Saturday, 01 August 2015 14:35

ብር እና ብራና

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(15 votes)

 ሊቀ ጉባኤ ነሲቡ አያሌው ደጃፍ ላይ ቁጭ ብለው ይተክዛሉ፡፡ ከጎጇቸው ደብዳቤውን ለሶስተኛ ጊዜ አነበቡት፡፡ አንብበውት ሲጨርሱ፣ የእስቴን ተራሮች አሻግረው እያዩ በረጅሙ ተነፈሱ፡፡ ከተራሮቹ በስተጀርባ፣ ልጃቸው ምሳሌ ይታያቸዋል፡፡ እቅፍ አበባ ይዞ፣ እያሰቀለለ ሲጠብቃቸው ይታያቸዋል። ለክብር የታጨ ልጃቸው፣ የእሳቸውን መምጣት ናፍቆ፣ መንገድ መንገዱን ሲያይ በሩቁ ይታያቸዋል፡፡  
“የለም!... እንዲህ አጥብቆ እየለመነኝማ አልቀርም!...” አሉ ሊቀ ጉባኤ ነሲቡ፣ ለሶስተኛ ጊዜ ሃሳባቸውን እየቀየሩ፡፡
ሊቀሩ አስበው ነበር፡፡ ነገሩን በጥሞና ሲያሰላስሉት ግን፣ መቅረት እንደሌለባቸው ገባቸው። ይሄን ደብዳቤ አንብቦ ለመቅረት መወሰን፣ ከአንድ ልጃቸው ጋር ለመቆራረጥ መወሰን ነው፡፡ የአብራካቸውን ክፋይ ምሳሌን ማሳዘን ነው፡፡ ምሳሌ የእሳቸውን መምጣት አጥብቆ እንደሚፈልገው ነው፣ ደብዳቤው በግልጽ የሚነግራቸው፡፡ ካልመጡ እንደሚያዝንባቸው ነው፣ እያረጋገጠላቸው ያለው፡፡
“አደራህን አብዬ!... ትቀርና አዝኘብህም አላባራ!...” ብሏቸዋል ምሳሌ፡፡
እንዲህ እያላቸው መቅረት የለባቸውም፡፡ እንደምንም ብለው ደርሰው መምጣት አለባቸው። ደግሞም ከመሄድ የሚከለክላቸው፣ ያን ያህል አንገብጋቢ ጉዳይ የለባቸውም፡፡ ወቅቱ ክረምት ነው፡፡ ስራ አይበዛባቸውም፡፡ ሰኔ ግም ሲል አንስቶ፣ መስከረም እስኪጠባ ድረስ ከብራና ስራ አረፍ ብለው ነው የሚከርሙት፡፡ የሚያርፉት ግን እረፍት ፈልገው አይደለም፤ የክረምት ጸሃይ ለብራና ስራ የዘፈዘፉትን እርጥብ ቆዳን ቶሎ የማድረቅ አቅም ስለሌላት እንጂ። ይሄን ደግሞ ምሳሌም ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ስራውን ለማን ትቼው ልምጣ ብዬ ነው የሚል ሰበብ ቢያቀርቡለት፣ በጄ ብሎ አይቀበላቸውም፡፡ ስለዚህ ማመንታታቸውን ትተው መሄድ ይኖርባቸዋል፡፡ ለአንድ አዳርም ቢሆን ከተማ ዘልቀው፣ የልጃቸውን ደስታ መካፈል ይገባቸዋል፡፡
ጥንታዊ ፅሁፎችንና ሃይማኖታዊ መረጃዎችን በብራና እየደጐሱ ጠርዘው ማስቀመጥ ከጀመሩ፣ ረጅም አመታት አልፈዋል፡፡ የፍየል ሌጦ ፍቀውና አለስልሰው፣ አስራ ሶስት ዳጐስ ያሉ የብራና መፅሐፍትን አበጅተዋል፡፡ በዚህ በጐ ስራቸውም ሲደነቁና ሲሞገሱ ነበር፡፡ ዝናቸው ከቀበሌው አልፎ እስከ ወረዳ ናኝቷል፡፡ የብራናው ጠቢብ ሊቀ ጉባኤ ነሲቡ አያሌው የበቁ ጥበበኛ ስለመሆናቸው ቀበሌው ይቅርና ወረዳውም ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ይህን ጥበብ ለልጃቸው ሊያወርሱት ብዙ ደክመዋል፡፡
