Monday, 27 July 2015 11:13

የሣሮን ዝምታ

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(13 votes)

  እነዚያ በክዋክብት መሀል የተሞሸሩ የሚመስሉ ዓይኖችዋ መኝታዬ ድረስ መጥተው ሲንቦገቦጉ፣አልጋዬን አልፈው ልቤ ለብቻዋ አገላብጠው ሲጠብሷት መነሳት ግድ አለኝ፡፡ ነፍሴ ብቻዋን እስክስታ እየመታች፣ በሳቅዋ ደወል ትዝታ ስትሰክር ውሎ ማደር ለምዶባታል፡፡ ግን በጧት ከባድ ነው፡፡ ገና ጀንበር ቅንድብዋን ሳትገልጥ፣ ገና አድማሳት በብርሃን ፌሽታ ቀሚስ ሳይቀይሩ …
ብድግ አልኩና ከወይራ ሰፈር ኮንዶሚኒየም ግቢ ወጣሁ፡፡ ደግነቱ ታክሲ አለመጥፋቱ፡፡ ከግራና ከቀኝ “ጦር ኃይሎች … ጦር ኃይሎች” እያሉ ዘፈኑን ጀመሩት፡፡ ብፈልግ አውጉስታ ጫፍ ድረስ---ካሰኘኝም ቀጠና ሁለት ሙሉ ወንጌል ድረስ እሳፈራለሁ፡፡ የወይራ ሰፈር ክፋቱ ኩላሊት እሰኪታመም ድረስ ታጭቆ መሄድ ነው፡፡ ዋናው ሰልፍ ይዞ አለመገተር ነው አልኩ በልቤ፡፡ በተለይ እንዲህ ናፍቆት ባሳደደ ቀን … ህይወት ለንቦጭዋን በጣለች ጊዜ፡፡
ትርጉም የለሽ ናት ህይወት፡- ልል ነበር፡፡ … ግን አንዱ ትርጉምዋ ይሄ አይደል! … በፍቅር ዓይኖች ጥቅሻ እየነፈሩ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ መንጎድ! … ተውኩትና አሰብኩ፡፡ ያበሳጨኝ የሳሮን ናፍቆ ብቻ አይደለም፡፡ አይኖችዋ የልቤን እርቃን በብርሃን ልምጭ ስለዠለጡትም አይመስለኝም፡፡ … እነዚያን የውበትና የፍስሀ ኃይላት መቆጣጠር ባለመቻሌ ነው፡፡ ስድስት ወር ሙሉ አብሬያት ስንገላወድ ኖሬ ፍቅረኛ ያለማድረጌ! አልጫ ነገር ነኝ! …
ቀጠና ሁለት ደረስኩና ቴዲ ካፌ ገባሁ፡፡ መስከረም የቡናው ማሽን ላይ ቆሟል፡፡ በድሩ ፈጥኖ  መጣና ታዘዘኝ፤ ወይም አየኝ፡፡ ጠቀስኩት፡፡ ከማኪያቶ ሌላ ጠጥቼ አላውቅም፡፡
ብርጭቆዋ እስክትሰክር ድረስ አጣፍጦ ሰራልኝ፡፡ እያጣጣምኩ አወረድኳት፡፡ አሁን ግን በጧት መውጣቴ ምን እንደሚረባኝ አላወኩም፡፡ ሽሽት መሆኑ ነው፡፡ ብቻዬን አልጋ ላይ ስታገኘኝ እንዳትዘነጣጥለኝ ፈራሁ፡፡ ልቤን---አንጀቴን---ኩላሊቴን----ጉበቴን…. ከራስ ፀጉር እስከ እግር ጥፍሬ! …
 በካፌው የግድግዳ መስታወት ውጭው ወለል ብሎ ይታያል፡፡ ታክሲዎች ተደርድረዋል፡፡ ቀራንዮና የሺ ደበሌ ይጠራሉ፡፡ ከፊሉ ደግሞ ከወይራ ሰፈር መጥተው ቆመዋል፡፡ ሰው ይተራመሳል፡፡ ከታች ከቻይና ኤምባሲ በኩል የሚመጣው፣ እንደገና ወደ ታች የሚወርደው ብዙ ነው፡፡
“እ…. እንዴት ነበር? ማኪያቶው?”  አለኝ መስከረም! የአውራ ጣቴን ቀስሬ አሳየሁት፡፡ ቀሽት ነው ማለቴ ነው፡፡ ማመስገን ነበረብኝ… አንዳንዴ ደንበኛ ደስ ሲለው፣ ደስ እንዲላቸው ምላሽ ይፈልጋሉ፡፡ ቲፕ እንኳ ቢቀር የአንደበት ምስጋና!
