Saturday, 27 June 2015 08:28

እንግሊዝ በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ ኢትዮጵያን አስጠነቀቀች ተባለ

Written by 
Rate this item
(14 votes)

“የአቶ አንዳርጋቸው አያያዝ የአገራቱን ግንኙነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው”
- የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍሊፕ ሃሞንድ

   የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፊሊፕ ሃሞንድ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው በኢትዮጵያ በእስር ላይ የሚገኙት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የሚገኙበት ሁኔታና አያያዛቸው፣ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው ሲሉ ለኢትዮጵያ መንግስት ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን ዘ ጋርዲያን ዘገበ፡፡
አቶ አንዳርጋቸው የቆንስላ ድጋፍ ማግኘት በማይችሉበት ወይም ይግባኝ የመጠየቅ መብት ባላገኙበት ሁኔታ በግልጽ በማይታወቅ ስፍራ ከሰው ተነጥለው ለብቻቸው መታሰራቸውን ያወገዙት ውጭ ጉዳይ ሚነስትሩ፣ የኢትዮጵያ መንግስት በግለሰቡ ጉዳይ ላይ አፋጣኝ ማሻሻል እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፊሊፕ ሃሞንድ ባለፈው ረቡዕ ከኢትዮጵያው አቻቸው ከዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጋር በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ ዙሪያ በስልክ ባደረጉት ውይይት፣ ግለሰቡ እስሩን በህግ ለመቃዎም ዕድል ባላገኙበት ሁኔታ ከሰው ተነጥለው ላለፈው አንድ አመት በእስር ላይ መቆየታቸው ያሳስበኛል ብለዋል፡፡
አቶ አንዳርጋቸውን በየጊዜው ለመጎብኘት የምንችልበት ሁኔታ እንዲመቻችልን ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም፣ የኢትዮጵያ መንግስት ቃል ከመግባት ባሻገር ተገቢ ምላሽ ሊሰጠን አለመቻሉ አሳዝኖኛል ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ ላቀረብነው ጥያቄ ምላሽ አለመስጠቱ ተቀባይነት የለውም፣ በግለሰቡ ጉዳይ ዙሪያ ይህ ነው የሚባል መሻሻል አለመታየቱም ትልቅ ስፍራ የምንሰጠውን የሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው ሲሉ ለዶ/ር ቴዎድሮስ መናገራቸውንም ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር፣ ለአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እና ለቤተሰባቸው የሚያደርገውን
የቆንስላ ድጋፍ ለወደፊትም እንደሚቀጥል ሃሞንድ ተናግረዋል፡፡የአቶ አንዳርጋቸው ጠበቃ ቤን ኩፐር በበኩላቸው፤ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግለሰቡ ከሰው ተነጥለው መታሰራቸውንና መጎብኘት እንዳለባቸው በማረጋገጥ እስሩን መቃወሙ አስደስቶናል፣ ይሄም ሆኖ የእንግሊዝ መንግስት አቶ አንዳርጋቸው ከእስር ተለቀው ወደ እንግሊዝ በመመለስ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚገናኙበትን ሁኔታ እንዲያመቻችልን እንጠይቃለን ማለታቸውንም ዘገባው ጠቁሟል፡፡ የተመድ የስቃይ ጉዳዮች ምርመራ ልዩ ባለሙያ ጁዋን ሜንዴዝ በበኩላቸው፤ የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌን አያያዝ በተመለከተ ምርመራ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ
ለሁለቱም አገራት መንግስታት ማስታወቃቸውን ጋዜጣው ጠቁሟል፡፡

Read 7972 times