Saturday, 18 July 2015 11:46

ሙሴቬኒ የብሩንዲን ግጭት ለማስቆም ድርድር ሊያደርጉ ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

- አወዛጋቢው የአገሪቱ ምርጫ ማክሰኞ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል
- ክልላዊው ፍርድ ቤት ግጭቱን ማጣራት ጀምሯል
       በመጪው ማክሰኞ ይከናወናል ተብሎ ከሚጠበቀው የብሩንዲ ምርጫ ጋር በተያያዘ በአገሪቱ የተቀሰቀሰውን ግጭት መፍታት የሚቻልበትን ሁኔታ ለመፍጠር የአገሪቱ የፖለቲካ ሃይሎች በኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩሪ ሙሴቬኒ አደራዳሪነት ውይይት ሊያደርጉ ነው ሲል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገበ፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለወራት የዘለቀውን የብሩንዲ ግጭት ለማስቆምና በፖለቲካ ሃይሎች መካከል የተፈጠረውን ችግር በድርድር ለመፍታት ሙከራ ቢያደርግም ሳይሳካለት ቀርቷል ያለው ዘገባው፤ ዩሪ ሙሴቬኒ የአገሪቱን መንግስትና የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮችን ለማደራደር ባለፈው ማክሰኞ ቡጁምቡራ መግባታቸውን ገልጿል፡፡
አምስት የምስራቅ አፍሪካ አገራትን በአባልነት በያዘው የኢስት አፍሪካ ኮሚዩኒቲ ድርድሩን እንዲመሩ ባለፈው ሳምንት የተመረጡት ሙሴቬኒ፣ በመጪው ማክሰኞ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀውን አወዛጋቢ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሰላማዊ ለማድረግና ተልዕኳቸውን ለማሳካት የቻሉትን ሁሉ ጥረት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡ ሙሴቬኒ ባለፈው ማክሰኞ ከብሩንዲ ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ መወያየታቸውንም ዘገባው ገልጿል። ክልላዊው የምስራቅ አፍሪካ የፍትህ ፍርድ ቤት በበኩሉ፤ በብሩንዲ የተከሰተውን ግጭት በተመለከተ ከሳምንታት በፊት የቀረበለትን ክስ በታንዛኒያ መዲና አሩሻ ባለፈው ማክሰኞ የምርመራ ሂደት መጀመሩን አስታውቋል፡፡
ፓን አፍሪካን ሎየርስ አሶሴሽንና ኢስት አፍሪካን ሲቪል ሶሳይቲ ፎረም የመሰረቱት ክስ፣ የብሩንዲ የህገመንግስት ፍርድ ቤት ለግጭቱ መንስኤ የሆኑት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ በምርጫው መሳተፍ ይችላሉ በሚል ያስተላለፈውን ውሳኔ እንዲሻር የሚጠይቅ ነው ተብሏል፡፡
ፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ ባለፈው ሚያዚያ ወር ላይ ህገ መንግስቱ ከሚፈቅድላቸው ውጪ ለሶስተኛ ዙር በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለመወዳደር ማስታወቃቸውን ተከትሎ በአገሪቱ በተቀሰቀሰውና ለወራት በዘለቀው ግጭት ከ77 ሰዎች በላይ ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውንና ከ100ሺህ በላይ ዜጎችም ወደ ጎረቤት አገራት መሰደዳቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡

Read 2064 times