Monday, 27 July 2015 11:24

ጆርጅ ክሉኒ ከአፍሪካ ጦርነት ትርፍ በሚያጋብሱት ላይ ዘመቻ ጀመረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 አንጋፋው የሆሊውድ የፊልም ተዋናይ ጆርጅ ክሉኒ፤ የአፍሪካን አስከፊ ግጭቶች በገንዘብ የሚደግፉና ከጦርነቱ የሚጠቀሙ ወገኖችን በመከታተል ለፍርድ ለማቅረብ የሚያስችል አዲሰ ፕሮጀክት ባለፈው ሰኞ መጀመሩን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ ክሉኒ ከአሜሪካዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ጆን ፕሬንደርጋስት ጋር “The Sentry” በተባለ ፕሮጀክት ላይ በጋራ ለመስራት የተቀላቀለ ሲሆን ፕሮጀክቱ በግጭት ቀጠናዎቹ ውስጥና ውጭ ያለውን የገንዘብ ፍሰት በመመርመር፣ ለፖሊሲ አውጭዎች ውጤታማ እርምጃ መውሰድ የሚያስችላቸውን ግብአቶች ለመስጠት ያለመ ነው ተብሏል፡፡
ፕሮጀክቱ መረጃ በማሰባሰብ፣ የመስክ ጥናት በማካሄድና የትንተና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ጦርነቶች እንዴት በገንዘብ እንደሚደገፉና ትርፍ እንደሚገኝባቸው ለማጋለጥ ያቀደ ሲሆን ሰዎች በድረገፅ የሚያውቋቸውን መረጃዎችና ምስጢሮች ስማቸውን ሳይገልፁ እንዲጠቁሙ ያበረታታል፡፡  የ54 ዓመቱ ክሉኒ እና ፕሬንደርጋስት ለሮይተርስ እንደገለፁት፤ የዚህ ፕሮጀክት ዓላማ፤ “የጦርነት አትራፊዎች ከወንጀላቸው ያገኙት የነበረውን ጥቅም መንፈግ ነው” ብለዋል፡፡ “ከጦርነቱ የሚጠቀሙ ሰዎች ላደረሱት ጉዳት ዋጋ ሲከፍሉ ሰላም ለማስፈንና ሰብዓዊ መብት ለማስከበር አቅም ይፈጠራል” ብሏል የሁለት ጊዜ ኦስካር አሸናፊው ክሉኒ በሰጠው መግለጫ፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የአፍሪካ ጉብኝታቸውን ከመጀመራቸው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ የተጀመረው ፕሮጀክት፣ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳንን ጨምሮ ከሰሜን ምስራቅ እስከ ማዕከላዊ አፍሪካ ያሉ ግጭቶችን በገንዘብ የመደገፍ እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል ይመረምራል ብሏል ሮይተርስ፡፡
አዲሱ ፕሮጀክት ክሉኒ ከእነብራድ ፒትና ማት ዴመን የመሳሰሉ ተዋናዮች ጋር በመሰረተው “Not on our watch” የተሰኘ ድርጅትም ድጋፍ እንደሚደረግለት ታውቋል፡፡ የቀድሞው የአሜሪካ ፀጥታ ም/ቤት የአፍሪካ ዳይሬክተር የነበሩት ፕሬንደርጋስት እና ክሉኒ በሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ላይ ሲሰሩ የአሁኑ የመጀመሪያቸው አይደለም፡፡    

Read 1818 times