Saturday, 27 June 2015 09:20

ኢህአዴግ፣ ከቻይና ትችት ይገጥመዋል ብሎ ማን አሰበ?

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(12 votes)

መንግስት ሁሉም ላይ ገናና ሆነ”፤ “ኢንቨስትመንትና የገበያ ኢኮኖሚ አልተስፋፋም

    የኢትዮጵያና የቻይና መንግስታት፣ “በመሃላችን ነፋስ እንዳይገባ” የሚሉ የቅርብ ወዳጆች ይመስላሉ። አንዱ የሌላኛውን ስም በክፉ አያነሳም። አንዱ ሌላውን የሚያስከፋ ቃል አይወጣውም (ኢህአዴግ በአፍላ የስልጣን ዘመኑ፣ የያኔው ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ ከተናገሯት አንዲት ዓረፍተነገር በስተቀር)።
“የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል ድረስ እንደግፋለን” ነበር ያሉ አቶ ታምራት። ያኔ፣ ከኢህአዴግ መሪዎች አፍ የማይጠፋ የዘወትር አባባል ነው። ችግሩ ምንድነው? አቶ ታምራት ስለ ታይዋን ነው የተናገሩት።
የቻይና መንግስት ደግሞ፣ በታይዋን ጉዳይ እንዲህ አይነት ነገር መስማት ያሳብደዋል። በታይዋን ጉዳይ ላይ ድርድር አያውቅም። ከቻይና ጋር ለመቆራረጥ ካልፈለገ በቀር፣ የትኛውም መንግስት ለታይዋን የእውቅና ድጋፍ አይሰጥም። ኢህአዴግም ብዙ ሳይቆይ፣ “የራስን እድል... እስከመገንጠል” የሚባለው ነገር ለቻይና አይሰራም በማለት አስተባብሏል። ለቻይና የማይበጅ ከሆነ ለኢትዮጵያስ ታዲያ ለምን?  መጨረሻ ላይ፣ “ስለ ቻይና እኛ ምን አገባን?” በሚል ነው ኢህአዴግ ጉዳዩን በአጭሩ ዘግቶ የተገላገለው። ከአቶ ታምራት ያመለጠው ዓረፍተነገር አልተደገመም።
ከዚያ ወዲህ፣ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲና ኢህአዴግ እርስበርስ ሲደናነቁ ነው የምንሰማቸው፡፡ እንደ ታላቅና ታናሽ ወንድም ናቸው ብንልም ማጋነን አይሆንም። በሁለት በሦስት ዓመት በሚካሄደው የኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ፣ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ሃላፊዎች በተጋባዥነት እየመጡ፡፡ “ጓድ” “ጓድ” ሲባባሉ አይተናል።
ምን ይሄ ብቻ? የኢህአዴግ ካድሬዎች በየጊዜው ቻይና እየሄዱ የፖለቲካና የፓርቲ አደረጃጀት ስልጠና ይሰጣቸዋል፡፡ (አስገራሚው ነገር ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የቻይና መንግስት ላይ ቅሬታ ሲያቀርቡ አይደመጥም። እንደሚመስለኝ የኢህአዴግና የቻይና አይነት ግንኙነት ይመቻቸዋል፡፡ ቅሬታቸው በኢህአዴግ ቦታ እኔ መቀመጥ ነበረብኝ የሚል ነው፡፡)
በአጭሩ የቻይና ወዳጅነት፣ ኢህአዴግ የሚኮራበትና ተቃዋሚዎች የሚመኙት ነገር ነው ልንል እንችላለን፡፡
በዚህ መሃል፣ የቻይና መንግስት ኢህአዴግን በመተቸት ቅሬታ ሲያቀርብ አስቡት፡፡ ትልቅ ዜና አይደለም?
