Saturday, 18 July 2015 11:35

ስኳር ከእነ አካቴው ቢቀርብን ምን እናጣለን?

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(8 votes)

ለዓመታት ዋጋው ዝቅና ከፍ እያለ ሲያማርረን ከርሞ፣ ዛሬ ዋጋው ብቻ ሳይሆን ገበያ ውስጥ አለመገኘቱ የሚያስጨንቀን ስኳር፣ በጤናችን ላይ ቀላል የማይባል መዘዝ እንደሚያስከትል የሥነ ምግብ ተመራማሪዎች ይገልፃሉ፡፡
ለመሆኑ ይህንን ዋጋው ጣራ ከመንካቱም በላይ እንደ ልባችን መሸመት ያልቻልነውን ስኳር ባንጠቀም ምን ይቀርብናል?
የሥነ ምግብ ባለሙያዋ ወ/ሮ ህሊና ታደሰ እንደሚናገሩት፤ ለሰውነታችን አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን በምንገባቸው ምግቦችና መጠጦች ውስጥ በበቂ መጠን የምናገኝ በመሆኑ ተጨማሪ ስኳር ለምግብነትና ለመጠጥነት በምንጠቀምባቸው ነገሮች ውስጥ መጨመሩ በሰውነታችን ውስጥ ከአስፈላጊ መጠን በላይ የሆነ ስኳር እንዲጠራቀም ያደርገዋል፤ይህ ደግሞ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እጅግ ያመዝናል፡፡  
ለምግብነትም ሆነ ለመጠጥነት በምንጠቀምባቸው ነገሮች ውስጥ ስኳርን አለመጨመራችን የጣዕም ቀማሽ ህዋሳቶቻችንን ስሜት ለተወሰነ ጊዜ ቅር ከማሰኘት የዘለለ ጉዳት እንደሌለው የሚናገሩት ባለሙያዋ፣ የምንወስደውን የስኳር መጠን እየጨመርን በሄድን ቁጥር ከመጠን ላለፈ የክብደት መጨመር፣ ለስትሮክ፣ ለስኳር ህመምና ሌሎች በጤና ላይ ከባድ ችግር ለሚያስከትሉ በሽታዎች የመጋለጥ ዕድላችንም እየጨመረ እንደሚሄድ ጠቁመዋል፡፡
የሥነምግብ ተመራማሪዎች ስኳርን እጅግ አደገኛ በሆኑ አራት ትላልቅ ምድቦች ይከፍሉታል፡፡ አነዚህም ሱክሮስ፣ ፍሩክቶስ፣ የማር ስኳርና የብቅል ስኳር እየተባሉ የሚጠሩት ናቸው፡፡
ሱክሮስ
ለቤት ውስጥ ፍጆታ የምናውለው፣ ሻይ ቡናን ለማጣፈጥ የምንጠቀምበትና አሁን ገበያ ውስጥ እንደልብ ልናገኘው ያልቻልነው ስኳር ነው፡፡ ይህ የስኳር ዓይነት ምንም ዓይነት ቫይታሚንም ሆነ ማዕድን የሌለው ሲሆን ይህንን የስኳር አይነት ባለመጠቀማችን በሰውነታችን ላይ የሚያስከትልብን የጤና ችግር የለም፡፡ ይልቁንም ይህንን የስኳር አይነት አብዝተን መጠቀማችን ለሞት ሊዳርጉን ለሚችሉ ከባድ የጤና ችግሮች ሊያጋልጠን እንደሚችል የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡  
ፍሩክቶስ
በአትክልቶች ውስጥ የሚገኝና የደም ውስጥ ቅባትን በመጨመር የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ የስኳር አይነት በመጠኑ ከተወሰደ ለጤና ጠቃሚ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን ይዟል፡፡ ከመጠን ካለፈ ግን ችግር ማስከተሉ የማይቀር ነው፡፡ ህፃናትና ሰውነታቸው በበሽታና በልዩ ልዩ ምክንያቶች የተጐዱ ሰዎች የዚህ ዓይነቱ ስኳር በመጠኑ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ኃይል፣ አቅምና ብርታትንም በመስጠት ይታወቃል፡፡
የማር ስኳር
ይህ የስኳር ዓይነት በማር ውስጥ የሚገኝ ሲሆን የስኳር ይዘቱም እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ በአንድ ማንኪያ ማር ውስጥ 65 ካሎሪ ይገኛል፡፡ ተመሳሳይ መጠን ባለው ስኳር ውስጥ የሚገኘው የካሎሪ መጠን ግን 48 ብቻ ነው፡፡ ይህ የስኳር ዓይነት በመጠኑ ሲወሰድ የሰውነታችን አቅም ይጨምራል፣ እርጅናን ይከላከላል (የሰውነታችን ሴሎች ሥራቸውን በአግባቡ ለማከናወን እንዲችሉ ያደርጋቸዋል) በሌላ በኩል መጠኑን ያለፈ የማር ስኳር የበሽታ ምንጭ ይሆናል፡፡  
የብቅል ስኳር
በጥራጥሬዎች መብላላት ውስጥ የሚገኝና ከፍተኛ የስኳር ይዘት ያለው የስኳር ዓይነት ነው፡፡ ይህ ስኳር በሰውነታችን ውስጥ የሚገኙ ኢንዛይሞችና ቫይታሚኖችን በመምጠጥ ሰውነታችንን ያዳክመዋል፡፡ ብዙውን ጊዜ ብቅል ነክ በሆኑ ነገሮች የተሠሩ መጠጦችን አብዝተው የጠጡ ሰዎች ሰውነታቸው ሲደክምና ሲገረጣ የሚታየው በመጠጡ ውስጥ ያለውና በብቅል (በጥራጣሬዎች) መብላላት ሳቢያ የሚፈጠረው ስኳር በሰውነታቸው ውስጥ ያሉ ኢንዛይሞችን በመምጠጥ ስለሚያዳክማቸው ነው፡፡
የሥነምግብ ባለሙያዋ እንደሚናገሩት፤ በለስላሳ መጠጣችንም ሆነ ብቅል ነክ በሆኑ ነገሮች ተሠርተው ጥቅም ላይ የሚውሉ መጠጦችን አዘውትሮ መጠቀም ጤንነትን በእጅጉ የሚጐዳ ነው፡፡ በአንድ ጠርሙስ የለስላሳ መጠጥ ውስጥ 10 ማንኪያ ስኳርና 150 ካሎሪ እንደሚገኝ የጠቆሙት ባለሙያዋ፤ አንድ ሰው በቀን ከ12 ማንኪያ በላይ ስኳር መጠቀም እንደሌለበት ተናግረዋል፡፡
እየጣፈጡን የምንወስዳቸው ምግቦችና መጠጦች መዘዛቸው ከባድ በመሆኑም ጥንቃቄ ልንወስድ እንደሚገባ የስነምግብ ባለሙያዎች ያሳስባሉ፡፡     

Read 8845 times