Saturday, 04 July 2015 10:44

የሴት ልጅ ግርዛትን ማስቆም ፈታኝ ሆኗል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

ቤተሰቧና የአካባቢው ህብረተሰብ ለአምስት ቀናት ጭንቅ ውስጥ ነው የከረሙት፡፡ ባህላዊ መድሃኒቶችን ሲያደርጉና በየእምነታቸው ሲፀልዩ ሰንብተዋል፡፡ ደፍሮ ወደ ህክምና ተቋም የመውሰድ ሃሳብን የሰነዘረ ግን አንድም አልነበረም፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሴት ልጆች ላይ የሚፈፀም ግርዛት ወንጀል እንደሆነ ሲነገር ሰምተዋል። ለዓመታት ከዘር ዘር ሲወራረስ የመጣውንና ሁሉም ሲፈጽመው የኖረውን ይህን የግርዛት ተግባር ወንጀል ነው ብሎ አምኖ መቀበል ለአካባቢው ህብረተሰብ እጅግ ከባድ ነበር፡፡ እናም ድርጊቱን በድብቅ ይፈጽሙታል፡፡ እንዲህ እንደአሁኑ ዓይነት ፈታኝ ገጠመኞች ካልደረሱ በስተቀር ማንም ይህንን ድርጊታቸውን ለማወቅና ለማስቆም ይችላል ብለው አያስቡም፡፡
የግርዛት አገልግሎቱን የሚሰጡት የ68 አመቷ ወ/ሮ፤ በአካባቢው ህብረተሰብ ዘንድ እጅግ የተከበረ ስምና ዝና ያላቸው፤ “እጅሽ ይባረክ” የተባለላቸው ባለሙያ ናቸው። በግርዛት ሥራ ላይ ከተሰማሩበት ካለፉት 40 ዓመታት ጀምሮ እስከዛሬም ድረስ ለበርካታ ወንድና ሴት ልጆች የግርዛት አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ ቀደም ሲል ሥራቸውን የሚሰሩት በግልጽና በአደባባይ ነበር፡፡
በእጃቸው ተገርዘው አድገው የተዳሩ ሴቶች በርካታ ናቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ግርዛትን በአደባባይ መፈፀም አዳገታቸው፡፡ በሚስጢር ለማከናወንም ተገደዱ፡፡ የሴት ልጆች ግርዛት ለጤና ችግር የሚያስከትል እንደሆነና በወንጀል እንደሚያስቀጣም በወረዳው የሥራ ኃላፊዎች በተደጋጋሚ ተነግሮአቸዋል፡፡ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡም አስጠንቅቀዋቸው ነበር፡፡
 “እናቴ ተገርዛለች፣ እኔንም አስገርዛኛለች እኔ ደግሞ ልጆቼን ገርዣለሁ፡፡ ግን ምንም አልሆንንም፡፡ መቼም የዛሬ ልጆች ሰለጠንን ብላችሁ የማታመጡት ነገር የለም” ሲሉ ይሟገታሉ ፤ የሴትን ልጅ ግርዛት ጉዳት አንስቶ ለሚሞግታቸው፡፡
ወይዘሮዋ የግርዛት አገልግሎት የሚሰጡበት ዕቃና ሥፍራ ንፅህናውን ያልጠበቀና ለበሽታ የሚያጋልጥ ነው፡፡ የሶስት ዓመቷ ህፃን የደረሰባትና ቤተሰቦቿንና የአካባቢዋን ሰዎች ጭንቅ ውስጥ የከተታቸውም በዚሁ ንፅህና በጐደለው ዕቃ በተደረገላት ግርዛት ሳቢያ የደረሰባት የጤና ጉዳት ነው፡፡ በግርዛት ሳቢያ ያለአግባብ ከተተለተለው የህፃኗ እምቡጥ ሰውነት ሌላ ኢንፌክሽኑ የፈጠረው የጤና ችግር ስቃይዋን እጥፍ ድርብ አድርጐባታል፡፡ ሁኔታዋ እየባሰ ሲሄድ ቤተሰቦቿ በአካባቢያቸው ወደሚገኝ የጤና ጣቢያ ይዘዋት ሄዱ፡፡ እንደ እሣት የሚፋጀው ሰውነቷ የሥቃይዋን መጠን አፍ አውጥቶ ይናገራል፡፡
በጤና ጣቢያው ምርመራ ያደረገላት ሃኪም ህፃኗ ንፅህናው ባልተጠበቀ መሣሪያ በተደረገላት ግርዛት ምክንያት ለከፍተኛ ኢንፌክሽን መጋለጧንና ይህም በወቅቱ ህክምና ባለማግኘቱ ወደከፋ ደረጃ መሸጋገሩን አረጋገጠ፡፡ ህፃኗ ለከፍተኛ ህክምና ወደ አዲስ አበባ መሄድ እንደሚኖርባትም ወሰነ፡፡ ሁኔታው እጅግ አሳዛኝ ነበር፡፡ ወላጆች የሶስት ዓመቷን ህፃን ይዘው ወደ አዲስ አበባ ቢመጡም ከሞት ሊታደጓት ግን አልቻሉም። በግርዛት ሳቢያ በተፈጠረባት ከባድ ኢንፌክሽን ህፃኗ ህይወቷን አጣች፡፡
