Saturday, 27 June 2015 08:31

የፎሪ፣ የፎሪ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(12 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ይቺን ስሙኝማ…ባል ሚስቱን… “እኔ ብሞት ሌላ ባል ታገቢያለሽ?” ሲል ይጠይቃታል፡፡ እሷም…
“በጭራሽ አላገባም፣” ትለዋለች፡፡
እሱም…
“ታዲያ ካላገባሽ ከማን ጋር ትኖሪያለሽ?” ሲል ይጠይቃታል፡፡ እሷም…
“ከእህቴ ጋር እኖራለሁ፣” ትላለች፡፡ አያይዛም… “አንተስ፣ እኔ ብሞት ሌላ ሚስት ታገባለህ!” ስትል ትጠይቀዋለች፡፡ ምን ብሎ ቢመለስላት ጥሩ ነው…“በጭራሽ፣ እኔም ከእህትሽ ጋር እኖራለሁ፡፡”
ልፊ ሲላት አንድ እንጨት አስራ አረፈች፡፡እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ነገርዬዋን ከነቢይ ላይ የተዋስኳት ነች፡፡ የሸገር የጨዋታ እንግዳ ላይ ከመዓዛ ጋር ሲጨዋወቱ የጥንት የስፖርት አስተማሪውን ትውስታ ሲያወራ የተናገራት ነች። የሆነ ጨዋታ ላይ አንዱ የቡድናቸው ተጫዋች ኳሷን እየገፋና እያታለለ ይገሰግሳል፡፡ አሰልጣኝም በሜዳው ጠርዝ እኩል እየሮጠ ያበረታታዋል፡፡ ታዲያላችሁ… ተጫዋች ሆዬ ከዳር ዳር ኳሷን ይዞ ሄዶ ጎል አጠገብ ይደርስና ኳሷን ይቀመስልሽ ይላታል፡፡ ኳስ ሆዬ ወደ ውጪ! ይሄኔ እኩል ሲሮጥ የነበረው አሰልጣኝ ይበሽቅና ተጫዋቹን በስም ጠርቶ ምን ቢለው ጥሩ ነው…
“የፎሪ፣ የፎሪ ቅድም አታወጣውም ነበር!” ምን ያድርግ…ትንፋሹን አስጨርሶት ጉድ ሲያደርገው!
እናማ….እኛም ትንፋሻችን እያለቀ ጉድ እየሆንን ዘንድሮ ‘የፎሪ፣ የፎሪ…’ የሚያሰኙ መአት ነገሮች አሉን፡፡
እግረ መንገዴን…ሚስት ትንሽ ሲደባብራት ትከርማለች፡፡ እናላችሁ…ወደ ሀኪም ዘንድ ሄዳ ትመለሳለች፡፡ ባልም…
“ዶክተሩ ምን አለሽ?” ይላታል፡፡ እሷም…
“አንድ ወር በባህር ዳርቻ፣ ሁለት ሳምንት በገጠር ነፋሻ ስፍራ፣ አንድ ሳምንት ደግሞ ከአገር ውጪ እንዳሳለፍ መከረኝ፣” ትለዋለች፡፡ ባልም አጉረምርሞ ዝም ይላል፡፡ ሚስትም…
“እሺ ውዴ፣ መጀመሪያ ወዴት ነው የምትወስደኝ?” ትለዋለች፡፡ ምን ቢላት ጥሩ ነው…
“ወደ ሌላ ዶክተር…”
ልፊ ሲላት አንድ እንጨት አስራ አረፈች!
እናላችሁ…“የፎሪ፣ የፎሪ…” የሚያሰኙ መአት ነገሮች አሉን፡፡ የሆነ መሥሪያ ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ይጠራል፡፡ ሠራተኛውም ስለ መቶ አንድ ችግሮቹ አለቆቹን ወጥሮ ሊይዝ “ይለያል ዘንድሮ…”
ምናምን እያለ ቀኑን ይጠብቃል፡፡ ታዲያላችሁ…በስብሰባው ቀን ጠዋት ምን ይሆናል… ‘አጣዳፊ
በሆነ ሥራ ምክንያት የዛሬው ስብሰባ ላልተወሰነ ጊዜ ተላልፏል’ የሚል ማስታወቂያ ይለጠፋል፡፡ አንድ ሳምንት ሙሉ ሲያምጥ የኖረ ሠራተኛ ሁላ እጢው ዱብ ይልላችኋል፡፡“የፎሪ፣ የፎሪ…” ማን ስብሰባ ጥሩ አላቸው! ነገርዬው እኮ… “ልፋ ያለው አንድ እንጨት ያስራል፣” አይነት ነው፡፡
የሆነች እንትናዬ በ‘አዲስ ጓደኝነት’ ትመጣለች። እናላችሁ…ማኪያቶ፣ ብላክ ፎረስት ኬክ፣ ቺዝ በርገር፣ ክትፎ ምናምን ስትጋበዝ ትከርማለች፡፡ አጅሬው ደግሞ…አለ አይደል… “ሁሉም ሙሉ፣ ሁሉ ዝግጁ” ይልና የ‘እነሆ በረከት’ ጥያቄ ያቀርባል፡፡ይሄኔ እሷዬዋ…“እኔ’ኮ ሌላ ሰው አለኝ፣” ትለዋለች፡፡ ምን! ሌላ ሰው ብሎ ነገር ምንድነው? ያ ሁሉ ቺዝ በርገርስ!… ያ ሁሉ ብላክ ፎረስት ኬክስ!... የዮሐንስ ክትፎስ!
