Monday, 27 July 2015 10:20

ሞራሊቲ የራስን ጥቅም ማስጠበቅ ብቻ አይደለም

Written by  -ደረጄ ወዳጅ-(በአ.ዩ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(2 votes)

  “የደራሲው መብት በሕግ የተጠበቀ ነው፡፡ ደራሲውን በቅድሚያ በፅሁፍ ሳያስፈቅዱ፤መጽሀፉን በከፊልም ሆን በሙሉ ማባዛት፤መተርጎምና ማሰራጨት፤ እንዲሁም በኤሌክትሮኒክ፤ በመካኒካል፤በፎቶ ኮፒ፤ በድምፅ በመቅረፅ፤ በመሳሰሉትና በሌላም መንገድ መገልበጥ ወይም ማስተላለፍ በሕግ ያስቀጣል፡፡”

        ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ ከላይ በትዕምርተ ጥቅስ ውስጥ ያስቀመጥኩት በአቶ አስራት አብርሃም፣ፍኖተ ቃኤል፣ በሚለው መጽሀፉ በመጀመሪያዎቹ ገፆች ላይ የተፃፈው የባለቤትነትን መብት የሚያስጠብቅ ጠንከር ያለ የማስጠንቀቂያ መልእክት ነው፡፡ የእኔ አትኩሮት መልእክቱ በራሱ ችግር አለው የሚል እምነት ኖሮኝ ሳይሆን ጸሐፊው የዚህን ያህል ስለ ባለቤትነት ግንዛቤ እያለው ለምን “መምህሬ እና ጓደኛዬ” የሚለው የዶ/ር ዳኛቸው አሰፋን የአእምሮ ሥራ (ማለትም በተለያዩ መጽሄቶች፣ጋዜጦች---የጻፉቸውንና በተለያዩ ጊዜያት በቃለ ምልልስ የሰጣቸውን ሃሳቦች) ከእሱ ፈቃድ ወጪ “የዳኛቸው ሀሳቦች” በሚል ርእስ በአቶ ሙሀመድ ሀሰን የታተመውን መጽሐፍ----እንዴት በዋነኛነት የአከፋፋይነቱን ሚና ሊረከብ ቻለ? በመጀመሪያ ይህ የአስራት አብርሃም የባለቤትነት ማስጠንቀቂያ መልእክት እና እየተፈጸመ ያለው ተግባር በእጅጉ እንደሚፋለስና እንደሚቃረን በግልፅ የሚታይ እውነታ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ከዚህም እውነታ በመነሳት በዚህ ጽሑፍ ለማተኮር የፈለግሁት የዶ/ር ዳኛቸው “ተማሪ እና ወዳጅ ነኝ” የሚለው አስራት አብርሃምን አስነዋሪ ተግባር ከሞራል ተጠያቂነት አንጻር መፈተሽ ነው፡፡ ለዚህም በቀዳሚነት የሞራል እሳቤና ተግባሮት ከፍልስፍና አንፃር ምን እንደሚመስል በጥቅሉ ካስቀመጥኩ በኋላ በቀጣይም  ይህ ሰው እያደረገ ያለውን ኢ-ሞራላዊ ተግባር በሦስት ዋና ዋና ነጥቦች በቅደም ተከተላቸው መሠረት አቀርባቸዋለሁ፡፡

የሞራል እሳቤ እና ተግባሮት ከፍልስፍና አንፃር
በጥንታዊው ግሪክ የነበሩት ታላላቅ ፈላስፎች( ሶቅራጥስ፤ፕሌቶን እና አሪስቶትል) ህይወታቸውን በሙሉ ከሶፊስቶች ጋር ሲሟገቱ እንደኖሩ በተለያዩ ድርሳናቸው በተደጋጋሚ ይገልጻሉ፡፡ የዚህም ዋነኛ ምክንያታቸው ደግም የሶፊስቶች አስተምህሮት የነገሮችን እውነተኛ ምንነት ከመፈለግ ይልቅ የግለሰቦች የመናገር ችሎታና አፈቀላጤነት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ሲሆን ይህም አንድ ግለሰብ ከነገሩ ተጨባጭ እውነታ ውጪ የንግግር ክህሎትን በመጠቀም ሌሎችን በመርታት በሚገኝ ጊዜያዊ እውቀት ላይ የሚያተኩሩ በመሆናቸው ነበር፡፡ በዚህም ዕይታቸው መሠረት ለማንኛውም ዓይነት እሳቤ ኑባሬያዊ የሆነ እውቀት የለም የሚል እምነት ያላቸው ሲሆን ለእነርሱ እውቀት እንደየግለሰቦች ትንታኔ እና ዕይታ የሚለያይ እንደሆነ ይገልጸሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሶፊስቶች እውቀትን በራሱ እንደ ግብ የሚመለከቱ ሳይሆን ዋነኛ የገቢ ማግኛ ምንጫቸው በማድረግ፣ ከእውነታው ይልቅ ወደ ንግድ የሚያተኩሩ በመሆናቸውም ጭምር ነበር፡፡
