Saturday, 11 July 2015 10:50

የኢትዮጵያ ጦር ወደ ሶማሊያ መግባቱ ተነገረ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ተልዕኮው በአልሻባብ ላይ ጥቃት መሰንዘር ነው ተብሏል

ከባድ መሳሪያ የታጠቁ 3ሺህ ያህል ወታደሮችን የያዘ የኢትዮጵያ ጦር፣ በአልሻባብ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ባለፈው ሰኞ ወደ ሶማሊያ መግባቱን ዘ ኔሽን ጋዜጣ ከትናንት በስቲያ ዘገበ፡፡ከሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ በ450 ኪሎ ሜትሮች ርቃ በምትገኘዋ ዶሎ ከተማ የሚኖሩ የአይን እማኞችን በመጥቀስ ዘገባው እንዳለው፣ ከባድ መሳሪያ የታጠቁና በታንክ የታገዙ የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደ ሉኩ ከተማ ሲጓዙ የታዩ ሲሆን የአካባቢው ነዋሪዎችም ወታደሮቹ የሚያመሩት በአልሻባብ ቁጥጥር ስር ወደምትገኘው ባርዴሬ ከተማ ሳይሆን አይቀርም ሲሉ ግምታቸውን ሰጥተዋል፡፡ባርዴሬ በሶማሊያ ጌዶ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ከተሞች በአልሻባብ ቁጥጥር ስር የምትገኝ ብቸኛዋ ከተማ ናት ያለው ዘገባው፤ አልሻባብ በተለይም በተያዘው የረመዳን ጾም ወቅት በሶማሊያ መንግስትና በአሚሶም ጦር ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጿል፡፡የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ በበኩሉ፤ የኢትዮጵያ ጦር እ.ኤ.አ በ2006 አሸባሪውን አልሻባብ ለመደምሰስ ወደ ሶማሊያ መግባቱን አስታውሶ፣ ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያትም የኢትዮጵያ ጦር በተደጋጋሚ የሶማሊያን ድንበር አልፎ መግባቱን ገልጧል፡፡አልሻባብ በሶማሊያ ውስጥ ይዟቸው ከነበሩ አብዛኞቹ አካባቢዎች ቢለቅም መጠነ ሰፊ ጥቃት መሰንዘሩን ገፍቶበታል ያለው ዘገባው፤ ባለፈው ማክሰኞ በሰሜን ምስራቅ ኬንያ በፈጸመው ጥቃት 14 ሰዎችን መግደሉንም አክሎ አስታውሷል፡፡

Read 3136 times