Monday, 27 July 2015 10:50

የመፅሀፍ ትርጉም ምንድነው?!

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(12 votes)

   ምንም ነገር የማይሞቀው ምንም ነገር የማይበርደው ሰው መሆን አማረኝ፡፡ ወሬ የሙቀት እና የቅዝቃዜ ምንጭ የሆነበት ማህበረሰብ ውስጥ ሆኜ በሰው ሰራሽ አደጋ እየተጠቃሁ በመቸገሬ ምክንያት ነው፡፡
በወሬ በኩል የፌስ ቡክ ማህበረሰብን የሚያክል የለም፡፡ በወሬ የተገነባ ማህበረሰብ በወሬ ይፈርሳል፡፡ ፌስ ቡክ መተዳደሪያ ደንብ የለውም፡፡ ጓደኝነት በምን ምክንያት እንደተመሰረተ፣ በምን ምክንያት እንደፈረሰ አይታወቅም፡፡
ማንነቱን ለማጣት የማይፈልግ ካለ “stoic” በመሆን ብቻ ነው መትረፍ የሚችለው፡፡ “እስቶይክ” ሆኖ ለመትረፍ ጆሮን በጥጥ ወይንም በዳባ መድፈን ብቻ ነው የሚያዋጣው አማራጭ፡፡ ማንን ታዳምጣለህ? ብትሉኝ “ሁሉንም” ነው መልሴ፡፡ ሁሉንም የሚያዳምጥ ማንንም በቅጡ አይሰማም፡፡ “አይሰማም” የሚለው ቃል ከሰው የማድመጥ ተፈጥሮ ጋር ሳይሆን … ከምጣድ የመጋል ችሎታ ጋር የሚተሳሰር ባህርይ ነው፡፡ ምጣድ በኮሬንቲ እሳት ወይ በማገዶ እሳት ነው የሚሰማው፡፡ ምጣድ እውቀትን ወይንም ምክንያታዊነትን በእሳት መልክ ከተሰጠው ብቻ ይቀበላል፡፡
የፌስቡክ ማህበረሰብ የሚሰማው ጫጫታን ነው፡፡ ጫጫታ “ያሰማዋል”  .. ይሰማዋል፡፡ ጫጫታ ውል የለውም፡፡ እረኛም የሚያግደው አይደለም፡፡ በሆነ ቅፅበት ተሰብስቦ … የነበረበት ቦታ ቅፅበቷ ስታልፍ ተከማችቶ አይገኝም፡፡ ሲሰበሰብ ይንጫጫል … ጫጫታው ድጋፍ ሊመስል ይችላል .. ወይንም ደግሞ ተቃውሞ፡፡ ሊመስል የቻለውን ያህል ሆኖ ያለመገኘት አቅም አለው፡፡
በአንድ ወቅት አንድ ወዳጅ “መፅሐፍትን ለማንበብ የሚያበረታታ ፅሁፍ ፃፍ” ብሎ ወተወተኝ፡፡ ስለ መፅሐፍት መነበብ ከሚገደው በላይ የመፅሀፍት ንባብን አበረታትቶ ወይንም ያበረታታ መስሎ የሚቀበለው ብር እንዳለ አውቄያለሁ፡፡ እኔም ሳይገደኝ እንድፅፍ እሱም ሳይገደው ለማስተዋወቅ ነው ያሰበው፡፡ ሌላ ግድ የሌለው ድርጅት ደግሞ እሱ እና እኔን ይከፍለናል፤ በዚህ ተስማማን፡፡ በዚህ ስምምነት ውስጥ እውነት ከእነ አድራሻዋም የለችም፡፡
አዎ ሲወራ እሰማለሁ፡፡ መፅሐፍ ማንበብ ዋናው ነገር ስለመሆኑ፡፡ “መፅሐፍ” የሚባለው ነገር ምን እንደሆነ በጥንቃቄ መመርመር ሳያስፈልገኝ አይቀርም፡፡ ለመሆኑ ተጨባጭ መፅሐፍ ተብሎ የሚጠራ ነገር አለ? .. ልክ “Virtue” (ሰናይ) እንደሚባለው ፅንሰ ሀሳብ፣ መፅሐፍ የሚባለውም ነገር የሆነ Abstract Concept ስላለመሆኑ ማረጋገጥ አልቻልኩም፡፡ ሰናይነት ወይንም እኩይነት (Vice) በሆነ ተጨባጭ የሰውኛ ማንነት ላይ ተንፀባርቆ እስካላገኘን ድረስ ነገርየው በሰማይ ላይ የተንጠለጠለ ፅንሰ ሀሳብ ነው፡፡
