Monday, 27 July 2015 10:10

ጉብኝቴ በዲሞክራሲና ሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል - ኦባማ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(24 votes)

 ተቃዋሚዎች ኦባማ በአፍሪካ ህብረት በሚያደርጉት ንግግር ላይ እንዲገኙ ተጋብዘዋል
            በኢትዮጵያ ይፈፀማሉ የተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በቸልታ እንዳያልፉ ተጠይቀዋል
                           
   ፕሬዚዳንት ኦባማ በኬንያና በኢትዮጵያ በሚያደርጉት ጉብኝት፣ በዲሞክራሲና በሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ መሻሻል እንዲፈጠር ግፊት ሊያደርጉ እንደሚችሉ የጠቆሙ ሲሆን በኬንያ ተቃዋሚዎችን እንደሚያነጋግሩ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ማክሰኞ እለት ፕሬዚዳንቱ በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ  በሚያደርጉት ንግግር ላይ እንዲገኙ የተጋበዙ ሲሆን በስብሰባው ላይ የአፍሪካ አገራት ተወካዮችና የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ይሳተፋሉ፡፡
የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያን ሲጐበኙ እኛንም ያነጋግሩን የሚል ደብዳቤ በአዲስ አበባ ለሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ማስገባታቸው የሚታወቅ ሲሆን እስካሁን ፕሬዚዳንቱ ፓርቲዎችን በተናጠል የማነጋገር ዕቅድ እንዳልያዙ የኤምባሲ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የኢዴፓ የሥራ አስፈፃሚ አባልና የጥናትና ምርምር ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ ሦስቱ ፓርቲዎች ለኤምባሲው ያስገቡት ደብዳቤ ፕሬዚዳንቱ ፅ/ቤት (ዋይት ሃውስ) መድረሱን ያረጋገጡ ሲሆን ምናልባት ሊያነጋግሩን ከፈቀዱ በሚል በሃገሪቱ በምርጫ ስርአት እንዲሁም በዲሞክራሲና የህግ የበላይነት ዙሪያ ከፕሬዚዳንት ኦባማ ጋር ለመወያየት ከፍተኛ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ፓርቲዎቹ ዕድሉ ከተገኘ ለባራክ ኦባማ በእጅ የሚሰጥ ደብዳቤም በጋራ እያዘጋጁ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ለፕሬዚዳንቱ የሚቀርበው ደብዳቤ በሃገሪቱ ስላለው የምርጫ ስርአት፣ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ፣ የፕሬስ ነፃነት እንዲሁም የዲሞክራሲና የህግ የበላይነትን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በስፋት የሚያብራራ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡  
ፕሬዚዳንቱ ጉብኝታቸውን አስመልክቶ በትናንትናው እለት ለቢቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ፤ ዋነኛ የጉብኝታቸው አላማ በኢኮኖሚያዊ ትብብር፣ እንዲሁም በፀጥታና ሽብርተኝነትን በመከላከል ዙሪያ ውይይት ለማድረግ መሆኑን አበክረው ተናግረዋል፡፡
ኦባማ በኬንያ በሚኖራቸው ቆይታ በንግድ ፈጠራ  ጉባኤ ላይ እንደሚሳተፉ ጠቁመው ወጣት የንግድ ስራ ፈጣሪዎችን እንደሚያበረታቱና በሙስናና በግልፅ አሰራር ዙሪያ መንግስት ስለሚከተለው አካሄድ ውይይት እንደሚያደርጉ ገልፀዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ወደ ስልጣን ሲመጡ “አሜሪካ የምትፈልገው ጠንካራ የዲሞክራሲ ተቋማት እንጂ ጠንካራ ግለሰቦችን አይደለም” ሲሉ መናገራቸውን በመጥቀስ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በፓርላማው አንድም ተቃዋሚ በሌለበት እንዲሁም የኬንያው ፕሬዚዳንት በወንጀል ተከሰው ምርመራ እየተደረገባቸው ባለበት ሁኔታና ጠንካራ መንግስታዊ ተቋማት ሳይኖሩ ጉብኝት የማድረጋቸውን አግባብነት በተመለከተ ከቢቢሲው ጋዜጠኛ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ የተባለውን ያህል ባይሆንም ችግሮች እንዳሉ ጠቁመው ጉብኝቱ በሃገራቱ ውስጥ የሰብአዊ መብት አያያዝ እንዲሻሻልና የሲቪክ ማህበረሰብ ተሳትፎ እንዳይገደብ ግፊት የምንፈጥርበት አጋጣሚ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የሊበራል ርዕዮተ ዓለም ተከታይ ያልሆነችውን በርማን መጎብኘታቸውን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፤ ከጉብኝታቸው በኋላ የሃገሪቱ ዲሞክራሲና የሰብአዊ መብት አያያዝ እንደተሻሻለ ገልፀው፣ በሁለቱ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት የሚያደርጉት ጉብኝትም ተመሳሳይ ተፅዕኖ ሊፈጥር እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