ከላይ ከጠቀስኩት ባህርያቸው አንፃር የሞራል አስተምህሮታቸውም ግለሰባዊነት ላይ የሚያተኩር ሲሆን እንደ እነርሱ እምነት አንድ ሰው ሞራሊቲ፣ ጥሩ ወይም መጥፎ ድርጊት ሊፈፅም የሚችለው በስተመጨረሻ ሊያስገኝለት የሚችለውን ትርፍ እና ኪሳራ በማሰብ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ በዚህም የእውቀት ዕይታቸው የተነሳ ከላይ በጠቀስኳቸው ታላላቅ ፈላስፎች ክፉኛ ትችት ይደርስባቸው ነበር፡፡ የዚህም ምክንያት ደግም ለእነዚህ ፈላስፎች የሞራልቲ እሳቤዎችም ሆኑ ጥያቄዎች በባህርያቸው ማኅበረሰባዊ ይዘት ያላቸው በመሆናቸው ተግባሮታቸው እንደ ግለሰቦች ፍላጎትና ምኞት የሚከናወን እንዳልሆነ በአፅንኦት ይገልፃሉ፡፡ ይኽም በመሆኑ ማንኛቸውም ዓይነት የሞራል ተግባሮቶች የሚከናወኑት እኛ የሰው ልጆች ምክንያታዊነትን በመጠቀም ሁላችንም የምንስማማባቸው ሕግ እና ደንቦችን መሠረት በማድረግ እንደሆነም ጭምር ያስረዳሉ፡፡
ፕሌቶ “ዘ ሪፐብሊክ” በሚለው ድርሳኑ ስለ ሞራል ምንነት በአስተማሪው ሶቅራጥስ እና በሶፊስቶች መካከል የነበረውን ምይይጥ (ዲያሎግ) በሰፊው የሚያቀርብ ሲሆን በመጨረሻም ሶቅራጥስ የሶፊስቶቹን የሞራል ዕይታ ለማረቅ ችሏል፡፡ ለሶቅራጥስ የሞራል ተግባሮቶች የሚከናወኑት በሚገኘው ትርፍ ወይም በሚታጣው ኪሳራ ሳይሆን እኛ የሰው ልጆች ምክንያታዊነትን በመጠቀም የምንፈፅማቸው ድርጊቶች እንደሆኑ ያስረዳል፡፡ ስለዚህም ማንኛውም ሰው ኑባሬያዊ የሆነ የሞራል እውቀት ያለው በመሆኑ፣ ይህንንም በአግባቡ በመተግባር ሰላማዊ ህይወትን እንድንመራና ግቦቻችንን ወይም ዓላማዎቻችንን እንድናከናውን ያስችለናል፡፡ ይኽም ሲባል ማንኛውም ሀገረ-መንግሥት፤ማኅበረሰብ የሚተዳደርባቸውን ሕግም ሆነ ደንብ ሲያርቅ የሞራል እውቀትን መሠረት በማድረግ ሲሆን በዚህም ግለሰቦች የማንንም መብት ሳይነኩ በማኅበረሰቡ ውስጥ እንዴት እና በምን መልኩ መኖርና ሥራቸውን ማከናውን እንዳለባቸው የሚገልፀ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እነዚህ የሞራል ሕጎች በሃይማኖት አስተምህሮት ሥር የተካተቱ ሲሆን ለዚህም በዋነኝነት አስተዋጽኦ ያደረገው በመካከለኛው ዘመን የነበረው የሀገረ-መንግሥት እና የሃይማኖት የአስተዳደር ትስስር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይኽም ሃይማኖታዊ የሞራል አስተምሮት ከዓለማዊ ሕግ በተጨማሪ ግለሰቦች እራሳቸውን ከማንኛቸዉም ክፋት እንዲቆጠብ በማድረግ አሁን እስካለንበት ዘመን ድረስ አስተዋጽኦው ከፍተኛ እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ እኔም ከእነዚህ የሞራል እሳቤዎችና ተግባሮቶች በመነሳት፣አቶ አስራት አብርሃም  በዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ላይ እያከናወነ ያለው ኢ-ሞራላዊ የሆኑ ድርጊቶቹን ሦስት ዋቢ የሆኑ ነጥቦችን በማንሳት  በቀጣይነት እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ፡፡  

ከሞራል ተጠያቂነት የማያመልጥባቸው ምክንያቶች