መፅሐፍ ቅዱስ ለምሳሌ፤ ቅዱስነትን ከመፅሐፍ ጋር አጣምሮ ሰማይ ላይ የተንጠለጠለውን ፅንሰ ሀሳብ ወደ ምድራዊ ትርጓሜ የሚያመጣ ነው፡፡ መፅሐፍ ቅዱስ… መፅሐፍ ብቻ ቢሆን ወይንም ቅዱስ ብቻ ቢሆን … የተፈጠረውን፣ የተዋሀደውን ትርጉም አይሰጠንም፡፡ ቅዱስ የሆኑ ምድራዊ ሰዎች በመፅሐፉ አለም ላይ ምን እንደሚመስሉ እናነባለን… ስለ ሰማዩ ሰናይነት በምድራዊ ፊደላት አንብበን የቆምንበትን ከራቀን ቅዱስነት ጋር አመሳክረን እንረዳለን፡፡
“ቅዱስነት” ብቻውን ምድራዊ መወከያ እስካልተቆራኘው ድረስ ተንሳፋፊ ፅንሰ ሀሳብ እንደሆነው “መፅሐፍነትም” ብቻውን ትርጉም የለሽ ነገር ነው፡፡
መፅሐፍነታቸው ከፅንሰ ሀሳብነት ላይ ብቻ ሆነው ህይወቴን በውስጣቸው ማጥመድ ያልቻልኩባቸውን ነገሮች ቤቴ ውስጥ ደርድሬያቸዋለሁ፡፡ ከእነዚህ መፅሀፍ ተብለው ከተሰየሙ ነገሮች ውስጥ አንደኛው ዳጎስ ያለ ገፅ ያለው፣ ጠንካራ ልባስ ወይንም ቅርፊት የተለበጠ .. “የማርክሲስት ሌኒኒስት መዝገበ ቃላት” የሚል የዳቦ ስም የወጣለት ነው፡፡ መፅሀፉን እንደ ጣውላ ቴሌቪዥኔን ለማስቀመጫነት ነው የምገለገልበት፡፡ ከፅንሰ ሀሳባዊ አገልግሎቱ ይበልጥ ተጨባጭ አገልግሎቱ ለእኔ ይጠቅመኛል፡፡
በዚሁ አንፃር መፅሀፍትን መመልከት ጀምሬአለሁ፡፡ ዝም ብሎ “መፅሐፍ” ብሎ ነገር የለም፡፡ የወረቀት ክምችት የተጠረዘበት መፅሐፍ… “የወረቀት ክምችት” ተብሎ ግልፅ ያልሆነ ማንነቱ ወደተገለፀው እና ተጨባጭ ምንነቱ መስተካከል አለበት፡፡ በኬሻ ውስጥ የተጠራቀመ ቁሻሻ … “ቁሻሻ” ተብሎ የተጠራው አስፈላጊነቱ በማለቁ ነው፡፡ የከረሜላ ልጣጭ ለእኔ የማይጠቅመኝ… የከረሜላ ዋናው ትርጉም ጣፋጭነቱ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ነው፡፡ ድቡልቡል ባልጩት ብጠቀልልበት ነገርዬው የከረሜላን ትርጉም አይሰጠኝም፡፡
መፅሐፍም በወረቀትነቱ ብቻ ከልጣጭ የበለጠ ትርጉም የለውም፡፡ በፊት ትምህርት ቤት ሳለን የተማርንባቸውን ደብተሮች በኪሎ ለባለ ሱቅ እንሸጥ ነበር፡፡ ትምህርትን በውስጡ የያዘ ደብተር የትምህርቱ ጊዜ ሲያልቅ አስፈላጊነቱም ያበቃል፡፡ አንድ አስፈላጊነት ሲያበቃ ሌላ አስፈላጊነትን ቀድሞ በነበረው ፋንታ ተክቶ ነው፡፡ ከትምህርት ደብተሮቹ ጋር መፅሐፍትም ለኪሎ ገበያ ይቀርባሉ፡፡ ስኳር እና እርድ ይጠቀለልባቸዋል፡፡
መፅሐፍ ስለተጠረዘ ብቻ መፅሀፍ ሆኖ አይቆይም፡፡ እያንዳንዱ መፅሐፍ ከወረቀትነቱ ባሻገር ያለ አንዳች “ምንነቱ” ፅኑ ካልሆነ … በስተመጨረሻ ወረቀቱ ብቻ ይቀራል፡፡ አንዱ አስፈላጊነት utility ወደ ሌላ ይሸጋገራል፡፡ የአበባ ውበቱ ያለው በፍካት ወቅት ነው፡፡ ከጠወለገ በኋላ አበባም ለማገዶ የማይሆን ጭራሮ ነው፡፡
