Saturday, 08 August 2015 08:50

ቪሲዲና ዲቪዲ ኮፒ እንዳይዳረጉ የሚከላከል ዘዴ ተገኘ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(10 votes)

     አያሌ አርቲስቶች ለረዥም ጊዜ የጮሁበትና በሠላማዊ ሰልፍ የተቃወሙትን ህገ ወጥ የኮፒ ራይት ጥሰት የሚያስቀር ዘዴ መፈጠሩን የኮምፒዩተር ባለሙያው ልዑልሰገድ ደጉ ለአዲስ አድማስ ገለፀ፡፡በሲዲ ቴክኖሎጂ ማባዛትና ኤዲቲንግ እንዲሁም የውጭ ፊልሞችን በማባዛትና በማከፋፈል ሥራ ላይ የተሰማራው ልዑልሰገድ፣ ሲዲዎች ኮፒ እንዳይደረጉ፣ ፊልሞችና ዘፈኖች ወደ ፍላሽ  ሜሞሪና አይፓድ እንዲሁም ወደተለያዩ ስልኮች እንዳይገለበጡ የሚከላከል ዘዴ መስራቱን ተናግሯል፡፡ በሲዲ ላይ ያለ ነገር ኮፒ እንዳይደረግ የሚከላከሉ 5 ዓይነት ዘዴዎች መሥራቱን የጠቀሰው ባለሙያው፤ ማንኛውም ሰው ቪሲዲዎችና ዲቪዲዎችን ማጫወት እንጂ ማባዛትም ሆነ ፋይሎችን መስረቅ፣ ኮምፒዩተር ላይ አስቀምጦ ኮፒ ፔስት፣ ዘፈኖችን ወስዶ ሌላ ኮምፒዩተር ላይ ማድረግ እንደማይችል ተናግሯል።
አዲሱ ዘዴ አርቲስቶች የአዕምሮ ሃብታቸውን ከመዘረፍ እንደሚታደጋቸው ጠቁሞ ከአሁን በኋላ አርቲስቶች ከእሱ ጋር በመመካከርና ማስተራቸውን በማስቀረፅ የኮፒ ራይት ጥሰትን መከላከል እንደሚችሉ አስታውቋል፡፡ ልዑልሰገድ ሥራውን ቃሊቲ ለሚገኘውና ኦሪጂናል ሲዲ ለሚያባዛው ሱፐር ሻይን ኩባንያ ወስዶ ከመሞከሩት በኋላ ኮፒ ማድረግ እንደማይቻል ማረጋገጣቸውን ተናግሯል፡፡ ይህን ስራ ሲሰራ ድጋፍ ያደረጉለትን ሰዎች ያመሰገነው ልዑልሰገድ፤ በተለይ አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ ላደረገለት ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋና አቅርቧል፡፡

Read 4721 times