Saturday, 01 August 2015 14:24

ውሸትና ሮቦት…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(13 votes)

“ውሸት ስንናገር በጥፊ የሚያጠናግር ሮቦት በየቦታው ይተከልልንማ!”
                    
   እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ… የመዋሸት ነገር ካነሳን አይቀር…ይቺን ስሙኝማ… አባት ሆዬ ማንም ሰው ውሸት በተናገረ ጊዜ በጥፊ የሚያጮል ሮቦት ይገዛል፡፡ ከዛም አንድ ቀን እራት ላይ ሊሞክረው ይወስናል። አባትየውም ልጁን “ከሰዓት በኋላ የት ነበርክ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ልጁም…
“ትምህርት ቤት ነበርኩ…” ይላል፡፡
ሮቦቱ በጥፊ ያጮለዋል፡፡
ልጁም … “ጓዷኛዬ ቤት ቪዲዮ እያየሁ ነበር፡” ሲል አስተካከለ፡፡ አባትየውም…
“ምን አይነት ፊልም አየህ?” ይለዋል፡፡
“የካራቴ…” ምናምን ብሎ ሲጀምር ሮቦቱ ደግሞ በጥፊ ያጮለዋል፡፡
ልጅየውም ጣደፍ ብሎ…“እሺ፣ የወሲብ ፊልም ሳይ ነበር…” ይላል፡፡ አባትየው ቆጣ ይልና…
“እኔ በአንተ ዕድሜ ሳለሁ እንዲህ አይነት የብልግና ፊልም አይቼ አላውቅም…” ይላል፡፡
ሮቦቱ በጥፊ ያጠናግረዋል፡፡
ይሄን ጊዜ እናትየው ከት ብላ ትስቅና… “ምን ያድርግ ምንም ቢሆን የአንተ ልጅ አይደል…” ትላለች፡፡
ሮቦቱ በጥፊ አጠናግሯት አረፈላችሁ፡፡
ውሸት ስንናገር በጥፊ የሚያጠናግር ሮቦት በየቦታው ይተከልልንማ!
ኮሚክ እኮ ነው…ብዙ ጊዜ በአንድ ጉዳይ ላይ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ሁለቱም እውነት ሊሆኑ አይችሉም አይደል! ለምሳሌ ይህ ‘አምደኚስት’ ወይ አጭር ነው፣ ወይ ረጅም ነው። አጭርም፣ ረጅምም የሚሆንበት ተአምር ገና አልተከሰተም፡፡ (‘ገለጻ’ ተሰጥቶ ልብ ውልቅ አይነት ነገር አይመስልም!) ዘንድሮ ግን “አጭር ነው…” የሚለውም ‘እውነት’ ነው፣ “ረጅም ነው…” የሚለውም ‘እውነት’ ነው፡፡ በቃ…እንዲህ ስንሆንስ! እኛ ዘንድ በአንድ ጉዳይ ላይ የተሰጡ አሥር የተለያዩና የማይገናኙ ነገሮች ‘እውነት’ ይሆናሉ፡፡ ልክ ነዋ… ሁላችንም እውነተኛ “…እኔና እኔ ብቻ…” እያልን ነዋ!
ውሸት ስንናገር በጥፊ የሚያጠናግር ሮቦት በየቦታው ይተከልልንማ!
አንድ ቄስ የሳምንቱን ጉባኤ ሲጨርሱ እንዲህ ይላሉ፡፡ “በሚቀጥለው እሁድ ስለሚዋሹ ሰዎች እናወራለን፡፡  ለእሱም ለመዘጋጀት ሁላችሁም የማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ አሥራ ሰባትን አንብባችሁ ኑ፣” ይላሉ፡፡
በተከታዩ እሁድ አዳራሹ ጢም ይላል፡፡ ቄሱም… “ባለፈው ሰንበት እንዳልኳችሁ የማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ አሥራ ሰባትን አንብባችሁ እንደመጣችሁ እምነቴ ነው፡፡ ስንቶቻችሁ ናችሁ ያነበባችሁት?” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡
ተሰበሳቢዎቹ በሙሉ እጃቸውን ያወጣሉ፡፡ ቄሱ ምን አሉ መሰላችሁ…
“ዛሬ ስለ እናንተ ነው ማውራት የፈለግሁት። የማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ አሥራ ሰባት የለውም።”
ውሸት ስንናገር በጥፊ የሚያጠናግር ሮቦት በየቦታው ይተከልልንማ!
