Monday, 27 July 2015 11:02

5ሺ ኬንያውያን እርቃናቸውን ሊወጡ ተዘጋጅተው ነበር!

Written by 
Rate this item
(4 votes)

                ለኦባማ በወንድና በሴት መካከል ያለውን ልዩነት እናሳያለን ይላሉ
  የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በስልጣን ዘመናቸው 11ኛ ሰዓት ላይ የፈቀዱት የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ በአገራቸው ተቃውሞ አላስነሳባቸውም ይሆናል፡፡ በአባታቸው አገር ኬንያ ግን ተዝቶባቸው ነበር፡፡ ኦባማ በኬንያው ጉብኝታቸው የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ መብትን የተመለከተ ጉዳይ እንዳያነሱ የሪፐብሊካን ሊበርቲ ፓርቲ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ድጋፍ ሲያሰባስብ ነው የሰነበተው፡፡
የፓርቲው መሪ ቪንሰንት ኪዳላ፤ 1ሺ እርቃን ሴቶችና 4ሺ እርቃን ወንዶች በተቃውሞ ሰልፉ እንደሚሳተፉ አስታውቀው ነበር፡፡ በኦባማ የኬንያ ጉብኝት ዋዜማ ላይ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው የተቃውሞ ሰልፍ፤ ለፕሬዚዳንቱ የወንድና የሴትን ልዩነት ለማሳየት ያለመ ነበር ተብሏል፡፡በመጨረሻው ሰዓት ላይ ግን የእርቃን ተቃውሞው ለጊዜው መሰረዙን የሰልፉ አደራጅ አስታውቋል፡፡ የሪፐብሊካን ሊበርቲ ፓርቲ መሪ ቪንሰንት ኪዳላ፤ ከመንግሥት ቢሮ ስልክ ተደውሎ የእርቃን ተቃውሞ ሰልፉን እንዲሰርዙ መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡
“ስልክ ደዋዩ፤ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዩሁሩ ኬንያታ ከባራክ ኦባማ ጋር በግብረ ሰዶማውያን መብት ዙሪያ ለመወያየት እንዳላቀዱና የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻን እንደማይደግፉ ገልጾልኛል” ሲሉ የፓርቲው መሪ ሚዲያ ተናግረዋል፡፡ከብሄራዊ ደህንነት ኮሚቴም ስልክ ተደውሎ፣ የተቃውሞ ሰልፉ እንዳይደረግ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ኪዳላ ገልፀዋል፡፡ ማንነቱን ያልገለፀው ደዋይ፤ “የተቃውሞ ሰልፉን ማድረግ የሽብር ጥቃት ከመፈፀም እኩል ነው” ብሎኛል ሲሉ የፓርቲው መሪ አስረድተዋል፡፡
የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻን በመቃወም ሊካሄድ ታስቦ የነበረው ሰልፍ ለጊዜው ይሰረዝ እንጂ ከእነአካቴው እንደማይቀር አዘጋጆቹ አስታውቀዋል፡፡ ፓርቲው በሰጠው መግለጫም፤ ሰልፉ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል ነው ያለው፡፡ ጊዜውን ግን አልገለፀም፡፡ ለማንኛውም ኦቦማ አምልጠዋል!!

Read 3587 times