስቀመጥ ልምዱ አለኝ፡፡ እንደውም “ባህላዊ መድኀኒትና የጤና አጠባበቅ” በሚል ርዕስ ስር ያዘጋጀሁትና ለህትመት ዝግጁ የሆነ ሦስት ጥራዝ ፅሁፍ አለኝ፡፡ አሁንም እያጠራቀምኩ ነው፡፡ ጊዜው ሲደርስ ወደ መፅሃፍነት ተቀይሮ ህብረተሰቡ እንዲያነበው፣ እንዲማርበትና በቀላሉ ጤናውን ለመጠበቅ የሚችልበትን መንገድ እንዲያውቅበት ለማድረግ እየተዘጋጀሁ ነው፡፡
በአገራችን የባህል መድኀኒቶች በስፋት የሚገኙባቸው አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው? በቀላሉ ከሚገኙና ለጤና ጠቃሚ ከሆኑ ባህላዊ መድኀኒቶች መካከል ጥቂቶቹን ቢገልፁልን?
በአገራችን በአብዛኛው የወይንአደጋ አካባቢ ባህላዊ መድኀኒቶች በስፋት የሚገኙባቸው አካባቢዎች ናቸው። በቆላና በደጋ አካባቢዎችም የሚገኙ መድኀኒቶች አሉ። በደብረዘይት ናዝሬትና አካባቢው መድኀኒቶቹ በስፋት ከሚገኙባቸው ቦታዎች የሚጠቀሱ ናቸው። እንደልብ ከሚገኙና በቀላሉ መፍትሄ ከሚሰጡን መድሀኒቶች መካከል ደግሞ እነ ዳማከሴ፣ ጤናአዳምና መሰል ነገሮች ይጠቀሳሉ፡፡ ለምሳሌ ሰናፍጭ ሁላችንም በቀላሉ የምናገኘው ለእባጭ ፍቱን የሆነ መድኀኒት ነው፡፡ እነዚህን በቀላሉ አግኝቶ በመጠቀም ብዙ ገንዘብ ሊያስወጡ ከሚችሉ ቀላል የጤና ችግሮች መፍትሄ ማግኘት ይቻላል።
ዕፅዋቶቹን በኮስሞቲክስ ደረጃ ለመሥራትና ጥቅም ላይ ለማዋል ያደረጋችሁት ሙከራ አለ?
ዕፀዋትን በኮስሞቲክስ ደረጃ ለማዘጋጀት የሚያስችል ጥናት አድርገናል፡፡ ለተለያዩ የቆዳ ችግሮችና ለማድያት የሚውሉ መድኀኒቶችንም ሰርተናል፡፡ ይህን በዘመናዊ መንገድ በኮስሞቲክስ ደረጃ ለመስራትና ጥቅም ላይ ለማዋል ሃሳቡ ቢኖረኝም መሟላት የሚገባቸው በርካታ ጉዳዮች ስላሉ አሁን ባለንበት ሁኔታ ይህንን ማድረግ አልቻልንም፡፡
በአንድ ወቅት ከጫት የወይን መጠጥ ሰርተው ከፍተኛ አድናቆትን አትርፈው ነበር? እሱ ጉዳይ የት ደረሰ?
