Saturday, 18 July 2015 11:25

ዲሞክራሲ ለእኛ “User Friendly” አይደለም!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(14 votes)

• ኒዮሊበራሎች ቀላል ሲያደንቁን ሰነበቱ…
• ለኢትዮጵያ ህፃናት ዲሞክራሲ በጡጦ ይሰጣቸው!
• የዲሞክራሲ ነገር ለዛሬው ትውልድ ዘገየ (too late!)

   እናንተዬ …ለካስ      ኒዮሊበራሎችን   አናውቃቸውም። ሰይጣን ነበር እኮ የምናስመስላቸው። (የቀለም አብዮት ጠንሳሽ ምናምን እያልን!) …ኢህአዴግንማ ተውት! ከተቃዋሚ ፓርቲዎች እንደ አንዱ ነበር የሚቆጥራቸው፡፡ (የሚያወርድባቸው ስድብ ትዝ አላችሁ!) አንዳንዴማ… በአስቸጋሪ የአማርኛ ተረቶች አጅቦ የሚያዥጐደጉድባቸው ነገር በእንግሊዝኛ ለመተርጐምም ሳያስቸግር አይቀርም (ለብልሃቱ ይሆን እንዴ?!) የሆኖ ሆኖ ግን ሰሞኑን እንዳየናቸው እነሱ ቂም አልያዙም፡፡ (እኔም ኒዮሊበራል ሆኛለሁ!)
እናላችሁ…በ3ኛው ዓለምአቀፍ የፋይናንስ ጉባኤ ለልማት ላይ ብዙዎቹ የኒዮሊበራል አቀንቃኞች በሚያስገርም ሁኔታ የጦቢያን የዕድገት ለውጥ እያደነቁ Congra… Celebration…ምናምን ዓይነት ውደሳዎች… ሲያዘንቡብን ነው የሰነበቱት። በእርግጥ በደረቁ ቢሆን ኖሮ ትንሽ ያሰለቸን ነበር (የኢህአዴግን አላውቅም!) ደግነቱ ግን ገንዘባቸውን እያወጡ  ነው ያደነቁን፡፡ (መታደል እኮ ነው!) ለሆቴል አልጋ… ለምግብና መጠጣቸው… ምሽት ላይ ሲዝናኑ… የመኪና ኪራይ… ከመዲናዋ ወጣ ብለው የቱሪዝም መስህቦችን ሲጐበኙ… ቀላል ይከፍላሉ (ጨዋታው እኮ በዶላር ነው!) በነገራችን ላይ በኮንፍረንስ ቱሪዝም ዙሪያ በEBC ማብራሪያ ሲሰጡ የሰማኋቸው ተርብ ተናጋሪ፤ በሰሞኑ ጉባኤ ጦቢያ በትንሹ እስከ 20 ሚ.ዶላር ገቢ ማግኘቷን ገምተዋል፡፡ ግማሹ ራሱ እኮ ቀልድ አይደለም (ያውም በጠፋ ምንዛሪ!) እኚሁ ባለሙያ (ካድሬማ ፕሮፓጋንዳ እንጂ ኢኮኖሚ አያውቅም!) የጉባኤ ቱሪዝም ላይ አተኩረን ከሰራን - የውጭ ምንዛሪ ገቢያችንን በቀላሉ ማሳደግ እንደምንችል ተናግረዋል። (ነቄ ባለሙያ ብያለሁ!) ይታያችሁ… በ5 ቀናት ከ5ሺ በላይ የጉባኤ ተሳታፊዎችን “ቤት ለእንግዳ” ብቻ ስላልን 20 ሚ. ዶላር (400 ሚ. ብር ገደማ እኮ ነው!) ከዘጋን ምን እንፈልጋለን? (መንግስት የአንድ ወር ታክስ ይማረን!) በቀጣዩ ሳምንት ደሞ ኦባማ አሉልን፣ (ጊዜው የኛ እኮ  ነው!) በነሐሴ እንዲሁ በዳያስፖራ እንጥለቀለቃለን (ብቻ እንደ ሚሊኒየሙ ጉድ እንዳይሰሩን!) እናላችሁ… ያኔ ኢህአዴግ ባለ 2 ዲጂት ዕድገት ምናምን የሚለውም ነገር በደንብ ይገባናል፡፡ (ካጣጣምነው አዎ!)