ይህንን በአካባቢው ህብረተሰብ ዘንድ ከፍተኛ ሐዘን ጥሎ ያለፈውንና ከጥቂት ዓመታት በፊት በሥፍራው የተፈፀመውን ታሪክ ያጫወቱኝ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በጋሞጐፋ ዞን ቁጫ ወረዳ በምትገኝ አንዲት የገጠር ቀበሌ ውስጥ ያነጋገርኳቸው የ72 ዓመቱ የዕድሜ ባለፀጋ አቶ ዋቴሮ ዳልኬ ናቸው። ሥፍራው የሴት ልጅ ግርዛት፣ ያለዕድሜ ጋብቻ፣ ጠለፋና፣ የጉልበት ብዝበዛ በስፋት የሚከወንበት ሥፍራም እንደሆነ ይነገራል፡፡ ችግሩ በተለይ ቀደም ባሉት ዓመታት በስፋት የሚታይ እንደነበርና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየቀነሰ መምጣቱን ነግረውኛል፡፡ የአካባቢው ማህበረሰብ ሴት ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት መላክ አግባብ እንዳልሆነ የሚያምን ሲሆን ሴቶች ልጆች በቤት ውስጥ ሥራ እናታቸውን ከማገዝና በላይ በላይ የሚወለዱ እህት ወንድሞቻቸውን ከማሳደግ የዘለለ ተግባር እንደማያከናውኑም አቶ ዋቴሮ ዳልኬ ነግረውኛል፡፡
ያለዕድሜ ጋብቻን አሊያም ጠለፋን በሚፈጽሙ ወንጀለኞች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ጠንካራ  ባለመሆኑ ድርጊቱ አሁንም ድረስ መቀጠሉን አዛውንቱ አጫውተውኛል፡፡ ከዓመታት በፊት በ3 ዓመቷ ህፃን ላይ የደረሰውንና ለሞት ያበቃትን ጉዳይ ግርዛቱ ምርቅዝ ሆኖባት ሲሉ ይገልፁታል እንጂ በመገረዟ ምክንያት ለችግር መጋለጧን አያምኑም፡፡ እሣቸውም የወለዷቸውን አራት ሴት ልጆች በእኚሁ ሴት ማስገረዛቸውን አልሸሸጉም፡፡ “ሴት ልጅ ካልተገረዘች አታድብም፣ እግር ታወጣለች፣ እቃ አይበረክትላትም” ሲሉ ይናገራሉ - አዛውንቱ፡፡    
“የጋራ ጥረታችንን በማጐልበት ያለ ዕድሜ ጋብቻን እናስቁም” በሚል መሪ ቃል የተከበረውን የዘንድሮውን የአፍሪካ ህፃናት ቀን በዓልን፣ ፕላን ኢንተርናሽናል ከወላይታ ልማት ማህበር ጋር በመተባበር በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ ውስጥ አክብሯል፡፡ በዚህ በዓል ላይ በክልሉ የሚፈፀሙና ሴቶችን ለከፍተኛ ችግር የሚያጋልጡ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን አስመልክቶ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጐባቸዋል፡፡ በወላይታ ዞን ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ መምሪያ የቀረበ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው፤ ክልሉ የሴት ልጅ ግርዛት፣ በህፃናት ላይ የወሲብ ጥቃትን መፈፀም፣ ለወንድ ህፃናት ቅድሚያ መስጠት፣ ጠለፋ፣ ድርብ ጋብቻ፣ ያለዕድሜ ጋብቻና የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ ---- በሥፋት የሚፈጸምበት ሥፍራ ነው፡፡
የሴት ልጅ ግርዛትን አስመልክቶ ጥናቱ ይፋ ባደረገው መረጃ፤ በክልሉ ወላይታ ዞን በሁሉም ወረዳዎች በገጠርና ከተማ፣ በሁሉም የክርስትና እና የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ግርዛት ይፈፀማል። ባለፈው አመት የዞኑ ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ መምሪያ ባደረገው ጥናት፣ ዕድሜያቸው ከ7-10 ከሆነ 1094 ሴቶች መካከል 600 የሚሆኑት (ከግማሽ በላይ) ሴቶች ተገርዘዋል፡፡ የአካባቢው ማህበረሰብ በሴት ልጆች ላይ ግርዛት ከሚፈጽምባቸው ምክንያቶች መካከል፡- ሴት ልጅን ቀዝቃዛና የተረጋጋች ለማድረግ፣ የወሲብ ፍላጐቷን ለመቀነስና፣ ድንግልናዋን ለመጠበቅ የሚሉት የሚጠቀሱ ሲሆን ግርዛቱ በባህላዊ መንገድና በድብቅ እንደሚፈጸምም ጥናቱ ጠቁሟል። ሴቶች በግርዛት ሳቢያ የሚደርስባቸው የጤና ችግሮች በሚል ጥናቱ ከጠቀሳቸው መካከል፤ ውስጥ ደም መፍሰስ፣ ቴታኖስ (ኢንፌክሽን) ሽንት የመሽናት ችግርና ሞት ይገኙባቸዋል፡፡
የህፃናት ጉልበት ብዝበዛን አስመልክቶ በጥናቱ ላይ የሰፈረው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ህፃናት ከትውልድ ቀዬአቸው ተፈናቅለው ወደ ከተማ ሲወጡ የተሻለ ኑሮ ይኖራሉ፤ ቤተሰቦቻቸውንም ይደጉማሉ በሚል መነሻ ከዞኑ ውጪ በሚገኙ ከተሞች፣ በኦሮሚያ ክልል ገጠር አካባቢዎች እንዲሰደዱ ይደረጋሉ፡፡  ከ2004-2005 ዓ.ም ባለው የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ 1442 ህፃናት ከተለያዩ ገጠር ወረዳዎችና ከተሞች የህገወጥ አዘዋዋሪዎች ሰለባ በመሆን ሄደው፣ በአስቸጋሪ ሁኔታ ከሚገኙበት ሥፍራ ተይዘው ወደየወላጆቻቸው እንዲመለሱ ተደርገዋል፡፡  
