Monday, 27 July 2015 11:12

የልብ በሽታን ለመከላከል … ክብደትዎን ይቀንሱ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

    ክብደትን መቀነስ የልብ በሽታን ለማስወገድ ትክክለኛውመንገድ ነው፡፡ ከፍተኛ የሰውነት ክብደት የደም ቅዳ ሴሎቻችን እንዲጠቡ ያደርጋቸዋል፡፡ በዚህ ሳቢያም የኮሌስትሮል ዝቃጮች እንዲሰበሰቡና እጢ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ ይህ ደግሞ አደገኛ የልብ ህመም እንዲከሰትብዎ ምክንያት ይሆናል፡፡ ክብደትዎን በመቀነስ በተለይም የሆድ አካባቢ ቦርጭዎን በማጥፋት የደም ቅዳ ሴሎች ሥራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ ይርዱዋቸው፡፡

         የምግብዎን ዓይነት እና መጠን ያስተካክሉ

    ለመልካም ጤንነት ከሚመከረው የምግብ ዓይነትና መጠን በላይ መመገብ ለከፍተኛ የሰውነት ክብደትና የኮሌስትሮል መጠን ያጋልጣል፡፡ የሚመገቡት ምግብ በዓይነቱና በመጠኑ የተስተካከለ እንዲሆን ያድርጉ፡፡ ከየዕለታዊ  የምግብ ገበታዎ ላይ አትክልትና ፍራፍሬዎች መኖራቸውን ያረጋግጡ፡፡ ገበታዎ የተመጠነ እንዲሆንም ያድርጉ፡፡
ጭንቀትዎን ያስወግዱ
ከፍተኛ ጭንቀት የደም ግፊት ይጨምራል፡፡ በደም ቅዳዎች ውስጥ እጢ እንዲፈጠር የሚያደርጉ ነገሮችንም ያባብሳል፡፡ ይህም ለልብ በሽታ ያጋልጣል፡፡ ከልብ በሽታ ለመጠበቅ ከፈለጉ ጭንቀትና ውጥረትን ያስወግዱ፡፡
ያልተፈተጉ/ ገለባቸው ያልተለየ/ እህሎችን ለምግብነት ይምረጡ
ገለባው ያልተነሳላቸውት (ያልተፈተጉ/እህሎች ጥሩ የአሰርና የሌሎች አልሚ ምግቦች ምንጮች ናቸው፡፡
    እንደ ቫይታሚን ኢ፣ ታያሚን፣ ሪቦፍላቪንና ናያሊን ያሉ ቫይታሚኖች እንዲሁም ማግኒዚየም፣ ፎስፈረስ፣ ዚንክና ብረት መሰል ማዕድናት የሚገኙት ባልተፈተጉ እህሎች ውስጥ ነው፡፡ ባልተፈተጉ እህሎች ውስጥ የሚገኙት ቫይታሚኖችና ማዕድናት፣ የደም ግፊትንና የልብ ጤንነትን በመቆጣጠሩ ረገድ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል ለምሳሌ ለመጥቀስ ያህል ካልተፈተገ ገብስ ወይም ስንዴ የተሰሩ ዳቦዎች፣ ቡናማ ሩዝ፣ ካልተፈተገ በቆሎ የሚሰሩ ምግቦች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
አነስተኛ የስብ መጠን ያላቸውን የፕሮቲን ምንጮች ይምረጡ
ቀይ ሥጋ፣ ዶሮና ዓሳ አነስተኛ የስብ መጠን ያላቸው የፕሮቲን ምንጮች ናቸው፡፡ የእንቁላል ነጩ ክፍል፣ የወተት ተዋፅኦዎችም ከአነስተኛ የስብ መጠን ውስጥ የሚመደቡ ናቸው፡፡ ዓሣ አነስተኛ የስብ መጠን ያለው የፕሮቲን ምንጭ ነው፡፡ የተወሰኑ የዓሣ ዓይነቶች ደግሞ የደም ውስጥ ስቦችን በመቀነስ በድንገተኛ የልብ ህመም የመሞት አደጋን በሚቀንሱትና ኦሜጋ 3 ፋቲ አሲድ ተብለው በሚታወቁ ማዕድናት የበለፀጉ ናቸው፡፡ ሌሎች ኦሜጋ 3 ፋቲ አሲዶች ምንጮች አኩሪ አተርና ተልባ ናቸው፡፡
በምግብ ውስጥ የሚኖረውን የጨው መጠን ይቀንሱ
ብዙ ጨው መመገብ ለከፍተኛ የደም ግፊት አስተዋፅኦ በማድረግ ለስርዓተ ልብ መዛባት ችግር ያጋልጣል፡፡ በምግባችን ውስጥ የሚገኘውን ጨው መቀነስ ጤናማ ልብ እንዲኖረን ከሚረዳን የአመጋገብ ሥርዓት ውስጥ ዋንኛው ነው፡፡ አንድ ጤናማ ሰው በቀን ውስጥ መውሰድ የሚኖርበት የጨው መጠን ከአንድ የሻይ ማንኪያ መብለጥ የለበትም፡፡
ኦቾሎኒ ለልብ ጤንነት
እንደ መክሰስ ያለ ነገር ካማረዎ፣ ኮሌስትሮል በመቀነስ የታወቀውን ኦቾሎኒ ይጠቀሙ፡፡
ኦቾሎኒ ጉዳት በማያስከትሉ ስቦች የተሞላና ጎጂ ስቦችን ከሰውታችን በማስወገድ የሚታወቅ ምግብ ነው፡፡     በርካታ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፤ በየዕለቱ ጥቂት ኦቾሎኒን የሚመገቡ ሰዎች ከልብ በሽታ የመያዝ ዕድላቸው በእጅጉ ቀንሶ ተገኝቷል፡፡ ኦቾሎኒ በከፍተኛ ስብና ካሎሪ የተሞላ ስለሆነ በአንድ ጊዜ ከአንድ እፍኝ  በላይ አይጠቀሙ፡፡ በስኳር ወይም በቸኮሌት ጣፍጠው ከተዘጋጁ ኦቾሎኒዎች ይጠበቁ፡፡
የአካል እንቅስቃሴ ያድርጉ
በሳምንት ለ5 ቀናት በቀን ለ30 ደቂቃ ያህል ቀለል ያሉ የአካል እንቅስቃሴዎችን ያድርጉ፡፡ እንደ ኤሮቢክስ ያሉ ወይንም የልብን ጡንቻዎች ለማሰራት ይጠቅማሉ እንደሚባሉት የእግር ጉዞ አይነት እንቅስቃሴዎች በልብ ድካምና በሌሎች የልብ በሽታዎች የመጠቃት ዕድልን ይቀንሳሉ፡፡ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች በበዙ ቁጥር ጠቀሜታቸውም በዚያው ልክ እየጨመረ ይሄዳልና፣ በየዕለቱ አካላዊ እንቅስቃሴ ያድርጉ፡፡

Read 9324 times