ደብዳቤዋን እያጣጠፉ ልጃቸውን አሰቡት። አንድ ልጃቸውን ምሳሌን ከወግ ለማድረስ ብዙ ደክመዋል። የስማቸው መጠሪያ ሊያደርጉት፣ የቻሉትን ያህል ታትረዋል፡፡ ሃብት ንብረታቸውን ብቻ ሳይሆን፣ ታላቅ ሙያቸውን ጭምር ሊያወርሱት አስበው ነበር። ከአያታቸው ከመሪጌታ ልዑለ-ቃል የወረሱትን ክቡር ሙያ፣ ይዘውት መቀበር አልፈለጉም፡፡ በእጃቸው ላይ ያለውን ጥበብ፣ ለብቸኛ ልጃቸው ለምሳሌ ሊያወርሱት ሞክረዋል። ገና ልጅ ሳለ ጀምሮ ነው ለጥበብ ውርስ ያጩት፡፡ በለጋነቱ ነው ለውርስ ሊያዘጋጁት የሞከሩት፡፡
በግም ሆነ ፍየል ሲያርዱ፣ እሱን ይዘው ነበር። የታረደውን እንስሳ እግር ወጥሮ እንዲይዝላቸው ያደርጉና፣ እሳቸው ቆዳ ገፈፋቸውን ይጀምራሉ። ቆዳውን እየገፈፉ፣ ደደቡን እየቀፈፉ ጥበብ ያስተምሩታል፡፡ የገፈፉትን ቆዳ በመወጠሪያ እንጨታቸው ላይ ሲቃቁም፣ አጠገባቸው ሆኖ ጅማት ያቀብላቸው ነበር፡፡ ቆዳው ላይ የቀረውን ስጋ ያስፍቁት፣ ጸጉሩንም በመጥረቢያ ያስላጩት ነበር፡፡ የብራናን ጥበብ ያስተምሩት ነበር፡፡
“ልብ ብለህ እይ!...” ይሉት ነበር፣ የደረቀውን ቆዳ በወስፌ እየበሱ ውግ ሲያበጁ፡፡
“እሺ!...” ይላቸው ነበር በግማሽ ልብ ሆኖ፡፡
“እየውልህ... እነዚህ ምልክቶች ከአርዕስቱ እስከ ኅዳጉ ያሉት መስመሮች ጠባብና ሠፊ እንዳይሆኑ የሚረዱ ናቸው፡፡ ታዲያ ውጉ መስመሩን መጠበቅ አለበት!... መዛነፍ የለበትም!... ልክ እንደዚህ... አየኸው አይደል?...ጥሩ ቁም ፀሐፊ መስመሩን በሚገባ ጠብቆ መጻፍ አለበት፤ አለበለዚያ ይወቀስበታል... ገባህ አይደል ምስዬ?...” ቀና ብለው ሳያዩት ይጠይቁታል፡፡
“አዎ!...” በርቀት ወደሚጫወቱት ጓደኞቹ እያየ ይመልስላቸዋል፡፡
“እንግዲህ እኔም እየደከምኩ ነው... ነገ ከነገ ወዲያ አንተ ነህ ብራና እምታዘጋጀው!... ስለዚህ ልብ ብለህ ተስተማር!...” ይሉታል፡፡
ይህ የዘለለት አደራቸው፣ የሰርክ ምክራቸው ነበር፡፡
ማፈፊያቸው ወድቆ እንዳይቀር፣ መረመሚያ ድንጋያቸው ከንቱ እንዳይሆን በማሰብ ነበር፣ ልጃቸውን ሙያ ለማስተማር የተጉት፡፡ ያም ሆኖ ግን፣ ልፋት ድካማቸው ፍሬ አላፈራም፡፡ ያሰቡት አልሆነላቸውም፡፡ ከአያታቸው የወረሱትን የቁም ጽሕፈት ሙያ ሊያወርሱት ያጩት ልጃቸው፣ እያደገ ሲመጣ ሙያውን ማናናቅ አመጣ፡፡ በክብር ያወረሱትን የሸምበቆ መቃ ወርውሮ፣ የኬንያ ቢክ አነሳ፡፡
