Saturday, 11 July 2015 13:01

ጊዮርጊስ ታዛ ስር

Written by  መሐመድ ነስሩ
Rate this item
(12 votes)

 ሰንበትን በዚያ ባለፈ ባገደመ ቁጥር ያያቸዋል -ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ቅጽር ስር፤ መናኛ ልብስ ለብሰው ባነጠፋት ጨርቅ ላይ ሲመፀወቱ፡፡
…ፈፅሞ ያላሰበው ቦታ ላይ ነው ያያቸው፤ ኮከብ ቆጣሪም ሊገምተው የማይችል የመሰለው ቦታ ላይ፡፡ ለማመን ተቸግሮ ነበር፡፡ ግንባራቸው ላይ የተጋደመው ጠባሳ ነው ጥርጣሬውን የከላት። እንደ መንገድ ላይ የትራፊክ መስመሮች ዘና ብሎ የተጋደመው ጠቋራ ጠባሳ!...
ሰውዬውን የማወቅ ፍላጐቱ ጣራ ነካ፡፡ አዲስ ነገር በማወቅ የሚያገኘው ደስታ ከወይን ጠጅ በላቀ ነፍሱን ያስተፈሲህለታል፡፡ ከሴት ገላ በላይ ውስጡን ያሞቀዋል፡፡
በአዲስ አበባ “የልመና ሙያ” ላይ ሊያደርግ ላሰበው ጥናት ጥሩ መነሻ እንደሚሆኑት አመነ፡፡
ከቀናት በኋላም ዘባተሎ ለብሶ፣ ፀጉሩን ከማበጠሪያ አኳርፎ ለተበጣጠሰ ሸራ እግሩን ድሮ…ወደ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አቀና፡፡
…ከሰውዬው አጠገብ ተቀመጠ፡፡
“አዲስ ትመስላለህ…ጃል?!”
“አዎ…አባት!”
“ፊትህ የመከራ በትር ያረፈበት አይመስልም፡፡ ምን ገጠመህ ታዲያ ልጄ?!”
ያጠናውን ቃለ ተውኔት መጫወት ነበረበት፡፡
“ቤተሰቦቼ አልቀዋል፡፡ የምኖርባትን ቤት አባቴ የባንክ ዕዳ ነበረበትና መንግስት ወረሰው፡፡ እንዳልሸከም የጀርባ ህመም አለብኝ፡፡ ምርጫ ሳጣ ልለምን በቃሁ አባቴ፡፡”
ፊቱ የሀዘን ጥላ አጠላ፡፡
…በሀዘኔታ ተመልክተውት ፊታቸውን ወደ መንገደኛው መለሱ፡፡
ወጭ ወራጅ…ሂያጅ መንገዱን ሞልቶታል…ጥጋቱን  የኔ ቢጤዎች ተደርድረዋል፡፡
ቅዳሴ ይሰማል፡፡ መንገደኞች ደፋ ቀና እያሉ ያልፋሉ፤ እየተሳለሙ፡፡ ምዕመናን ነጠላ እንደተከናነቡ በሩን ይስማሉ፡፡
ገሚሶቹ ወደ ውስጥ ዘልቀው ታድመዋል፡፡
…ናሆም አዛውንቱን አስተዋለ፡፡ የተጐሳቆለ ሰውነት የላቸውም፡፡ ጠይም ፊታቸው በችግር እሳት የተጠበሰ አይደለም፡፡
“አባት…”
“አቤት ልጄ”
“እንዴት ነው ስራው?”
“ይመስገን ለፈጣሪ…ሰው ደግ ነው ይመፀውታል። የኛ ሰው ሃይማኖተኛ ነው፡፡ ፈሪሀ እግዚአብሔር ልቡ አድሯል፡፡ የተቸገረን መርዳት ልማዱ ነው፡፡ ይመስገን ለፈጣሪ ልጄ ይመስገን!”
ናሆም ስሜታቸውን ከገጽታቸው ለማጥናት እየሞከረ ያዳምጣል፡፡
እኝህ ሰው ዛሬ ያሉበት ቦታና ከቀናት በፊት የታዩበት ቦታ እጅግ የተራራቁ ናቸው፡፡ ርቀታቸው በሰማይና በምድር ሊመሰል ይችላል፡፡
ሆቴል…ጊዮን ሆቴል ሙሉ ልብስ ለብሰው…ከረባት አስረው…ከሁለት ወጣቶች ጋር ደብሊው ቢኤም የቤት መኪና እያሽከረከሩ ሲወጡ ነበር ያያቸው፡፡
ዓይኖቹ የድሮ ዓይኖቹ ነበሩ…ሰውየውም ራሳቸው፡፡
“ይቅርታ ያድርጉልኝና አባት…”
“ምነው ልጄ?!”
“ምን ያህል ጊዜ ሆነዎ?”
“ምኑ?”
“እዚህ ቦታ መቀመጥ ከጀመሩ…”
የውሃ ጠብታ ድንጋይ እንዲሰብር… ቀስ በቀስ ነው…. የምስጢሩን ቅርፊት መስበር የፈለገው፡፡ ለዘብተኛ ሆኖ በልዝብ ቃላት ወደ ግቡ እያዘገመ ነው፡፡  
“ይመስገን ፈጣሪ…ይኸው ሶስተኛ ዓመቴ መጣ።” ፊታቸውን አነበበ፡፡ ኩራትና ትካዜ የተዳቀሉበት መጢቃ ስሜት!