መፅሐፍ ምን ማለት እንደሆነ ለማወቅ ሰው ምን እንደሆነ በቅድሚያ ማወቅ ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡ ግን “ሰው” ራሱ አብስትራክት ፅንሰ ሀሳብ ነው፡፡ ድሮ በጥንቃቄ ይያዝ የነበረ ደብተር አሁን ግን በኪሎ የሚሸጥ ደብተር ሆኖ እንደዘቀጠው ሁሉ … ድሮ መሳፍንት ተብሎ ጥሩ ስፍራ ይደረደር የነበረ ሰውነት ማንነቱ በኪሎ ሚዛን እንኳን ትርጉም የማይሰጥ ተራ ይሆናል፡፡
“መፅሐፍነት” ብቻውን ቋሚ ትርጉም እንደሌለው፤ ሰውነትም ብቻውን መለኪያ አይፈጥርም፡፡ ሰው ከሚለው ጎን “ምን አይነት ሰው?” የሚለው (essence) መግለጫ ክፍት ቦታ ትርጉም ግዴታ መሞላት ያስፍልገዋል፡፡ “ምን ዓይነት ሰው” ብቻ ሳይሆን ምን አይነት ሰው በምን አይነት ዘመን? የሚለውንም መመለስ ያሻል፡፡
በዶስቶዮቭስኪ የተደረሰ መፅሐፍ እና የአሜሪካ ዜግነት መታወቂያ ያለው ሰው በአሁኑ ዘመን የመፅሐፍነትን እና የሰውነት ሁነኛ መለኪያ ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡ በማርክሲስት መዝገበ ቃላት መፅሐፍ እና በደርግ ዘመን ካድሬ ከነበረ ሰው በወቅታዊው የተፈላጊነት ገበያ ተመን ዋጋ  የሌላቸው ይመስለኛል፡፡ ከመሰለኝ ደግሞ (ብዙ ጊዜ) ነው!
የሰውም ምንነት በተገለባባጭ የርዕዮተ ዓለም ገበያ እና የርዕዮተ አለሙን ሚዛን በሚዘውረው ኢኮኖሚ ሀያልነት ውስጥ ያለ ፅኑ ዋልታ የሚዋዥቅ ነው፡፡ የፈለገ ቢዋዥቅም … በስተመጨረሻ ሰውን ከእንስሳ ዓለም ጋር አንድ የሚያደርገው የተፈጥሮ ልክ ግን ስፍራውን ስቶ አያውቅም፡፡ መፅሐፍም ሲጠቃለል ወረቀት …ሰውም በስተመጨረሻ እንስሳ ነው፡፡
እናም የ“ሰው” ምንነት ፍቺ በሀሊዮት ምክንያት ቢዋዥቅም የተፈጥሮ እንስሳነቱ ግን አስተማማኝ ሆኖ ይቀጥላል፡፡ በዛው አንፃር መፅሐፍም በውስጡ የያዘው “ምንነት” እንደ ገበያ ተፈላጊነቱ ወይንም እንደ ወረትነቱ - ቢለዋወጥም … ዋና የተፈጥሮ ማንነቱ፣ ወረቀትነቱ አስተማማኝ ሆኖ ይዘልቃል፡፡
ከፌስቡክ ማህበረሰብ ተነስቼ ወደ መፅሐፍት የማንነት ዓለም ያሳበርኩት ሰውን እና የመፅሐፍትን ግንኙነት በበለጠ ለመረዳት የሚያስችል ወቅታዊ ማስረጃ ከፌስቡክ ማግኘት ስለሚቻል ነው፡፡ የሰውን ተለዋዋጭ ማንነት ከመፅሐፍት ተለዋዋጭ ትርጉም ጋር ለውሶ ለማጣጣም ከዚህ ማህበረሰብ የበለጠ ማሳያ የሚኖር አይመስለኝም፡፡
መፅሐፍት ከወረቀት በላይ ከሰው በላይ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ወይንም ከሰውም ከወረቀትም በታች፡፡ ይሄንን ሊያደርጋቸው የሚችለው ሰው ራሱ ነው፡፡ የሰው የማንነት ትርጉም ከፍ ባለባቸው ዘመኖች የመፅሐፍትም የማንነት ትርጉም ከፍ ይላል፡፡ ሰው የማንነት ትርጉሙን ከፍ የሚያደርገው በእውቀት ብቻ ነው… እውቀት ደግሞ ተጠራቅሞ የሚገኘው በመፅሐፍት ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ሰው በትክክለኛው /በሚመጥነው/ የራሱ ማንነት ውስጥ ተጠራቅሞ ሲገኝ በመፅሐፍ ውስጥም የሰው ማንነት ውሎ ይነበባል፡፡
