Saturday, 08 August 2015 09:27

ሁሉን አውቅ ባዩ!

Written by  ተርጓሚ - ሌ.ግ ደራሲ ፡- ሶመርሴት ሞም
Rate this item
(6 votes)

ማክስ ኬላዳ ተብሎ የሚጠራውን ሰውዬ ገና በቅጡ ሳልተዋወቀው ልጠላው ዝግጁ ሆኜ ነበር፡፡ ጦርነቱ ገና እንደተጠናቀቀ በመሆኑ በመርከቦቹ ላይ የሚሳፈሩት ተጓዦች ከልክ በላይ በዝተዋል፡፡ አግባብ ያለው መስተንግዶ ማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል፤ የተገኘውን ሁሉ አሜን ብሎ መቀበል ግድ ነበር፡፡
አንድ ክፍል ለብቻ ማግኘትማ አይታሰብም። እኔ ግን ከማን ጋር ክፍል እንደምጋራ ሲነገረኝ መንፈሴ ተጐዳ፤ውስጤ ተሰበረ፡፡ ከማንም ጋር ለአስራ አራት ቀናት አብሮ በመርከብ መክረም አድካሚ ቢሆንም (እኔ ደግሞ ከሳንፍራንሲስኮ ወደ ዮኮሃማ የምሄድ ነኝ) እንደ ምንም ታግሼ በጣም ሳልከፋ እጓዝ ነበር፡፡ ይባስ ብሎ ግን፣ አብሮኝ የሚጓዘው ማክስ ኬላዳ ሆኖ አረፈው፡፡ እንትናም ይሁን እንቶኔ ባልገደደኝ ነበር…
ገና መርከቧ ላይ ከመሳፈሬ የኬላዳን ጓዝ ስፍራውን ተቆጣጥሮት አገኘሁት፡፡ ገና ስመለከተው አላስደሰተኝም ኮተቱ፡፡ ሻንጣዎቹ ብዙ የተለጣጠፉ እስቲከር ነገሮች ተሸፍነዋል፡፡ የልብስ ሳጥኑ ደግሞ ከመጠን በላይ የገዘፈ ነው። የመፀዳጃ ቤት መገልገያዎቹን ሜዳ ላይ አዝረክርኮዋቸዋል። የሚጠቀመው ሽቶ ደግሞ የተመረጠ ስለሆነ መዐዛው፤ በፊት መታጠቢያው ሳህን አቅራቢያ ያንዣብባል፡፡ ከወርቅ እጀታ የተሰራ የፀጉር ማበጠሪያው፣ ለምንጣፍ መጥረጊያ ቢውል የበለጠ ይሻል ነበር፡፡ ሚስተር ኬላዳን በፍፁም አልወደውም፡፡
ወደ ማጨሻ ክፍሉ አዘገምኩ፡፡ የካርታ መጫወቻ አዝዤ “ሶሊቴር” መደርደር ያዝኩ፡፡ ሶሊቴር ለትዕግስት… ትዕግስትም ሶሊቴር፡፡ ገና ጨዋታውን ከመጀመሬ አንድ ሰውዬ አጠገቤ መጥቶ “ስምህ…እንትና ነው ወይንስ ተሳስቻለሁ” እያለ ይጨቀጭቀኝ ጀመር፡፡ “እኔ ሚስተር ኬላዳ ነኝ” ሲል አከለበት - የሚያብለጨልጩ መደዳ ጥርሶቹን አሰልፎ፡፡ ከዚያ ተቀመጠ፡፡
“አዎ…አብረን በአንድ ክፍል ነው የምንጓዝ መሰለኝ፣ እድለኝነት ብዬ ነው የምጠራው አጋጣሚውን… ከማን ጋር እንደምትገጣጠም መቼም በህይወት ላይ መገመት አይቻልም፡፡ እንግሊዛዊ መሆንህን ሲነግሩኝ “እሰይ እድሌ” አልኩ፡፡ እኛ እንግሊዛዊያን ከሀገራችን ውጭ ስንጓዝ ጥምረት መፍጠር ይበጀናል፡፡ የምልህ ይገባሀል አይደል?”
