Saturday, 11 July 2015 11:48

“እሹሩሩ”- ዘመናዊ የሞግዚቶች ስልጠና ማዕከል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

ከ800 በላይ ሰዎች ተመራቂዎቹን ለመቅጠር ተመዝግበው ይጠባበቃሉ
- የሰለጠኑ ሞግዚቶች የሙያ ምዘና ብቃት ፈተና (coc) ይወስዳሉ
- ከማዕከሉ የተመረቁ ሞግዚቶች በ1500 ብር መነሻ ደሞዝ ይቀጠራሉ

     በሰለጠነው ዓለም የህፃናት አያያዝና አስተዳደግ ራሱን የቻለ ሳይንስ ሆኖ በከፍተኛ ደረጃ ትምህርት የሚሰጥበት ሙያ ነው፡፡ ትውልድን በጥሩ ሥነ ምግባር ቀርፆና አንፆ ለማሳደግ ለሚያስችለው ለዚህ ትልቅ ኃላፊነት ለመታጨት ሥነ - ልቦናዊ ዝግጅት በእጅጉ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ህፃናት ጤናቸው በአግባቡ ተጠብቆ፣ በአካልና በአዕምሮ ዳብረው፣ በሥነ ምግባር ታንፀው እንዲያድጉ አሳዳጊዎቻቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ።
እዚህ አገራችን ይህ የህፃናት እንክብካቤና አያያዝ ሙያ ልዩ ስልጠናና ዕውቀት የሚያስፈልገው መሆኑ እንኳን እምብዛም በማይታወቅበት ሁኔታ የህፃናት አያያዝ፣ አስተዳደግና እንክብካቤ ላይ የንድፈ ሃሳብና የተግባር ስልጠና በመስጠት፣ አሰልጥኖና የሙያ ብቃት ምዘናን አስፈትኖ በብቃት እያስመረቀ ሥራ የሚያስቀጥር አንድ ተቋም መኖሩን ሰማንና ወደዚያው አመራን፡፡
እሹሩሩ የሞግዚቶች ማሰልጠኛ የሚል ስያሜ የተሰጠውን የስልጠና ማዕከል ጎብኝተን፣ ለማዕከሉ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ለአቶ ሰለሞን ሙሉጌታ ስለ ተቋሙ አመሰራረትና ስለ ስልጠናው አጠቃላይ ሁኔታ አጭር ቃለ ምልልስ አደረግንላቸው፡፡
ማዕከሉን ለመመስረት ሃሳቡ እንዴት መጣ?
ይህንን የስልጠና ማዕከል ለመክፈት የቻልነው በራሳችን በቤታችን ላይ በደረሰ አጋጣሚ ተነስተን ነው፡፡ የመጀመሪያ ልጃችንን እንደወለድን፣ ያው እንደ አብዛኛው ሰው የህይወት ሩጫችንን ለመሮጥ ልጃችንን ለሞግዚት ሰጥተን ከቤት ወጣን፡፡ ከቀናት በኋላ ልጃችን ላይ አዳዲስ ባህርያትን ማስተዋል ጀመርን፡፡ ከዚህም ሌላ ልጃችን ሞግዚቷ የምትናገረውን ቋንቋ መልመዱ ደስታን ቢሰጠንም፣እንዴት ሊለምድ ቻለ የሚለው ነገር በጣም አሳሰበን፡፡ በተጨማሪም ከሞግዚቷ የወረሳቸው አንዳንድ ባህሪያት ሁኔታውን ትኩረት ሰጥተን ማየት እንዳለብን የሚያስገነዝቡ ነበሩ፡፡ ልጁ እናቱንም አባቱንም እየመሰለ አልሄደም፡፡ ሁኔታው ትንሽ አስደንጋጭ ነበር፡፡