እናላችሁ…ውሸትና እውነቱ እየተደበላለቀ ግራ ተጋብተናል፡፡ የምር እኮ የማይዋሽ ማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ነው…ወይስ የውሸት ትንታኔ ተለውጧል! የምር እኮ… እኛም ‘ውሸት’ በምንሰማበት ጊዜ ደማችን ‘አናታችን ላይ መውጣቱ’ ቀረ መሰለኝ፡፡
ስሙኝ የደምን አናት ላይ መውጣት ካነሳን አይቀር ይቺን ቀልድ ቢጤ ስሙኝማ…አንድ ሀኪም ታካሚውን “ጌታው ከፍተኛ የደም ግፊት አለብህ፡፡ ከቤተሰብ የወረስከው ነው?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
ታካሚውም… “ይመስለኛል…” ይላል፡፡ ዶክተሩም…
“ከአባትህ ወገን ነው ከእናትህ ወገን?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
ታካሚውም “ኧረ ከሚስቴ ቤተሰብ ወገን ነው!”  ይላል፡፡ ዶክተሩም ግራ ይገባውና…
“እንዴት ነው ከሚስትህ ቤተሰብ ወገን የደም ብዛት በሽታ የምትወርሰው?” ይለዋል፡፡ እሱዬው ምን ቢል ጥሩ ነው…
“ዶክተር፣ የሚስቴን ቤተሰቦች ስላላየኻቸው ነው እንዲሀ የምትለው፡፡”  አሪፍ አይደል፡፡ የምር ግን አማቶች ባይኖሩ ኖሮ ባልና ሚስት ማንን ‘ይረግሙ‘ ነበር!
እናላችሁ….እውነትና ውሸት እየተቀየጡ መለየት ቸግሮናል፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ነገሬ ብላችሁ እነኚህ ‘ታላላቅ’ የዜና ማሰራጫዎች የሚያሰሟቸውን ዜናዎች አዳምጡማ፡፡ ፈረንጆች… “በመስመሮች መሀል ማንበብ…” የሚሏት ነገር አለች አይደል… ‘በመስመሮች መሀል’ አዳምጡማ! በተመሳሳይ ዜና ላይ የተለያዩ ‘መረጃዎች’ ይሰጧችኋል፡፡ አለ አይደል… የዩክሬይኑን ተኩስ ማቆም ስምምነት ያፈረሰችውን የመጀመሪያ ጥይት የተኮሱት ወይ አማጺዎች ናቸው ወይ የመንግሥት ወታደሮች ናቸው፡፡
አንዱ “አማጺዎች” ሲል ሌላው “የመንግሥት ወታደሮች” ካለ…አለ አይደል…አንደኛቸው ‘ዋሽተዋል’ ማለት ነው፡፡ ለነገሩ ዘንድሮ ዜና ‘የሚዘገበው’ እንደ ሚዲያ ተቋማቱ ‘ፍላጎት’ ከሆነ ሰንብቷል፡፡
የምር ግን አሁን በእኛ ሚዲያዎች ላይ ‘እውነት’ና ‘ውሸት’ ይለይ ቢባል… ራሱን የቻለ ግብረ ኃይል ባያስፈልግ ነው! አሁን፣ አሁንማ ደረትን ነፍቶ ‘ውሸት’ መናገር የጥበብ ጉዳይ እንጂ የ‘አጉል ባህሪይ መለያ’ መሆኑ ቀርቷል፡፡