ግን እንደ ትልቅ ዜና ሲወራ አልሰማንም፡፡ ለምን? እሺ… ኢህአዴግ፣ “ከወንድም የቻይና መንግስት” እና “ከቻይና ኮሙኒስት ጓዶች” የተሰነዘረበትን ትችት ለመደበቅ እንደሚፈልግ አያጠራጥርም፡፡ “ገመናዬን አላሳይም” ቢል አይገርምም፡፡ ነገር ግን፣ ኢህአዴግን የሚቃወሙ ፓርቲዎች፣ ፖለቲከኞችና ምሁራንስ ለምን ዜናውን አይተው እንዳላዩ አለፉት? በድንጋጤ ክው ብለው፣ አንደበታቸው ተለጉሞ ይሆን?
እስቲ ይታያችሁ፡፡ “የፌደራል መንግስት በሁሉም ነገር ላይ ገናና ሆኗል” የሚል ትችት ከቻይና በኩል ሲመጣ በዝምታ ይታለፋል? “የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በእድገት ጐዳና እንዲቀጥል፤ ከአገር ውስጥና ከውጭ የሚመጣ የግል ኢንቨስትመንትን በአወንታ የሚያስተናግድ አመቺ ስርዓት አልተፈጠረም፡፡ የገበያ ኢኮኖሚ አልተስፋፋም” የሚል ወቀሳ ከቻይና መንግስት ሲሰነዘር ዝም ይባላል?
በቅርቡ የመጡት የቻይና አምባሳደር ይህንን ቅሬታና ትችት ለኢህአዴግ ባለስልጣናት እንዳቀረቡ ዘኢኮኖሚስት መጽሔት ገልጿል - ከምርጫው ማግስት ባወጣው ዘገባው፡፡
ቻይናን እንደ አርአያና እንደ መሪ ኮከብ የሚያዩ በርካታ መንግስታት ቢኖሩም፤ በአፍሪካ ምድር ኢህአዴግን የሚስተካከል እንደሌለ በመግለጽ ነው ዘኢኮኖሚስት ዘገባውን የሚጀምረው፡፡ በዚያው ልክ የቻይና መንግስት በካድሬ ስልጠና፣ በብድር እና በንግድ ዋና የኢህአዴግ አለኝታ ሆኗል፡፡
እንዲያም ሆኖ፣ የታሰበው ያህል ለውጥ አልመጣም። ከኤክስፖርት የሚገኘው ገቢ ባለፉት አምስት አመታት ንቅንቅ አላለም፡፡ ዘንድሮ ወደ 10 ቢሊዮን ዶላር ገደማ እንዲደርስ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ እዚያው 3 ቢሊዮን ደላር ገደማ ላይ ተኝቷል፡፡
ኤክስፖርትን የሚያሳድግ፣ በተለይም ደግሞ በየአመቱ ከዩኒቨርሲቲ የሚመረቁ በመቶ ሺ ለሚቆጠሩ ወጣቶች የስራ እድል የሚፈጥር የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ከመንፏቀቅ አልፎ ያን ያህልም መራመድ አልቻለም፡፡ ለምን? መንግስት ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት የፕሮጀክት እቅዶችን ስላላወጣ አይደለም፡፡
እንዲያውም፣ የመንግስት ፕሮጀክቶች ናቸው በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የገነኑት፡፡ ግን እንደተለመደው የመንግስት ፕሮጀክቶችን በመፈልፈል፣ በዚያው መጠን የሃብት ብክነትና ሙስና እንዲስፋፋ ከማመቻቸት ያለፈ ደህና ውጤት እንደማይገኝ ለአስር አመታት ያለ ውጤት የተጓተቱት የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክቶችን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
