Saturday, 08 August 2015 08:49

“የሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ” አባላት ይግባኝ ሊጠይቁ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

       በአሸባሪነት ከ7 አመት እስከ 22 አመት የሚደርስ ፅኑ እስራት የተፈረደባቸው “የሙስሊሙ መፍትሔ
አፈላላጊ ኮሚቴ” አባላት፣ የተላለፈባቸውን ፍርድ በመቃወም ለጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ እንደሚጠይቁ ጠበቆቻቸው ገለፁ፡፡ ጉዳዩን ላለፉት ሶስት አመታት ገደማ ሲመረምር የቆየው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት፤ በተከሳሾቹ ላይ የእስራት ውሣኔ ያሳለፈው ባለፈው ሰኞ ሐምሌ 27 ነበር፡፡
ፍ/ቤቱ አቡበከር አህመድ፣ አህመዲን ጀበል፣ ያሲን ኑሩና ካሚል ሸምሱ በ22 ዓመት ፅኑ እስራ እንዲቀጡ ሲወስን፤ በድሩ ሁሴን፣ ሳቢር ይርጉ፣ መሃመድ አባተ፣ አቡበከር አለሙና ሙኒር ሁሴን በ18 ዓመት እንዲሁም ሼህ መከተ ሙሔ፣ አህመድ ሙስጠፋ፣ ሼህ ሰኢድ አሊ፣ ሙባረክ አደምና ካሊድ ኢብራሂም እያንዳንዳቸው በ15 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል፡፡ ሙራድ ሽኩር፣ ኑሩ ቱርኪ፣ ሼህ ባህሩ ኡመርና ጋዜጠኛ የሱፍ ጌታቸው ደግሞ የሰባት ዓመት እስር እንደተላለፈባቸው
ይታወሳል፡፡ የተከሳሾቹ ጠበቆች በበኩላቸው፤ ውሳኔውን በመቃወም ለጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ እንደሚጠይቁ ጠቁመው የፍርድ ውሳኔው በሰነድ ተገልብጦ እስኪሰጣቸው እየጠበቁ መሆኑን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ ከጠበቆቹ አንዱ የሆኑት አቶ መሃመድ አብደላ፤ “ከተከሳሾቹ ጋር በመነጋገር ለጠቅላይ
ፍ/ቤት ይግባኝ በማለት ወስነናል” ብለዋል፡፡ ከ3 ዓመታት በፊት የአውሊያ ኢስላማዊ ት/ቤት ተማሪዎች “መንግስት በሙስሊሙ ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን ያቁም፣ ገለልተኛ መጅሊስ ይቋቋም፣ የአህበሽ አስተምህሮ በግድ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ አይጫን” በሚል ካነሷቸው ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ፣ መንግሥት 31 ግለሰቦችን በአሸባሪነት ጠርጥሮ ፍ/ቤት ማቅረቡ የሚታወስ ሲሆን 13 ያህሉ በመሃል በነፃ ተሰናብተው፣ በ18 ተከሳሾች ላይ ጉዳዩን ሲመረምር የከረመው ፍ/ቤት፤ ባለፈው ሰኞ ከ7-22 ዓመት ፅኑ እስር እንደወሰነባቸው ይታወቃል፡፡

Read 2334 times