Monday, 27 July 2015 11:30

ገንዘቤ የወርቅ ሜዳልያ ጉጉቷ ጨምሯል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

    የምትሰለጥነው ከወንዶች ጋር ነው፡፡
                   በዓለም ሻምፒዮና በ5ሺ፤ በ1500 ወይንስ በሁለቱም?
                   ከሪከርድ ይልቅ ከእንግዲህ የምጓጓው ለወርቅ ሜዳልያዎች ነው፡፡
                   ዘንድሮ በዳይመንድ ሊግ 4 ውድድሮች አሸንፋ 40ሺ ዶላር አግኝታለች፡፡
    የ24 አመቷ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ዘመናዊ የስኬት ሞዴል ልትሆን እንደምትበቃ ሰሞኑን በመላው ዓለም የተሰራጩ ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡ አትሌት ገንዘቤ 2015 ከገባ በኋላ ባስመዘገበቻቸው ውጤቶች በሁሉም የውድድር መደቦች ከዓለም ሴት አትሌቶች በ1404 ነጥብ አንደኛ ደረጃ ላይ እንደሆነች በኦል አትሌቲክስ ድረገፅ የሰፈረው መረጃ ያመለክታል፡፡ በውድድር ዘመኑ ላይ በአራት የዳይመንድ ሊግ ድሎች በማስመዝገብ በ5000 ሜትር የደረጃ ሰንጠረዡን በ6 ነጥብ ልዩነት  የምትመራው ገንዘቤ እስከ 40ሺ ዶላር የተሸለመች ሲሆን ለዳይመንድ ዋንጫው ግንባር ቀደም ተፎካካሪ ሆናለች፡፡
በ2015 የውድድር ዘመን መግቢያ በዓለም አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር የኮከብ አትሌቶች ምርጫ ከመጨረሻዎቹ ሶስት እጩዎች አንዷ የነበረችው ገንዘቤ፤ ከዚያ በኋላ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የላውረስ አዋርድ ተሸላሚ ለመሆን በቅታለች፡፡ በከወር በኋላ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ቤጂንግ ላይ የምታስመዘግበው ውጤት በዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ ያለተቀናቃኝ ተሸላሚ እንድትሆን ያበቃታል፡፡ ገንዘቤ ዲባባ ከእነ ደራርቱ፤ ጌጤ ዋሚ፤ እጅጋየሁ ዲባባ፤ ጥሩነሽ እና መሰረት ደፋር በኋላ በሚያስገርም የአትሌቲክስ ስብእና ወደ ዓለም የወጣች የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ዘመናዊ የስኬት ሞዴል ሆና መታየት ያለባት አትሌት ናት፡፡ በአሁኑ ወቅት በስፖርቱ አለም በተለይ በአትሌቲክስ ውድድሮች ሪከርዶችን ለማስመዝገብ እጅግ ወሳኝ ከሆነው ተፈጥሯዊ ክህሎት ባሻገር ሌሎች ቅድመ ዝግጅቶችን በተሟላ መንገድ በማግኘት ገንዘቤ ዲባባ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ወቅታዊ የመነሻ ምልክት መሆን ትችላለች፡፡ በተለያዩ ውድድሮች ለሪከርድ ፍጥነት የሚመደቡ አሯሯጮችን በመጠቀም ፤ በቴክኖሎጂ የታገዙ የመሮጫ ጫማዎችና ትጥቆችን በተሟላ ሁኔታ በማግኘት፤ ዘመናዊ ህክምናዎች እና መድሃኒቶች በአጭር ጊዜ ከጉዳት ለማገገም በመቻል፤ እጅግ ዘመናዊ የስልጠና፤ የአመጋገብ እና የስነልቦና ዝግጅቶች በማድረግ ገንዘቤ ዲባባ ከሷ በፊት ከነበሩ አትሌቶች የላቀ እድገት በማሳየት ላይ ናት፡፡
በዓለም አትሌቲክስ ባለፉት 5 የውድድር ዘመናት ገንና እየወጣች ያለችው ገንዘቤ ካስመዘገባቻቸው ከፍተኛ ውጤቶች መካከል 2 የወርቅ ሜዳልያዎች በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ፤ 1 የብር ሜዳልያ በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ማግኘቷ ይጠቀሳል፡፡ ከዚያ ባሻገር 3 የፍፃሜ ውድድሮች በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ያደረገችበት ልምድ አላት፡፡ በዳይመንድ ሊግ በ1500 እና በ5ሺ ሜትር ዋንኛ ተቀናቃኝ የሆነችው ገንዘቤ በአጠቃላይ በ8 ከተሞች ስምንት አስደናቂ ድሎች በዳይመንድ ሊግ ውድድሮችም አስመዝግባለች፡፡
ቤጂንግ ላይ በ5ሺ ፤1500 ሜትር ወይንስ በሁለቱም?