ታዲያ “የፎሪ፣ የፎሪ…” መጀመሪያ የብላክ ፎረስት ኬኩ ጊዜ ሰው አለኝ አትልም ነበር!
ነገርዬው እኮ… “ልፋ ያለው አንድ እንጨት ያስራል፣” አይነት ነው፡፡እናማ…‘የፎሪ፣ የፎሪ…’ የሚያሰኙ መአት ነገሮች አሉን፡፡ ‘ከሐምሌ አንድ ቀን ጀምሮ ለመላው ሠራተኛ የሁለት ደረጃ የደሞዝ እድገት ይሰጣል’ ይባልና ሠራተኛ ሆዬ ቢጠብቅ ምንም፣ ቢጠብቅ ምንም፡፡ ታዲያላችሁ… ወደ መጋቢት አካባቢ አስቸኳይ ስብሰባ ይጠራና…“ድርጅቱ የበጀት እጥረት ስለገጠመው የደሞዝ እድገቱ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል…” ይባላል፡፡ ሠራተኛው እኮ ገና ለገና ገንዘብ
አገኛለሁ ብሎ ስንት ነገር በዱቤ ወስዷል!
‘የፎሪ፣ የፎሪ…’ መጀመሪያውኑ ማን ቃል ገቡ አላቸው፡፡ነገርዬው እኮ… “ልፋ ያለው አንድ እንጨት ያስራል፣” አይነት ነው፡፡ስሙኝማ…እግረ መንገዴን ይቺን ስሙኝማ…ሚስት ባሏን ምን ትለዋለች…
“ጋዜጣ በሆንኩ ብዬ እመኛለሁ፡፡” ባልም…
“ለምን?” ይላታል፡፡ እሷም…
“ምክንያቱም ቀኑን ሙሉ ይዘኸኝ ትውል ነበር፣” ትለዋለች፡፡ ባልም…
“እኔም ጋዜጣ ብትሆኚ ብዬ እመኛለሁ፣” ይላታል፡፡ እሷም…
“ለምን?” ትለዋለች፡፡ ምን ብሎ ቢመልስላት ጥሩ ነው…
“ምክንያቱም በየቀኑ አዳዲስ ጋዜጣ እይዛለሁ…” ብሏት አረፈ፡፡ ካላጣችው ማመሳከሪያ ማን በጋዜጣ
‘ተቀኚ’ አላት!
እናላችሁ “የፎሪ፣ የፎሪ…” የሚያሰኙ መአት ነገሮች አሉ፡፡‘ምግብ በአዲስ መልክ ጀምረናል’ ተብሎ ይለጠፋል፡፡ እናላችሁ… እኛም “እስቲ እንሞክረው...” ብለን እንገባለን፡፡ ሹሮ ሆዬ እንኳን ልትሻሻል ብሶባት አብሲት ነገር ሆና ትመጣለች፡፡ ቂ…ቂ…ቂ….
ሀሳብ አለን… አንዳንድ ምግብ ቤቶች ከሹሮ አብሲቱ ጋር ትንሿን ምጣድ አብራችሁ አቅረቡልንማ!
አሀ…አንደኛውን ጋግረን የሹሮ እንጀራን በጤፍ እንጀራ እያጣበቅን እንበላለና!
እናማ… “የፎሪ፣ የፎሪ…” መጀመሪያውኑ ማን… “ምግብ በአዲስ መልክ ጀምረናል…” ቅብጥርስዮ በሉ
አላቸው!
