Saturday, 04 February 2012 11:32

ቢዝነስ የሚጠነሰሰው ከሃሳብ ነው! ትምህርት ያቋረጡትን ወደ ት/ቤት በመመለስ መበልፀግ

Written by  ኢዮብ ካሣ
Rate this item
(1 Vote)

ሰዎች ከትምህርት ጋር ዝምድና የሚፈጥሩበትን መንገድ መቀየር ለዛምቢያው መምህርና ሥራ ፈጣሪ (entrepreneur) ለሮዝየስ ስያትዋምቦ የህይወቱ ዋና ሥራ ሆኗል፡፡ስያትዋምቦ በዛምቢያ መዲና ሉሳካ የሚገኘው “Great North Road Academy” የተሰኘ የግል ት/ቤት መስራች ነው፡፡ትምህርት ቤቱ ትምህርት ያቋረጡ በማንኛውም እድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎችን ወደ ትምህርት እንዲመለሱ የሚያበረታታ ሲሆን በየክፍሎቹ ንቁ የመማር ተሳትፎን ለማበረታታት የሚያግዙ ፕሮጀክተሮች ተገጥመዋል፡፡ ክፍል መጥተው መማር የማይችሉ ትምህርት ፈላጊዎች ደግሞ በርቀት ትምህርት ፕሮግራም መመዝገብ የሚችሉ ሲሆን ትምህርቶቹ በዲቪዲዎችና በሲዲዎች ተቀርፀው እቤታቸው እንዲያጠኑት ይሰጣቸዋል፡፡

ትምህርቱን በመደበኛ መንገድ የተከታተለው ሚ/ር ስያትዋምቦ፤ ከዛምቢያ ዩኒቨርስቲ በትምህርት (education) ዘርፍ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡ ከምረቃ በኋላ ግን የእድሜ አቻዎቹን ፈለግ ላለመከተል እንደወሰነ ይናገራል፡፡

“የመንግስት መ/ቤት ለመግባት አልፈለግሁኝም፡፡ ሌላ የትም ቦታ የመቀጠር ፍላጐትም አልነበረኝም፡፡ እናም ማድረግ የነበረብኝ ልቤን መፈተሽ ነው… በዩኒቨርስቲ የተማርኩትን መፈተሽ… እናም አንድ ነገር ለመፍጠር እነዚያን ክህሎቶች መጠቀም ጀመርኩኝ፡፡” ሲል ተናግሯል ለቢቢሲ አፍሪካን ድሪም፡፡ ለትምህርት ባለው ጥልቅ ፍቅርና የራሱ አለቃ ለመሆን ከነበረው ቁርጠኝነት አንፃር በግል ት/ቤት የገበያ ዘርፍ ክፍተት እንደነበረ ተገነዘበ፡፡

“አብዛኛዎቹን የግል ት/ቤቶች ብትመለከቷቸው የሚተዳደሩት በመምህራን ሳይሆን በንግድ ሰዎች ነው፡፡ ስለዚህ ከትምህርት ጋር የተያያዘ የተለየ ነገር ይዤ መምጣት ፈለግሁኝ” ብሏል - ሥራ ፈጣሪው ስያትዋምቦ፡፡

ትምህርት ቤቱ ከመከፈቱና ሥራ ከመጀመሩ በፊት ግን ሃሳቡ በህዝቡ ዘንድ መሸጥ ወይም መተዋወቅ ነበረበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ህዝቡ ጋ መሄድ ወይም መድረስ የግድ ነበር፡፡ ሚ/ር ስያትዋምቦም ሃሳቡን የሸጠው ህዝብ ውስጥ እየገባ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ “አንዳንድ በራሪ ወረቀቶችን ማሳተምና ሰዎች ጋ መደወል ጀመርኩ፡፡ አስታውሳለሁ… ገና በጅምር ላይ ሳለን አንዳንዴ ቢሮዬን ለቅቄ እወጣና… በየጐዳናው እየተዘዋወርኩ ሰዎች አነጋግር ነበር” ብሏል ለቢቢሲ ጋዜጠኛው ለሙቱና ቻንዳ ሲያጫውተው፡፡

ስያትዋምቦ ሊከፍተው ያቀደው የግል ትምህርት ቤት እንዴት አገልግሎት እንደሚሰጥና እንዴት ከሌሎቹ የግል ት/ቤቶች ልቆ እንደሚወጣ በዓይነ ህሊናው መሳል የቻለው በእነዚህ ቀደምት የጅምር ምዕራፎች ነበር፡፡