እንደአይኤኤኤፍ ዘገባ በመካከለኛ ርቀት የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድሮች በልዩ ብቃት ፍፁም የበላይነት ያሳየ አትሌት ብዙም አጋጥሞ አያውቅም፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ግን የ24 ዓመቷ ገንዘቤ ዲባባ በቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሁለት የዓለም ሻምፒዮናነት የወርቅ ሜዳልያዎችን ከመጎናፀፏም በላይ፤ በያዝነው የውድድር ዘመን በ1500 እና በ3000 ሜትር የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድሮች ከአንድ ጊዜ በላይ የዓለም ሪከርድ በማስመዝገብ ተሳክቶላታል፡፡
‹‹ከቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድር ተሳታፊነት ወደ ትራክ ለመዞር አስቸጋሪነቱ የተለመደ ነው፡፡ በርግጥ የትራክ ውድድር ለእኔ የሚቀለኝ ይመስለኛል፡፡ ግን መሮጥ የምፈልገው በቤት ውስጥ አትሌቲክስ መወዳደርን ነው፡፡ የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድርን የምመርጠው ባለው ሞቅ ያለ ድባብ እና በመሮጫ መሙ ማጠር ነው›› በማለት ገንዘቤ ተናግራለች፡፡ የገንዘቤ ዲባባ አሰልጣኝ ጃማ አደን ይባላል፡፡ ዘንድሮ በልምምድ ፕሮግራማቸው ከአሰልጣኟ ጋር ለትራክ ውድድሮች ውጤታማነት በመስራት ላይ ማዘንበላቸውን ለአይኤኤኤፍ ዘጋቢ የገለፀችው ገንዘቤ ዲባባ፤ ‹‹ብዙውን ግዜ ልምምድ የምሰራው ከወንዶች አትሌት ጋር በመሆኑ ብቃቴን አንዳጎለብት ጥሩ ግፊት ተፈጥሮልኛል›› ብላለች፡፡ ከአሰልጣኝ ጃማ አደን ጋር ከገንዘቤ ዲባባ ጋር  የሚሰለጥኑት ሌሎቹ ወንድ አትሌቶች በ800 ሜትር የዓለም ሻምፒዮና የነሐስ ሜዳልያ ባለቤት የሆነው የጅቡቲው አይናለህ ሱሌይማንና እና የኳታሩ አትሌት ሙሴባ ባላ ይጠቀሳሉ፡፡ጃማ ሞሃመድ አደን በትውልዱ ሶማሊያዊ ሲሆን አገሩን ወክሎ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች በመካከከለኛ ርቀት ይሮጥ የነበረ ነው፡፡ በ እኤአ በተደረገ የዓለም ሻምፒዮና እና በ ኦሎምፒክ ሶማሊያን በመወከል የተሳተፈም አትሌት ነው፡፡ በ800 እና በ1500 ሜትር የተዋጣለት አትሌት ነበር፡፡
በአትሌቲክስ መወዳደር ካቆመ በኋላ ወደ ስልጠናው የገባው ጃማ በኤክሰርሳይስ ፊዝዮሎጂ ከጆርጅ ሜሰን ዩኒቨርስቲ ማስትሬት ዲግሪ የተቀበለ ሲሆን፤ በ1987 እኤአ ላይ በዓለም ሻምፒዮና ለሶማሊያ የወቅር ሜዳልያ ያስገኘው የመካከለኛ ርቀት ሯጭ አብዲ ቢዬሌ አሰልጣኝ በመሆን ያገኘው ስኬት ታዋቂ አድርጎታል፡፡ አሁን ከኢትዮጵያዊቷ ገንዘቤ ዲባባ ጋር በመስራት በስልጠና ሙያው በከፍተኛ ደረጃ ስሙ እየገነነ መጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ባለፈው ሳምንት ባወጣው በ15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የሚሳተፈው