እናም፣ “ፌደራል መንግስት በሁሉም ነገር ላይ ገናና ሆኗል፣ የገበያ ኢኮኖሚ አልተስፋፋም” የሚል ቅሬታና ትችት ቢሰነዘር ተገቢ ነው፡፡ ምናልባት… ትችቱ ከቻይና መምጣቱ አስገራሚ ሊመስል ይችላል፡፡
ነገር ግን አስገራሚ አይደለም፡፡ የቻይና ባለስልጣናት የአገራቸውን ታሪክ ካልዘነጉ በቀር፣ ሁለት ዋና ቁም ነገሮችን ሊስቱ አይችሉም፡፡ ከ40 ዓመታት በፊት፣ ከአፍሪካም የከፋ ድህነት ተዘፍቃ በነበረችው የያኔዋ ቻይና ውስጥ፣ እስከ 20 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በረሃብ ማለቃቸውን ያስታውሳሉ፡፡ እና የቻይና የረሃብ ታሪክ እንዴት ተቀየረ? ይሄ አንደኛው ቁም ነገር ነው። የቻይና መንግስት ዛሬም ድረስ በአገሪቱ ኢኮኖሚ እና በዜጐች ኑሮ ላይ እጅጉን በአገሬም ገናና ቢሆንም፤ ከ40 አመት በፊት ግን በብዙ እጥፍ በሁሉም ነገር ላይ የገነነ እንደነበር አይረሱትም፡፡ ይሄ ሁለተኛው ቁም ነገር ነው። የግል ሃሳብ፣ የግል ንብረት፣ የግል ህይወት የሚባሉ ነገሮችን ጨርሶ ወደማጥፋት ደርሶ ነበር፡፡
“የህብረት ስራ ማህበር”፣ “የልማት ሰራዊት”፣ “የ1ለ5 አደረጃጀት”…በሚባለው አቅጣጫ እስከ መጨረሻው እስከ ጥግ ድረስ እንደመሄድ ማለት ነው፡፡
በያኔዋ ቻይና፣ በቃ…እያንዳንዱ ገበሬ በማህበር ተደራጅቷል፡፡ በግል ማሳ ማረስ፣ ሰራተኛ መቅጠር፣ አምርቶ መሸጥ ቀርቷል፡፡ የእርሻ ማሳ፣ የእርሻ ስራ፣ የእንስሳት እርባታም ጭምር፣ የእርሻ ምርት… ሁሉም የጋራ ሆኗል - የማህበር፡፡ አስተዋይ እና ፈዛዛ፣ ታታሪና ሰነፍ…እንደ እኩል ነው የሚታዩት፡፡ ሁሉም ነገር በማህበር ሆኖ የለ? አስተዋዩና ፈዛዛው በእኩል ድምጽ ውሳኔ ያስተላልፋሉ - ሃሳባቸው እኩል ባይሆንም፡፡ ታታሪውና ሰነፉ እኩል የስራ ሰዓት ያስመዘግባሉ - እኩል ሙያና ታታሪነት ባይኖራቸውም፡፡ እኩል ተሸምተው ምርት ይካፈላሉ - የማምረት ብቃታቸው እኩል ባይሆንም። ከጋራ ምርት ብዙ ድርሻ ለመውሰድ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሽሚያ አይገርምም - ይህንን የሚዳኙ ራሽን አከፋፋይ ቢሮክራቶች ይፈጠራሉ፡፡ የጋራ ስራ ላይ ግን የመሻማት ልምድ ሳይሆን የመለገም ልምድ ነው የሚስፋፋው - ይህንን የሚቆጣጠሩ  ካድሬዎች ይፈጠራሉ፡፡
ታታሪና ሰነፍ እኩል ምርት የሚሻሙበትና በስራ መለገምን የሚያስፋፋ ስርዓት በሰፈነባት በያኔዋ ቻይና፣ ድህነት ተባብሶ ሚሊዮኖች በረሃብ አልቀዋል፡፡
