Saturday, 04 February 2012 11:42

ያያ የስፖርት መንደር ስራ ጀመረ ለኦሎምፒያኖች ነፃ አገልግሎት ይሰጣል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

በሱልልታ የተገነባው ያያ የስፖርት መንደር መንደር ባለፈው ሳምንት በይፋ ስራ የጀመረ ሲሆን በለንደን ኦሎምፒክ ተሳታፊ ለሚሆነው የኢትዮጵያ ቡድን አትሌቶች ነፃ አገልገሎት ለመስጠት ቃል ገባ፡፡ የስፖርት መንደሩ ስራ መጀመሩን በይፋ ባሳወቀበት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተገኘው ሃይሌ ገብረስላሴ የስፖርት መንደሩን መገንባት ፈርቀዳጅ ተግባር  ብሎ አድንቆታል፡፡ ይህ አይነት የስፖርተ መሰረተ ልማት በፌደሬሽኑ ብቻሳይሆንበሌሎች ባለድርሻ አካላት ባለቤት ኖሮት መስፋፋት አለበት ያለው ሃይሌ ከአዲስ አበባ ውጭም በበቆጂ በማይጨው በጎጃምም መስፋፋት እንዳለበት አሳስቧል፡፡ በኬንያ ተመሳሳይ የልምምድ እና የስፖርት ማዕከላት መስፋፋታቸው ውጤታማነታቸውን ከማሳደጉም በላይ በርካታ አትሌቶችን ለማፍራት እድል የፈጠረ ተመሳሳይ የመሰረተ ልማት እንቅስቃሴ ነው፡፡

ሃይሌ በስፖርቱ መነገድ ቀጣይ እድገትን ማረጋገጥ ስለሆነ ህጋዊ መሰረት ኖሮት በስፋት እንዲቀጥል ሲመክር ፓውላ ራድክሊፍ ብዙ ዶላር በማውጣት የለንደን ኦሎምፒክ ዝግጅቷን በኬንያ እያደረገች መሆኗን በምሳሌነት ጠቅሶ የስፖርት መንደሮችና የልምምድ ማዕከሎችን ማስፋፋት ለአገር ውስጥ አትሌቶች ከሚሰጠው ጉልህ ጥቅም ባሻገር የውጭ አገር አትሌቶችን በመሳብ የውጭ ምንዛሬ የማስገኘት ከፍተኛ አቅም ይኖረዋል ብሏል፡፡ ወደፊት በተመሳሳይ የመሰረተ ልማት አቅጣጫ የመስራት ፍላጎቱን በመግለጫው ያስታወቀው ሃይሌ ከዮሴፍ ክብሩ ጋር በሽርክና ሊሰራ የፈቀደው የስፖርት መንደሩን ፈርቀዳጅነት ለመደገፍ መሆኑንም ተናግሯል፡፡ ያያ የስፖርት መንደር አጠቃላይ ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ሲገባደድ እስከ 80 ሚሊዮን ብር ይፈጃል፡፡ የስፖርት መንደሩ ከሁለት ዓመት በፊት  በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ካናዳዊ በሆነው ዮሴፍ ክቡር  90 በመቶ ድርሻ የተመሰረተ ሲሆን በ1992 እና 93 እኤአ ለካናዳ የሮጠ አትሌት ነበር፡፡ ለስፖርት መንደሩ ግንባታ መሳካት ሃይሌ በገንዘብ ካደረገው ድጋፍ በተጨማሪ በአማካሪነት እና ሞራል በመስጠት ላደረገለት ድጋፍ ያመሰገነው ዮሴፍ ሱልልታ በርካታ የኢትዮጵያ አትሌቶች ለልምምድ የሚመርጡት አካባቢ በመሆኑ ለመንደሩ ግንባታ እንደተመረጠ ገልፆ አትሌቶች ብዙውን ጊዜ ልምምድ ሰርተው ላባቸው ሳይደርቅ ወደ ከተማ የሚመለሱበትን ሁኔታ ስለሚያስቀር ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣቸዋል ብሏል፡፡ ከዮሴፍ ክብሩ ጋር  የኦሎምፒክ ሻምፒዮኑ ሃይሌ ገብረስላሴ ፤ የአትሌት ማናጀሩ በላይ ወላሼ እና ተመስገን አለሙ ሌሎቹ የያያ የስፖርት መንደር ባለድርሻዎች ናቸው፡፡ የስፖርት መንደሩ ደረጃውን የጠበቀ የስፖርት መሰረተ ልማትን ለአገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ አትሌቶች የሚሰጥበት የተሟላ አቅም ይኖረዋል፡፡ ከአዲስ አበባ መሃል 11 ኪሎሜትር ርቃ በምትገኘው ሱልልታ የተገነባው የስፖርት መንደሩ በ50ሺ ሄክታር ላይ የተገነባ ሲሆን ለ30 ሰዎች መኝታ በማቅረብ ባለ አራት ኮከብ ደረጃ የሆቴል መዝናኛ አገልግሎት የሚሰጥ ነው፡፡ በ250 ካሬ ላይ የሰፈረ ጂምናዚዬም ያለው የስፖርት መንደሩ ባለ 400ሜ የመሮጫ መም፤ የእግር ኳስ ሜዳ ፤የፈረስ መጋለቢያ መስክ እና የህፃናት መጫወቻ ስፍራ አለው፡፡  የስቲም ባዝ፤  የፊዝዮ ቴራፒና የማሳጅ አገልግሎትም ይገኝበታል፡፡ የስፖርት መንደሩ አገልግሎት መስጠት ቢጀምርም  ሙሉ ለሙሉ ግንባታው ሲያበቃ የመዋኛ ገንዳ፤ የቴኒስ ሜዳ እና መለስተኛ የጎልፍ መጫወቻ መስክ ይኖረዋል፡፡ የስፖርት መንደሩ ለአገር ውስጥ አትሌቶች ሁነኛ የመለማመጃና የማረፍያ አገልግሎት ከመስጠቱም በላይ ለ50 ሰዎችም የስራ እድል የፈጠረ ሆኗል፡፡

 

 

 

Read 2265 times Last modified on Saturday, 04 February 2012 11:45