“ተምሬ ዶክተር መሆን ነው የምፈልገው!...” በማለት እቅጩን ነገራቸው፡፡
ሊቀ ጉባኤ ነሲቡ አያሌው ከማዘን ውጪ ምንም ማድረግ አልቻሉም፡፡ ያዘኑት በልጃቸው በምሳሌ አልነበረም፤ በዘመኑ እንጂ፡፡ ልባም ልጅ የጠፋበት፣ ለጥንታዊ ጥበብ ዋጋ የማይሰጥበት የጉድ ዘመን ላይ እንደደረሱ ተሰምቷቸዋል፡፡ እንደሳቸው ብራና ዳምጠው፤ ቀለም በጥብጠው፣ መቃ ቀርጸው ታሪክን በብራና እየደጎሱ እዚህ ያደረሱ ሊቃውንት፣ ሙያቸውን የሚያወርሱት ልባም ልጅ ያጡበት ክፉ ዘመን እንደመጣ ገብቷቸዋል፡፡ አዘኑ እንጂ አስገድደው ሙያ ሊያስተምሩት አልሞከሩም፡፡ ተምሮ ሰው ከሆነም አንድ ነገር ነው ብለው ተውት፡፡ ዋናው ለወግ ማዕረግ መብቃቱ ነው በሚል ተጽናኑ።
ትምህርቱን ሲጨርስ ግን፣ መልሰው አዘኑ። ምሳሌ እንደጓደኞቹ ለዩኒቨርሲቲ የሚያበቃውን ውጤት አላመጣም፡፡ እንዳሰቡት ለወግ ማዕረግ አልበቃም፡፡ ያን ያህል ዘመን ተምሮ፣ አጉል ሆኖ መቅረቱ ሲበዛ አሳዘናቸው፡፡ በወጡ በገቡ ቁጥር፣ እያዩት መብሰልሰል ሆነ ስራቸው፡፡ በዚህ መልኩ አመታትን ገፉ፡፡
ታች አምና ጥር ላይ...
“አብዬ!... ልሄድ ነው!...” አላቸው አንድ ማለዳ፡፡
“ኸት ነው ምትኸድ?...” ደንግጠው ጠየቁት፡፡
“ከተማ...” ፈራ ተባ እያለ መለሰላቸው፡፡
“ምን ታረግ?...” ግራ ተጋብተዋል፡፡
“ልደራጅ!...” ለስለስ ብሎ ነገራቸው፡፡
ልጃቸው ምን እያላቸው እንደሆነ ሊገባቸው አልቻለም፡፡ ለቀናት ከዘለቀ ማብራሪያው፣ ከጽኑ ተቃውሟቸው፣ ከሳምንታት ኩርፊያው፣ ከወራት ማመንታታቸው... ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው፣ እንዳፈቀደህ ሁን ብለው የፈቀዱለት፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ የመደራጀት ሃሳቡን የተቀበሉት፣ እሱ እንዳለው ለትልቅ ነገር ይበቃል ብለው ስላሰቡ አልነበረም። በስተርጅና ትቷቸው ወደ ከተማ እንዲያቀና የፈቀዱለት፣ የእሱ ንዝንዝ ከዘመድ አዝማድ ወቀሳ ጋር ተደማምሮ ስላማረራቸው ብቻ ነበር፡፡  
ምሳሌ ከተማ ገባ፡፡ ከተማ ገብቶ ተደራጀ፡፡ ተደራጅቶ ውጤታማ ሆነ፡፡ በሞዴልነት ተመርጦ፣ ለሽልማት ታጨ፡፡
“ትዝ ይልሃል አብዬ?... ʻአደራህን ጎብዝልኝ ልጀ፤ ለወግ ማረግ በቅተህ ሳላይህ ሞት እንዳይቀድመኝʼ እያልህ ትመክረኝም አልነበር?... ይሄውልህ እኔ ልጅህ ሞትን ቀደምኩት!... ለወግ መብቃቴን ባይንህ ልታይ ነው!... በዞን ደረጃ ተመርጬ ልሸለም ነው!... ሽልማቱ የሐምሌ አቦ ዕለት ነውና፣ መጥተህ ተጎኔ እንድትቆም... አደራ አብዬ!...” አላቸው ደብዳቤ ልኮ።
