Saturday, 18 July 2015 11:44

“...ግልጽ ውይይት ...በስነተዋልዶ ጤና ዙሪያ...”

Written by  ዮዲት ባይሳ (ከኢሶግ)
Rate this item
(0 votes)

  “...አንዳንድ እርእሶችን ዝም ብለን ሸፋፍነን የምናልፍባቸው ግዜያት አሉ፡፡ ምክንያቱም ጠለቅ ብለን ካወራን ቤተሰቦች ሌላ ነገር ሊያስቡ ይችላሉ፡፡”
“...የወርአበባዬ የመጣ የመጀመሪያ ቀን... በጣም ነበር የደነገጥኩት አስቀድማ እናቴ ብትነግረኝ ኖሮ... ላልደነግጥ እችል ነበር፡፡ ስነግራት አደግሽ ማለት እኮ ነው ...ብቻ ነበር ያለችኝ”
ከላይ ያነበባችሁት ለዚህ እትም የተጋበዙት እንግዶች ከተናገሩት እውነታ የተወሰደ ነው፡፡ ሌላ እውነታም ታነቡ ዘንድ እነሆ...   
ልጅቷ ከትምህርት ቤት የተሰጣትን የቤት ስራ ይዛ ወደ እቤት ተመልሳለች፡፡ እቤት ስትደርስ ያገኘችው ታላቅ እህቷን ነበር፡፡ ወዲያው “የወር አበባ ምንድነው?” አለቻት ጮክ ብላ በነጻነት...፡፡ እንዳሰበችው ለጥያቄዋ መልስ ሳይሆን ጥፊ ነበር ያገኘችው፡፡ ጥፊ ያደነዘዘውን ጉንጯን በእጇ ይዛ “ጠይቁ ተብለን እኮ ነው” አለች እያለቀሰች፡፡ እህት ነገሩን በዝምታ ለማለፍ ብትሞክርም ልጅት ቀጥላለች “እሺ ጋሼን ብጠይቀው ይነግረኛል?” አባቷን ማለቷ ነበር፡፡ “...ሁለተኛ ከሰው ፊት እንዲህ ብለሽ ስታወሪ እንዳልሰማሽ...” ከባድ ማስጠንቀቂያ ከሌላ ዱላ ጋር...፡፡ ለካስ የቤት ስራው ይህ ነበር፡፡ የአካባቢ ሳይንስ መምህራቸው “የወርአበባ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ቤተሰቦቻችሁን ጠይቃችሁ እንድትመጡ፡፡” ብሎ ነበር። እሷም እንደታዘዘቸው ነበር ያደረገችው ያላሰበችው ዱብእዳ ገጠማት እንጂ፡፡
ታሪኩ ይህን ፅሁፍ ሳዘጋጅ የስራ ባልደረባዬ “የመጨረሻ ልጄ የቤት ስራ” ብላ ያጫወተችኝ ነው። ምናልባትም ይህ የብዙዎቻችን ገጠመኝ ሊሆን ይችላል። ስንቶቻችን ነን በስነተዋልዶ ጤናም ይሁን በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ለምናነሳቸው ጥያቄዎች ትክክለኛ መልስ እያገኘን ያደግን? ምላሻችሁን መገመት አያዳግትም፡፡      
በተለያየ ግዜ የተደረጉ ጥናቶች ወላጆች በስነተዋዶጤና ጉዳዮች ላይ ከልጆቻቸው ጋር ግልፅ የሆነ ውይይት ለማድረግ ምቾት እንደማይሰማቸው እና ይህን ለማድረግም ያላቸው ተነሳሽነት ዝቅተኛ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ወጣቶች በተገቢው ግዜ ማግኘት የሚገባቸውን ትምህርት ወይም ደግሞ መረጃ ሳያገኙ ይቀራሉ፡፡
ለዚህ እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱት ነገሮች መካከል ወላጆች ይህን መሰል ጉዳዮችን የማሳወቅ ግዴታ የትምህርት ቤቶች ነው ብለው በማሰባቸው እንደሆነ በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን የስነተዋልዶ ጤናን እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ትምህርቶችን ለልጆች ለመስጠት ወላጆች ወይንም ቤተሰቦች በጣም ቅርብ መሆናቸው እሙን ነው፡፡
