Saturday, 28 January 2012 14:15

ቀነኒሳና ማናጀሩ በአፋጣኙ እርምጃ ረክተዋል አትሌቶች በዱባይ ማራቶን አሸብረቀዋል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በአትሌቶች ላይ ከዲስፕሊን በተገናኘ ጥሎ የነበረውን እገዳ ከ1 ሳምንት በኋላ ማንሳቱ በመላው ዓለም ተመሰገነ፡፡ ፌደሬሽኑ ከአትሌቶች ጋር ባደረገው አስቸኳይ ውይይት እገዳውን ለማንሳት መወሰኑን የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሲያወድሱ ኢትዮጵያውያን ሯጮች በኦሎምፒክ መድረክ ያላቸው ክብርና ዝና ጐልቶ ወጥቷል፡፡ በሌላ በኩል ከእገዳው ጋር በተያያዘ ለአትሌቶች መብት በመከራከር ጉልህ ጥረት ያደረገው ቀነኒሳ በቀለ እና ማናጀሩ ጆስ ሄርማንስ ሁላችንም ለኢትዮጵያ የተሻለ ውጤት ተግተን መስራት እንፈልጋለን በሚል ለውሳኔው ተግባራዊነት ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ትናንት በተደረገው የዱባይ ማራቶን ላይ እገዳው ከተነሳ ከ3 ቀናት በኋላ ለመሳተፍ የቻሉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች ከፍተኛ የበላይነት በማሳየትና ለኦሎምፒክ የሚያበቃቸውን ሚኒማ በማግኘት አሸንፈዋል፡፡

የቀነኒሳ ሚና ቀነኒሳ የኦሎምፒክ ድርብ የወርቅ ሜዳልያ ባለቤት ብቻ ሳይሆን በ5ሺና በ10ሺ የዓለም ሪኮርድ ከያዘ ከ8 ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡ ፌደሬሽኑ ጥሎ ያነሳውን እገዳ በበዓል ዋዜማ መስማቱን መጥፎ አጋጣሚ ያለው ቀነኒሳ በርካታ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የእገዳውን ውሳኔ የኢትዮጵያን የለንደን ኦሎምፒክ የሜዳልያ ተስፋ አደጋ ላይ የጣለ ማለታቸው የፌዴሽኑን ውሳኔ ለትችት እንደዳረገ ገልጿል፡፡ እገዳውን ለማንሳት ፌደሬሽኑ አትሌቶች፤ አሰልጣኞችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሲወያዩ በመድረኩ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ለአትሌቶች በመከራከር ግንባር ቀደም ሚና መጫወቱን የገለፁት ማናጀሩ ጆስ ሄርማንስ ናቸው፡፡ እገዳው በተነሳበት ማግስት ቀነኒሳ በ1 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያስገባውን የሞንዶ ትራክ ከጅቡቲ ወደብ በማምጣት ስራ ተጠምዶ እንደነበርም የተናገሩት ጆስ ሄርማንስ የሁለቱንም ፍላጐት በኦሎምፒክ ለኢትዮትያ የተሻለ ውጤት ማስመዘገብ ነው ብለዋል፡፡ የዱባይ ገድል ትናንት በተደረገው የዱባይ ማራቶን ላይ ከ1 ሳምንት በፊት በፌደሬሽን ታግደው የነበሩት አትሌቶች እገዳው ከተነሳ ከ3 ቀናት በኋላ ተሳትፈዋል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች በዱባይ ማራቶን በሁለቱም ፆታዎች ለኦሎምፒክ የሚያበቃቸውን ሚኒማ በማግኘት አስደናቂ ውጤት አግኝተዋል፡፡ በወንዶች ምድብ የ21 ዓመቱ አየለ አብሽሮ የመጀመርያውን የማራቶን ውድድር አድርጎ በ1ኛነት ሲያሸንፍ፤ ሌሎቹ ኢትዮጵያዊ ማራቶኒስቶች ዲኖ ሰፈር ከማልና ማርቆስ ገነቴ እስከ 3ኛ ተከታትለው በመግባት የኢትዮጵያውያን የበላይነትን አረጋግጠዋል፡፡ ለማራቶን ውድድሩ ከፍተኛ ዝግጅት በማድረጉ የማሸነፍ ሞራል እንደነበረው ከድሉ በኋላ የገለፀው አትሌት አየለ አብሽሮ በቀጣይ በኦሎምፒክ ተሳትፎ ማድረግ ከቻለ ልዩ ታሪክ ለመስራት ፍላጎት እንዳለው ተናግሯል፡፡ በዱባይ ማራቶን 3 ጊዜ ያሸነፈውና በ2008 ሪኮርዱን አስመዝግቦ ከነበረው ኃይሌ ገ/ስላሴ ሰዓት 30 ሰኮንዶች በማሻሻል በ2 ሰዓት ከ04 ደቂቃ ከ23 ሰኮንድ በሆነ ጊዜ አዲስ የዱባይ ማራቶን ሪኮርድ በአትሌት አየለ አብሽሮ ተመዝግቧል፡፡ ይህ ሰዓቱ በማራቶን ታሪክ 6ኛውን ፈጣን ሰዓት ሆኗል፡፡ አትሌት አየለ አብሽሮ በዱባይ ማራቶን አሸናፊነቱ 250ሺ ዶላር ያገኘ ሲሆን አትሌት ዲኖ ሰፈር 100ሺ ዶላር ማርቆስ ገነቴ 50ሺ ዶላር ተቀብለዋል፡፡ ከ5 እስከ እስከ 10 ባለው ደረጃም ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ተከታትለው በመግባት የበላይ ሆነዋል፡፡