ብዙዎቹ ኮሙኒስት ካድሬዎች ለዚህ ደንታ አልነበራቸውም፡፡ እነሱን የሚያስጨንቃቸው ሌላ ነገር ነው፡፡ ለምሳሌ ከአንዲት የገጠር መንደር የተላከ መረጃ ምንኛ እንዳስቆጣቸው ተመልከቱ፡፡ የትንሿ መንደር ነዋሪዎች ምን አጠፉ? ገናናው መንግስት ባዘዛቸው መሰረት በማህበር ተደራጅተዋል - ሁሉም ነገር የጋራ ነው ተብሏል፡፡ ነገር ግን፣ በጋራ እየሰሩ በጋራ ምርት የሚከፋፈሉ ይመስላሉ እንጂ፣ በሚስጥር የእርሻ ማሳ ለየብቻ ተከፋፍለው በግል ማረስና ማምረት ጀምረዋል። ለይምሰል ተሰብስበው የስራ እቅድና የምርት ክፍፍል ላይ ውሳኔ ያስተላልፋሉ፡፡ ነገር ግን የየግላቸውን አቅምና አላማ ይዘው፣ የግል እቅድ እያወጡ ነው የሚሰሩት፡፡ የስራ ተቆጣጣሪ የለም፡፡ ሁሉም ለራሱ ሲል ነው ተግቶ መስራት ያለበት፡፡
የስራ ውጤታቸውንና ምርታቸውንም ይወስዳሉ - ሽሚያ የለም፡፡ ራሽን የሚያከፋፍል ካድሬም አያስፈልጋቸውም፡፡
እንግዲህ ብዙ መቶ ሚሊዮን ህዝብ ባላት አገር ውስጥ፣ ይሄው የትንሿ መንደር ነዋሪዎች ድርጊት እንደ ትልቅ ወንጀል ተቆጥሮ፣ እንደ ትልቅ የአገር ክህደት ታይቶ ነው ጉዳዩ ለፕሬዚዳንቱ እስከመቅረብ የደረሰው። “አብዮታዊ እርምጃ” እንዲወስድባቸም ሃሳብ ቀርቧል፡፡
የፕሬዚዳንት ዴንግ ዚያዎፒንግ ውሳኔ ግን፣ “እስቲ፣ ምንም እንዳላወቅን ዝም እንበላቸውና የት እንደሚደርሱ እንያቸው” የሚል ነበር፡፡ እውነትም፣ እየቆየ ሲታይ የመንደሪቷ ነዋሪዎች በክህደት ወንጀል የአገሪቱን መንግስት አላስወገዱም፡፡ ረሃብን ነው ያስወገዱት፡፡
በአጭር ጊዜ ውስጥ የአብዛኛው ነዋሪ ምርትና ኑሮ ተሻሻለ፡፡ ፈዛዛው ነዋሪ የአስተዋይ ጐረቤቱን ሃሳብ ስብሰባ ላይ በክፋት በማፍረስ ለመርካት አይጣጣርም። ይልቅስ፣ ከአስተዋይ ጐረቤቱ የመማር እድል ያገኛል፡፡
ሰነፉ ሰውዬ አዳዲስ የዳተኛና የልግመኛ ዘዴዎችን እየፈለፈለ፣ በታታሪ ጐረቤቱ ልፋት ከተገኘው የጋራ ምርት የበለጠ ድርሻ ለመውሰድ የሽሚያ ተንኮል ሲሸርብ አያድርም፡፡ ይልቅስ፣ የታታሪ ጐረቤቱን ምርታማነት እያየ አርአያነቱን ተከትሎ ለስራ የመነሳሳት እድል ያገኛል፡፡
የዚያች መንደር ነዋሪዎች፣ ከጋራ ድህነት ተገላገሉ። ሁሉም እንደየአቅሙና እንደየጥረቱ በግል እያመረተ ህይወቱን የማሻሻል እድል አገኘ፡፡ ዚያዎፒንግ የዛሬ 40 ዓመት የዚህችን መንደር ታሪክ ነው በመላ አገሪቱ እንዲደገምና የገበያ ኢኮኖሚ እንዲስፋፋ መንገድ የጠረጉት፡፡ እስከዛሬም አልተቋረጠም፡፡ እናም የመንግስት ገናናነት ሙሉ ለሙሉ ባይወገድም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ፣ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሙሉ ለሙሉ ባይሰፍንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ከግል ኢንቨስትመንት ጋር እየተስፋፋ፤ ቻይና ባለፉት 30 ዓመታት በብልጽግና ጐዳና ትልቅ ለውጥ አስመዘገበች፡፡ ይህንን በቅጡ የሚገነዘብ ሰው፤ የቻይና መንግስት ኢህአዴግን መተቸቱ፣ “የፌደራል መንግስት ገናናነት በዛ”፣ “የገበያ ኢኮኖሚና የግል ኡንቨስትመንት አልተስፋፋም” የሚል ወቀሳ ማቅረቡ አስገራሚ አይሆንበትም፡፡