ሊቀ ጉባኤ ነሲቡ አያሌው ደብዳቤዋን እያጣጠፉ ወሰኑ፡፡
“የለም!... እንዲህ እያለኝማ አልቀርም!...” አሉ ለራሳቸው፡፡
አልቀሩም፡፡ ከእስቴ ተነስተው ልጃቸው ወደሚሸለምባት ከተማ ዘለቁ፡፡ አዳራሹ ውስጥ ተቀምጠው፣ በደስታ ተፍለቀለቁ፡፡ በደቡብ ጎንደር ዞን የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትና ለሞዴል ስራ ፈጣሪ ወጣቶች በተዘጋጀው የሽልማት ስነስርዓት ላይ ታደሙ፡፡ እድሜ ለልጃቸው ከፍ ያለ ቦታ ተሰጣቸው፡፡ ከተርታው ታዳሚ በፊት፣ ከዞኑ ባለስልጣናት በኋላ ባለው ረድፍ ላይ ተቀምጠው፣ በኩራት ደረታቸውን ነፉ፡፡
ወትሮም አገር ያወቃቸው ጸሃይ የሞቃቸው ባለግርማ ሊቅ ነበሩ፣ ዛሬ ደግሞ የበለጠ ሞገስ ደረቡ። እኒህ አረፋ የመሰለ ጥምጣም አድርገው አዳራሹን በብርሃን ያጥለቀለቁት ሰው፤ የእስቴው ጸሃይ ሊቀ ጉባኤ ነሲቡ አያሌው ናቸው፡፡ እሳቸው ከንባብ እስከ ጾመ ድጓ፣ ከምዕራፍ እስከ ድጓ ጠንቅቀው የተማሩት፣ ቅኔና አቋቋምን፣ መዋሥዕትና ዝማሬን በወጉ የዘለቁት ስመጥሩ ሊቀ ጉባኤ ነሲቡ አያሌው ሊቅ ናቸው፡፡ ከአያት ቅድመ አያቶቻቸው የወረሱትን የብራና ጥበብ በወጉ እየከወኑ ለዘመናት የዘለቁት ታላቅ ባለሙያ፣ ዛሬ ደግሞ በልጃቸው በምሳሌ ሌላ የክብር ካባ ደርበው በኩራት ህዝቡ መሃል ተጎልለዋል፡፡
ከፊታቸው የተደረደሩትን የዞኑ ባለስልጣናት፣ አትኩረው አንድ በአንድ ያያሉ ሊቀ ጉባኤ ነሲቡ። ከመካከላቸው የሚያውቁትና የሚያውቃቸው፣ ቢያንስ አንድ እንኳን ባለስልጣን እንደማይጠፋ እርግጠኛ ናቸው፡፡ ከአምስት አመታት በፊት፣ በእስቴ ወረዳ የባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት አዘጋጅነት፣ የቅርስ ጥበቃ ኤግዚቢሽንና አውደ ጥናት ተካሂዶ ነበር። እሳቸውም የዝግጅቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ በክብር ተጋብዘው ነበር፡፡ የአመታት ልፋት ድካማቸው ውጤት የሆኑ፣ እያንዳንዳቸው ከ150 በላይ ገፆች ያሏቸውን 13 ያህል የብራና መፅሃፍቶቻቸውን ለእይታ አቅርበው ነበር፡፡ ስለብራና ታሪካዊ አመጣጥ፣ ስለብራና አዘገጃጀት፣ ስለብራና ጥበብ ወዘተ ለጎብኝዎች ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተው ነበር፡፡