ሞባይሌን አውጥቼ ልደውልላት አሰብኩ፡፡ ግን ደግሞ በዚህ ጠዋት ምን ብዬ ነው የምደውልላት! … ስድስት ወር ሙሉ ሳንቀላፋ ቆይቼ ዛሬ በዛሬ ምን ልፈጥር ነው? … የዛሬ አራት ዓመት የኮሌጅ ጓደኛዬ ያለችኝ ትዝ ይለኛል፡፡ “… እንዴ መቼ ነው ከእንቅልፍህ የምትባንነው! ኧረ ንቃ!” ብላኝ ነበር፡፡ ለዚያውም ከተለያየን በኋላ ያንን ያህል ስታወራኝ፣ ያን ያህል  ጉያዬ ውስጥ ስትገባ፣ ጡት እንደምትጠባ ወላድ ዝም ብዬ ማለፌ የገባኝ ቆይቶ ነው፡፡ አሁን ሳሮንስ እንደዚያ ሆና ከሆነ ለማንኛውም ይለይላታል፡፡
ለነገሩ አሁን ብደውል እንኳ ምናልባት ሥራ ላይ ልትሆን ትችላለች፡፡ የሬዲዮ ስቱዲዮ ቴክኒሻን ናት፡፡ የእነርሱ ሥራ አንዳንዴ በምሽትም ሊሆን ይችላል፡፡ ማለዳም እንደ ወፍ ከሚንጫጫው ጋዜጠኛ ጋር አጅባ ትንጫጫ ይሆናል፡፡ የአዳም ፍጡር፣ ጧት ማታ እንጀራ! ጧት ማታ ኑሮ! … ወደ ፍልስፍናው መሄድ አስቤ፣ ፍልስፍና ትንሽ ችኮ ነው፡፡ ፍቅር ለስላሳ ነው፡፡ ፍቅር አበባ ቢሆን፣ ፍልስፍና እሾህ ነው፡፡ በጧት ደ‘ሞ እሾህ ምን አመጣው?
ሚስቴ ብትሆን ግን ያስጠላኝ ነበር፡፡ ከሞቀ መኝታችን ውስጥ ምዝዝ ብላ ጥላኝ ስትሄድ አንጀቴ ይቃጠላል፡፡ በተለይ በክረምት! … ለነገሩ ሲጀመርስ አገባታለሁ ብዬ መች አሰብኩ፡፡ ድንገት ስለ አርክቴክቸር ላወራ ሬዲዮ ጣቢያ ተጋብዤ ስተነትን አይደል አይን ለአይን የተጋጨነው፡፡ ከዚያ በኋላ ከስቱዲዮ ስወጣ ጨብጣኝ፤“ንግግርህ ያምራል!” እነዚያ ኳስ አይኖቿ ናቸው እየተከተሉ እንደ ርችት ሲፈነዱብኝ የከረሙት፡፡
ያን ያህል ግን ማራኪ ንግግር ነበረኝ እንዴ? … ያወራሁት ስለ ኪነ-ህንፃ የየዘመኑ መልክነትና የጀርባ ትርጓሜ ነበር፡፡ ምናልባት ስለ አውድም አውርቼ ይሆናል፡፡ በርግጥም ከታላላቅ ሰዎች ሀሳብ ጋር አጣጥሜ ትንሽ ውበት ነስንሼለት ነበር፡፡ … ግን ለቅን ልቦና … በርዋን ለከፈተች ነፍስ ያ በቂ ነው፡፡ ልብዋ በር ላይ ውሻ አስራ ቢሆን አስደንግጦኝ ነበር፡፡ የልብዋ በር ግን የአበባ እርሻ ነው፡፡ ያስታውቃል፡፡
ማልታ “… ሃይ ድጋፌ!” አለኝ ድንገት፡፡
ቀና ብዬ አየሁት፡፡ የፊት ጥርሶቹ የሉም፡፡ ባርኔጣውን እያስተካከለ - ተቀመጠ፡፡
“ሰማህ ዛሬ አርሰናል!”
