Monday, 27 July 2015 10:08

ሴናተር ኦባማ - በድሬደዋ (የዛሬ 9 ዓመት)

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(12 votes)

ጊዜው 1998 ዓ.ም፡፡ ወቅቱ እንደ አሁኑ ክረምት ነው፡፡ ድሬዳዋ በደረሰባት ድንገተኛ የጐርፍ አደጋ ከ260 በላይ ነዋሪዎቿ ለህልፈት የተዳረጉበት ክፉ ጊዜ ነበር፡፡ ሐምሌ 29 እኩለ ሌሊት ላይ ከከተማዋ ደጋማ አጐራባች አካባቢዎች ተጠራቅሞ የመጣው ጐርፍ ያስከተለው አደጋ ከሞቱት በተጨማሪ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎችን ከመኖሪያ ቤታቸው አፈናቅሏቸዋል፡፡
የከተማዋ አስተዳደር በጐርፍ አደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጐች ለመታደግ አቅም አጠረው። በአደጋው ቤት ንብረታቸውን ያጡ በርካቶች በየትምህርት ቤቶቹ እንዲጠለሉ ቢደረግም ሁኔታው ከአቅም በላይ ሆነ፡፡
ይሄኔ ነው ለጋሽ ድርጅቶች የእርዳታ እጃቸውን እንዲዘረጉ ጥሪ የቀረበው። ለጥሪው አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ቀዳሚነቱን የያዘው የአሜሪካ ባህር ኃይል፤ ጅቡቲ ከሚገኘው ካምፑ እያንዳንዳቸው 28 ሰዎችን የሚይዙ 60 ድንኳኖችን በመጫን ድሬዳዋ ከተማ ደረሰ፡፡ ይህ እርዳታ በወቅቱ እጅግ ከፍተኛ ግምት የተሰጠውና የብዙዎችን ህይወት የታደገ ነበር፡፡ ድንኳኖቹ በአደጋው ምክንያት ቤት ንብረታቸውን ላጡት ነዋሪዎች፣ አስተዳደሩ ቤት ሰርቶ እስከሚሰጣቸው ድረስ ለመጠለያነት አገልግለዋል፡፡
ይህንን የባህር ኃይሉን በጐ ተግባር ለመጐብኘት የአሁኑ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት፣ የዚያን ጊዜው የኢሊኖይሱ ሴናተር ባራክ ኦባማ ድሬዳዋ የገቡት አደጋው ከተከሰተ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ነበር። በወቅቱ ለኦባማ በአስተርጓሚነት ይሰራ የነበረው ወጣት ሄኖክ ወንድሙ፤ “ኦባማ ቀለል ያለና ተጫዋች ነበር፤ በድሬዳዋ ከተማ በተከሰተው አደጋም እጅግ ማዘኑን አስታውሳለሁ ብሏል፡፡ ያኔ ሄኖክ የሁለተኛ ዓመት የህግ ተማሪ ሲሆን ኦባማም የህግ ምሩቅ መሆኑን ነግሮኝ ነበር ይላል፡፡
ኦባማ ወደ አገሩ ከተመለሰ በኋላ ከሄኖክ ጋር የተነሱትን ፎቶግራፍ በኢሜይል እንደላከለት የሚናገረው ሄኖክ፤ ፎቶግራፉ በወቅቱ ብዙ ስሜት እንዳልሰጠው ያስታውሳል፡፡ ፎቶውን ለረዥም ጊዜ ረስቶት እንደቆየ ጠቁሞ ኦባማ ፕሬዚዳንት ሆነው ሲመረጡ ፎቶው በቅርብ ጓደኛው አማካኝነት ለአደባባይ መብቃቱን ገልጿል፡፡
በአሁኑ ወቅት በግል የንግድ ሥራ የሚተዳደረው ሄኖክ፤ ከኦባማ ጋር አብሮ የተነሳውን ፎቶ በሞባይል ስልኩ ላይ ስክሪንሴቨር ያደረገው ሲሆን ብዙዎች ግን እንደሚጠራጠሩትና በፎቶሾፕ የተሰራ ነው እንደሚሉት ይናገራል፡፡ ሆኖም ከአገሪቱ ታላላቅ ባለስልጣናት አስቀድሞ ከመጀመሪያው የአሜሪካ ጥቁር ፕሬዚዳንት ጋር ፎቶ ለመነሳት የቻለ ብቸኛ ኢትዮጵያዊ መሆኑን በኩራት ይገልፃል፡፡
ሴናተሩ ኦባማ ድሬን በጐበኙበት ወቅት ለፕሬዚዳንትነት እንደሚወዳደሩ ይወራ ነበር የሚለው ሌላው የድሬ ነዋሪ ካሊድ ኢስማኤል፤ በአሜሪካ ባህር ኃይል የተደረገውን እርዳታ እንዲመለከቱ ተጋብዘው ከነበሩት የአሜሪካ ወታደራዊ ባለስልጣናት ይልቅ ለኦባማ ጠንከር ያለ ጥበቃ ይደረግላቸው እንደነበርም ያስታውሳል፡፡
ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ሴናተር ኦባማ ወደ ድሬዳዋ የመጡት በጅቡቲ በኩል ሲሆን በወቅቱም ጅቡቲ የሚገኘውን የአፍሪካ ቀንድ ፀረ ሽብር ጥምር ግብረ ኃይል እንቅስቃሴን በመጐብኘት ላይ ነበሩ። ድሬዳዋ ሲገቡ የተደረገላቸው ጥበቃ እምብዛም የተጠናከረ አልነበረም፡፡ በሶስት አጃቢዎችና በጥቂት መኪኖች የኢትዮጵያን ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ የረገጡት ሴናተር ኦባማ፤ አሁን ግን ኢትዮጵያን የሚጐበኙት በከፍተኛ ወታደራዊ አጀብ ነው። ፕሬዚዳንቱ በኬንያና በኢትዮጵያ ለሚያደርጉት ጉብኝት እስከ 2 ቢሊዮን ብር የሚገመት ገንዘብ ወጪ እንደሚደረግ የሚገመት ሲሆን አብዛኛው ወጪም ለጥበቃና ደህንነታቸው የሚውል ነው ተብሏል፡፡ ለኦባማ የሚደረገው ጥበቃ በልዩ ትእዛዝ በተሰሩና ጥይት በማይበሳቸው መኪኖች፣ በተጠናከረ የአየር ላይ ጥበቃ፣ በሃምሳ ስድስት ልዩ ተሽከርካሪዎችና ከ250 በላይ በሚሆኑ የደህንነት ሠራተኞች የተደራጀ ነው፡፡

Read 6025 times