ያለዕድሜ ጋብቻን አስመልክቶም በጥናቱ ላይ የሰፈረው መረጃ እንደሚያመለክተው ሴት ልጅን ያለ ፍላጐቷ በማስገደድ የሚፈፀሙ ጋብቻዎችና ጠለፋ በስፋት ይታያሉ፡፡ በተለይም በዞኑ ቆላማና ዳር በሆኑ ወረዳዎች ማለትም በሁምቦ፣ በዳወይዴ፣ ቦሎሶ ቦንቤ፣ ኪንዶ ኦይሻ፣ ኪንዶ ዲዳዬ፣ ዳሞት ፑላስ፣ ዳሞት ሶሬና ዱጉና ፉንጐ ወረዳዎች ላይ ድርጊቱ በስፋት ይፈፀማሉ፡፡
ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ በተለያዩ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ማለትም ያለዕድሜ ጋብቻ፣ በጠለፋ፣ በአስገድዶ መድፈር፣ በጉልበት ብዝበዛና በሌሎችም ምክንያቶች ትምህርት ያጡ ህፃናት ችግሮቻቸውን በመቅረፍ ትምህርታቸውን ለመከታተል የሚችሉበትን መንገድ በማመቻቸቱ ረገድ በክልሉና በዞኑ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ ተግባራት መካከልም በዞኑ ገጠራማ አካባቢዎች በሚገኙ አንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች ውስጥ የተሰሩትና በድርጅቱ ድጋፍ የሚደረግላቸው ማዕከላት ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ድርጅቱ ከሳምሰንግ የኤሌክትሮኒክስ ኩባንያ ጋር በመተባበር በፀሐይ ኃይል የሚሰራ ተንቀሳቃሽ የኮምፒዩተር ማስተማሪያ ክፍል በክልሉ ጋሞጐፋ ዞን ቁጫ ወረዳ ዲንኬ ሙሉ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ውሰጥ አቋቁሟል፡፡
በአንድ ጊዜ 25 ተጠቃሚዎችን የማያስተናግደው ይኸው የኮምፒዩተር ማስተማሪያ ማዕከል በ65 ኢንች ዲጂታል ስክሪን ተማሪዎችን የኮምፒውተር ዕውቀት ለማስጨበጥ እንዲያስችል ተደርጐ የተሰራ ነው፡፡ በማዕከሉ ውስጥ የሚገኙት ሃያ አምስት ዘመናዊ ላፕቶፕ ኮምፒውተሮች የኢንተርኔት አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ለማድረግ ጥረት በመደረግ ላይ እንደሆነም በማዕከሉ የምረቃ ፕሮግራም ላይ ተገልጿል፡፡
የጋሞጐፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የፋይናንስና ኢኮኖሚ መምሪያ ኃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ በማዕከሉ ምረቃ ላይ እንደተናገሩት ድርጅቶቹ ህፃናትን በማስተማርና በማብቃት ተግባሩ ላይ እያከናወኑ ያሉትን ተግባር አድንቀው ህፃናት የነገ አገር ተረካቢ ችግኞች በመሆናቸው በችግኙ ላይ መሥራት የተሻለ ምርትን ለማግኘት ያስችላል ብለዋል፡፡
በዞኑ ቀደም ሲል በስፋት ይታዩ የነበሩት ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ቀንሰው ሴቶች ከወንዶች እኩል በትምህርቱም ሆነ በልማቱ ዘርፍ ተሳታፊ የሚሆኑበት ዘመን እንዲመጣም ምኞታቸውን ገልፀዋል፡፡
በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ግርዛትን ጨምሮ ሌሎች ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በማስወገድ ሴት ልጆችን ለማብቃት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። ፕላን ኢንተርናሽናል እነዚህን ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ለማስወገድና በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለማስቆም የሚያደርገው ዘመቻም ሊበረታታ የሚገባው ነው፡፡ ሴት ልጅን ማስተማር ህብረተሰብን ማስተማር እንዲሉ ነውና፡፡

Read 4363 times