ሰው ከራሱ ማንነት ሲወርድ መፅሐፍትም ሰው በሰየመላቸው የማንነት ትርጉማቸው ይወርዳሉ፡፡ የወረደ መፅሐፍ ወደ ወረቀትነቱ … የወረደ ሰው ወደ እንስሳነቱ ሲያቆለቁሉ መሀል መንገድ ላይ ይገናኛሉ፡፡ የወረደው ሰው የቅኔውን ፅሁፍ ወደ ሽንት ቤት ወረቀትነት ቀይሮ ለወቅታዊ ጥሪው ሊገለገልበት ይችላል፡፡
የመፅሐፍት መብዛትን ከሰው መብዛት ለይቼ አልገነዘበውም፡፡ መፅሐፍት የሚያዝሉት ጭብጥ /እውቀት/ እየጠራ፣ እየነፀረ ከመጣ ሰውም ጥራቱን በሀቀኛ ጎዳና እያጣጣመ መሆኑን ያመለክተኛል፡፡
በተደጋጋሚ ራሴ ስናገር የማደምጠው እና የሚያስቀኝ አባባል አለ፡፡ እኔ ራሴ እየወረድኩ በመምጣቴ ምክንያት መሆን አለበት ድሮ እንደ መመሪያ አምንበት የነበረው ነገር ዛሬ ሳላምንበት እንደው ከንፈር ለማልፋት ብቻ ስደጋግመው በውስጤ የሚያስቀኝ፡፡
“በመፅሐፍት መደርደሪያዬ ላይ ሀምሳ ምርጥ መፅሐፍት እንዲኖሩኝ ነው የምፈልገው” እላለሁ፡፡ “ሀምሳዎቹ መፅሐፍት የምድርን እውቀት በኦርጅናልነት ያበረከቱት መሆን አለባቸው፡፡ ከእነዚህ መፅሐፍት ውስጥ ነው ሌሎቹ እንደ አፈር የፈሉት የሰው ልጅ ድርሰቶች የተገኙት፡፡ እነዚህን ሀምሳ መፅሀፍት ከተቆጣጠርኩ፣ አለሙን እና የራሴን ማንነት በራሴ እጅ በህይወት ዘመኔ ውስጥ አንፀዋለሁ”
እነዚህ ሀምሳ መፅሃፍት የትኞቹ እንደሆኑ አላወቅሁኝም፡፡ ከሀምሳዎቹ መሀል ሊጠቀሱ ይችላሉ ብዬ የምጠረጥራቸው አሉ፡፡ ግን በስተመጨረሻ ምን ዋጋ አለው … መፅሐፍቱን ሳገኝ እኔ ራሴን ማግኘት አቅቶኝ ከሆነ!
እኔና የዓለም ህዝብ አንድ ላይ ግልብ ከሆንን ምን ዋጋ አለው? መፅሐፍቱ በሰው ተፅፈው እኛ ዘመን ላይ ሲደርሱ የወፍ ቋንቋ ከሆኑብን፣ አጥረን የአባቶቻችን የስልጣኔ ሱሪ ከረዘመን፣ እንደ አረጀ አንበሳ የጫጫታ ዝንብ ከወረረን፣ በወጣትነታችን እውቀትን ለመቀበል እና ለማሸጋገር ሳንችል ካረጀን? … ምን ዋጋ አለው?
T.5 Eliot “I grow old, I grow old / I wear the bottom of my trousers rolled” ያለው ይሄንን ከሰውነት “ቁመና” መዝቀጥ፣ ማጠር አጢኖ ሳይሆን አይቀርም፡፡
መፅሐፍትን ለማንበብ መጀመሪያ ማንበብ መቻል ይቀድማል፡፡ መፅሐፍን መፃፍ ደግሞ ሁለት እጥፍ ይቀድማል፡፡ በአጭሩ ስለ መፅሐፍት ሚዛናችን አብዝተን ማሰብ ይኖርብናል፡፡

Read 5526 times Last modified on Monday, 27 July 2015 11:02