በኬንያ በሚያደርጉት የ3 ቀናት ጉብኝት ከግብረሰዶማውያን መብት ተቆርቋሪነታቸው ጋር በተያያዘ ተቃውሞ ሊገጥማቸው እንደሚችል ከቢቢሲ ጋዜጠኛ የተጠየቁት ፕሬዚዳንቱ፤ “እኔ በፆታ እኩልነት አምናለሁ፤ እንዲከበርም እታገላለሁ፤ በአፍሪካ ያለውን ነገር አውቃለሁ፣ ከዚህ ቀደም በሴኔጋል ባደረኩት ጉብኝት እንዲህ ያለው ስጋት አጋጥሞ ነበር፤ በጋዜጣዊ መግለጫዬ ላይ ግን ስለጉዳዩ በቀጥታ አላነሳሁም፤ አሁንም የሚሆነው ተመሳሳይ ነው” ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ፕሬዚዳንት ኦባማ፤ በኢትዮጵያና በኬንያ በሚያደርጉት ጉብኝት በዲሞክራሲና የሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው ከየሃገራቱ መንግስታት ጋር እንዲወያዩ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና ግለሰቦች በደብዳቤ እንደጠየቁ ታውቋል፡፡
በመጪው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ይወዳደራሉ ተብለው የሚጠበቁት ሴናተር ማርኮ ሩቤዩ፤ ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያን በሚጐበኙበት ወቅት በሰብአዊ መብት አያያዝ ጉዳይ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ በፃፉት ደብዳቤ አሳስበዋል፡፡
“ምንም እንኳ አሜሪካ እና ኢትዮጵያ አሸባሪነትን ለመዋጋት በጋራ ቢቆሙም ኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶችን ስትጥስ አሜሪካ አይቶ እንዳላየ ማለፍ የለባትም” ያሉት ሴናተሩ፤ በኢትዮጵያ ያለው የፕሬስ ነፃነት ጉዳይም ትኩረት እንዲደረግበት በደብዳቤያቸው ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ጉብኝቱን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፤ የኦባማና የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ውይይት በዋናነት በሰላም ማስከበርና በኢኮኖሚ ትብብር ላይ ያተኩራል ብሏል፡፡
ከጉብኝቱ ቀደም ብሎ ዋሽንግተን ፖስት እና ዘ ጋርዲያን የተባሉት ታዋቂ ጋዜጦች፤ ኦባማ የፕሬስ ነፃነት ያልተከበረባትና ዲሞክራሲያዊ ተቋማት ያልተጠናከሩባትን ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው፣ ዓለም የዲሞክራሲ ፅንሰ ሃሳብን በተንሸዋረረ መልኩ እንዲገነዘብ የሚያደርግ ነው ሲሉ ተቃውሟቸውን መግለፃቸው አይዘነጋም፡፡
ፕሬዚዳንቱ በሁለቱ ሃገራት በሚያደርጉት ጉብኝት ከአጃቢ ልኡካኖች በተጨማሪ 20 የአሜሪካ ከፍተኛ የህግ ባለሙያዎችም አብረዋቸው እንደሚጓዙ ታውቋል፡፡
ባራክ ኦባማ በስልጣን ዘመናቸው ከአፍሪካ አገራት ጋና፣ ግብፅ፣ ታንዛኒያ፣ ሴኔጋልና ደቡብ አፍሪካን የጎበኙ ሲሆን የአሁኑ የኬንያና የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው የመጨረሻ የአፍሪካ ጉብኝት ሊሆን እንደሚችል የፖለቲካ ተንታኞች ጠቁመዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ኦባማ በነገው ዕለት ማታ የኬንያ ጉብኝታቸውን አጠናቀው አዲስ አበባ እንደሚገቡ የሚጠበቅ ሲሆን ሰኞ እለት በብሄራዊ ቤተመንግሥት አቀባበል ይደረግላቸዋል፡፡ በዚያው እለት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምና ከፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ጋር በደቡብ ሱዳንና በአካባቢያዊ የደህንነት ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ ተብሏል፡፡ በእለቱም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምና ፕሬዚዳንት ኦባማ ለጋዜጠኞች መግለጫ ይሰጣሉ፡፡
በማክሰኞ ቀን ውሏቸው ከሲቪል ማህበረሰቡ ከተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት የሚያደርጉ ሲሆን በመቀጠልም ከአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ዲላማኒ ዙማና ከህብረቱ አባል ሀገራት መሪዎች ጋር በምግብ ዋስትና እና ቀጣይነት ያለው ልማት ለማረጋገጥ በሚደረጉ ኢኮኖሚያዊ ጥረቶች ዙሪያ ይወያያሉ ተብሏል፡፡

Read 4592 times