በወቅቱ ከዞኑ ተወክለው በስነስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙ አንድ ባለስልጣንም፣ እጃቸውን ጨብጠው አድናቆታቸውን ሰጥተዋቸው ነበር፡፡ የብራና ጥበብን በዞን ደረጃ ለማስፋፋትና ሙያው ለትውልድ እንዲተላለፍ ለማስቻል በሚደረገው ጥረት፣ ሊቀ ጉባኤ ነሲቡም ትልቅ ሚና መጫወት እንደሚችሉ ነግረዋቸው ነበር፡፡ ሚናቸውን በአግባቡ መጫወት እንዲችሉ፣ ከሚመለከተው የመንግስት አካል ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አረጋግጠውላቸው ነበር - ከዚያ በኋላ ዘወር ብለው ባያዩዋቸውም፡፡
ሊቀ ጉባኤ ነሲቡ ያንን አጋጣሚ አስታውሰው ነው ፍለጋ የጀመሩት፡፡ እኒያ እጃቸውን ጨብጠው ያደነቋቸው ባለስልጣን፣ ከፊታቸው ከተደረደሩት ባለስልጣናት አንዱ ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠርጥረዋል። ለዚህ ነው ጀርባቸውን ሰጥተዋቸው ከፊታቸው የተደረደሩትን ባለስልጣናት በአትኩሮት የሚቃኙት። አንገታቸውን አርዝመው ባለስልጣኑን ፈለጓቸው፡፡ ለነገሩ አምስት አመት ረጅም ነው፣ ሲሉ አሰቡ ሊቀ ጉባኤ ነሲቡ፡፡ የዛሬ ጊዜ መልክ፣ አምስት አመት አይቆይም፡፡ ሰውዬው ተለውጠው ሊሆን ይችላል፡፡ አይተው ላይለዩዋቸው ይችላሉ። ምን ይሄ ብቻ... የዛሬ ጊዜ ስልጣን፣ ይሄን ያህል ጊዜ ወንበር ላይ አያስቀምጥም፡፡ ከዚያ ጊዜ ወዲህ በእነሱ ቀበሌ ገበሬ ማህበር እንኳን፣ ስንቱ ተሹሞ ስንቱ ተሽሯል። ሰውየውም ተሽረው ይሆናል፡፡ ይሄን ሲያስቡ ነው ሊቀ ጉባኤ፣ ባለስልጣኑን ትተው ተሸላሚ ልጃቸውን ምሳሌን መፈለግ የጀመሩት፡፡
“ክቡራንና ክቡራት እንግዶቻችን!... በደቡብ ጎንደር ዞን፣ በቆዳና የቆዳ ውጤቶች ዘርፍ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ሞዴል የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትና አንቀሳቃሾች ሽልማት የሚሰጥበት ሰዓት ላይ ደርሰናል!... ተሸላሚዎችና የተሸላሚ ቤተሰቦች፣ በድጋሚ እንኳን ደስ አላችሁ!...” የሚል አስገምጋሚ ንግግር ከድምጽ ማጉያው ተሰማ፡፡
ይህን ተከትሎ አዳራሹ ተናጠ፡፡ ጣራ እሚነቅል ፉጨት፣ እልልታና ጭብጨባ ተዋህዶ አዳራሹን አናወጠው፡፡ ሊቀ ጉባኤ ነሲቡ የልብ ምታቸው ጨመረ፡፡ በደስታ ሰክረው፣ በጉጉት እንደተዋጡ ወደ መድረኩ አንጋጠጡ፡፡ ልጃቸው ወደ ክብር የሚጠራባት፣ ስማቸውን የሚያስጠራባት፣ ለዘመናት የናፈቋት፣ ለአመታት የጠበቋት ያቺ ልዩ ቅጽበት ደረሰች!...