በመጀመሪያ ያደረግነው ነገር በልጅቷ ላይ የምናያቸው ትክክል ያልሆኑ ባህርያትን እንድታስተካክል ማድረግ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ችግሩ በእኛ ቤት ብቻ ያለመሆኑንና የዚህ ዓይነት ችግር ሲያጋጥም መፍትሄ ሊያስገኝ የሚችል ተቋም መኖር አለመኖሩን ለማጥናት ሙከራ አደረግን፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ያየነው እውነታ፣ ህፃናት በቤታቸው ውስጥ በቅርበት በሚያዩዋቸው ነገሮች እንደሚቀረፁ ነው፡፡ የሞግዚቶቻቸውን ቋንቋ እና ባህርያት ወርሰው እንዳገኘናቸው ልጆች ሁሉ፣ ቤት ውስጥ ቲቪ በየዕለቱ በማየት፣ በአረብ ቻናል ቲቪ ተቀርጸው አረብኛ ሁሉ መናገር የሚችሉ ልጆች ገጥመውናል፡፡
ጉዳዩን ስንመለከተው ክፍተቱ በጣም ሰፊ ነው። የተወሰኑ ጥያቄዎችን አዘጋጅተን በህፃናት መዋያ፣ በዴይኬር፣ በህፃናት ማሳደጊያዎች ውስጥ እየተዘዋወርን መጠየቅ ጀመርን፡፡ በአብዛኛዎቹ (በሁሉም ማለት ይቻላል) ውስጥ ያገኘናቸው የህፃናቱ ተንከባካቢ በመሆን የተቀጠሩት ሠራተኞች ስራቸውን እንደማይወዱት፣ በደመወዛቸው ደስተኛ እንዳልሆኑ፣ ሳይንሳዊ የሆነ የልጅ አያያዝ፣ አስተዳደግና ቅጣት የማያውቁ እንደሆኑ ተረዳን። በቤታችን ውስጥ የመጀመሪያውና ትልቅ ለውጥ ያገኘንበት ሁኔታ አበረታታንና ስራውን ለመስራት ውሳኔ ላይ ደረስን፡፡ ለአንድ ዓመት ያህል ጉዳዩን ስናጠናና ስንዘጋጅ ቆይተን፣ በ2005 ዓ.ም መስከረም ወር ላይ ማዕከሉን ከባለቤቴ ከወ/ሮ ምህረት አበራ ጋር አቋቋምነው፡፡
ሥራውን ስትጀምሩ ከሰዎች ምን አስተያየት አገኛችሁ?  ስራው በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነትን ያገኝልናል የሚል እምነት ነበራችሁ?
ስልጠና መስጠቱን ስንጀምር ምን እየሰራህ ነው ብለው የተገረሙብኝ ብዙዎች ነበሩ፡፡ እንዴት ይህንን ስራ ብለህ ታስባለህ፣ ማንም ሊቀበልህ አይችልም ሁሉ ብለውኝ ነበር፡፡ እኛ ግን እርግጠኛ ነበርን፡፡ አሁን ያለንበት ጊዜ የሩጫና የሥራ ነው፡፡ በርካታ እናቶች ልጆቻቸውን ለሞግዚት በመስጠት የህይወት ሩጫቸውን ለመሮጥ ከቤታቸው መውጣታቸው እየተለመደ ነው፡፡ በዚህ ምክንያትም ልጆች የሚያድጉት በሞግዚቶቻቸው እጅ ነው፡፡ ያቺ ልጅ አሳዳጊ ሞግዚት ደግሞ ስለ ልጅ አያያዝና አስተዳደግ በቂ ዕውቀትና ግንዛቤ ያላትና ልጆችን የምትወድ መሆን ይኖርባታል፡፡ ይህቺን ሞግዚት አሰልጥኖ ለሥራ የሚያዘጋጅ ተቋም ማቋቋሙ ምንግዜም ቢሆን ተቀባይነት ማግኘቱ የማይቀር ነው፡፡ በዚህ እምነት ነበረን፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በቤታችን ውስጥ ባለችው የልጃችን ሞግዚት ላይ ያገኘነው ለውጥ ትልቅ ብርታት ሰጠን እናም ቀደም ሲል እንሰራቸው የነበሩትን ስራዎች ሁሉ ትተን ሙሉ ጊዜያችንን ለስልጠና ማዕከሉ ሰጥተን ስራችንን ቀጠልን፡፡ ቀስ በቀስ ሰልጣኞች እየመጡ መመዝገብና መሰልጠን ጀመሩ፡፡ በመቀጠልም የሰለጠኑ ሞግዚቶችን ለመቅጠር የሚፈልጉ ግለሰቦችና ተቋማት መምጣት ጀመሩ፡፡
 የምትሰጡት ምን ዓይነት ስልጠና ነው? ለምን ያህል ጊዜስ ነው የሚሰለጥኑት?