አይኔን ጨፍኜ ገለጥኩት… “195 (ቁጥር) እንግሊዛዊ ነህ?” ብዬ ጠየቅሁት፤ ቅጥ ባጣ ዘዬ፡፡
“ይልቅስ እኔ አሜሪካዊ መስዬህ ነበር እንዴ?…ደሜ እስከ ጀርባ አጥንቴ የዘለቀ እንግሊዛዊ ነኝ ለማረጋገጥ ካስፈለገ---” ከኪሱ መታወቂያውን አውጥቶ አፍንጫዬ ስር በኩራት እየተንጠራራ አወዛወዘው፡፡
ሚስተር ኬላዳ አጠር ብሎ ደልደል ያለ ፍጡር ነው፣ ሙልጭ ተደርጐ ፂሙን የተላጨ፣ ቆዳው በፀሐይ ጠቆር ያለበት፣ ረጅም የተቆለመመ አፍንጫ የተሸከመ፣ ውሃማ አብረቅራቂ አይን ያለው ሰው ነው፡፡ ረጅም ሀርማ ጥቁር ፀጉሩ የመጠቅለል አዝማሚያ አለው፡፡ ድምፁ---ንግግሩ በጣም የተባ፣ ምንም ከእንግሊዝ ቋንቋ ውጭ የተቀየጠ ቅላፄ የማይገኝበት፣ ከንግግሩ ጋር የሚያደርገው የእጆቹ እንቅስቃሴ የገነኑ ናቸው፡፡
እንደው መታወቂያውን በጥንቃቄ ብመረምረው የሆነ ፀሐያማ ሀገር ላይ የተወለደ እንጂ ከጨፍጋጋዋ እንግሊዝ የተቀዳ አለመሆኑ እንደሚገኝበት አልጠራጠርም፡፡
“ምን ትወስዳለህ?” ብሎ ጠየቀኝ፡፡ በጥርጣሬ ገረመምኩት፡፡ መጠጥ ተከልክሏል፤ ባይከለከልም መርከቢቷ ድርቀት የመታት አይነት ናት፡፡ ግን ሚስተር ኬላዳ ያንን የሩቅ ምስራቅ ሳቁን ብልጭ አድርጐ “ዊስኪ በሶዳ ወይንስ ደረቅ ማርቲኒ?” ሲል አማረጠኝ “መናገር ብቻ ነው ካንተ የሚጠበቀው” ብሎ ከግራና ከቀኝ ኪሱ ሁለት ጠርሙሶች መዘዘ፡፡ ማርቲኒ መረጥኩኝ፤ አስተናጋጁን ጠርቼ በሰፍነግ በረዶና ብርጭቆዎች እንዲያወጣልኝ አዘዝኩት፡፡
“ጥሩ ኮክቴል” አልኩት፡፡
“ይሄ ከመጣበት ስፍራ ገና ሌላም ይከተላል፤ በመርከቢቷ ላይ ጓደኞች ካሉህ ጥራቸው፤ በዓለም ላይ ያለውን ሁሉ መጠጥ የጫነ ሰው አለ በላቸው”
ሚስተር ኬላዳ የመቀባጠር መንፈሱ አይሎበታል፡፡ ስለ ኒውዮርክና ስለ ሳንፍራንሲስኮ አወራ፡፡ ስለ ትያትሮች፣ ስለ ስዕሎችና ስለ ፖለቲካ ጠረቀ፡፡ በርግጥ ሀገር ወዳድ ዜጋ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የእንግሊዙ ባንዲራ የቀለም ዥንጉርጉር ይመስላል ግን ከሀገሪቷ ዜጋ ውጭ በሆነ ሰው እጅ ሲያዝ  መቅኖውን ያጣል፡፡ ከሚስተር ኬላዳ ጋር ተለማመድን፡፡ ግን ስሜን “ሚስተር” የሚለውን ተቀጥላ ቆርጦ እንዲጠራኝ አልፈቀድኩለትም፡፡ እሱም እኔን ለማስደሰት ሲል እንደሚመቸኝ ስሜን በመጥራት ተባበረኝ፡፡
ገና መጀመሪያ አብሮኝ ሲቀመጥ ከእርሱ ጋር ለመጨዋወት ስል የካርታ ጨዋታዬን አቋርጬው ነበር። ወሬያችን በቂ ያህል ከቀጠለ በኋላ ወደ ጨዋታዬ ተመለስኩ። “ሶስትን አራት ላይ አድርጋት” አለኝ ሚስተር ኬልዳ፡፡
በሶሊቴር ጨዋታ ላይ ገና የገለበጣችሁት ካርታ፣የሚቀመጥበትን ቦታ ለመፈለግ ፋታ ሳታገኙ ሌላ ሰው ቸኩሎ ሲያመለክታችሁ ያበሳጫል፡፡  