ደግሞም ካሁን በፊት ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ትችት አይደለም፡፡
ከ25 ዓመት በፊት ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማርያም ተመሳሳይ ትችት አጋጥሟቸዋል፡፡ ለጉብኝት ወደ ቻይና ያቀኑት ኮ/ል መንግስቱ፣ “ጓድ…ጓዶች…” እየተባባሉ ነው ከቻይና ባለስልጣናት ጋር የተወያዩት፡፡
የጦር መሳሪያ እንደሚፈልጉ የተናገሩት ኮ/ል መንግስቱ፣ የብስክሌት ፋብሪካ ለመክፈትም እርዳታ ስጡኝ የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ከቻይና ጓዶች ያገኙት ምላሽ ግን ትችት ነው፡፡  የፕሬዚዳንቱ ተግሳፅም ተጨምሮበታል፡፡ መንግስት የገነነበት የኮሙኒዝም ኢኮኖሚ ለኢትዮጵያም ሆነ ለሌሎች አገራት እንዳልበጀ የገለፁት የቻይና ፕሬዚዳንት፣ ኮሙኒዝምን ከመዘመርና የመንግስት ፋብሪካ ለመክፈት ከመሯሯጥ ይልቅ ለአገርህ የሚበጃት የግል ኢንቨስትመንትና የገበያ ኢኮኖሚ ላይ ብታተኩር ነው የሚል ምክር ለግሰዋል - ለኮ/ል መንግስቱ፡፡ ደግሞስ፣ ተራራ በበዛበት አገር የብስክሌት ፋብሪካ ለመክፈት መሯሯጥ ምን ትርጉም አለው?
ኮ/ል መንግስቱ፣ ከወንድም የቻይና መንግስት በተሰረዘባቸው ትችትና በጓዶች ተግሳፅ አልተደሰቱም፡፡
ግን ጥሩ ምክር ነበር ያገኙት፡፡ አመት ሳይቆይ ነው፤ ዋና የኮሙኒዝም አቀንቃኟ ሶቭዬት ህብረትና አጃቢዎቿ የምስራቅ አውሮፓ መንግስታት በኢኮኖሚ ቀውስ ሲዳከሙ ቆይተው የተንኮታኮቱት፡፡
ቻይና አልተንኮታኮተችም፡፡ ምን ለማለት ፈልጌ ነው? መንግስት ያልገነነበት የገበያ ኢኮኖሚ፣ ብቸኛው የብልጽግና መንገድ እንደሆነ ያሳየች ቀዳሚዋ አገር አሜሪካ እያለች ቻይናን እንደ ዋና አርአያ ማየት ስህተት ቢሆንም፤ ከቻይና ታሪክ ጠቃሚ ቁምነገር መማር እንችላለን፡፡
“የመንግስት ገናናነነትን መቀነስ፣ የግል ኢንቨስትመንትንና የገበያ ኢኮኖሚን ማስፋፋት ይበጃችኋል” የሚለው የቻይና መንግስት ምክርም ጥሩ ነው፡፡ ኢህአዴግ ጥሩ ምክር ሲያጋጥመው መስማት አለበት፡፡ ሊያስብበት ይገባል፡፡ ተቃዋሚዎችም በበኩላቸው ትንሽም ይሁን ትልቅ፣ ኢህአዴግ ጠቃሚ ምክሮችን አገናዝቦ እንዲቀበል ግፊት ማድረግ አለባቸው። የኢኮኖሚ ነፃነት አስተማማኝ የብልጽግና መንገድ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ውሎ አድሮ ለፖለቲካ ነፃነትም አጋዥ ይሆናል፡፡     

Read 3480 times