ሊጨቀጭቀኝ ነው፡፡ ዝም አልኩት፡፡
“ድሮ መንግስቱ ወርቁ! … ፓ!... ለጊዮርጊስ ሲጫወቱ!”
ፈረደብኝ፡፡
“በል ልጋብዝህ ቡና ጠጣ!”
“እዚህ ቤት ማልታ የለም!..”
“በቃ ቡና ጠጣ!”
ከንፈሩን አጣመመ፡፡
“እኔ የራሴ ኳስ ሜዳ ውስጥ ነኝ” ልለው ፈልጌ ተውኩት፡፡
ማልታ ደስ ሳይለው ቡና አዝዞ አጠገቤ ተቀመጠ፡፡ ብቻዬን መሆን ፈልጌ ነበር፡፡ ይሉኝታ አልያዘኝም፡፡ የሁለታችንንም ከፍዬ ቁልቁል ወደ ቸኮላት ካፌ ወረድኩ፡፡ እዚያ ሰገነት ላይ ወጥቼ ቁልቁል እያየሁ፣ቢያሻኝ ማንጎራጎር ባይሆን ስልክ ደውዬ እንደ ልቤ ማውራት እችላለሁ፡፡ ማኪያቶ መድገም አልፈለግሁም፡፡ በቅመም ያበደ ሻይ አምጪልኝ አልኳት፡፡ ፈገግተኛ አስተናጋጅ ናት፡፡
እዚያ አሰብኩ፤ ቴአትር ልጋብዛት ይሆን? መቸም እሷ ከቴአትር ይልቅ ፊልም እንደምትመርጥ አውቃለሁ፡፡ እኔ ግን ፊልም ማየት አይመቸኝም፡፡ አእምሮ እንዳስለመዱት ነው፡፡ ጎመንም ሆነ ጮማ እንደ ሰውየው ነው፡፡ ታክሲ ይዤ ወደ ሜክሲኮ ብሄድ የመገናኘት ዕድልም ይኖረን ነበር፡፡ ግን ደ‘ሞ የጦር ኃይሎችን የታክሲ ፍልሚያ ማን ይችለዋል! … ማርፈድ አለብኝ፡፡
 ብቻ ክብ ቀይ ፊትዋ፣ ጥርሶችዋና ድምፅዋ እየመጡ ይረብሹኛል፡፡ ሰሞኑን የፌስ ቡክ አካውንት የከፈትኩትም፣ እስዋ እየከፈተች ስታቀረቅር አይቼ ነው፡፡ ፍቅር ያጃጅላል’ኮ… #ታዲያ ፌስቡክ ውስጥ ለምን አልፈልጋትም፡፡ ደግሞስ ፕሮፋይሏን ለምን አላነበውም፡- ጥሩ ዘዴ መጣልኝ; አልኩና አጎነበስኩ፡፡ ከፈትኩት፡፡
ፌስቡክ ብዙ ደስ አይለኝም፡፡ ጓደኞቹ ሲያወሩኝና ሲያሳዩኝ ብዙ ነገሩ ግልብ ነው፡፡ ውስጧ የማይታወቅ የሴት ሥዕል እያዩ ማጨብጨብ አይደል እንዴ! … ድንቅ ነው! … ልዩ ነሽ! ማለት፡፡ ውስጧ ሲታይ ደግሞ ገለባ ሆነ ትገኛለች፡፡ በዚያ ውብ መልኳ የተገረመን ወንድ እንደገና እንደ እንስሳ እርቃን በማሳየት ፍየልነቷን ታስመሰክራለች፡፡ ወንዱስ ቢሆን? ጢሙን አንዠርግጎ አንበሳ በመሰለ ፊቱ፣ የህፃን ልጅ ቀልድ ሲቀልድ ወይም ወደ ተወለደበት ቀንና ሥዕል ሲወርድ ይደብራል፡፡
የሳሮንን ከፍቼ አየሁት፡፡ ብዙ ሳሮኖች አሉ፡፡ ጥቁር፣ ጠይም፣ የቀይ ዳማ፡፡ ፀጉረ ዞማ፣ ፀጉረ ቁርንድድ! … አቤት የሄዋን ዘሮች! ወዲያው የሄድኩት ወደ ራሴ ሳሮን ነው፡፡ ፎቶግራፏን ተራ በተራ ፈተሽኩ፡፡ ሰውነቴ ሳላውቀው በላብ ተነከረ፡፡