ወንዶችም ሆኑ ሴት ልጆች የስነተዋልዶ ጤና ላይ በቂ እውቀት እና ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ነገር ግን ሴቶች ከወንዶች በተለየ መልኩ የተለያዩ አካላዊ ለውጦችን ስለሚያስተናግዱ፤ እንዲሁም የዛሬ ሴት ልጆች የነገ እናቶች በመሆናቸው በዚህ ዙሪያ ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡
በጉርምስና ግዜ የሚከሰት አከላዊ እድገትን እና የባህሪ ለውጦችን፣ ወሲባዊ ግንኙነት በሰዎች ህይወት ውስጥ የሚኖረውን ቦታ እንዲሁም ሌሎች ጤና ነክ ጉዳዮች ለውይይት ቀርበው ወጣቶች በቂ ግንዛቤ ሊያገኙባቸው ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡
ለዚህ እትም ከጋበዝናቸው ወጣቶች መካከል አንድዋ ሰራዊት ትባላለች፡፡ ሰራዊት በአስራዎቹ የእድሜ ክልል ላይ የምትገኝ ታዳጊ ነች፡፡
ከቤተሰቦቿ ጋር ጥሩ የሚባል ግንኙነት እንዳላት እና በማንኛውም ጉዳይ ላይ ግልፅ ውይይት እንደሚያደርጉ ትመሰክራለች፡፡ ይህ የሆነው “ግልፅነት በእኛ ቤተሰብ ውስጥ ያለ እና እንደ ባህል የያዝነው ነገር ስለሆነ ነው” ትላለች፡፡ “በይበልጥ  ከአባቴ ጋር  ነው የምናወራው። እቤታችን ውስጥ ግልፅ ውይት ስላለ ለእኔ ያን ያህል ከባድ አይደለም፡፡” ይሁን እንጂ... ግልፅ ውይይት ቢያድርጉም የውይይት እርእሶቹ በእጅጉ የተገደቡ እንደሆኑም አልሸሸገችም፡፡
“...አንዳንድ እርእሶችን ዝም ብለን ሸፋፍነን የምናልፍባቸው ግዜያት አሉ፡፡ ምክንያቱም ጠለቅ ብለን ካወራን ቤተሰቦች ሌላ ነገር ሊያስቡ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ወሲብ ነክ ጥያቄዎችን በምትጠይቂበት ግዜ ወላጆች ነገሩን ያደረግሽው ወይም ለማድረግ ሀሳብ እንዳለሽ ሊያስቡ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ እኔም ደፍሬ አልጠይቅም እነሱም ይህን ጉዳይ አያነሱትም፡፡”
ሌላዋ ወጣት ሜሮን ትባላለች፡፡ ሜሮን የ22 አመት ወጣት ነች፡፡ አሁን ላይ ሜሮን የስነተዋልዶ ጤና ጉዳዮችን በሚመለከት ያላት ግንዛቤ በቂ የሚባል እንደሆነ ትናገራለች፡፡ ነገር ግን ይህ ከቤተሰቦቿ ጋር በምታደርገው ውይይት የመጣ ሳይሆን ከትምህርት ቤት እንዲሁም በግል ከተለያዩ መረጃዎች ያገኘሁት ነው ትላለች፡፡
“በእኛ ቤተሰብ ውስጥ በዚህ ጉዳይ ላይ ውይይት ብሎ ነገር ኖሮ አያውቅም፡፡ እኔም ሆንኩ እህቶቼ ብዙውን ነገር ያወቅነው ከትምህርት ቤት እና ከተለያዩ መረጃዎች ነው፡፡ አስታውሳለሁ ...የወርአበባዬ የመጣ የመጀመሪያ ቀን በጣም ነበር የደነገጥኩት፤ ይህ ነገር እንደሚፈጠር አስቀድማ እናቴ ብትነግረኝ ኖሮ ምናልባት ያን ያህል ላልደነግጥ እችል ነበር፡፡ ከሆነ በኋላ እንኳን ስነግራት አደግሽ ማለት እኮ ነው ብቻ ነበር ያለችኝ”  
በሀገራችን ከቤተሰብ ወይም ከአሳዳጊ ጋር ይህን መሰል ውይይቶችን ማድረግ የተለመደ አይደለም። ውይይት ለማድረግ ሀሳብ ይሰጣል ያልነውን መረጃ ለንባብ ብለናል፡፡
//////////////////////////////
በስነተዋልዶ ጤና ዙሪያ  ወላጆች እና ልጆቻቸው የሚኖራቸውን ግንኙነት እንዴት ማጠንከር ይቻላል?