“እንግዶቻችን አንዴ ጸጥታ!... የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ዘርፍ ተሸላሚዎችን ከመጥራታችን በፊት፤ በዘርፉ የተመዘገቡ ውጤቶችን፣ አበረታች ውጤቶችን፣ ያጋጠሙ ችግሮችንና መወሰድ የሚገባቸውን እርምጃዎችና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በተመለከተ አጭር ገለጻ ይደረጋል። ይህን ገለጻ የሚያደርጉልን የዞኑ የጥቃቅንና አነስተኛ...” የዝግጅቱ መሪ በአስገምጋሚ ድምጹ የጀመረውን ንግግር ጨርሰው የሚሰሙበት ትዕግስት አልነበራቸውም - ሊቀ ጉባኤ ነሲቡ፡፡
“ምን ያለው ነው አያ!... ወሬው ተሸለሟቸው በኋላ አይደርስም ነበር!?...” እየተነጫነጩ ተናገሩ፡፡
አጭር ገለጻ ሊያደርጉ የተጋበዙት ሰው፣ መድረኩን ለመልቀቅ የፈለጉ አይመስሉም፡፡
“እኔን አጭር ያርገኝ!... ፍሬ ፍሬውን ተናግሮ እንደመውረድ፣ ወግን እንደ መጫኛ ማስረዘም ሙያ መሰላቸው እንዴ?...” በንዴት ጦፈው ለራሳቸው ሲያወሩ፣ ከጎናቸው ከተቀመጡ ባለ ከረባት ሰው ጋር ተያዩ፡፡
ሊቀ ጉባኤ ነሲቡ የሰውዬውን ከረባት ሲያዩ ደንገጥ አሉ፡፡ የወንበር እጥረት ወደዚህኛው መደዳ ያሻገራቸው፣ ትራፊ ባለስልጣን ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠርጥረዋል፡፡ በባለስልጣኑ ፊት አጉል ነገር መናገር፣ አጉል ነገር ሊያስከትል ይችላል ሲሉ ሰጉ፡፡ ከመድረኩ የሚሰማውን ረጅም መግለጫ በመጫኛ መመሰላቸው፣ መዘዘዝ ሊያመጣ እንደሚችል አሰቡ።  ይሄም ሆኖ ግን፣ ስጋታቸውን ማሳወቅ አልፈለጉም። በሆነ ባልሆነው አቂያቂር የሚያወጣ፣ መንገደኛ ታዳሚ እንዳልሆኑ ማሳየት ፈልገዋል - የተሸላሚ አባት መሆናቸውን እንደዋዛ ማሳወቅ፡፡
“ምን ማለታቸው ነው!?... ልጆቻችንን ለማሸለም ጓጉተን፣ ያን ያህል አገር አቋርጠን ለመጣን አባቶች እንኳን አያስቡም?...” አሉ ሊቀ ጉባኤ ነሲቡ ለስለስ ብለው፣ ለባለከረባቱ በሚሰማ ድምጽ፡፡
ባለከረባቱ ከመድረኩ የሚሰጠውን ገለጻ በጥሞና እየተከታተሉ ስለነበር አልሰሟቸውም፡፡
ሊቀ ጉባኤ ፊታቸውንም ጆሯቸውንም ወደ መድረኩ መለሱ፡፡ መድረኩ ላይ የቆሙት ሰው፣ አሁንም እያወሩ ነው፡፡ ሊቀ ጉባኤ ሰውዬውን ሲያዩ ደንገጥ አሉ፡፡ አይናቸውን አሻሹና ደግመው ሰውዬውን አዩዋቸው፡፡ ለማመን አልቻሉም። እሳቸው ናቸው፡፡ ከአምስት አመታት በፊት፣ በእስቴ ወረዳ የባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት አዘጋጅነት፣ በተከናወነው የቅርስ ጥበቃ ኤግዚቢሽንና አውደ ጥናት ላይ ከዞኑ ተወክለው በክብር እንግድነት የተሳተፉት ባለስልጣን ናቸው፡፡