“ከሌሎች ት/ቤቶች በምን የተለየን ልንሆን እንችላለን የሚለውን ማየት ጀመርን እናም የትምህርት ሥርዓታችንን ማዘመን፤ በት/ቤታችን ውስጥ የማይማሩትም ቢሆኑ እቤታቸው ተቀምጠው ምርጥ አገልግሎት እንደሚያገኙ ማረጋገጥን የመሳሰሉ አዳዲስ ሃሳቦችን ማፍለቅ ጀመርን፡፡ ይሄ ነው አሁን ያለንበት ደረጃ ላይ ከፍ አድርጐ እንድንታይ ያደረግን” ይላል - የዛምቢያው መምህር፡፡ ብዙ ሰዎች ግን በእቅዶቹ ላይ እምብዛም እምነት አልጣሉበትም፡፡

የሥራውን እቅዶች ለማስረዳት 50 ገደማ ለሚሆኑ ባንኮችና ድርጅቶች ፕሮፖዛል መፃፉን የሚያወሳው ሥራ ፈጣሪው፤ አንድም አዎንታዊ ምላሽ አለማግኘቱን ያስታውሳል፡፡ እሱ ግን ይሄን እንደ ሽንፈት (failure) አይቆጥረውም፡፡ ትልቅ ትምህርት ሆኖኛል ይላል፡፡

ለመሆኑ ምን አይነት ትልቅ ትምህርት ይሆን ያገኘው? “ሌሎች ሰዎች ወይም ሌሎች ድርጅቶች ላይ መመርኮዝ እንደማይገባ ተገንዝቤአለሁ፡፡ ልስራው ብለህ ከወሰንክ እኮ በራስህም ልትሰራው ትችላለህ፡፡ እኔ ለምሳሌ ይሄን ሁሉ የወረቀት ሥራ ለብቻዬ መወጣት አዳጋች ይሆንብኛል፤ ግን እሰራዋለሁ፤ ስለዚህ በራሴ ብቆም ይሻለኛል፡፡” አንድም ድርጅት ዞር ብሎ ያላየው ስያትዋምቦ፤ ፊቱን ወደ ክፉ ጊዜ ጓደኞቹ መመለሱ አልቀረም፡፡ እነሱም ግን አላሳፈሩትም፡፡ 15ሺ ዶላር ወይም ከ240 ሺ ብር በላይ ድጋፍ አድርገውለታል፡፡ ይሄንንና የግሉን ገንዘብ አንድ ላይ አድርጐ ነው ሃሳቡን ወደ ተግባር የለወጠው - “Great North Road Academy” በተከፈተ በመጀመርያው ወር ከ30 በላይ ተማሪዎችን የመዘገበ ሲሆን ዛሬ 700 ገደማ ተማሪዎች እና ከ30 የሚበልጡ ሠራተኞች አሉት፡፡

እሱ ቢዝነስ ለመጀመር ትልቅ ካፒታል ከመጠቀሙ አንፃር ቢዝነስ መጀመር እየፈለጉ እንደሱ የገንዘብ ምንጭ ለሌላቸው ወገኖች ምላሹ ምን ይሆን? “ቢዝነስ የምትጀምረው በገንዘብ አይደለም፤ በሃሳብ ነው፡፡ ያም ሃሳብ ማደግ አለበት” የሚለው ስያትዋምቦ፤ “ሃሳብ ነው ገንዘብ ወዳለበት የሚመራህ፡፡ እኔም ያንን ሃሳቤን ማሳደግ ነበረብኝ፡፡ ሃሳቡ ሲያድግ… ያኔ ነው አእምሮዬ ክፍተቱን ለመሙላት ጥቂት ገንዘብ ማግኘት ትችላለህ የሚለኝ፡፡ በርግጥ ቢዝነስ ለማስተዳደር ዋናው ጉዳይ ገንዘብ አይደለም ቢዝነስን የሚመራው አእምሮ ነው” ብሏል፡፡

አሁን የዛምቢያው ሥራ ፈጣሪ ትኩረቱን የፈተና መምሪያ ወደማዘጋጀት አዙሯል፡፡ እ.ኤ.አ በ2006 ዓ.ም ነበር “Exams Made Easy” የሚል መፅሃፍ የማዘጋጀት ሃሳብ የመጣለት፡፡ የተወሰኑ ቅጂዎችም በአገር ውስጥ አሳተመ፡፡ ሆኖም የህትመቱ ዋጋ ከአቅም በላይ ስለሆነበት ፊቱን ወደ ቻይና ለማዞር ተገደደ፡፡“50 ሺ ገደማ ካሳተምን በኋላ ነገሩ ፈታኝ ሆነብን፤ ምክንያቱም አገር ወስጥ መፅሃፍ ማሳተም በጣም ውድ ነበር” - ይላል ስያትዋምቦ፡፡