በቀዳሚነት የምንመለከተው በዓለማችን ከሚኖሩ ነገሮች ሁሉ ከሞራል ተጠያቂነት ነፃ ሊሆኑ የሚችሉት ህጻናት፤እንስሳት እና ግዑዝ ነገሮች ሲሆኑ ይኽውም ከላይ ባለው ክፍል እንዳስረዳሁት የሞራል ሕጎች የሚተገበሩት ምክንያታዊነት ላይ ተመሥርተው በመሆናቸውና እነዚህ ሦስቱ የጠቀስኳቸውም ይኽንን ሟሟላት የማይችሉ በመሆናቸው ነው፡፡ ስለዚህም ማንኛውም  ክፉ እና በጎውን መለየት የሚችል ሰው፣ በዚህ መሥፈርት መሠረት ከሞራል ተጠያቂነት ሊያመልጥ አይችልም፡፡ ይኽንን ስል ግን በህክምና የተረጋገጠ የአእምሮ ህሙማንን ከሞራል ተጠያቂነት አንፃር የማይካተቱ መሆናቸውን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ ከእዚህ በመነሳት የአስራትን የሞራል ተጠያቂነት ስንመዝነው፣ ክፉውን እና በጎዎቹን ከሚለዩት ወገን ውስጥ የሚካተት በመሆኑ እንዲሁም እኔ እና ዶ/ር ዳኛቸውን ባገኘን ጊዜ ሁሉ “እስር ቤት መታሰሩን” እንጂ አማኑኤል ሆስፒታል ገብቶ እንደነበር ነግሮን ስለማያውቅ፣በዚህ ምዘና መሠረት በምንም መልኩ ከሞራል ተጠያቂነት ማምለጥ አይችልም፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የምንመለከተው ደግሞ አንድ ግለሰብ ከእውቀት ማነስ የሞራል ግድፈት ሊፈፅም ይችላል፡፡ ሆኖም ይኽንን  ስህተቱን በተለያየ መንገድ በሚያገኘው የሞራል አስተምህሮቶች ሊያርም ይችላል፡፡ ነገር ግን የአስራት አብርሃምን ምግባር ስንመለከተው የእራሱ መጽሐፍ በማንኛውም መልኩ ከእርሱ ፈቃድ ውጪ ማሳተም፤ማሰራጨት፤ማባዛት እንደማይቻል በአፅንኦት ያሳስባል፡፡ ይኽም የሚያሳየው አስራት ስለ ግለሰብ  የባለቤትነት መብት ጠንቅቆ እንደሚያውቅ ሲሆን በዶ/ር ዳኛቸው ላይ እየፈጸመ ያለው መጥፎ ድርጊት ባለማወቅ የሠራው ስህተት እንዳልሆነ በግልፅ ያሳያል፡፡ ከዚህም በመነሳት ይኸው ግለሰብ በራሱ ላይ እንዳይፈፀምበት የሚፈልገውን ነገር ለምን በሌሎች ላይ ማለትም በዶ/ር ዳኛቸው ላይ ሊፈፅም ቻለ? የሚል ጥያቄ በአእምሯችን ሊያጭርብን ይችላል፡፡
ለዚህ የእኔ ምላሽ ሊሆን የሚችለው፣በዚህ ጽሑፍ በመጀመሪያው ክፍል በሶፊስቶቹ እና በፈላስፋዎቹ የነበረውን የሞራል የዕይታ ልዩነት በአግባቡ ሊያስረዳን እንደሚችል አምናለሁ፡፡ ሶፊስቶቹ ማንኛውንም ዓይነት የሞራል ተግባራት የሚያከናውኑት ከሚያገኙት ጥቅም አንፃር ብቻ ሲሆን በዚህም የተነሳ በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ዘንድ ያስወግዛቸው እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይኽ የአስራትም ድርጊት የሚያሳየን ልክ እንደ ሶፊስቶቹ የእራሱ ለሆኑት ንብረቶቹ ብቻ የሞራል ሕጎችን የሚጠቀምባቸው ሲሆን በተቃራኒው ደግም እነዚህን ሕጎች በመጣስ፣ የዶ/ር ዳኛቸውን የእምሮአዊ ንብረቶችን ካለእርሱ ፈቃድ እንደወጡ እያወቀ፣ የግል ጥቅሙን ብቻ በማየት፣በዋነኛነት እያሻሻጠ ያለ በመሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን ሞራሊቲ የእራስን ደህንንት ማስጠበቂያ ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ደህንነት በተግባር ማክበር መቻል እንደሆነ አስራት መረዳት ይኖርበታል፡፡   