በሴቶች ምድብ ደግሞ ልታሸንፍ የበቃችው በ2 ሰዓት ከ19 ደቂቃ ከ31 ሰኮንድ በሆነ ጊዜ አሰለፈች መርጊያ ስትሆን አምና በተመሳሳይ ውድድር ያገኘችውን ድል በማስጠበቋ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማት ተናግራለች፡፡ የ27 ዓመቷ አሰለፈች በድሉ የራሷን ምርጥ የማራቶን ሰዓትም አስመዝግባ 250ሺ ዶላርም ተሸልማለች፡፡ ሌላዋ ኢትዮጵያዊት ማሬ ዲባባ 3ኛ ደረጃ በማግኘት ጨርሳ 100ሺ ዶላር ተቀብላለች፡፡

ቀጣዩ የለንደን ኦሎምፒክ ሚኒማ ማሟያ የሆነውና ታላላቅ ማራቶኒስቶችን በማሳተፍ በሚያዝያ ወር የሚደረገው የለንደን ማራቶን ነው፡፡ በለንደን ማራቶን ፀጋዬ ከበደ፤ ፈይሳ ሌሊሳ፤ በዙ ወርቁና አብርሃም ጨርቆሴ በወንዶች ምድብ ተሳታፊ እንደሚሆኑም ይጠበቃል፡፡ በዚሁ ውድድር ላይ የዓለም የማራቶን ሪከርድን የያዘው ኬንያዊው ፓትሪክ ማኩ እና ሌሎች የኬንያ ምርጥ ሯጮች ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡

በሌላ በኩል ከሳምንት በኋላ በቦስተን በሚደረገው የ2 ማይል የቤት ውስጥ ውድድር የኦሎምፒክ ድርብ የወርቅ ሜዳልያ ባለቤቷ ጥሩነሽ ዲባባ እና በቤት ውስጥ ውድድር 9 ሪኮርዶችን ያስመዘገበችው መሰረት ደፋር ተሳታፊ መሆናቸው ትኩረት ስቧል፡፡

 

 

 

 

 

Read 2910 times Last modified on Saturday, 28 January 2012 14:24