በማዕከላችን ለስልጠና የሚመጡት ሰልጣኞች የሚያገኙት የቲኦሪና የተግባር ትምህርት ነው፡፡ ቲኦሪው 20%፣ ተግባሩ 80% የሚሆን ድርሻ አለው፡፡ ስልጠናው የሚጀመረው ሰልጣኞቹ ስለ ግል ንፅህና አጠባበቅ፣ ስለ ህፃናት አያያዝና አስተዳደግ አጠቃላይ የቲኦሪ ትምህርት በመስጠት ነው፡፡ ከዚያ በመቀጠል በቲኦሪ የተማሩትን በተግባር የሚያጠኑበትና የሚለማመዱበት ራሱን የቻለ ለህፃናት አስተዳደግ የሚያስፈልጉ ነገሮችን በሙሉ ያሟላ ማዕከል ውስጥ የተግባር ስልጠና እንዲያገኙ ይደረጋል። የህፃናት አያያዝ፣ አልባሳትና ዳይፐር መቀየር፣ ህፃኑን መንከባከብ፣ ህፃናትን ማጠብ፣ ንፅህናቸውን መጠበቅ፣ ማስተኛት፣ ማጥባት ማቀፍ፣ ምግብ መመገብ፣ የልብስ ንፅህና አጠባበቅ፣ የህፃናት ምግብ አዘገጃጀት ሁሉ ይማራሉ፡፡ ለዚህ ተብለው የተዘጋጁና በውድ ዋጋ ከውጭ አገር ያስመጣናቸው መጥባትና መፀዳዳት የሚችሉ አሻንጉሊቶች አሉን፡፡ ትምህርቱ የሚሰጠውም በእነዚህ አሻንጉሊቶች ነው፡፡ ህፃናቱ በድንገት ቢታመሙባቸው ምን ዓይነት እርምጃ መውሰድ እንደሚገባቸው፣ በህፃናቱ ላይ የሚስተዋሉ ለውጦችን እያዩ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ የሚቻልበትን መንገድ መፈለግ፣ ልጆች ዳይፐር እንዲያቆሙ እንዴት ማድረግ ይቻላል፣ የልጆች ምግብን ከብክነት መከላከል የሚቻልበት መንገድ እንዴት ነው ---- የሚሉ ነገሮችን ሁሉ እናስተምራለን፡፡
የስልጠና ጊዜያችን በሁለት ይከፈላል፡- አንዱ የአንድ ወር ከአስራ አምስት ቀን ሲሆን ስልጠናው በሣምንት ለስድስት ቀናት የሚሰጥ ይሆናል፡፡ ሁለተኛው የሶስት ወራት ስልጠና ነው፡፡ በሳምንት 3 ቀን ሰልጣኞቹ በመረጡበት ጊዜ የሚሰጥ ነው፡፡
ለስልጠና የሚመጡ ሰልጣኞችን የምትመርጡበት መስፈርት አላችሁ?
አለን፡፡ ለምዝገባ የሚመጡ ሰልጣኞችን የምንቀበልበት መስፈርት አለን፡፡ ከሁሉም የምናስቀድመው ግን የሰልጣኛችንን ባህርይ ነው። ከልጆች ጋር የመሆን ፍላጐት እንዳላት፣ ኃላፊነት የሚሰማት እንደሆነች ሁሉ በሚገባ እናያለን፡፡
አንዳንድ የባህርይ ችግሮች ካሉ፣ ባሉን የስነልቡና ባለሙያዎች በመታገዝ ወደ ትክክለኛው መንገድ እንዲመጡ እናደርጋቸዋለን፡፡ ይህ ካልሆነም ከስልጠናው ይሰናበታሉ፡፡ ምክንያቱም ሰልጣኞቻችን ተመርቀው ሥራ ሲጀምሩ እንደ ሌላ ሙያ የሚገናኙት ከኮምፒዩተር፣ ከማሽንና ከወረቀት ጋር አይደለም፡፡ ከፍተኛ ጥንቃቄና እንክብካቤን ከሚፈልጉ ህፃናት ጋር ነው፡፡ ስለዚህም ትልቅ ጥንቃቄን የሚፈልግ ሥራ ነው፡፡
ሰልጣኞቹ ለሙያው ብቁ ናቸው ተብለው ለሥራ ዝግጁ የሚሆኑት መቼ ነው?
የቲኦሪና የተግባር ትምህርቱን ያጠናቅቃሉ። የቡድን ሥራዎቻቸውን ይሠራሉ፣ የመመረቂያ ጽሑፎች ያዘጋጃሉ፡፡ አፓረንትሺፕ ይወጣሉ፡፡ ይህንን ከአጠናቀቁ በኋላ ከአዲስ አበባ ፖሊስ፣ ከሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ እና ከ IOM ጋር በመተባበር ከወንጀል መከላከል የሚችሉበትን መንገድ አስመልክቶ ስልጠና ይሰጣቸዋል። ይህንን ሲያጠናቅቁም በሙያ ብቃት ምዘና ኤጀንሲ የሚሰጠውን የሙያ ምዘና ብቃት ፈተና (COC) እንዲወስዱ እናደርጋለን፡፡
በዚህ መልኩ ያሰለጠናቸውን 75 ሞግዚቶች፣ በቅርቡ በሳሮማሪያ ሆቴል በተደረገ ሥነስርዓት አስመርቀናል፡፡ ይህም በአገሪቱ የሙያ ምዘና ብቃት ማረጋገጫ የወሰዱ ሞግዚቶችን ለመጀመሪያ ጊዜ አሰልጥኖ ያስመረቀ ማዕከል እንድንሆን አድርጐናል፡፡
እስከ አሁን በአጠቃላይ ምን ያህል ሰልጣኞችን አሰልጥናችሁ አስቀጠራችሁ?