ሊቀ ጉባኤ ሰውዬውን ደግመው አዩዋቸው። እሳቸው ናቸው!... እጃቸውን ጨብጠው አድናቆታቸውን የሰጧቸው፤ የብራና ጥበብን በዞን ደረጃ ለማስፋፋትና ሙያው ለትውልድ እንዲተላለፍ ለማስቻል በሚደረገው ጥረት፣ ትልቅ ሚና መጫወት እንደሚችሉ የነገሯቸው፤ ከሚመለከተው የመንግስት አካል ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ቃል የገቡላቸው፤ ቃል ገብተውላቸው ሲያበቁ የት እንደገቡ ያላወቋቸው ባለስልጣን ናቸው ገለጻ እያደረጉ ያሉት፡፡
“በቆዳና የቆዳ ውጤቶችን ዘርፍ ላይ ከሚታዩት ችግሮች ሌላው፣ በዞኑ የሚታየው የቆዳ ብክነት ነው። እውነቴን ነው የምላችሁ፣ በዞናችን ከፍተኛ ቁጥር ያለው የተለያዩ እንስሳት ቆዳ ያለ አግባብ እየባከነ ነው ያለው፡፡ እዚህ ላይ አንድ ተሞክሮዬን ማንሳት እችላለሁ...” አሉና በግርምት ተውጠው ታዳሚውን ተመለከቱ፡፡
ሊቀ ጉባኤ ነሲቡ መመምጣታቸው ተደሰቱ፡፡ እንኳንም አመንትተው አልቀሩ፡፡ ቢቀሩ ኖሮ ልጃቸው ምሳሌ በክብር ሲሸለም አያዩም ነበር፡፡ ቢቀሩ ኖሮ እኒህን መድረኩ ላይ ቆመው ንግግር የሚያደርጉትን ባለስልጣን ዳግም አያገኟቸውም ነበር፡፡ እንኳንም መጡ፡፡ ባለስልጣኑ ንግግራቸውን ከጨረሱ በኋላ፣ ተከታትለው ያገኟቸዋል፡፡ የገቡላቸውን ቃል ያስታውሷቸዋል፡፡ የብራና ጥበባቸው ያለ ወራሽ ሊቀር አፋፍ ላይ መድረሱን ይነግሯቸዋል። በእስቴ ወረዳ ያለው የብራና ጥበብ ዕየተዳከመ መምጣቱን፣ በብዙ ልፋትና ድካም የተዘጋጁ በርካታ የብራና መጻሕፍት የተለያዩ ጉዳትና ጥፋት እየደረሰባቸው አንዲሚገኙ ያስረዷቸዋል፡፡ የእሳት ቃጠሎ፣ ለብዙ ጊዜ ለአገልግሎት ማዋል፣ እርጥበት ቦታ ማስቀመጥ፣ ሕገወጥ ዝውውር፣ የአቀማመጥ ችግር፣ የተለያዩ ነፍሳት፣ ብልና አይጥ የመሳሰሉት አደጋዎች የብራና መጻሕፍቱን እያጠፏቸው እንደሚገኙ ያረጋግጡላቸዋል፡፡ ከዚያ በጋራ መፍትሄ ይፈልጋሉ።
ሊቀ ጉባኤ በጣም ደስ አላቸው፡፡ ደስ እያላቸው የባለስልጣኑን ከመድረክ መውረድ በጉጉት ተጠባበቁ።
“ምን ሆነ መሰላችሁ... ከአምስት ወይም ከስድስት አመታት በፊት ይመስለኛል... ለስራ ጉዳይ ወደ እስቴ ወረዳ ሄጄ ነበር...” ባለስልጣኑ ተሞክሯቸውን ማጋራት ቀጠሉ፡፡
“ልክ ነው!...” አሉ ሊቀ ጉባኤ ነሲቡ ድንገት አምልጧቸው፡፡
ባለስልጣኑ የቃለ ጉባኤ ነሲቡን እማኝነት አልሰሙም፡፡ ወደ እስቴ ወረዳ ለስራ ጉዳይ በሄዱበት ወቅት ያጋጠማቸውን ነገር መተረክ ያዙ፡፡