“ተሳበ…ተሳበ…አስርን በፍላወር ላይ” ልቤ በንዴት እየተንጨረጨረ ተጫውቼ ጨረስኩ፡፡ ጨርሼ ገና ሳላስቀምጠው ከእጄ ነጥቆ “የካርታ አስማት ላሳይህ?” አለኝ፡፡
“አይ የካርታ አስማት አልወድም” አልኩት፡፡
“እቺን ብቻ ላሳይህ አንዴ”
አንድ ሳይሆን ሶስት አሳየኝ፡፡ ከዚያ የእራት ጠረጴዛው በሰው ሳይሞላ ቦታ መያዝ እንደምፈልግ ነገርኩት፡፡
“ችግር የለውም…ለእኔና ላንተ አጠገብ ላጠገብ ቦታ ይዣለሁ፤የተሻለ ነው ብዬ አስቤ ነው” አለኝ፡፡
ሚስተር ኬላዳን እጠላዋለሁ፡፡ አብሮ ክፍል መጋራቱ ይቅር፣ አብሮ ሶስት ምግብ በቀን ውስጥ መመገቡም ይሁን፣ በመርከቧ ዙሪያ እየተዘዋወርኩ ብቻዬን መሆንም አልችልም ማለት ነው፡፡ ዞር በል ማለት የማይቻል አይነት ችኮ ሰው ነው፡፡ አለመፈለጉ የማይገባውን ፍጥረት ምን ማድረግ ይቻላል? እሱ አንተን በማግኘቱ እንደተደሰተው፣አንተም ከእሱ ጋር በመሆንህ የደስታ ፍሰሀ የሚሞላህ ይመስለዋል፡፡
በራስህ የግል መኖሪያ ቤት ውስጥ ቢሆን ከደረጃው ቁልቁል በካልቾ አንከባለኸው፣ በሩን ፊቱ ላይ ልትጠረቅምበት ትችል ነበር፤ እንደማትፈልገው ይግባው አይግባው ሳይጨንቅህ…፡፡ ከሰዎች ጋር መቀላቀል የሚያክለው የለም። በሦስት ቀን ጊዜ ውስጥ መርከቡ ላይ ያሉትን ሰዎች በጠቅላላ ተወዳጃቸው፡፡ ሁሉንም ነገር አካሂያጅ ሆነ። ስፖርቱን የሚዳኝ፣ ጨረታውን የሚያጧጡፍ፣ የዘፈን ቅንብር የሚያቀናጅ፣ በሁሉም ቦታ ሁሌም የሚገኝ ሰው ሆኖ ቁጭ አለ፡፡ በእርግጠኝነት ግን በመርከቡ ላይ በአንደኛ ደረጃ ሁሉም ሰው የሚጠላው እሱኑ ነበር፡፡
“ሚስተር ሁሉንም አውቅ ባይ” የሚል ቅጽል ስም ወጣለት፡፡ ቅጽሉን እሱ ፊት ስንጠቀምም ይሰማል፡፡ እንደ ማንቆለጳጰስ ቆጠረው፡፡
በተለይ በምግብ ወቅት ከሁሉም ጊዜያት በበለጠ ትዕግስት አስጨራሽ ይሆናል፡፡ ከአንድ ሰዓት በላይ ያግተናል። ደስተኛና ልባዊ ጨዋታውን ይግተናል፡፡ ጭቅጭቅ ይወዳል…ወሬኛ ተጨቃጫቂ ነው፡፡ ስለ ሁሉም ጉዳይ ከማንም የተሻለ ያውቃል፡፡ የአዋቂ ኩራቱን ለመወጣት እንዲችል የሚከራከረው ሰው ይሻል፡፡ በማንኛውም አይነት አርዕስት ላይ የፈለገ ተራ ጉዳይ እንኳን ቢሆን ወደ እሱ አስተሳሰብ አንፃር አምጥቶ እስካላንበረከከህ ድረስ አይተውህም፡፡ ሊሳሳት እንደሚችል ተከስቶለት አያውቅም። ሁሉን አዋቂ ነው፡፡
ለመብል የምንቀመጠው በዶክተሩ ጠረጴዛ ዙሪያ ነበር፡፡ ዶክተሩ ስልቹ፣ እኔ ደግሞ ስለ ምንም ክርክር ጉዳዬ አለመሆኑ ለሚስተር ኬላዳ የተመቸ አጋጣሚ ፈጠረለት፡፡ ሰይጣናዊ እርግጠኝነቱን በዙሪያው ለማጽናት፡፡ ይህ ሁኔታ የማይጥመውና ዝም ብሎ መቀበል የማይወደው ራምሴ የተባለው ሰው ብቻ ነው፡፡ እሱም በዚሁ ጠረጴዛ ዙሪያ ለመብል የሚዳበል ነው፡፡
