Saturday, 11 July 2015 11:33

የቅንጅት አመራሮች በገንዘብ ምዝበራ እየተወነጃጀሉ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

    የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ አመራሮች በገንዝብ ምዝበራ፣ በህገ ወጥ ሰነዶች ዝግጅትና በፓርቲ ስም ግለሰቦችን ወደ ውጭ ሃገር ልኮ ጥገኝነት በማመቻቸት እርስ በርስ እየተወነጃጀሉ ሲሆን የፓርቲው ላዕላይ ም/ቤት፣ ዋና ፀሐፊውን እና የህግ ክፍል ኃላፊ የነበሩትን አመራሮች ከፓርቲው ባሯል፡፡
ባለፈው ሰኔ 22 የላዕላይ ም/ቤት ባደረገው ስብሰባ፣ ከፓርቲው ተባረዋል የተባሉት የፓርቲው ዋና ፀሐፊ አቶ ሳሳሁልህ ከበደ እና የፓርቲው የህግ ክፍል ኃላፊ አቶ ሲራክ መኮንን፤ የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ አየለ ጫሚሶ በአመራር ዘመናቸው በፓርቲው ስም ፈፅመዋል ያሏቸውን ህገ ወጥ ተግባራት ለአዲስ አድማስ ዘርዝረዋል።ፕሬዚዳንቱ ፈፅመውታል ከተባሉት ወንጀሎች መካከል ፓርቲው ለዋና ፅ/ቤትነት የተከራየው ቤት በወር 660 ብር የሚከፈልበት ቢሆንም ፕሬዚዳንቱ በወር 1790 ብር እንደሚከፈልበት አስመስለው በማጭበርበር በ7 ዓመት ውስጥ ከ144ሺህ ብር በላይ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል የሚለው ይገኝበታል፡፡ የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ አየለ ጫሚሶ በበኩላቸው፤ የቀረበባቸው ውንጀላ ሃሰተኛ መሆኑን ጠቅሰው መዝገብ ቤት፣ ሂሳብ ሹምና ዋና ጸሃፊው አቶ ሳሳሁልህ እንደሆኑና ድርጊቱን የፈፀሙትም እሳቸው መሆናቸውን በመግለፅ በጉዳዩ ላይም ፓርቲው ክስ መስርቶ በህግ ሂደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡አመራሮቹ በሀሰተኛ ሰነድ ዝግጅት ላይም እርስ በርሳቸው እየተወነጃጀሉ ነው፡፡ በተገኙ ሃሰተኛ ሰነዶች ክስ ለመመስረት በዝግጅት ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በታገዱ ሰዎችና በሞተ ሰው ስም በተለያዩ ጊዜያት ወደ 17 ሺህ 500 ብር ገደማ ወጪ አድርገው ለግል ጥቅማቸው አውለዋል በሚል ቅሬታ የተወነጀሉ ፕሬዚዳንቱ በበኩላቸው፤ “ውንጀላው ሃሰተኛ ነው፤ በህይወት ያሉ ሰዎችና የፓርቲው አባላት ለሚያስፈልጋቸው ወጪዎች የተሰጠ ገንዘብ ነው፤ የሞቱ ተብለው የተዘረዘሩ ግለሰቦችም የፓርቲው አመራር ሆነው እየሰሩ ያሉ ናቸው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የፓርቲው ህጋዊ ማህተም የፓርቲው ፀሐፊ እጅ ተቀምጦ ሳለ ፕሬዚዳንቱ የራሳቸውን ህገ ወጥ ማህተም አስቀረፅው ይጠቀማሉ የሚለውን በተመለከተ ሲመልሱም ማህተም የሚቀመጠው ዋና ፀሐፊው ጋር ነው እንጂ እኔ ጋር አይደለም፤ ህገ ወጥ ማህተምም አላስቀረፅኩም ቢሉም ሆኖም ህጋዊውን የፓርቲ ማህተም ዋና ፀሐፊው ከፓርቲው ሲባረሩ ለማስረከብ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ፓርቲው ለሚመለከታቸው የህግ አካላት አሳውቆ አዲስ ማህተም ማስቀረፁን አምነዋል፡፡ፕሬዚዳንቱ አቶ አየለ ጫሜሶ ፓርቲውን በመሪነት ከያዙ ጀምሮ የገዛ ልጆቻቸው እና 37 የሚሆኑ ግለሰቦች ከአገር እንዲወጡና ጥገኝነት እንዲያገኙ፣ መንግስት ግለሰቦቹ ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደፈፀመባቸው አድርገው ሰነዶች አዘጋጅተዋል የሚል አቤቱታ የቀረበባቸው ሲሆን አቶ አየለ በበኩላቸው፤ “ስለ ቤተሰቦቼ እነዚህ ግለሰቦች አይመለከታቸውም፤ እኔ በፓርቲው ስም ማንንም በዚህ መንገድ ወደ ውጪ አልኩም” ብለዋል፡፡ አክለውም ዋና ጸሐፊው አቶ ሳሳሁልህ በዋና ፀሐፊነታቸው ስልጣን ተጠቅመው፣ የፓርቲውን ማህተም በመጠቀም ለበርካቶች ተመሳሳይ የድጋፍ ሰነድና የፓርቲ አባልነት መታወቂያ ፓርቲው ሳያወቅ ሲሰጡ እንደከረሙ ማስረጃ አሰባስበናል
ብለዋል፡፡ ጉዳዩንም በቅርቡ በፍ/ቤት ክስ መስርተው በህግ እንደሚፋረዷቸው አቶ አየለ ገልፀዋል፡፡
በአጠቃላይ የፓርቲው ፕሬዚዳንት የተለያዩ የተጭበረበሩ ሰነዶችን በመጠቀም በድምሩ በመቶ ሺህ
የሚቆጠር ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል፣ ህገ ወጥ ማህተም አስቀርፀው ሰዎችን ወደ ውጭ ሲልኩ ነበር የሚል ውንጀላ ከእነ አቶ ሲራክ መኮንን ቢሰነዘርባቸውም ፕሬዚዳንቱ በበኩላቸው፤ ዋና ፀሐፊው አቶ ሳሳሁልህ እና ባልደረባቸው አቶ ሲራክ በመመሳጠር ፓርቲውን መዝብረዋል እንጂ በኔ ላይ ያቀረቡት ውንጀላዎች ሃሰተኛ ናቸው፣ ማስረጃ ካላቸው በህግ ይፋረዱኝ ብለዋል፡፡

Read 4040 times