Saturday, 01 August 2015 14:49

አሜሪካ ለዜጎቿ የሽብር ጥቃት ማስጠንቀቂያ ሰጠች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 አሜሪካ በመላው አለም የሚገኙ ዜጎቿ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ አይሲስን የመሳሰሉ አሸባሪ ቡድኖች ከሚሰነዝሯቸው የሽብር ጥቃቶች ራሳቸውን እንዲጠብቁ ማስጠንቀቋን ዘ ሂንዱ ታይምስ ዘገበ፡፡
አሜሪካ በኢራቅ በሚገኘው አይሲስ ላይ ጥቃት መሰንዘሯን ተከትሎ፣ ቡድኑ የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጥ ማሳወቁን ያስታወሰው ዘገባው፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ቡድኑ በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮፓና በእስያ አገራት በሚኖሩ አሜሪካውያንም ሆነ በምዕራባውያን አገራት ዜጎች ላይ የሽብር ጥቃት ሊሰነዝር ስለሚችል ተገቢው ጥንቃቄ እንዲደረግ ማሳሰቡን ጠቁሟል፡፡
ከአይሲስ በተጨማሪ በህንድ የሚንቀሳቀሱት ሌቲን የመሳሰሉ የሽብር ቡድኖች ከሰሞኑ በአገሪቱ ጥቃት ሊሰነዝሩ ይችላሉ ያለው የአሜሪካ መንግስት ማስጠንቀቂያ፣ በህንድ የሚኖሩ አሜሪካውያንም ራሳቸውን ከጥቃት እንዲጠብቁ አሳስቧል፡፡
በምዕራባውያን አገራት ላይ የከፋ ጥላቻ ያላቸው ሃረካት ኡል ጂሃዲ ኢስላሚ እና ሃረካት ኡል ሙጅሃዲንን የመሳሰሉ እስላማዊ አክራሪ ቡድኖች በህንድ በስፋት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ጠቁሞም፣ቡድኖቹ ከዚህ ቀደምም በምዕራባውያን አገራት ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ የሽብር ጥቃቶችን ሲፈጽሙና በርካቶችን ለህልፈተ ህይወት ሲዳርጉ እንደነበር አስታውሷል፡፡
አሸባሪ ቡድኖች በደቡብ እስያ አገራት የሽብር ጥቃት ሊፈጽሙ እንደሚችሉ የሚያመለክቱ መረጃዎች ደርሰውኛል ያለው የአሜሪካ መንግስት፣ ጥቃቶቹ በአሜሪካውያንና በተቋማቷ ላይ ያነጣጠሩ ሊሆኑ እንደሚችሉም ጠቁሟል፡፡

Read 1899 times