እግረ መንገዴን…አንዱ ምን አለ መሰላችሁ…“ወንዶች ‘ቅድሚያ ለሴቶች’ ብለው ሴቶችን ፊት ፊት የሚያስቀድሙት ለትህትና ሳይሆን መቀመጫቸውን ለማየት ነው” አለ አሉ፡፡ እንዴት፣ እንዴት አድርጎ ቢያስበው ነው! ነገርዬውማ፣
መቼስ ለምን ይዋሻል… አለ አይደል….እውነቱን ለመናገር እንኳ ‘ፊት፣ ፊታችን’ ሆኖልን አንገታችንን
መቶ ሰማንያ ዲግሪ እየጠመዘዝን ‘እሱኑ’ ስንገረምም አይደል እንዴ የምንውለው! ይሄ ‘ጂም’
የሚሉት ነገር ‘ከቦታው እያጠፋው’ አስቸገረን እንጂ!  ቂ…ቂ…ቂ…
እናማ…“የፎሪ፣ የፎሪ…” የሚያሰኙ መአት ነገሮች አሉ፡፡
ደግሞላችሁ…የእኔ ቢጤ ‘ጠሀፊ’ ነገር… “ምን የመሰለ አዲስ አሪፍ መጽሐፍ አውጥቻለሁና አንበቡልኝ…” ምናምን ነገር ሲደሰኩር ይከርማል፡፡ ከዛም አንባቢ እየሸመተ ማንበብ፡ ቢያነብ፣ ቢያነብ የተባለውን “አሪፍ…” ምናምን ነገር አያገኝም፣ ባዶ ይሆንበታል፡፡ (‘እንደ በፊቶቹ መጽሐፍት... ማለት ይቻላል፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…) ከዛማ የተበሳጨ አንባቢ... “ምን አለ በተወደደ ወረቀት ባይጫወቱበት... ምናምን አይነት አስተያየት ሲበዛ የኔ ቢጤው ‘ፉዞ’ ነገር ሆኖ ቁጭ ይልላችኋል፡፡ አሀ… መጀመሪያውኑ “የፎሪ፣ የፎሪ…”… አለ አይደል… “አሪፍ መጽሐፍ…” ምናምን ማን በሉ አለን!እናማ…“የፎሪ፣ የፎሪ…” የሚያሰኙ መአት ነገሮች አሉ፡፡ይቺን ስሙኝማ…ሴትዮዋ ባሏን ‘ይማግጣል’ ብላ ትጠረጥረዋለች፡፡ ትሄድና ሽጉጥ ትገዛለች።
በማግስቱ ባሏን ከምትጠራጠራት ሴት ጋር እጅ ከፍንጅ (‘መርፌና ክር’ ሆነው…) ትይዛቸዋለች። ሽጉጧን ታወጣና ራሷ ግንባር ላይ ትደግናለች፡፡ ይሄን ጊዜ ባሏ ራሷን እንዳትገድል ይለምናታል፡፡ እሷ ምን ብትለው ጥሩ ነው…“ዝም በል፣ ከሀዲ! የእኔን ጨርሼ ወደ አንተ ነው የምዞረው!” ከሞኝ እንትናዬ ይሰውራችሁማ፡፡
“የፎሪ፣ የፎሪ…” ማን ሽጉጥ ግዢ አላት! ቂ…ቂ…ቂ…
ይቺን ስሙኝማ…ሚስት ባሏን…
“ከመጋባታችን በፊት ስንት የሴት ጓደኞች ነበሩህ?” ስትል ትጠይቀዋለች፡፡ባል ዝም ብሎ ይቀመጣል፡፡ እሷም… “ምን ይዘጋሀል፣ ንገረኝ እንጂ!” ስትል ትጮህበታለች፡፡ እሱ ምን ይላል… “ረጋ በይ፣ ገና እየቆጠርኩ ነው፡፡ አ…አሥራ አራት፣ አሥራ አምስት…” ሲል እሷዬዋ ታብዳለች አይገልጻትም፡፡ “ማን ቁጠርልኝ አለህ!  ማን ስለ ሴት ጓደኞችህ አውራልኝ አለህ!” ምናምን እያለች ቤቱን ታምሰዋለች፡፡ አሀ…“የፎሪ፣ የፎሪ…” ማን “የሴት ጓደኞችህ…” ምናምን ብላ ነገር ቀስቅሺ አላት!እኔ የምለው…እንትና ተጠቃለልክ እንዴ! የምር ለካስ… “ውሽማ ሲቆይ ባል ይሆናል፣” የሚባለው እውነት ነውና!በገባህበት እግርህ ደግመህ እንዳትወጣና… “የፎሪ፣ የፎሪ…” አስብለህ እንዳታስተርተንማ፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…እናማ… “የፎሪ፣ የፎሪ…” የሚያሰኙን ነገሮች በዝተዋል፡፡
ደህና ሰንበቱልኝማ!

Read 2920 times