ስለዚህ ህትመቱ በቻይና እንዲከናወን ወሰነ፡፡ መፃህፍቱ ቻይና ታተሙና ወደ ዳሬሰላም በመርከብ ተጫኑ፡፡ ዳሬሰላም ግን አልደረሱም፡፡

አንድ መርከብ መፃህፍት ከመንገድ ላይ ተጠለፈ፡፡ ማን ጠልፎት ይሆን? ባለታሪኩ ይናገራል:-

“መፃህፍቱን የጫነው መርከብ ሶማሊያ ወስጥ ተጠለፈ፡፡ እስቲ አስቡት… የመፅሃፍቱ ምርቃት ሁለት ሳምንት ብቻ ነበር የቀረው፡፡ የማውቃቸውን ሰዎች፣ ሚኒስትሮችንና ሌሎችንም እንግዶች ጋብዣለሁ፡፡ እና ምን ይዋጠኝ? ምርቃቱን መሰረዝ? ጥሩ ምርጫ አልነበረም፡፡ አገር ውስጥ በታተሙት ጥቂት ቅጂዎች የምርቃቱ ሥነ ስርአት እንዲከናወን አደረኩኝ” ሲል ያጋጠመውን የመፃህፍት ጠለፋ ለቢቢሲው ጋዜጠኛ አውግቶታል፡፡

አያችሁልኝ… በቅፅበት የስኬት ማማ ላይ እንደማይወጣ! ከጥቃቅን እስከ አገር የሚያህሉ ችግሮችና ውጣ ውረዶች ታልፎ ነው የሚሹት ግብ ላይ የሚደረሰው፡፡ ይሄ ደግሞ ለዛምቢያው ተወላጅ ብቻ አይደለም፡፡ ለአሜሪካውም፣ ለአውሮፓውም፣ ለእስያውም፣ ለኢትዮጵያዊውም እኩል ይሰራል፡፡ የስኬት ፎርሙላው ይሄው ነው፡፡ ችግሮች+ በተስፋ የተሞላ ጥረት + ሌላ ውጣ ውረድ + ፅናት + በትእግስት የታጀበ ትጋት= ስኬት… ነው ነገሩ፡፡ ወደዛምቢያው መምህር እንመለስ፡፡

ስያትዋምቦ አሁን መፅሃፍቱን ከማሳደግ በተጨማሪ ት/ቤቱን ወደ ዩኒቨርስቲ የማስፋት እቅድ አለው፡፡ “አሁን መፅሃፉን ወደ ዲቪዲ ለውጨዋለሁ፡፡ አላማዬ ት/ቤቱን በቀጣዮቹ ሦስት ወይም አራት አመታት ወደ ዩኒቨርስቲ ማሳደግ ነው፡፡ ጥቂት መሬት ተሰጥቶኛል፡፡ አንደኛ ደረጃ፣ ሁለተኛ ደረጃና ዩኒቨርስቲንም የሚያካትት ኮምሌክስ ህንፃ ለመገንባት አልመናል፡፡ አሁን ሥራውን በገንዘብ የሚደግፈንን ፋይናንሰር እየመረመርን ነው፡፡ ከሦስት ዓመት በኋላ የህንፃው ግንባታ ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ብሏል - ዛምቢያዊው ሮዚየስ ስያትዋምቦ፡፡ ይሄ ሥራ ፈጣሪ እውነትም በአንደበቱ እንደገለፀው ቢዝነሱን የጀመረው ገንዘብ ይዞ አልነበረም - ሃሳብ እንጂ፡፡ ሁለተኛው ምዕራፍ ሃሳቡን ማሳደግ ነው ወይም ማብሰል፡፡ ሃሳቡ ሲበስል ገንዘብ ወዳለበት ይመራናል፡፡ ገንዘቡን ተጠቅመን ያሳደግነውን የቢዝነስ ሃሳብ ወደ ተግባር እንለውጣለን፡፡

ከአንደኛ ደረጀ ት/ቤት በመጀመር ዩኒቨርስቲ መገንባት ድረስ ልንጓዝ እንችላለን፡፡ ስኬትና ብልፅግና ማለትም ሌላ ሳይሆን ይኸው ነው፡፡ የማይክሮሶፍት መስራቹና ቢሊዬነሩ ቢል ጌትስ “ድሃ ሆኖ መወለድ ያንተ ጥፋት አይደለም፤ ድሃ ሆኖ መሞት ግን ያንተ ጥፋት ነው” ብሏል፡፡ ድሃ ሆነን ብንወለድም በልፅገን መሞት አለብን ነው ነገሩ፡፡ መታተር ነዋ!!

 

 

 

 

Read 3434 times Last modified on Saturday, 04 February 2012 11:37