“በወቅቱ አንድ የብራና ባለሙያ ጋር የመገናኘት አጋጣሚ ነበረኝ...” ብለው አጋጣሚያቸውን ማጋራት ቀጠሉ፡፡
“እኔ ነኝ!... ሊቀ ጉባኤ ነሲቡ አያሌው ነኝ!... እንዲያውም ጨብጠው አድንቀውኛል!...” በደስታ ጮህ ብለው ተናገሩ፡፡
በዙሪያቸው የተቀመጡ ሰዎች በሊቀ ጉባኤ ንግግር ተገርመው ማጉረምረም ጀመሩ፡፡
“እባካችሁ ጸጥታ!... እና ምንድነው...” ባለስልጣኑ ማስጠንቀቂያ ቢጤ ሰጥተው ንግግራቸውን ቀጠሉ።
እዚህ ላይ ነው፣ ሊቀ ጉባኤ ነሲቡ አያሌው በተቀመጡበት ው ሆነው የቀሩት፡፡
“ግለሰቡ ከ13 በላይ የብራና መፅሐፍትን ለማዘጋጀት ምን ያህል የፍየል ቆዳ እንሌጦ እንደፈጀባቸው ብነግራችሁ ለማመን ትቸገራላችሁ!... አስቡት እንግዲህ!... ያን ያህል የፍየል ሌጦ ለማይረባ ብራና ከሚውል ይልቅ፣ በአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ተደራጅተው፣ በቆዳና የቆዳ ውጤቶች ምርት ላይ ለሚሰሩ ወጣቶች በጥሬ እቃነት ቢቀርብ የሚኖረው ጠቀሜታ ምን ያህል ነበር?... እውነቴን ነው የምላችሁ... ይህ ሪሶርስን የሚያባክን ድርጊት ነው!...
“ወረዳው፣ ዞኑ፣ ክልሉ ብሎም አገሪቱ በቆዳና በቆዳ ውጤቶች ዘርፍ ሊያገኙት ይችሉ የነበሩትን ትልቅ ጥቅም ነው፣ መሰል የብራና ባለሙያዎች የሚያስቀሩት!... ባለፉት አስራ አምስት አመታት ብቻ፣ በዞናችን በርካታ ቁጥር ያለው ቆዳ ለብራና ዝግጅት ባክኗል!... በዚህም ዞኑ በቆዳና የቆዳ ውጤቶች ኤክስፖርት ሊያገኘው ይችል የነበረውን፣ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ አጥቷል!... የዞኑ የብራና ባለሙያዎች፣ እንደ አገር ከዘርፉ ሊኖረን የሚገባውን የተሻለ ተጠቃሚነት ነው እያሳጡን ያሉት!... በመሆኑም ዘርፉን ለማሳደግ በምናደርገው ጥረት፣ የብራና ባለሙያዎችን ከዚህ ቆዳን የማባከን ህገወጥ ተግባራቸው የመግታት ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል እላለሁ!... ጊዜያችሁን መሻማት አልፈልግም... በቀጥታ ወደ ሽልማት ስነስርዓቱ እንገባለን!... አመሰግናለሁ!...” ብለው ጨረሱ፡፡
ሰውዬው በደማቅ ጭብጨባ ታጅበው መውረዳቸውን አላዩም፣ አልሰሙም - ጉልበታቸው ላይ ተደፍተው ስቅስቅ ብለው የሚያለቅሱት ሊቀ ጉባኤ ነሲቡ፡፡
(በቅርቡ ለንባብ ከበቃው
“ባቡሩ ሲመጣ...” የተሰኘ መፀሃፍ የተወሰደ)

Read 4484 times