ልክ ነው፡፡ እሱ ጉዳይ በአጋጣሚ የተደረገ ነበር፡፡ ለመድኀኒት የሚሆን ዕፅዋት ፍለጋ ወደ ደብረዘይት ስሄድ በአጋጣሚ አግኝቼ የገዛሁትን ጫት ወደ ወይን ለመለወጥ የሚያስችል ጥናት አድርጌና የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅሜ እጅግ በጣም ጥሩ ጣዕም ያለው ወይን ለመስራት ችዬ ነበር፡፡ ጉዳዩ በወቅቱ ብዙ ትኩረት ስቦ ነበር፡፡ ዶክተር በጫት ወይን ሰርቶ ህዝቡን ሊያሳብደው ነው ሁሉ ብለውኝ ነበር፡፡ የተሰራው መጠጥ ልዩ ጣዕም የነበረው ቆንጆ ነበር፡፡ ወይኑን የቀመሱ በርካታ ሰዎችም የሰጡኝ አስተያየት ይኸው ነበር፡፡ ግን ሥራው የሚሰራው በእጅ (ያለምንም ማሽን) በመሆኑ እጅግ አድካሚና ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚጠይቅ ነበር፡፡ እንደውም ወይኑ በተመረተ ሰሞን ከአሜሪካን አገር ስለዚሁ ጉዳይ ሊያነጋግሩኝ ሰዎች መጥተው ነበር፡፡ ስለአሰራሬ በደንብ ከጠየቁኝና ካጠኑ በኋላ ወደአገራቸው ሄደው ጫትን ወደ መርፌነት በመቀየር ከፍተኛ የአዕምሮ መናወፅ ላጋጠማቸው ህሙማን በመስጠት ህሙማኑ ከተያዙበት የጭንቀትና ድብርት ስሜት እንዲወጡ ለማድረግ ችለዋል፡፡ አሁን ከምን አደረስከው ላልሽኝ ሥራው ከፍተኛ ድካምና ጥንቃቄን የሚጠይቅ ሥራ በመሆኑ ለጊዜው እምብዛም አልገፋሁበትም፡፡
የማህፀንና ፅንስ ህክምና ሙያው በቃ ቀረ ማለት ነው?
ኧረ አልቀረም፡፡ ለምን ይቀራል፡፡ ለዓመታት የተማርኩበትና የሰለጠንኩበት ሙያማ አይቀርም፡፡ እሱንም እሰራለሁ፡፡ ግን ህብረተሰቡን ሴት ወንድ ሳይል ላገለግልበት የምችልበት ሙያ የባህል ህክምናው በመሆኑ በዚህ ሙያ የበለጠ ለመስራት እፈልጋለሁ፡፡  
የባህል መድኀኒት ዕውቀትና ጥበብ እንዲስፋፋ፣ ለመጪው ትውልድም እንዲተላለፍ መንግስት ምን ማድረግ አለበት ብለው ያስባሉ? በእርስዎስ በኩል ምን እያደረጉ ያሉት ጥረት አለ?
ኢትዮጵያ ውስጥ ከ80 ሺ በላይ የባህል መድኀኒት አዋቂዎች ያሉ ቢሆንም በማህበር ተደራጅተው ያሉት ግን ከዘጠኝ ሺህ የሚበልጡ አይደሉም፡፡ ይህ ነገር በስፋት ሊሰራበት የሚገባና ህብረተሰቡን፣ መንግስትንም ሆነ አገርን ሊጠቅም የሚችል ትልቅ ተግባር በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶት በአግባቡ ሊሰራ ይገባል ሌሎች አገራት ከባህል ህክምና እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ እያገኙ ነው፡፡ ለምሳሌ ጀርመን በዓመት ከ380 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ከባህል መድኀኒት ገቢ ታገኛለች፡፡ በአፍሪካ ውስጥ በስፋት የሚሰራባቸው አገራት ደቡብ አፍሪካና ሞሪሺየስ ዋንኞቹ ናቸው፡፡ እኛ ዕፅዋቱ እያለን፣ ሃኪሙ እያለን አልተጠቀምንበትም፡፡ ስለዚህ ይህን ዕድል በስፋት ለመጠቀም የሚያስችል ሁኔታ ማመቻቸት፣ ሙያው ለትውልድ እንዲተላለፍ ማስተማር፣ በፅሁፍ ማቆየት ያስፈልጋል፡፡ በግሌ ህብረተሰቡን ለማስተማርና በርካታ ፅሁፎች፣ በመፃፍ ሙያውን ለትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይ ነኝ፡፡

Read 21985 times