እናላችሁ… አንዳንድ አገራት ኒዮሊበራል ቢሆኑም በዕድገታችን ሲደመሙ እንጂ ዓይናቸው ደም ሲለብስ ስላላየን… ኢህአዴግ ፍረጃውንና ታፔላ መለጠፉን ቀነስ ቢያደርግ ክፋት የለውም (ትዝብት እኮ ነው ትርፉ!)
እኔ የምላችሁ… ለዳያስፖራው ጉባኤ በEBC የሚደረገው ያልተለመደ በትህትና የተጠቀለለ ግብዣ… የኦባማን የኢትዮጵያ ጉብኝት በመቃወም ዋይት ሃውስ ደጃፍ ላይ ሰልፍ የወጡትንም ይጨምራል… ወይስ እንዴት ነው? (“አውቀው በድፍረት ሳያውቁ በስህተት” በሚል ታልፈው ከሆነ ብዬ እኮ ነው!) አንድ ነገር ግን ሁሌም ግርም ይለኛል፡፡ የአበሻ ልጅ በየቀኑ እንደ ጉድ ይሰደዳል፡፡ (በፖለቲካውም በኢኮኖሚውም እያኮረፈ!) ከዚያስ? የዳያስፖራ ጥሪ እንደጉድ ይዥጐደጐዳል፡፡ (በፀባይ ሆነ እንጂ “ሰዶ ማሳደድ እኮ ነው!”) መጀመሪያውኑ ተስማምቶ መኖር የአባት ነው፡፡  እንዴት ነው ግን በጦቢያ ምድር እንዲህ ኩርፊያ የነገሰው? (የዚያ ትውልድ ውርስ እንበለው?!)
ይኼውላችሁ… እኛ እንደሆን ዲሞክራሲ ኮከባችን አይደለም፡፡ ቢያንስ ግን ለህፃናቱ  የዲሞክራሲ ት/ቤቶች ማሰልጠኛዎች በየአካባቢው ቢከፈቱ ሸጋ ይመስለኛል፡፡ ከእኛ ተመክሮ ተምረን ህፃናቱን በማለዳ በዲሞክራሲ ጠበል ማስጠመቅ የእኛ ዕጣፈንታ እንዳይገጥማቸው ያግዛቸዋል። አያችሁ… የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር  ወይም የመንግስት ባለሥልጣን ከሆኑ በኋላ ከዲሞክራሲ ጋር ለመለማመድ መድከም ትርፉ ጊዜ ማባከን ብቻ ነው (በሩብ ክ/ዘመን እኮ የመጣ ለውጥ የለም!) እንደውም የኋሊት ጉዞ እንጂ፡፡ ኢህአዴግን ወይም ተቃዋሚን “አምባገነን” በሚል ለማውገዝ አይደለም፡፡ ሃቅ ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ ኢህአዴግም ሆነ ተቃዋሚዎች ሲፈጥራቸው ፀረ - ዲሞክራሲያዊ ሆነው እኮ አይደለም፡፡ ይልቁንም ስለማያውቁት ነው ወይም ስለማናውቀው፡፡
ከምሬ እኮ ነው… ዲሞክራሲ ባህላችን አይደለም። ከልጅነት እስከ ዕውቀት ትውውቅ የለንም፡፡ ባል ሚስቱን፣ አባት ልጁን፣ ተማሪ አስተማሪውን፣ አለቃ ሎሌውን፣ የቤት እመቤት የቤት ሠራተኛዋን… እንዴት ነው treat የሚያደርጉት?? (አሁንም ድረስ ባል ሚስቱን የሚቀጠቅጥበት አገር ውስጥ እኮ ነን!) እናላችሁ…እኛና ዲሞክራሲ ሩቅ ለሩቅ ነን፡፡ በቅርባችን የምናገኘው የሱን ተቃራኒ ነው፡፡ ዕድሜ ለደርግ! ጭቆናና አፈና ብርቃችን አይደለም! (ኖረነዋላ!) ነፃነትንና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ግን አናውቃቸውም ወይም ዋጋ አንሰጣቸውም። (መክሊታችን አይደለም!!) እንደ ትምህርት ቶሎ ቶሎ በማጥናት የሚደረስበት ደሞ አይደለም፡፡ (ስንቱ ምሁርና ሊቅ ዲሞክራት ይሆን ነበር!) ሌላው ቀርቶ ዲሞክራሲ የሰፈነበት አገር (የዲሞክራሲ ባህር ውስጥ እንደማለት!) በመቀመጥም የሚዋሃድ ነገር አይመስለኝም፡፡ (ዳያስፖራውን አታዩትም?!)