አንድ ጊዜ አንድ ሙዚቃ ዝግጅቶች ነገር የሚወድ ወዳጃችን ሲያጫውተን የሆነ ዝግጅት  ላይ ‘ሰርፕራይዝ’ እንግዳ ይኖራል ምናምን ተብሎ አይደለም ‘ሰርፕራይዝ’ እንግዳ በመደበኝነት ይመጣሉ የተባሉት እንኳን ሁሉም አልመጡም፡፡
እናላችሁ…በተለይ እንዲህ አይነት ነገሮች ላይ ችግሮች አሉ፡፡ ይመጣል የተባለው ‘ሰርፕራይዝ’ እንግዳ ስሙ ሲጠቀስ እኮ ራሱም ‘ሰርፕራይዝድ’ ሊሆን ይችላል! እናላችሁ…ውሸት በዝቷል፡፡
የ‘ሰርፕራይዝ’ ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…እሷዬዋ ባሏን ‘ሰርፕራይዝ’ ማድረግ ፈልጋለች፡፡ እናላችሁ… አንድ ቀን ማታ ከሥራ ሲመለስ በጣም ስስ የሆነ ፒጃማ ለብሳ ሶፋ ላይ ተቀምጣ ጠበቀችው፡፡ ነገርዬው ያልተለመደ ስለነበርም እሱዬውም…
“ዛሬ እንዴት ነው፣ ፏ ብለሻል!” ምናምን ብሎ ይቀላልዳል፡፡ እሷዬውም…
“ዛሬ ያዘጋጀሁልህን አታውቅም…” አለችው፡፡
“ምንድነው ያዘጋጅሽልኝ?” ይላታል፡፡ እሷም…
“መኝታ ቤት እንሂድና እጅና እግሬን ግጥም አድርገህ ከብረቱ ጋር አስረህ የፈለግኸውን ማድረግ ትችላለህ…” ትለዋለች፡፡
እንደተባለውም መኝታ ቤት ይሄዱና እጅና እግሯን ግጥም አድርጎ ያስራታል፡፡ ከዛላችሁ…እንግዲህ የፈለግኸውን አድርግ ብላው የለ… ቢራ አምሮት ኖሮ ወደ መጠጥ ቤት ሄዶላችሁ አረፈው፡፡
እንትናዬዎች… እንትናዎቻችሁን ‘ሰርፕራይዝ’ ለማድረግ ስትፈልጉ ከአልጋ ጋር መታሰር የሚለውን እንዳታስቡት፡፡
እግረ መንገዴን ይቺን ስሙኝማ…ሚስትየዋ ውሻዋ “ተቀመጭ…” ስትባል ቁጢጥ ብላ እንድትቀመጥ እያለማመደቻት ነው፡፡ ግን እንደፈለገችው ቶሎ ሊሰካላት አልቻለም፡፡ ይህን ያየው ባል ሆዬ ምን ይላታል…
“የእኔ ፍቅር፣ እንዲሳካልሽ ከፈለግሽ ተስፋ ሳትቆርጪ…” ሲል እሷ አቋርጣው ምን ብትለው ጥሩ ነው…
“ግዴለም አትንገረኝ.. እንኳን ቡቺን አንተም መጀመሪያ ላይ እንዲሁ ነበር ያስቸገርከኝ…” ብላ ከውሻ ጋር በአንድ ዓረፍተ ነገር ውስጥ ከትታው አረፈች!
እናላችሁ… ስለ ውሸት ስናወራ…አሁን አሁን ብዙ ማስታወቂያዎች ከ‘ማርኬቲንግ’ ዘዴነት ይልቅ…አለ አይደል… ወደ ‘ውሸትነት’ ይጠጋባችኋል፡፡  ምሽት አንድ ሰዓት ሳይሞላ ከሰለቸው ዘበኛው በስተቀር አንድም ሰው በማይገኝበት የህክምና ተቋም… ‘የሀያ አራት ሰዓት አገልግሎት’ አይነት ‘ፕሮሞሽን’ ብልጥነት ሳይሆን ‘ውሸት’ ነው፡፡
ውሸት ስንናገር በጥፊ የሚያጠናግር ሮቦት በየቦታው ይተከልልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3719 times