ራምሴ በአሜሪካ ቆንስላ መስሪያ ቤት ተቀጣሪ የሆነ፣ ኮቤ የተባለችው ቦታ ተልኮ በመስራት ላይ የሚገኝ፣ ከአሜሪካ ምስራቅ አካባቢ የተገኘ ወፍራም ሰው ነው፡፡ ጥብቅ ባለ ቆዳው ስር ልል ስጋው ተከምሮ ልብሶቹን ወጥሮ ይታያል፡፡ ወደ አሜሪካ ተመልሶ ሚስቱን ይዞ፣ ወደ ኮቤ ስራው ቦታ እየተጓዘ ነው፡፡ ሚስቱ ደግሞ ለአመት ያህል አሜሪካ ቤተሰቦቿ ዘንድ ስትጐበኝ ቆይታ ከባሏ ጋር ወደ ባህር ማዶ ህይወታቸው በመርከቡ እየተመለሱ ነው፡፡
የቆንስላው መስሪያ ቤት ባልየውን በቂ ገንዘብ አይከፍለውም፡፡ ስለዚህ ሚስትየዋ ርካሽ ልብስ ነው ዘወትር የምትለብሰው፤ግን ያንኑ ርካሽ ልብስ በጥንቃቄ መልበሱን ትችልበታለች፡፡ በአለባበሷ የሆነ ከፍታ ለራሷ ታጐናጽፋለች፡፡ እሷን ልብ ብዬ ባልተመለከትኳት ነበር፤ ግን በአሁኑ ጊዜ ሴቶች ላይ ከእነአካቴው የጠፋው የኩራት ፀጋ፣ በእሷ ላይ መገኘቱ እንዳስተውላት ግድ አለኝ፡፡ ልብስ ያጠለቀች አበባ አስመስሏታል፡፡
እነሆ በአንዱ ቀን በጠረጴዛው ዙሪያ ይካሄድ የነበረው ውይይት ወደ እንቁዎች አርዕስት ዞሮ ተገኘ፡፡ በጋዜጣዎች ላይ ጃፓናዊያን አርቴፊሻል እንቁ (Pearl) እየሰሩ ዋናውን በተመሳሳይ እየቀየሩ ስለመሆኑ በሰፊው እየተዘገበ የነበረበት ወቅት ነው፡፡ ዶክተሩ ሰውዬ፤ “በስተመጨረሻ አርቴፊሻሉ የዋናውን የቀድሞ ስፍራ መተካቱ እንደማይቀር” አስተያየቱን ሰነዘረ፡፡
“ምክንያቱም አሁንም እንኳን አምሳያዎቹ በጣም ጥሩ ናቸው፤ከጊዜ በኋላ እቅጩን መሆናቸው አያጠያይቅም” አለ፡፡
ሚስተር ኬላዳ እንደ ልማዱ ይኼንንም አርዕስት ወስዶ ያጣድፈው ጀመረ፡፡ ስለ እንቁ በአለም ላይ ያለውን እውቀት መዘርገፍ ያዘ፡፡ እርግጠኛ ነኝ ራምሴ ስለ እንቁ አንድም የሚያውቀው ነገር እንደሌለ፤ ግን የሚስተር ኬላዳ ንግግር ስላናደደው ብቻ ጥምዝ አስተያየቶችን መሰንዘር ጀመረ። በአምስት ደቂቃ ውስጥ የጥላቻ ክርክር ውስጥ ገብተው እኛንም ጨመሩን፡፡
ሚስተር ኬላዳ ሁሌም የሚነታረከው በጉልበት ቢሆንም የዚህ ክርክር ጉልበቱ ግን በተለየ አኳኋን በረታ። በተለይ ራምሴ የተናገረው አንድ ንግግር በጠበጠው፡፡ ምክንያቱም ከተቀመጠበት በድንገት ተነስቶ፤“ስለምናገረው ነገርማ በደንብ አውቃለሁ፡፡ አሁን ራሱ ወደ ጃፓን እያቀናሁ ያለሁት የጃፓን ሀገር የእንቁ ገበያን ለመገመት ነው፡፡ እኔ በእንቁ ስራ ላይ የተሰማራሁ ሰው ነኝ፤ ስለ ንግዱ ከእኔ በላይ ማንም ሊነግርህ የሚችል የለም፡፡ በዓለም ከሁሉም የበለጠው እንቁ የትኛው እንደሆነ አውቃለሁ፤ የማላውቀው ካለ ደግሞ … ለእውቀቴ የሚመጥን ስላልሆነ ብቻ ነው”
