Saturday, 11 July 2015 11:44

መሳም አምሮሽ፤ ጢም ጠልተሽ

Written by 
Rate this item
(27 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን በደጋው አገር የሚኖሩ ሁለት ጐረቤታም ገበሬዎች ነበሩ። ሁለቱም በሣር ቤት የሚኖሩና ኑሮ አልለወጥ ያላቸው ግን ታታሪ ሰዎች ነበሩ፡፡
“አንድ ቀን አንደኛው በድንገት የኑሮ ለውጥ አሳየ፡፡ የግቢውን አጥር አጠረ። የቤቱን የሣር ክዳን ወደ ቆርቆሮ ጣራ ለወጠ፡፡ ልጆቹ ደህና ደህና ይመገቡ፣ መልካም ልብስም ይለብሱ ጀመር፡፡
ጐረቤትየው ያየውን ለውጥ ማመን አቅቶት ወደ ወዳጁ ሄደና፤
“አያ እገሌ?” አለው፡፡
“አቤት” አለው፡፡
አብረን አንድ አካባቢ እያረስን እየኖርን በድንገት ምን ተዓምር ተፈጥሮ ነው እንዲህ የበለፀግከው?”
የተለወጠው ገበሬም፤
“ሚሥጥሩ ምን መሰለህ ወዳጄ፤ ታች ቆላ ወርጄ ማጭድ፣ ዶማ፣ አካፋ፣ ማረሻ ወዘተ ብዙ ብረታ ብረት ገዝቼ አመጣሁና ለደገኛው ገበሬ ቸበቸብኩት። ትርፉ ትርፍ እንዳይመስልህ! አንድ ሁለት ሶስቴ ተመላልሼ ይሄንን ሥራ ስሠራ ገንዘብ እንደ ጉድ እጄ ገባ!” አለው፡፡
ያም ገበሬ አመስግኖት ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ በነጋታው፤ በሬዎቹን ሸጠና ብሩን ይዞ ወደ ቆላ ገበያ ወረደ፡፡ ቆላ ያለ የብረታ ብረት ዘር አንድም ሳይቀረው ገዛና ተሸክሞ ወደ ደጋ ሊመለስ መንገድ ጀመረ፡፡ መንገዱ ወደ ቆላ ሲሄድ ቁልቁለት ነበረ፡፡ አሁን ግን ዳገት ነው፡፡
ግማሽ መንገድ እንኳ ሳይጓዝ በሸክሙ ብዛት ወገቡ ሊቆመጥ ደረሰ፡፡ መቀጠል አልቻለም፡፡ ተዝለፍልፎ፣ ላብ በላብ ሆኖ ወደቀ፡፡
መንገደኛ የሰፈሩ ሰው ወድቆ አየውና፤
“አያ እንቶኔ?”
“አቤት”
“ምነው ምን ገጠመህ?”
“ኧረ ተወኝ ወዳጄ፤ ያ ጐረቤቴ ስለ ብረታ ብረት ንግድ አማክሮኝ፣ እዚህ ወድቄ ቀረሁልህ፡፡”
“እንዴት?”
“ትርፉን ነግሮ መከራውን ሳይነግረኝ!”
*   *   *
በህይወት ውስጥ፣ ደረጃው ይለያይ እንጂ መስዋዕትነትን የማይጠይቅ ምንም ነገር የለም፡፡ ይህንን ልብ ያላለ ፖለቲከኛ ብዙ ዕድሜ አይኖረውም፡፡ በትንሽ በትልቁ ሲበሳጭ፣ ሲነጫነጭ፣ አቤቱታ ሲያበዛ፣ ነገረ ሥራው ሁሉ የዕድል እንጂ የትግል ሳይመስል፣ ማማረር እንጂ መማር ሳይዳዳው፤ በአጭር ይቀጫል፡፡ በዱሮ ጊዜ “ትግላችን እረዥም፣ ጉዟችን መራራ” የሚል መፈክር ነበር፡፡ ጣፋጭና አጭር ትግል የለም ለማለት ነው፡፡ ትግል ጠመዝማዛ እንጂ ቀጥ ያለ መስመር እንደሌለው የሚያፀኸይ ጭምር ነው፡፡ በታሪክ ዕውነተኛ ትግል ያካሄዱ የዓለም ድርጅቶች ወይም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያስተምሩን ይሄንን ነው፡፡ ሳይታክቱ መታገል፣ ሽንፈትን በፀጋ መቀበል፣ ጉድለትን መመርመር ለቀጣዮቹ ዓመታት፣ ከአሁኑ መዘጋጀት! ዕቅድን እጥጉ ድረስ ማቀድና የትላንቱን እንቅፋት እስከመጨረሻው ማጽዳት ተገቢ ነው፡፡ ባላንጣን አለመናቅና እስከፍፃሜው መገላገል ተገቢው የጉዞው ፋይዳ ነው፡፡ ይሄንን ሳንገነዘብ ትግሉ ውስጥ ከገባን ፀፀት ማትረፋችን አይቀሬ ነው፡፡ ሮበርት ብራውን የተባለ ፀሐፊ እንዲህ ይለናል፡-
“ከሙሴ ጀምሮ የኖሩ ታላላቅ መሪዎች የፈሩትን ጠላት ሙሉ በሙሉ መደምሰስ እንዳለባቸው ያውቃሉ፡፡ (ይህንን የተማሩት በከባድ መንገድ ይሆናል አንዳንዴ) ከተዳፈነ እሳት ውስጥ አንዲት ፍም ካለች ምንም ደብዛዛ ብትሆን ቀስ በቀስ እሳት ማስነሳቷ አይቀሬ ነው፡፡ ግማሽ መንገድ ሄዶ ማቆም ከጠቅላላ ማጥፋት የበለጠ ኪሣራ ላይ ሊጥለን ይችላል፡፡ ጠላት አገግሞ ሊበቀል ይችላል። ስለዚህ በአካልም፣ በመንፈስም ማድቀቅ ያስፈልጋል”
ግማሽ መንገድ ተጉዞ መቆምን የመሰለ አደጋ የለም፡፡ “የነብርን ጅራት አይይዙም፤ ከያዙም አይለቁም” የሚለውን የአበሻ ተረት በጽኑ ማስተዋል ብልህነት ነው፡፡
ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፤
“…የተወጋ በቅቶት ቢኛ፣ የወጋ መች እንቅልፍ አለው፤
የጅምሩን ሳይጨርሰው፡፡” የሚለን ይሄንኑ ነው፡፡
ገና በጠዋት መንገድ ስንጀምር ትርፉን ሲነግሩን መከራውንም አብረን ማስታወስ፣ ትግልን ስናስብ መስዋዕትነትን አብረን ማሰላሰል፤ እጅግ ወሳኝ መሆኑን ከልባችን እናጢን፡፡ አለበለዚያ “መሳም አምሮሽ፣ ጢም ጠልተሽ” እንዲሉ ይሆናል!!

Read 9023 times