እኔ እንደተረዳሁት… ዲሞክራሲ እንደ እነ አይፎን User friendly (ለአጠቃቀም ምቹ!) አይደለም፡፡ (ለአሁኑ ትውልድ ማለቴ ነው!) ቶሎ የሚለመድም የሚላመድም አልመሰለኝም (ስንት ዓመታችን?!) ፌስቡክ ላይ አንዱ የግል ሃሳቡን በማንፀባረቁ ወይም አቋሙን በመግለፁ የሚወርድበትን ውርጅብኝ እናውቀው የለ! እናላችሁ… ዲሞክራሲን ለምደን ላንለምደው ከምንታገልና ጊዜያችንን በከንቱ ከምናባክን… ለህፃናቱ መሰረት ብንጥልላቸው ትልቅ የአገር ውለታ ነው፡፡ (ለኛማ ዲሞክራሲ… It is too late!) መፍትሔው ለህፃናቱ የዲሞክራሲ ተማሪ ቤቶችን ማስፋፋት ነው (ዲሞክራሲ በጡጦ ሊሰጣቸው ይገባል!)
እንደኛ ወተት ተግተው ብቻ ወደ ቀይ ወጥ ከተሻገሩ፣ እኛኑ ነው የሚሆኑት (ይሄኔ ነው ፈረንጅ disaster የሚለው!) እውነቱን ልንገራችሁ አይደል… ከዲሞክራሲ ባህል የተፋታ ትውልድ ማለት የባከነ ነው፡፡ ለራሱም ለአገሩም የማይበጅ! ለሁሉ ነገር ጉልበት የሚቀናው! የአያቱን ጭስ የጠገበ ጦር ከተሰቀለበት ለማውረድ የሚጣደፍ! (በራሱ ዘመን የማይኖር!) እናም የእኛን ነገር እርሱት! (It is too late for democracy!) ይልቅስ የወደፊት አገር ተረካቢ ህፃናትን  ከደማቸው ጋር ዲሞክራሲን ለማዋሃድ እንትጋላቸው፡፡ እንደኛ ሲጐለምሱ የደሙ ዓይነት (A) ከዲሞክራሲ (O) ጋር አልጣጣም ይልባቸዋል - (ደሙ አላውቅህም ይለዋል - ዲሞክራሲን!)
እናላችሁ...የአገራችን ህዝብ ሳይማር እንዳስተማርን ሁሉ እኛም ዲሞክራት ሳንሆን ልጆቻችንን ዲሞክራት እናድርጋቸው! (ዲሞክራት ሳይሆኑ ዲሞክራት ያደረጉን ብለው ያመሰግኑናል!) ሌላ ምርጫ አለኝ ብትሉኝም አልሰማችሁም፡፡ (ዲሞክራሲ ኮከቤ አይደለም!!)

Read 5985 times