በሦስተኛ  ደረጃ አቶ አስራት አብርሃምን የሞራል ተጠያቂ ሊያደርገው የሚችለው፤”መምህሬ አና ጓደኛዬ” የሚለውን የዶ/ር ዳኛቸውን ጽሑፎች ካለእርሱ ፈቃድ እንደወጡና እርሱም ተባባሪ እንዳይሆን እየነገረው፣”እኔ እኮ ነጋዴ ነኝ” የሚል ምላሽ መስጠቱና  በመቀጠልም ዶ/ር ዳኛቸው ወደ ሕግ ከሚሄድ ይልቅ ከሚገኘው የመጽሐፉ ሽያጭ ገቢ  የተወሰነ ብር በድርድር ቢወስድ ይሻለዋል የሚል አቋም መያዙም ጭምር ነው፡፡ እነዚህ የአስራት መልሶች እጅጉኑ የሚያሳፍሩና ሶፊስታዊነቱን እንደቀጠለ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ሶፊስቶቹ እዉቀትን በራሱ እንደ ግብ ከማየት ይልቅ በሚያገኙት አጋጣሚ ሁሉ እየቸበቸቡ ለመክበር የሚፈልጉ ከመሆናቸው የተነሳ ብዙም ለእውነት ቦታ አይሰጡም፡፡
ከአስራት መልሶች መረዳት የምንችለው፣ ልክ እንደ ሶፊስቶቹ የራሱን ፍላጎት ለማስፈፀም ሲል እውነታውን ወደ ጎን በመተው፣ ዶ/ር ዳኛቸውን በጥቅም ለመደለል መሞከሩ በእጅጉ አሳፋሪ አና ኢ-ሞራላው ድርጊት እንደሆነ ማረጋገጫ ነው፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው ገንዘብ ለማግኘት ብሎ የሚጽፍ እንዳልሆነ ማንኛችንም ጠንቅቀን የምናውቀው እውነታ ነው፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው የሚፅፋቸውም ሆነ በሚዲያ የሚያደርጋቸው ቃለ-ምልልሶች አብዛኛውን ጊዜ ማኅበረሰቡ ይማርባቸዋል ብሎ የሚያምንባቸውን እንደሆነ ማንም የሚያውቀው ሀቅ ነው፡፡ አስራት ግን አንዴ “ዶ/ር ዳኛቸውን ጠንቅቄ አውቀዋለሁ”፣ በሌላ ጊዜ ደግም “አላውቀውም” በማለት ከእራሱ ጋር እንኳን መግባባት አልቻለም፤ ምክንያቱም ዶ/ር ዳኛቸው እሱ እንደሚፈልገው ሶፊስት መሆን ባለመቻሉ ነው፡፡
 አሁንም ቢሆን አስራት ሊገነዘበው ያልቻለው ጉዳይ አለ፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው ወደ ሕግ የሄደበት  ዋነኛው ምክንያት ገንዘብ ለማግኘት አይደለም፡፡ ፍትሕን ኢ-ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ማስተናገድ አግባብ እንዳልሆነ ስለሚያምን ነው፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው እኔንም ሆነ ጓደኞቼን በፍልስፍና ትምህርት ክፍል ሲያስተምረን፣የሞራል ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት እንዳለብን በአፅንኦት ይነግረን ነበር፡፡ አሁንም እያደረገ ያለው ነገር የሚያሳየው ለፍትሕና ለሞራል ሕግጋት ምን ያኽል ታማኝ እንደሆነ ነው፡፡  ጽሑፌን የማጠናቅቀው፣አቶ አስራት አብርሃም ባለፈው ሳምንት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋን በተመለከተ በአዲስ አድማስ ጋዜጣና እና በቁም ነገር መፅሄት ላይ ከጻፈው ውስጥ እየፈፀመ ያለውን የሞራል ግድፈት ለመሸፈን ከሞከረባቸው ምክንያቶች አንደኛው ላይ በማተኮር ነው፡፡እራሱን ብቸኛ በማስመሰል፣ዶ/ር ዳኛቸው ከጀርባው ሌሎች ሰዎችን በመያዝ እያጠቃኝ ነው ማለቱ አሁንም ሶፊስትነቱን እያጠናከረ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ አስራት  የሠራውን ስህተት ለመሸፈን ሲል ሌሎች ከነገሩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን አሉባልታዎች መንዛቱ፣እኔም ሆንኩ ሌሎች በእርሱ ላይ ትዝብትና ጥርጣሬ እንዲያድርብን ነው ያደረገው፡፡ምክንያቱም አስራት የሚነዛው አሉባልታና እውነታው የተገላቢጦሽ በመሆኑ ነው፡፡ “ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮሀል” እንደሚባለው ሁሉ፣ እርሱም መጀመሪያ መጽሐፉን ሲያከፋፍል፣ዶ/ር ዳኛቸውን ምንም አያመጣም ሲል እንዳልነበር፣ አሁን ደግሞ ሌላ የማይመስል አሉባልታዊ ምክንያት ማቅረቡ በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ ለነገሩማ ዶ/ር ዳኛቸው እርሱ እንደሚያወራው፣ ከጀርባው ሌሎች ሰዎች ቢኖሩት፣ መሀመድ ሀሰንም ሆነ እርሱ ይህቺን ተግባር እንደማይፈጽሙ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ስለ ዶ/ር ዳኛቸው ማንነት እኔ ብቻ ሳልሆን አንባቢው ሕዝብም ጭምር የሚያውቁት ስለሆነ፣ እራስን ከተጠያቂነት አድናለሁ ብሎ ሌላ ትዝብት ላይ መውደቅ ጥሩ አይደለም፡፡ ፡
በአጠቃላይ ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ አንድም ከላይ እንዳስቀመጥኩት፣የአስራት የመጽሐፍ የባለቤትነት መልእክት ግርምት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ዶ/ር ዳኛቸው እኔንም፣ሌሎችንም በፍልስፍና ትምህርት ክፍል ዉስጥ ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ማስትሬት ዲግሪ በእውቀት ኮትኩቶ ያሳደገን መምህራችንን በመሆኑ ያልተገባ ነገር ሲደረግበት ከጎኑ መሆናችንን ለማሳየትም ጭምር ነው፡፡ አቶ አስራት፤ዶ/ር ዳኛቸውን ጓደኛዬ ማለቱን ይተወውና ቢያንስ በመምህርነቱ ከግብረገብነት አንፃር እንኳን ሊያከብረው ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡
በመጨረሻም ለማንሳት የምወደው፣እኔን በሚመለከት አቶ መሀመድ ሀሰን በተለያዩ ሚዲያዎች ከመጽሐፉ መውጣት ጋር አያይዞ ሲጠቅሰኝ የሰነበተውን በተመለከተ ነው፡፡  አቶ መሀመድ እንደሚለው፤ዶ/ር ዳኛቸው መጽሐፉ በወጣበት ቀን ከደስታው የተነሳ አምቦ ዩኒቨርስቲ ለሚያስተምረው ወዳጁ በመደወል፣”ይሄ ጉደኛ ልጅ ጉድ የሆነ መጽሐፍ አወጣ; ብሎ ነግሮታል፡፡ እውነትም ይሄ ሰው ጉደኛ ነው ባይ ነኝ፤ምክንያቱም ዶ/ር ዳኛቸው በወቅቱ ከደሴ ወደ አዲስ አበባ እየመጣ ስለነበር፣ ስለ መጽሐፉ መውጣት እንኳን እኔ ነኝ ደውዬ  የነገርኩት፡፡ በእርግጥ ከእኔ በኋላ ሌሎች ሰዎችም ደውለው ነግረውታል፡፡
 እኔ ለአቶ መሀመድ ውሸት በወቅቱ መልስ ያልሰጠሁበት ምክንያት የጀርመኑ ፈላስፋ ኒቼ፣ ስለ ውሸት የተናገረውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ ለዚህ ፈላስፋ ውሸት ማለት በሬ ወለደ ወይም እንደ መሀመድ ሀሰን ያልተባለ ማውራት አይደለም፡፡ ለኒቼ ውሸት ማለት ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ እያዩ እንዳላዩ ማለፍ ነው፡፡ መሀመድ ሀሰን እንደተናገራቸው ያሉ ውሸቶች በማንኛውም ጊዜ ሊጠሩ ወይም ሊረጋገጡ የሚችሉ በመሆናቸው እኔም ብዙ ትኩረት አልሰጠዋቸውም ነበር፡፡

Read 3195 times