“ቤተሰብ …ልጆች የለዎትም?”
“ኧረ አለኝ ልጄ…ምን የመስሰሉ ሁለት ሸበላዎች አሉኝ…”
ቃላት እየመረጠ…ጥያቄዎችን ከመልሶቻቸው ስር ስር ማሶክሶክ ቀጠለ፡፡
“…አሀ …ታዲያ ከዚህ ከምፅዋት የሚገኝ ገንዘብ ከነቤተሰብ ያኖራል?!”
“እሱስ አዎ! የኛ ሰው ቸር ነው ብዬህ የለ!?”
“እህ …ታዲያ ልጆችዎ ምንም አይሰሩም?”
መልስ ለመስጠት ዘገዩ፡፡
“አባቴ!”
“አቤት ልጄ”
“ሰምተውኛል?”
“እ?”
“ልጆችዎ አይሰሩም?”
“…ይሰራሉ’ንጂ…ይመስገነው ለፈጣሪ የሁለት ድርጅቶች ስራ አስኪያጆች ናቸው፡፡”
“ምን አሉኝ?”
ሰምቷል፡፡ በደመነፍስ ነው መጠየቁ፡፡
“ሁለቱም ልጆቼ ጥሩ ስራ አላቸው፡፡ ስራ አስኪያጆች ናቸው…ክብሩ ይስፋ ለመድኃኒዓለም!”
“ምን ድርጅት ውስጥ ነው የሚሰሩት?”
“የግል ድርጅት ነው ልጄ”
“የማን ናቸው ድርጅቶቹ?”
“የኔ!”
የናሆም ግርምት እንደ ርችት ወደ ሰማይ ተተኮሰ።
“የ‘ርስዎ?!”
“አዎ ልጄ”
መደመሙን መደበቅ አልቻለም፡፡ ድብን ካለ ገጠር ወጥቶ መኸል ከተማ እንደተጣለ ባላገር ድንብርብር አለው፡፡ የአምልኮ ስርዓቶችን በቅጡ ሳይረዳ ቤተ አምልኮ እንደገባ አዲስ አማኝ ብዥ አለበት፡፡
“እና…እንዴት …ለምን?”
መጨረስ ከበደው፡፡
“እንዴትና ለምን ትለምናለህ ልትለኝ ነው?”
“ገብቶዎታል አባቴ”
“ሰፊ ታሪክ አለው፡፡” አሉ ጌሾ ወቅጠው እንደጋቱት ሰው ፊታቸውን አኮምጭጨው፡፡
“እባክዎን ባጭሩ ያጫውቱኝ?!”
አትኩረው ተመለከቱት፡፡ ከፍተኛ የማወቅ ጉጉት!
የተደበቀ ነገር በመግለጥ የሚረካ የሚመስል ትጉህ ወጣት!
“ይኸውልህ ልጄ…ልጆቼን እንደ አባትም እንደ እናትም ሆኜ ያሳደግኋቸው እኔ ነኝ፡፡ እናታቸው ገና ነፍስ በማወቂያቸው ዋዜማ ነው የሞተችብኝ!...”
በትካዜ ተዋጡ፡፡ በትዝታ መርከብ ተሰፈሩ፡፡ ከሰኮንዶች በኋላ፤
“…እንግዲህ በህይወቴ ያሉኝ እነዚህ ልጆች ብቻ ናቸው፡፡ ዘመድ አዝማድ ያለኝ! ሚስት የለኝ! ቢሆንም በልጆቼ ደስተኛ ነበርኩ፡፡ ታዲያልህ በአንድ የተረገመ ቀን ናዝሬት ቅርንጫፍ ላለው የንግድ ድርጅቴ ከመጀመሪያው ልጄ ጋር ዕቃ ጭነን ስንጓዝ የጭነት መኪናው ፍንግል አለ…”
አሁንም በዝምታ ቡልኮ ተጆቦኑ፡፡ “ሩቅ እንደሚያስቡ ያስታውቃሉ!” አለ ናሆም፡፡
“እኔ ይች ጭረት ነበረች ጉዳቴ” ግንባራቸው ላይ የተጋደመውን ጠባሳ እየጠቆሙት፡፡
“ለክፉ አልሰጠኝም፤ ልጄ ግን ክፉኛ ተጐዳ፡፡
ለሳምንት ነፍሱን አያውቅም ነበር፡፡”
መተከዙን አላቆሙም፡፡ አንድ ዐረፍተነገር ሲያገባድዱ አራት ነጥባቸው ቁዘማ ነው፡፡
“ሳሳሁ!...ሳሳሁ ልጄ ጨነቀኝ፡፡ ይሕን ልጄን ማጣት የዓይኔን ብርሃን ማጣት ሆነብኝ…ልቤን ማጣት ሆነብኝ…እናም…ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተሳልኩ፡፡”
“ምን ብለው?”
“ልጄን በህይወት ካተረፍክልኝ ለአምስት ዓመት ያህል በሳምንት ሰንበት ለምኜ ገንዘቡንም ለቤተክርስቲያንዋ ገቢ እንደማደርግ ተሳልኩ!
ወደ ላይ አንጋጠው፤
“ሞገስ ይብዛ ለአምላክ…ልጄ ከነሙሉ ጤንነቱ ተነሳልኝ”
ናሆም በነገሩ እየተደመመ፤ “ደህና ይሁኑ” በማለት ቦታውን ለቀቀ፡፡ ፈጽሞ ያልጠበቀው ነገር ቢገጥመውም ቤቱ የደረሰው “ለጥናቴ ጥሩ መንደርደሪያ አገኘሁ” ብሎ እያሰበ ነበር፡፡

Read 4120 times