እስከ አሁን ወደ 265 የሚሆኑ ሞግዚቶችን አሰልጥነን ሥራ አስቀጥረናል፡፡ እነዚህ መቀጠር የሚፈልጉት ናቸው። ከዚህ ውጪ በተለያዩ ምክንያቶች መቀጠር የማይፈልጉ (የራሳቸውን የልጆች ማቆያና መንከባከቢያ) መክፈት የሚፈልጉ፣ በሥራ ላይ ያሉ፣ ወደ ውጪ አገር ለመሄድ የሚሹ ሁሉ ስልጠናውን ይወስዳሉ፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰርተፍኬታቸውን አረጋግጦላቸው፣ ወደ ካናዳና አሜሪካ የሄዱ ሞግዚቶችም አሉን፡፡ ከዚህ ውጪ ያሉና ሥራ ለመቀጠር ፈልገው የሰለጠኑ ሞግዚቶቻችንን መነሻ ደመወዝ ከ1500 ብር በላይ በማድረግ በተለያዩ የግለሰብ ቤቶችና ተቋማት እንዲቀጠሩ አድርገናል፡፡ በ1500 ብር መነሻ ደመወዝ ተቀጥረው ዛሬ ደመወዛቸው ከ2500 ብር በላይ የሆነላቸው ሞግዚቶችም አሉን፡፡ ሰልጣኞቻችን ስልጠናውን ሲጨርሱ የመቀጠር ሥጋት አይኖርባቸውም፡፡
ገና ስልጠናውን በጨረሱ ሣምንት ከ1500 ብር በላይ ደመወዝተኛ ሆነው እንደሚቀጠሩ እርግጠኞች ነን፡፡ ሠልጣኞቻችን ስልጠናውን ሲያጠናቅቁ፣ ወስደው ለመቅጠር ተመዝግበው የሚጠባበቁ ከ800 በላይ ቀጣሪዎች አሉ፡፡
ከቀጣሪዎችና ከተቀጣሪዎቹ ኮሚሽን ትቀበላላችሁ?
ከቀጣሪዎቹ ኮሚሽን እንቀበላለን፡፡ ተቀጣሪዎቹ ግን የራሳችን ስለሆኑ እነሱ የሚከፍሉት ኮሚሽን የለም፡፡
ለስልጠናው ምን ያህል ክፍያ ይጠየቃል?
አንድ ሰልጣኝ ለስልጠና የሚያስፈልጉትን ነገሮች በሙሉ አጠቃሎ ከ3-4 ሺህ ብር የሚደርስ ወጪ ያስፈልገዋል፡፡ ኮርሱን በጨረሱ ማግስት መነሻ የ1500 ብር ደመወዝተኛ ይሆናሉ፡፡ ሥራ የማግኘቱ ዕድል ሰፊ ነው፡፡
ሥራ የማስቀጠር ፈቃድ አላችሁ?
የእኛ ሥራ ጐን ለጐን መሄድ የሚችል ሥራ ነው፡፡ ሙያተኛን አሰልጥኖና አብቅቶ መልቀቅ ሳይሆን የሰለጠነውን ኃይል መጠቀም ለሚገባው ሰው መስጠቱ ተገቢ ነው ብለን እናምናለን፡፡ እናም ከአዲስ አበባ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ህጋዊ የማስቀጠር ፈቃድ ተሰጥቶናል፡፡ ሰልጣኞቻችንን በበቂ ሁኔታ አሰልጥነን፣ከቀጣሪዎቻቸው ጋር ህጋዊ ውል እንዲፈራረሙ እያደረግን እናስቀጥራለን፡፡
 የሰልጣኞቻችሁ የቀለም ትምህርት ደረጃስ እምን ድረስ ነው?
ከአራተኛ ክፍል ተማሪ እስከ ሁለተኛ ድግሪ ያላቸውን ተቀብለን አሰልጥነናል፡፡ ዕድሜያቸው ከ20-53 ዓመት የሚሆናቸውን ተቀብለን አሰልጥነናል፡፡
በማዕከሉ የሚሰለጥኑት ሴቶች ብቻ ናቸው?