“ከስንት ወንዶች ጋር ነው ተቃቅፋ የተነሳቸው?… ከሦስት?” አጭበርባሪ ናት ለካ! ነደደኝ፡፡ ቆይ ፍቅረኛ አለኝ ማለት አትችልም እንዴ? … ይህን ያህል ስንግባባ! … ወይስ “ንፁህ ወንድሜ ነህ! … በሚል ሽንገላ ልትጠፈንገኝ! እንደዚያ የፍቅር እሳት የሚተፉ አይኖችዋ  በአይኖቼ በኩል ገብተው ልቤን ሲያርሱት አታውቅም? … ባላየው ይሻለኝ ነበር ይሆን? … ማየቴ ክፋት የለውም፡፡ ግን ለምን እንዳልነገረችኝ መጠየቅ አለብኝ፡፡
“ሻዩ አልተመቸህም?” አለችኝ አስተናጋጅዋ፡፡ ፊቷ ተለዋውጧል ማለት ነው፡፡
“አይ ደህና ነው!” አልኳትና ለሰው ስለሚጨነቁ ሰዎች አሰብኩ፡፡ ይህቺ አስተናጋጅ ባለችበት ሁኔታ ሰው እንዲያዝን አትፈልግም ማለት ነው---ብዬ የሳሮንን ሀጢያት ልጨምር ሞከርኩ፡፡ “ምናልባት የአጎትዋ ልጆች… የአክስቷ ልጆች ቢሆኑስ?” እንደገና ላየው ሞከርኩ፡፡ የአጎት ልጅ እንደዚህ ወገብ ጨምድዶ ፎቶ አይነሳም፡፡ ትከሻዋ ላይ እጁን ቢጥል ነው፡፡
ቁጥሯን መታሁ፡፡ በሳቅ ጀመረች፡፡ ዘንቦ እስኪያባራ ጠበቅሁ፡፡ የሰማይ ሙዚቃ ነው፡፡ ምትሀት አለው፡፡
“ምነው በሰላም”
“ፌስቡክሽን ከፍቼ አየሁት!”
ፀጥ አለች፡፡
“ምን አየህ?”
“ሁሉንም ነገር በተለይ ፎቶግራፎችሽ!”
“ፎቶግራፎቹን እቀይራቸዋለሁ ብዬ ነበር፣ ታሪኬን የሚያውቁ ሰዎች ከለከሉኝ;
“እንዴት?”
“አንዱ የዛሬ ዓመት ገደማ ያረገው ጓደኛዬ ነው፡፡”
“ወዴት ወደ ሰማይ?”
“አ…ዎ!”
“አልገባህም! … ቦይ ፍሬንዴ ነበረ! …”
“እ….ና?”
“ አ-ረ-ገ!”
“ምን ማለት ነው፡፡
“ከዚህ ዓለም ተለየ!”
“ታዲያ ሞተ አትይኝም!”
“ተ-ው! .. ተው!... እንደሱ አይባልም!”
“ከሌላው ሰው ይለያል እንዴ አሟሟቱ?”
“ተው ስለሞት አታውራ!”
“ምነው ሳሮን አዲስ አይደለም’ኮ!”
“ለኔ አዲስ ነው፡፡ … ከእርሱ ቀድመው ሦስት ቦይ ፍሬንዶቼ አርገዋል”
“ሞተዋል ማለት ነው?”
“አንተ በለው … እኔ ግን ዳግም እንዳይደርስብኝ - ይህን ቃል አትጠቀሚ ተብያለሁ፡፡ … ስለምፈራ ነው፡፡ ፎቶግራፋቸውን እንዳላወጣ ደ‘ሞ ቤተሰቦቻቸው ያዝናሉ!; አማተብኩ፡፡ የት አባቴ ልደበቃት? … እኔም የተንቀዠቀዥኩት ከእነርሱ ጋር ለማረግ ነው? ከኪሴ ውስጥ ሂሳቡን እንዴት አድርጌ እንዳወጣሁት አላውቅም፡፡ ጠረጴዛ ላይ ወርውሬ ሸሸሁ፡፡ “ቆይ መልስ አለህ!” የሚለው የአስተናጋጅዋ ድምፅ ተከትሎኛል፡፡ እኔቴ ዞር ብዬም አላየሁ፡፡ … የልቤ ምት ግን ይሰማኛል፡፡

Read 15864 times