Saturday, 27 June 2015 10:13

በናይጄሪያ ሴናተሮች የራሳቸውን ደሞዝ ለመቀነስ ህግ አረቀቁ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በናይጄሪያ መንግሥት ከፍተኛ ተከፋይ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የህግ አውጪ ባለሙያዎች (ሴናተሮች) የገዛ ራሳቸውን ደመወዝ ለመቀነስ የሚደነግግ ህግ ለማፅደቅ ሀሳብ እንዳቀረቡ ሮይተርስ ዘገበ፡፡
ናይጄሪያ የህግ አውጪ ሆነው የሚሰሩ 469 የከፍተኛ ፍትህ አባላት አሏት፡፡ እነዚህ ህግ አውጪዎች በዓመት የሚቀበሉት የደመወዝና ጥቅማ ጥቅም በጀት በሀገሩ ላይ ያሉት 36 ክልሎች በአመት ከሚመደብላቸው ገንዘብ የበለጠ እንደሆነ ማወቅ ተችሏል፡፡ እነዚህ ክልሎች በአማካይ እያንዳንዳቸው ከሚሊዮን ነዋሪዎች በላይ የሚያስተዳድሩ ናቸው፡፡  
 ለአስር አመታት ያህል በተለይም ከአለፉት አራት አመታት ጀምሮ የናይጄሪያ ኢኮኖሚ ባሽቆለቆለው የዓለም አቀፍ ነዳጅ ገበያ መንስኤነት አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱን ሮይተርስ ጠቁሟል፡፡ የናይጄሪያ መንግስት የሚተዳደረው ነዳጅ ተሸጦ ከሚገኘው ቀረጥ በመሆኑ፣ ከወደቀው የዓለም ነዳጅ ዋጋ ጋር የመንግስት የበጀት አቅምም ላሽቋል፡፡ በዚህም ምክኒያት በሌጎስ የሚገኝ ገለልተኛ ተቋም ቡድን የነዋሪዎቹን የገንዘብ አወጣጥ በቅርብ ሆኖ እየገመገመ ይገኛል፡፡
የዚሁ ተቋም መስራች የሆነው ኦሊሲዮን አጓበንዴ፤ ከሌላው መንግስታዊ ተከፋይ በተለየ ሁኔታ ገንዘብ የሚያገኙትን የፍትህ ስርዓት ባለሙያዎች፣ የህዝብ አገልጋይ መሆን ሲገባቸው ከመጠን ያለፈ የመንግስት በጀት ተጠቃሚ መሆናቸውን በመጠቆም አቤቱታ ያሰማል፡፡
ባለፈው ሳምንት በሌጎስ የወጣው ዴይሊ ሪፖርት፤ እያንዳንዱ የሴኔት አባል በዓመት ለልብስ መግዣ እንዲሆነው 105 ዶላር እንደሚሰጠው ዘግቧል፡፡ ባለፈው ሚያዚያ አዲሱን የፕሬዚዳንት ወንበር የተረከቡት ሞሀመድ ቦሀሪ፤ በሀገሪቱ ላይ የተንሰራፋውን የአባካኝነት ባህል እንደሚለውጡ ቃል መግባታቸው ይታወሳል፡፡ የሀገሪቱ ብሔራዊ ምክር ቤት አባላትም ከፕሬዚዳንቱ ጋር ሆነው ለመስራት በከፊል ተስማምተዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የህግ አውጪ ባለሙያዎቹም የፕሬዚዳንቱን አቋም በመደገፍ የሚከፈላቸውን ወርሀዊ ደሞዝ ዝቅ ለማድረግ ሀሳብ ማቅረብ ጀምረዋል፡፡ ከሀሳብ አቅራቢዎቹ መካከል የኮጂ ክልል ተወካይ በሰጠው አስተያየት፤ “በመንግስት ወጪ የተትረፈረፈ ህይወት ከእንግዲህ ልንመራ አንችልም” ሲል ተደምጧል፡፡ “የናይጄሪያ ህዝብ ይኼንን የደመወዝ አከፋፈል በአንድ ድምፅ ማውገዝ ይኖርበታል” ብሏል፡፡
በ2013 (እ.ኤ.አ) የአንድ በዝቅተኛ እርከን ላይ የሚገኝ ሴናተር (ህግ አውጪ) ዓመታዊ ገቢ 13,000 ዶላር ነበር። ግን በዚህ ደመወዙ ላይ ለመኖሪያ ቤት፣ ለቤት ቁሳቁስ እና መሰል ጥቅማጥቅሞች ከሚፈቀድለት ተጨማሪ ገቢ ጋር ተዳምሮ ወደ 115,000 ዶላር በዓመት እንደሚያገኝ የናይጄሪያ ጋዜጦች ጽፈዋል፡፡  
ከ2013 በኋላ ተጨማሪ ጥቅማ ጥቅሞች ተፈቅደውላቸዋል፡፡ ለምሳሌ፤ የውሎ አበል 930 ዶላር በእየለቱ፣ እንደዚሁም በየአራት ወሩ ደግሞ 38, 000 ዶላር --- በአመታዊው ደሞዝ ላይ ተጨማሪ መውሰድ ይችላሉ፡፡  
ከእነዚህ የህግ ባለሙያዎች የተጋነነ ደመወዝ ጋር የሀገሩ ዝቅተኛ የገቢ መጠን ሲነፃፀር በጣም ማስደንገጡ አልቀረም፡፡ የሀገሩ ዝቅተኛ ተከፋይ 18,000 ኒራ ወይንም 90 ዶላር በወር ነው የሚያገኘው፡፡
በናይጄሪያ ያለ ሴናተር በአሜሪካ በዝቅተኛ እርከን የሚከፈል ሴናተር ከሚያገኘው ገቢ ጋር ሲነፃፀር … በመካከላቸው ጥቂት ልዩነት ብቻ እንዳላቸው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እንደ ናይጄሪያ አይነት 75 በመቶ የመንግስት በጀት ከዘይት ቀረጥ ላይ በሚተማመን ሀገር፤ የዓለም የነዳጅ ገበያ ሲያሽቆለቁል… እንደ ቀድሞው ተንደላቀው ህይወታቸውን የሚመሩ ባለስልጣናት በአንፃራዊ ሁኔታ መለወጥ እንዳለበት የሚያመለክት ነው፡፡ 

Read 2303 times