Saturday, 11 July 2015 12:29

አገራቸውን ጥለው የተሰደዱ ሶርያውያን ከ4 ሚሊዮን በላይ ናቸው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሶርያ ለአመታት የዘለቀውን የእርስ በእርስ ግጭት በመሸሽ ወደተለያዩ አገራት የተሰደዱ የአገሪቱ ዜጎች ቁጥር ከ4 ሚሊዮን በላይ መድረሱንና ይህም ከአገሪቱ ህዝብ አንድ ስድስተኛ ያህሉን እንደሚሸፍን ማስታወቁን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
በሶርያ በ2011 የተቀሰቀሰው ግጭት እየተባባሰ መቀጠሉ የአገሪቱን ዜጎች ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ እንደከተታቸው የጠቆመው ዘገባው፣ ባለፉት አራት አመታት በግጭቱ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉ ዜጎች ቁጥር ከ230 ሺህ በላይ መድረሱንና አገራቸውን ጥለው ከተሰደዱት ከ4 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በተጨማሪ፣ ከ7 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑትም በአገራቸው ውስጥ መፈናቀላቸውን ገልጧል፡፡
በሶርያ የሚታየውን አስከፊ ሁኔታ፣ “የዚህ ትውልድ አስከፊው የሰብአዊ ቀውስ” ሲሉ የገለጹት የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ሃላፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ፣ የእርስ በእርስ ግጭቱ እያደረሰ ያለው ጥፋት እየከፋ መምጣቱንና ስደቱ በዚሁ ከቀጠለ፣ የስደተኞቹ ቁጥር በመጪዎቹ ስድስት ወራት 4.27 ሚሊዮን ሊደርስ ይችላል ብለዋል፡፡
የተመድ መረጃ እንደሚለው፤ በርካታ ሶርያውያን በተሰደዱባት ቱርክ፣ የስደተኞቹ ቁጥር 1.8 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ በድንበር አካባቢ ያለው ግጭት እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ የስደተኞቹ ቁጥር እንደሚያሻቅብ ይጠበቃል፡፡ በሊባኖስ 1.2 ሚሊዮን፣ በዮርዳኖስም 629ሺህ ያህል ሶርያውያን ስደተኞች እንደሚገኙ ተመድ አስታውቋል፡፡ በተለያዩ የአውሮፓ አገራት ጥገኝነት የጠየቁ ሶርያውያን ስደተኞች ቁጥር 270 ሺህ ያህል መድረሱንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Read 2152 times