ይህ ንግግር ለሁላችንም ዜና ነው የሆነብን፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ለሚስቱ ኬሌዳ በዚያ ሁሉ ልፍለፋው ውስጥ አንድም ቀን ሣት ብሎት ስራው ምን እንደሆነ ገልፆላት አለማወቁ ነው፡፡ የምናውቀው እስካሁን በአንዲት የንግድ ተልዕኮ ጉዳይ ወደ ጃፓን እያቀና መሆኑን ብቻ ነበር፡፡ በጠረጴዛው ዙሪያ ያለነውን በሙሉ “አፋችሁን አስያዝኳችሁ” በሚል የድል አድራጊነት ስሜት ተመለከተን፡፡
“እኔ በአይኔ አይቼ ላውቀው ያልቻልኩትን ፐርል ማንም ስለ እውነተኛነቱ ሊመሰክር አይችልም”
በእጁ ወደ ወይዘሮ ራምሴ አንገት እየጠቆመ፤“የምነግርሽን እመኚ ሚስ ራምሴ … ይኼ በአንገትሽ ያጠለቅሽው ጌጥ … የፈለገ ቢመጣ ዋጋው መቼም አይረክስም፡፡“
ወይዘሮዋ ፊቷ በድንገት ገርጥቶ …በእጇ አንገቷ ላይ ያለውን ሀብል ወደ ውስጥ አስገብታ ሸሸገችው፡፡ ባሏ፣ አቶ ራምሴ ወደ ጠረጴዛው ተጠግቶ ተደገፈ፡፡ ለእኛ የፈገግታ ጥቅሻ እየሰጠን “በጣም የሚያምር ሀብል ነው አይደል?” አለው ሚስተር ኬላዳን፡፡
“ወዲያው ነው አይቼ ያወቅሁት … እንዳየሁትም ‹አቤት ገዝቼ ብወስደው!› ብዬ ተመኝቻለሁ … ስንት ይሆን የምትሸጡት?” ጠየቃቸው ባልና ሚስቱን፡፡
ቀጠለና፤ “አሁን በገበያ ላይ ወደ አስራ አምስት ሺ ዶላር አካባቢ ነው፤ ግን አሜሪካ Fifth Avenue ከሄዳችሁ ደግሞ ሰላሳ ሺ ዶላር ይሏችኋል”
ራምሴ ሳቀ፤“በጣም ብነግርህ ትደነቃለህ … ሚስቴ ከአሜሪካ ከመነሳታችን ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ከአንድ ተራ ሱቅ ሀብሉን በአስራ ስምንት ዶላር ነው የገዛችው …”
ሚስተር ኬላዳ ፊቱ ተለዋወጠ፡፡
“ውሸታም … እውነተኛ እንቁ ብቻ ሳይሆን በዚህ የክር መጠን ከዚህ በላይ እንቁ የያዘ ሀብል የትም ከዚህ በፊት አይቼ አላውቅም፡፡
“ትወራረዳለህ?” አለ ባል አቶ ራምሴ “በመቶ ዶላር እንወራረድ!”
“እወራረዳለሁ!” ቸኩሎ ተስማማ ሚስተር ኬላዳ፡፡
“በማታውቀው ነገር ላይ ባትወራረድ ይሻላል” አለች ሚስቲቱ፤ ተጨንቃለች፡፡ ፊቷ ላይ የነበረው ፈገግታ ቀስ እያለ እየደበዘዘ ነው፡፡
“እንዴ ምን ማለትሽ ነው … እንደዚህ ዓይነት ነፃ ገንዘብማ ከተገኘ አልምረውም” አለ ባል
“እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል?” አለች ሚስት
“የእኔ ቃል ከእሱ ጋር ብቻ ነው መለኪያው”
“ሚስ ራምሴ ታውልቀውና ትስጠኝ … አንዴ ሀብሉን ልመልከተው … ተሳስቼ ከሆነ መቶ ዶላሩን እከፍላለሁ … መቶ ዶላር ያን ያህል እኔን አይጎዳኝም” አለ ሚስተር ኬላዳ
“ሆዴ አውልቂና ይየው! ስጪው” አለ ባል ሚስተር ራምሴ፤ ወይዘሮዋ አመነታች፡፡ እጆቿን ጨበጠች፡፡
“አይ ማድረግ አልችልም” አለች “ሚስተር ