Saturday, 04 July 2015 10:43

ለካስ ሳናውቀው የኒዮሊበራሊዝም አቀንቃኝ ሆነናል!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(10 votes)

የኢህአዴግ ካድሬዎች ከባድ ግምገማ ይጠብቃቸዋል
“የጎረቤት አገራት የተቃውሞ ሰልፍ እናዘጋጃለን”

     የሆነስ ሆነና የጋዜጣው ዜና ምንድነው? የጦቢያ ልጆች አሜሪካንን በመውደድ ከዓለም በሶስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ በጥናት መረጋገጡን የሚጠቁም ዘገባ ነው፡፡ ታዲያ አሜሪካንን መውደድ ምን ችግር አለው ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ አያችሁ----የአሜሪካ አፍቃሪ ሆነን Top 3 ውስጥ ገባን ማለት፣ ቀንደኛ የኒዮሊበራሊዝም አቀንቃኝ ሆንን ማለት ነው፡፡ (ኒዮሊበራሊዝምና አብዮታዊ ዲሞክራሲ ደግሞ ሆድና ጀርባ ናቸው!)
እኔ የምለው ግን----ላለፉት 24 ዓመታት ከቻይና ልዩ የቴክኒክ ድጋፍ የሚደረግለት የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም በገነነበት አገር፣ (ወደፊትም እኮ መግነኑ ይቀጥላል ተብሏል!) እንዴት ነው የአበሻ ዘር የኒዮሊበራሊዝም አቀንቃኝዋን (አሜሪካን ለማለት ነው!) በመውደድ ከዓለም 3ኛ ነው የሚባለው? (አገሪቱም ህዝቡም እንቆቅልሽ ሆነው አረፉት!) ከምሬ እኮ ነው----ህዝብና መንግስት አይደማመጡም ማለት ነው? (ከመቼ ወዲህ እንዳትሉኝ!) ይሄ እኮ ለሰሚውም ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ መንግስት በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ነው የምመራው ይላል፤ የሚመራው ህዝብ ግን የለየለት የኒዮሊበራሊዝም አቀንቃኝ ሆኗል፡፡ (ደግነቱ  ምርጫው በድል ተጠናቋል!)  
እስቲ በመሃል ደግሞ ለዶክትሬቱ ጥናት ለመስራት አማራ ክልል ሰንብቶ የመጣ ወዳጄ ያወጋኝን ላውጋችሁ፡፡ ወዳጄ እዚያው ጥናቱን በመስራት ላይ ሳለ፣ አንድ የሚያከብራቸው ምሁር ይደውሉለትና፤
 “ጎረምሳው፤ በሰላም ነው  የጠፋኸው?” ሲሉ ይጠይቁታል፡፡
ወዳጄም ጨዋታ አምሮት፤ “ምን ባክዎ---የአገሪቱን ችግር ለመፍታት ጥናት እያካሄድኩ ነው” ሲል ይመልስላቸዋል፡፡
ምሁሩም አንዴ ሳቃቸውን በረዥሙ ለቀቁትና፤ “አንተ ዝም ብለህ መመረቂያህን ሥራ ባክህ---እኛ ኢህአዴግን 100 ፐርሰንት የመረጥነው እኮ የአገሪቱን ችግር ይፈታልናል ብለን ነው!” ብለው በሳቅ አፈረሱኝ ሲል አወጋኝ (እኔም ሳቄን ለቀቅሁት!)
  አሁን ወደ ጀመርነው አጀንዳ እንመለስ፡፡ በነገራችን ላይ (ይቅርታ አድርጉልኝና) ዝም ብዬ ስጠረጥር  --ህዝቡ ብቻ ሳይሆን አንዳንድ የኢህአዴግ አባላትም ልባቸው ከቻይና ይልቅ ለአሜሪካ የሚያደላ ይመስለኛል፡፡ (አይፈረድባቸውም!) አያድርገውና አንድ ቀን ፓርቲያቸውን ቢያኮርፉ ወይም ቢያኮርፋቸው  የምታስጠጋቸው አሜሪካ እንጂ ቻይና አይደለችም፡፡ ተሳስቶ ቻይናን የፖለቲካ ጥገኝነት የጠየቀ ባለሥልጣን አለቀለት፡፡ በቻይንኛ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ተሃድሶ ይሰጠውና በክብር ለመጣበት አገር መንግስት ተላልፎ ይሰጣል፡፡ (ደግነቱ ማንም እግሩን ወደ ቻይና አያነሳም!)
 ኢህአዴግ እንዳይሰማኝ እንጂ አሜሪካን በመውደድ የተሰጠን ደረጃ በደንብ ተጭበርብሯል (ኦባማ ሲመጡ ቅሬታዬን አሰማለሁ!) አሁን ማን ይሙት---- የፊሊፒንሶች ፍቅር ከእኛ አይሎ ነው ለእነሱ 1ኛ ደረጃ የተሰጠው? (“አያውቁንም” አለ ዘፋኙ!) እንዴ የጦቢያ ባለሀብት በሉት ባለስልጣን፣አርቲስት በሉት አትሌት…ሚስቱ ስታረግዝ የሚሽቀዳደመው እኮ የአሜሪካንን ቪዛ ለማግኘት ነው (ልጁ አሜሪካ እንዲወለድለት!) ሳይደርሰን ቀርቶ እንጂ የአሜሪካ ዲቪን ያልሞላ የጦቢያ ልጅ እኮ የለም፡፡ ታዲያ ከዚህ በላይ አሜሪካንን መውደድ አለ እንዴ?! (ፊሊፒንሳውያንማ በተዓምር አይደርሱብንም!)
በነገራችን ላይ ለአሜሪካ ያለን ፍቅር እኮ ዛሬ የተፈጠረ አይደለም፡፡ በደርግ ዘመንም ቢሆን ሶሻሊስታዊ ሥርዓት በአገሪቱ ላይ እናነግሳለን ብለው እርስ በእርስ የተፋጁት የዚያ ትውልድ አባላት… የማታ ማታ የተሰደዱት እኮ ሩሲያ ወይም ኩባ አልነበረም፡፡ አሜሪካ እንጂ! የሚገርመው ያኔም እንዳሁኑ ደርግ ሶሻሊዝምን ሲያቀነቅን፣ ሰፊው ህዝብ በልቡ ቀንደኛ የኢምፔሪያሊዝም አቀንቃኝ ነበረ (መንግስትና ህዝብ ሲሸዋወድ እኮ ነው የኖረው!)
የደርግ፣ ታሪክ ስለሆነ እንተወውና ወደ ዛሬው እንመለስ፡፡ እናላችሁ---እንደ እኔ ከሆነ ለህዝባችን የኒዮሊበራሊዝም አቀንቃኝ መሆን ዋነኛ ተጠያቂው ራሱ ኢህአዴግ ነው፡፡ ለምን መሰላችሁ? ፓርቲው ላለፉት 24 ዓመታት እንዴት አብዮታዊ ዲሞክራሲን በእኛ ውስጥ ማስረፅ አቃተው? (የኢህአዴግ ካድሬዎች 1ለ5 ብቻ ነው እንዴ የሚያውቁት?) ከምሬ እኮ ነው … ምድረ ካድሬ ታሪካዊ ግምገማ ያስፈልገዋል፡፡ (ህዝቡን ግን በተሃድሶ ጠበል መሞከር ነው!)
እኔ የምለው ግን--- ኢትዮጵያውያን ቻይናን በመውደድ ከዓለም ስንተኛ የምንሆን ይመስላችኋል? (የቀለበት መንገዳችን ባለውለታ መሆኗን እንዳትዘነጉ!) በዚያ ላይ ገደኛ ናት (ተዓምረኛው ባለ 2 ዲጂት ዕድገት የመጣው እኮ ቻይና ጦቢያን ከረገጠች በኋላ ነው!) እንደው ለጠቅላላ ዕውቀት ያህል---በመላው ዓለም እነማን ቻይናን እንደ ነፍሳቸው እንደሚወዱ፣ እነማን ደግሞ ዓይንሽን ላፈር እንደሚሏት ቢጠና ጥሩ ነው። (አሜሪካ ስፖንሰር ካደረገች እንጂ ቻይናማ ንክች አታደርገውም!)
አኔ የምላችሁ----ለውጭ ዜጎች የተቃውሞ ሰልፍ በክፍያ ተጀመረ እንዴ? ባለፈው ሳምንት ኤርትራውያን በአዲስ አበባ ያደረጉትን ሰልፍ አይቼ እኮ ነው፡፡ (በዶላር ከሆነ ያዋጣል!) በተለይ አፍሪካ ውስጥ ከሆነ የደራ ገበያ አለው፡፡ ይኸውላችሁ አብዛኞቹ የአፍሪካ መንግስታት አምባገነን ስለሆኑ እንኳን የተቃውሞ የድጋፍ ሰልፍም አይፈቅዱም። ያኔ የአፍሪካ ተቃዋሚዎች ተራ በተራ ወደ ኢትዮጵያ በመደወል፣ ለሚፈልጉት ቀን ሰልፉን ቡክ ያስደርጋሉ፡፡ (ዘመናዊ ማኔጅመንት ግን ይፈልጋል!) በአገራችን ተቃዋሚዎች ለምዶብን መስቀል አደባባይን ሲጠይቁ፣ እየለማ ነው ወይም ሌላ ቦታ ምረጡ፣ በሚቀጥለው እንጂ በዚህኛው ሳምንት አይቻልም ---- ምናምን አይሰራም (ይሄ እኮ ፖለቲካ ሳይሆን ቢዝነስ ነው!)   
የኤርትራውያንን የአዲስ አበባ የተቃውሞ ሰልፍ የተመለከቱ አንድ የአገራችን የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ምን አሉ መሰላችሁ? “ከዚህ በኋላ እኛም ጋና ወይም ቦትስዋና ሄደን የተቃውሞ ሰልፍ እናደርጋለን” (“ባቄላ ቀረ ቢሉ--” የምትለዋን ተረት የሚተርቱ ኢህአዴጎች አይጠፉም!) በነገራችን ላይ ኤርትራውያን በጣም ነው ያሳዘኑኝ (በየቀኑ 5ሺ ኤርትራውያን ይሰደዳሉ ነው የተባለው?) እንደ እነሱ በመሪው የተጭበረበረና የተካደ ህዝብ ያለ አይመስለኝም፡፡ መጀመሪያ ላይ እኮ --ወዲ አፈወርቂ የእያንዳንዱ ኤርትራዊ ጀግና (Hero!) ነበሩ፡፡ ዛሬ ከ24 ዓመት በኋላ ግን--- ኤርትራውያን የአገራቸውን መሪ በመጥላት ከዓለም ቀዳሚ ህዝቦች ሳይሆኑ አይቀሩም! (በኤርትራ ነጻነትም ባርነትም አልተቻለም!) አንጋፋው ኢትዮጵያዊ ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም እንዲህ ያለነውን ይመስለኛል - “መክሸፍ” የሚሉት፡፡  (የራሳችን ምሳሌ አጥቼ እንዳይመስላችሁ!)

Read 4129 times