Saturday, 18 July 2015 11:45

የሰላም ኖቤል ተሸላሚው ዴዝሞን ቱቱ ሆስፒታል ገቡ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

     ከ10 አመታት በላይ የፕሮስቴት ካንሰር ህክምና ተከታትለዋል
   ደቡብ አፍሪካዊው የኖቤል የሰላም ተሸላሚ ሊቃነ ጳጳስ ዴዝሞን ቱቱ ባለፈው ማክሰኞ ባጋጠማቸው ህመም ኬፕታውን ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ገብተው ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኙ ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ምንነቱ በውል ባልተገለጸ በሽታ ተጠቅተው ሆስፒታል የገቡት የ83 አመቱ ዴዝሞን ቱቱ፤ ከአስር አመታት በላይ የፕሮስቴት ካንሰር ህክምና ሲደረግላቸው እንደቆየ ያስታወሰው ዘገባው፣ ወደ ሆስፒታል ያስገባቸው የሰሞኑ ህመም ግን፣ ከዚህ ጋር የተያያዘ መሆን አለመሆኑ አለመታወቁን ገልጿል፡፡ የዴዝሞን ቱቱ ልጅ ሞህ ቱቱ አባቷ ተገቢውን ህክምና በማግኘት ላይ እንደሆኑና በጥቂት ቀናት ውስጥ አገግመው ከሆስፒታል ይወጣሉ የሚል ተስፋ እንዳላት መናገሯን ዘገባው ጠቁሞ፣ ኢንፌክሽን ከመሆኑ ውጪ የህመማቸውን ምንነት በተመለከተ ዝርዝር መረጃ አለመገኘቱን ጠቁሟል፡፡
ከአስር አመታት በላይ በፕሮስቴት ካንሰር ህክምናቸውን ሲከታተሉ የቆዩት ዴዝሞን ቱቱ፣ ባለፈው ታህሳስ ወር ላይም ወደ ሮም ለመጓዝ ይዘውት ነበረውን እቅድ ህክምናቸውን ለመከታተል ሲሉ መሰረዛቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
የአፓርታይድ አገዛዝን በጽናት በመቃወም የሚታወቁት ዴዝሞን ቱቱ፤ እ.ኤ.አ በ1984 የኖቤል የሰላም ሽልማትን እንደተቀበሉና ከቀናት በፊትም ከባለቤታቸው ሊያ ጋር የጋብቻቸውን 60ኛ አመት በዓል ማክበራቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡

Read 1328 times