ጊዜያዊ የቡድን ስም ዝርዝር ላይ ገንዘቤ ዲባባ በ5000 እና በ1500 ሜትር እንድትሮጥ መርጧታል፡፡ ይህንኑ አስመልክቶ ግን የተረጋገጠ ነገር ከወዲሁ የለም፡፡ በዓለም ሻምፒዮናው ላይ በየትኛው ርቀት እንደምትወዳደር የምትወስነው በቅርብ ጊዜ ከአሰልጣኟ ጋር በመማከር እንደሆነ የገለፀችው ገንዘቤ፤ በአንድ ውድድር ለመሳተፍ ከወሰንን ምርጫዬ በ5000 ሜትር መሮጥ ነው ብላለች፡፡ ባለፉት የውድድር ዘመናት በሁለት የዓለም ሻምፒዮናዎች እንዲሁም በኦሎምፒክ በ1500 ሜትር ተሳትፋ ገንዘቤ ዲባባ ማጣርያዎቹን እያለፈች ለፍፃሜ ብትወዳደርም ከ8ኛ የተሻለ ደረጃ አላስመዘገበችም፡፡ በ2015 እኤአ ላይ እያስመዘገበች ካለችው ስኬት አንፃር አሁን ዋንኛው ጉጉቷ ከሪከርዶች ይልቅ በዓለም ሻምፒዮና ወይንም በኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያዎች ማግኘት እንደሆነ ገልፃለች፡፡
‹‹ሁሉም ከእኔ የሚጠብቀው የወርቅ ሜዳልያ ነው፡፡ እናም ይህን ማሳካት አለብኝ፡፡ በተለይ ታላቅ እህቴ ያገኘችውን ስኬት መድገም ወይም ማሻሻል  አለብኝ፡፡›› ስትል ተናግራለች፡፡ ‹‹ህልም አለኝ፡፡ በርግጥ ህልሜ ሪከርዶችን መስበር ብቻ አይደለም፡፡ ወደፊት ግን የ1500 ሜትር ብቻ ሳይሆን የ5000 ሜትር እና የ800 ሜትር ክብረወሰን መስበር እፈልጋለሁ›› በማለትም ስለወደፊት እቅዷ አስተያየት ሰጥታለች፡፡
ከወር በኋላ ቤጂንግ ላይ በሚካሄደው 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በ1500 እና በ5000 ሜትር ደርባ ስለመወዳደሯ ወይንም በአንዱ ርቀት ስለመወሰኗ የመጨረሻ ውሳኔዋ በጉጉት ከገንዘቤ ዲባባ ይጠበቃል፡፡ ከሞናኮው የ1500 ሜትር የዓለም ሪከርድ ሩጫዋ በኋላ በሰጠችው አስተያየት ከአሰልጣኟ ጋር በመመካከር የምትወስነው እንደሆነ የገለፀችው ገንዘቤ በዓለም ሻምፒዮና ላይ ዋናው ትኩረቷ 5000 ሺ ሜትር ላይ ለመወዳደር መሆኑን ጠቁማለች፡፡ በአካል በቃት፤ በዝግጅት ትኩረት እና በስነልቦናም ዝግጅቷ ለ5000 ሜትር መሆኑንም አስገንዝባለች፡፡ ሌትስራን ድረገፅ በሰራው ትንተና ገንዘቤ ቤጂንግ በምታስተናግደው 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሁለቱም ርቀቶች መሮጥ ትችላለች፡፡ የ1500 ሜትር ሁለት የማጣርያ ውድድሮች በዓለም ሻምፒዮናው አንደኛና ሁለተኛ ቀኖች እንዲሁም ፍፃሜው በአራተኛ ቀን ከተደረጉ በኋላ 5000 ሜትር ማጣርያው በስድስተኛው ቀን እንዲሁም ፍፃሜው በሻምፒዮናው 9ኛ ቀን ስለሚደረግ ለገንዘቤ የተመቸ መርሃ ግብር ነው ብሏል ሌትስ ራን ድረገፅ፡፡
ከሞናኮው የሪከርድ ገድል በኋላ ገንዘቤ ዲባባ በሰጠችው አስተያየት ክብረወሰኑን በማሳካቷ ታላቅ እህቷ ጥሩነሽ ዲባባ እና የኢትዮጵያ ህዝብም በተመሳሳይ ደስተኛ የሆናሉ ካለች በኋላ ወደፊት የርቀቱን ሪከርድ እንደምታሻሽል እና በ5 ሺህ ሜትርም ክብረ ወሰን ለመስበር መስራት ሌላው ትኩረቷ እንደሆነ ተናግራለች፡፡ የ5ሺ ሜትር ሪከርድ ለመስበር የሚኖራትን እቅድ ከዓለም ሻምፒዮናው በኋላ ለመተግበር እቅድም እንዳላት አስታውቃለች፡፡