እስከ አሁን ሁለት ወንድ ሰልጣኞችን ተቀብለናል፡፡ እኔ ይህ ነገር በጣም መለመድ ያለበት ጉዳይ ይመስለኛል። አባቶችም መሰልጠን አለባቸው፡፡ እናት ስትወልድ ከምጡና ከአስጨናቂው ጊዜ በኋላም ህፃኑን የመንከባከብ ኃላፊነት የሚወድቀው በእሷ ላይ ነው፡፡ አባት ለማገዝ ቢፈልግ እንኳን ይፈራል፡፡ ስልጠናውን ወስዶ ቢሆን ግን ይህ ችግር አይኖርም፡፡ ኃላፊነቱን ለመወጣት ይችላል። የወንድ ሰልጣኞችን ወደ ማዕከላችን መምጣት በጣም የምናበረታታው ጉዳይ ነው፡፡
 ምሩቃን ሞግዚቶችን ለመቅጠር ተመዝግበው የሚጠባበቁ 800 ሰዎች ጉዳይ በምን ያህል ጊዜ ይደርሳቸዋል?
እኛ አሁንም ሥራችንን እየሠራን ነው፡፡ ከሥር ከሥር እየመጡ የሚመዘገቡ ሰዎች አሉ፡፡ አሁን ለቀጣሪዎች የምንሰጠው የሶስት ወር ቀጠሮ ነው፡፡ ይህንን ረዥም ጥበቃ ለማስቀረት አሁን ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረግን ነው፡፡ አሁን ባለን ሁኔታ አስጨናቂ ነገሮች ከሌሉ የምንሰጠው የሶስት ወር ቀጠሮ ነው፡፡
አስጨናቂ ነገሮች ሲባል?
አንዳንድ ጊዜ ድንገተኛ ሁኔታዎች ሲከሰቱ ቅድሚያ የምንሰጥበት ሁኔታ አለ፡፡ ለምሣሌ እናት በህይወት ከሌለችና መሰል ችግሮች ሲከሰቱ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ይኖርብናል፡፡  
ህብረተሰቡ የሰለጠኑ ሞግዚቶችን ጠቀሜታ በሚገባ እንዲገነዘብ ምን መደረግ አለበት ትላላችሁ?
የሰለጠኑ ሞግዚቶች በሁሉም ህፃናት ባሉበት ሥፍራ ሁሉ ያስፈልጋሉ የሚል እምነት ቢኖረንም ከመኖሪያ ቤት በበለጠ በዴይኬሮች፣ በመዋዕለ ህፃናትና በህፃናት ማሳደጊያ ውስጥ መኖራቸው እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነው። ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ህፃናት መዋያ ሲያስገቡ የሚያዩት የግቢውን ንፁህ መሆን፣ የዕቃዎቹን መሟላት እንጂ በተቋሙ ውስጥ ያሉ ሙያተኞች በልጆች እንክብካቤ ላይ ያላቸውን ሙያዊ ብቃት አይደለም። ተቋማቱም ለቀጣዩ ዓመት ህንፃዎቻቸውን ከማደስ፣ አዳዲስ ዕቃዎችን ከማስገባቱ ጐን ለጐን በተቋሞቻቸው ውስጥ ያሉ ሙያተኞችን አቅም በማጐልበቱና ሙያዊ ስልጠና እንዲያገኙ በማድረጉ በኩል ቢተጉ ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡
የወደፊት ዕቅዳችሁ ምንድነው?
አሁን ማዕከሉን አጠናክረን ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የሰለጠኑ ሞግዚቶች ጥያቄ ለመመለስ ጥረት ማድረግ ነው ዓላማችን፡፡ ከዚህ በመቀጠልም ሌሎች ያሰብናቸውና በወረቀት ደረጃ ተሠርተው ያለቁ ፕሮጀክቶች አሉን። እንደየሁኔታው እነሱንም ተግባራዊ ማድረግ እንጀምራለን። አቅመ ደካማ ሰልጣኞችን በነፃ ማሰልጠን ቀደም ሲል እናደርገው የነበረና አሁንም የምንቀጥለው ተግባር ነው፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ ማዕከላችንን እያስፋፋን፣ሰልጣኞችን በበቂ ሁኔታ ተቀብለን በማሰልጠን፣ ብቁ ሙያተኛ ማድረግና ራሳቸውን ማስቻል እንፈልጋለን፡፡

Read 3738 times