ብዙ ወላጆች የስነተዋልዶ ጤናን የተመለከቱ ጉዳዮችን ከልጆቻቸው ጋር በግልፅ ለመወያየት ከባድ ሲሆንባቸው ይስተዋላል፡፡ ነገርግን በቤተሰብ ውስጥ ይህ አይነቱ ውይይት እንዲኖር ለማድረግ የሚረዱ መንገዶች አሉ፡፡
እናቶች ለልጆቻቸው በእጅጉ የቀረቡ እና የስነተዋልዶ ጤናን በተመለከተ የሚኖሩትን አካላዊውም ሆነ ስነልቦናዊ ጉዳዮችን ከልጆቻቸው ጋር ለመወያየት ዝግጁ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡
እናቶች ከወንዶችም ሆነ ከሴት ልጆቻቸው ጋር የቀረበ ግንኙነት መፍጠር እና ልጆቻቸው ነፃነት እንዲሰማቸው ማድረግ አለባቸው፡፡
ወላጆች የስነተዋልዶ ጤናን በተመለከተ በሚኖሩት ውይይቶች ላይ ሴቶችም ሆኑ ወንዶች ልጆቻቸው እንደ የወር አበባ ባሉ የስነተዋልዶ ጉዳዮች ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ስኬታማ ውይይቶች
አንዳንድ ቤተሰቦች ስነተዋልዶ ጤናን እንዲሁም ወሲብ ነክ ጉዳዮችን በተመለከተ ከልጆቻቸው ጋር ግልፅ የሆነ ውይይት ያደርጋሉ፡፡ ይህም የሚከተሉትን ሁኔታዎች ያካትታል፡-
ወላጆች ጥሩ አድማጭ መሆን
ወላጆች ልጆቻቸው ለሚያነሱላቸው ጥያቄዎች በቂ እና ታአማኒ ምላሾችን መስጠት
በውይይት ወቅት ልጆች የግል አመለካከታቸውን ያለ ምንም ተፅእኖ እንዲናገሩ መፍቀድ
ልጆች ጥብቅ የሆነ መመሪያ እንዲከተሉ ከማድረግ ይልቅ ቀርቦ ውይይት በማድረግ ሀሳብ ማቀበል
ይህ ሲሆን ልጆች በወላጆቻቸው ዘንድ ተሰሚነት እንዳላቸው እና ወላጆቻቸው ከጎናቸው እንደሆኑ ያስባሉ።
ውይይቱን የሚያውኩ ነገሮችን ማስወገድ
አንዳንድ ሁኔታዎች ውይይቱን ሊያውኩ እና ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊመሩት ይችላሉ፡፡ በውይይት ወቅት መወገድ ከሚገባቸው ሁኔታዎች መካከል፡-
ልጆ ከእርሶ ጋር ተመሳሳይ አቋም እንዲኖረው አለመጠበቅ
የያዙት ሀሳብ ትክክል ባይሆን በትእግስት ለማስረዳት መሞከር
ሀሳባቸውን ከመተቸት መቆጠብ ወይም አለመቆጣት
በንግግራቸው መሀል ጣልቃ አለመግባት
በጥሞና ማዳመጥ
ሁልግዜ የእርሶ መመሪያ እና ክትትል እደሚያስፈልጋቸው አለማሰብ “ምክሮ እንደሚያስፈልጋቸው ቢሰማዎት እንኳን አስቀድመው ምክንያቱን መንገር ይኖርቦታል።”
ወሲብ ነክ ጥያቄዎች ሲቀርብሎት ስለልጆ መጥፎ ወይም የተሳሳተ አመለካከት መያዝ የለቦትም፡፡ ቁጣ የተቀላቀለበት ምላሽ ልጆችዎ ዳግመኛ ተመሳሳይ ጥያቄዎችን እንዳያነሱ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡
ምንጭ፡-  Better health channel

Read 3344 times