ሪከርዶቿን  ከሷ በቀር የሚሰብር ላይኖር ይችላል
የ24 ዓመቷ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ ከሳምንት በፊት በሞናኮ በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር በ1500 ሜትር አዲስ የዓለም ሪከርድ ማስመዝገቧ በከፍተኛ ደረጃ የምትደንቅበት ሆኗል፡፡ በ1500 ሜትር ገንዘቤ የሰበረችው አዲስ የዓለም ሪከርድ በ3 ደቂቃዎች ከ50.07 ሴኮንዶች የተመዘገበ ነው፡፡ የመካከለኛ ርቀት ሪከርድን አንዲት ኢትዮጵያዊ ሴት አትሌት በዓለም የአትሌቲክስ መድረክ ለማስመዝገብ ስትበቃ ገንዘቤ ዲባባ በታሪክ የመጀመርያዋ ሆናለች፡፡ ገንዘቤ የሰበረችው የ1500 ሜትር ሬከርድ ለ22 ዓመታት በቻይናዊቷ ኩ ዩንሺያ የተያዘ እና ሰዓቱን ለማሻሻል የማይቻል ደረጃ ተደርሷል ተብሎ የነበረ ነው፡፡ ቻይናዊቷ አትሌት የ1500 ሜትር የዓለምን ክብረወሰን በ1993 እኤአ ላይ ቤጂንግ ውስጥ በተካሄደ ውድድር 3 ደቂቃ ከ 50 ሰክንድ ከ 46 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ይዛው ነበር፡፡ ከ22 ዓመታት በኋላ ገንዘቤ ስትሰብረው በ39 ሰከንዶች ፈጥና በመግባት ነው፡፡ በ1500 ሜትር ገንዘቤ ያስመዘገበችው ክብረወሰንን ራሷ ካልሆነች በቀር በሌላ አትሌት ለማሻሻል ብዙ ዓመታት ሊወስድ ይችላል እየተባለ ነው፡፡
የገንዘቤ 4 የዓለምና 6 የአፍሪካ ሪከርዶች
ገንዘቤ ዲባባ በሞናኮ ካስመዘገበችው የ1500 ሜትር አዲስ የዓለም ሪከርድ በኋላ በሩጫ ዘመኗ ያስመዘገበቻቸው የዓለም ሪከርዶች ብዛት 4 ሆነዋል፡፡
ከእነዚህ ሪከርዶች አራቱ የዓለም ሪከርድ ስድስቱ ደግሞ የአፍሪካ ሪከርድ ናቸው፡፡ ገንዘቤ ዲባባ በ1500ሜና በ3ሺ ሜትር የቤት ውስጥ ውድድሮች እንዲሁም በ2 ማይል ሩጫ የተመዘገቡት ሶስት የዓለም ሪከርዶችን ሌላ አትሌት በድጋሚ ሊሰብር የሚችለው ቢያንስ ከ5 አመታት በኋላ እንደሚሆን በባለሙያዎች ይገለፃል፡፡በሴቶች 5ሺ ሜትር ውድድር ጥሩነሽ ዲባባ የያዘችው ክብረወሰን ከተመዘገበ 6 ዓመታት አልፈዋል፡፡
 ይህን ክብረወሰን ለመስበር ገንዘቤ ዘንድሮ ካስመዘገበችው ፈጣን ሰዓት በ8 ሰከንዶች ፈጥና ርቀቱን መጨረስ ይጠበቅባታል፡፡
የገንዘቤ 4 የዓለም ሪከርዶች
1. በ1500 ሜትር ትራክ 3:50.07
2. በ1500 ሜትር የቤት ውስጥ አትሌቲክስ 3:50.07
3. በ3ሺ ሜትር የቤት ውስጥ አትሌቲክስ 8:16.60
4. በ5ሺ ሜትር የቤት ውስጥ አትሌቲክስ 14:18.86
የገንዘቤ 6 የአፍሪካ ሬከርዶች
1. በ1500 ሜትር በትራክ 3:50.07
2. በ1500 ሜትር የቤት ውስጥ አትሌቲክስ 3:50.07
3. በ3ሺ ሜትር የቤት ውስጥ አትሌቲክስ 8:16.60
4. በ5ሺ ሜትር የቤት ውስጥ አትሌቲክስ 14:18.86
5. በ2000 ሜትር ትራክ 5:27.50
6. በ3ሺ ሜትር ትራክ 8:26.21

Read 3635 times