Monday, 27 July 2015 11:11

ታይፎይድ … ሰውን ብቻ የሚያጠቃው በሽታ

Written by 
Rate this item
(17 votes)

  የታይፎይድ አምጪ ባክቴሪያ የሚከሰተው በሰው ላይ ብቻ ነው
            ለበሽታው የሚታዘዙ አብዛኛዎቹ መድኀኒቶች ከበሽታው ጋር ተላምደዋል
    አብዛኛውን ጊዜ በተበከለ ምግብና ውሃ ሳቢያ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈውና በተለምዶ የአንጀት ተስቦ እየተባለ የሚጠራው ታይፎይድ መነሻው “ሳልሞኔላ ታይፊ” የሚባል ባክቴሪያ ነው፡፡ ይህ ባክቴሪያ የሚኖረው (ህይወት የሚያገኘው) በሰው ልጅ አንጀት ውስጥ ብቻ ነው፡፡
በሽታው በሽታ አምጪ በሆነው ባክቴሪያ በተበከለ ምግብና መጠጥ አማካኝነት በወረርሽኝ መልክ ሊከሰት ይችላል፡፡
በበሽታው የተያዘ ሰው በጥቂት ቀናት ውስጥ ምልክቶችን ማሳየት ይጀምራል፡፡ ከበሽታው ምልክቶች መካከል ትኩሳት ዋንኛው ሲሆን ራስ ምታት፣ ሰውነትን የመቀረጣጠፍና መገጣጠሚያ አካባቢ የሚኖር የህመም ስሜት ከምልክቶቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸነው፡፡
እ.ኤ.አ በ1862 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን 16ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት አብርሃም ሊንከን ለሞት ማብቃቱ የሚነገርለት ታይፎይድ አሁንም በዓለማችን በየዓመቱ ከ220 ሺህ በላይ ሰዎችን ለሞት እየዳረገ ይገኛል፡፡
ከጥቂት የሰሜን አፍሪካ አገራትና ከደቡብ አፍሪካ በስተቀር በመላው የአፍሪካ አገራት በስፋት መኖሩ የሚነገረው የታይፎይድ በሽታ በተለይ የሃሞት ከረጢት እና እጢ ያለባቸው ሰዎች በይበልጥ ያጠቃል፡፡ ባክቴሪያው ከአንጀት ውስጥ በደም ተሸካሚነት ወደ ሃሞት ከረጢት ሊሄድና በዚያ ተደብቆ ህመምተኛውን ሊያጠቃና በሰገራ አማካኝነት ወደሌሎች ሰዎች ሊተላለፍ ይችላል፡፡
ሳልሞኔላ ታይፊ በሚባል ባክቴሪያ ሳቢያ የሚከሰተውን ይህንኑ የታይፎይድ በሽታ ለማከም ጥቅም ላይ የሚውሉት መድኀኒቶች በአብዛኛው ከበሽታው ጋር የመላመድ ባህርይን አምጥተዋል፡፡
ቀደም ሲል በጥቅም ላይ ይውሉ የነበሩና የታይፎይድ በሽታን ለማከም ያገለግሉ ከነበሩ መድኀኒቶች መካከል አሞክሳሲሊን፣ ክሎሞፌኒከልና፣ ስትሬፕቶማይሰን የተባሉት መድኀኒቶች ሙሉ በሙሉ ከበሽታው ጋር በመላመዳቸውና የሚያስከትሉት የጎንዮሽ ጉዳቶችም እየጨመሩ በመምጣታቸው ከአገልግሎት ውጪ እንዲሆኑ እየተደረጉ ነው፡፡
 በአሁኑ ወቅት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው ሲፕ ሮፋሎክሳሲን የተባለው መድኀኒት ነው፡፡
በሽታው በወቅቱ ህክምና ካላገኘ ለሞት ሊዳርግ የሚችልና በቀላሉ ከሰው ወደሰው በተበከለ ምግብና መጠጥ ሳቢያ ሊተላለፍ የሚል በሽታ ነው፡፡
 በተለይ እንዲህ ክረምት በሚሆንባቸው ወቅቶች ለመጠጥነት የምንጠቀመውን ውሃና የምንመገበውን ምግብ በጥንቃቄ መያዙ በታይፎይድ ከመያዝ እንደሚታደገን ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

Read 13215 times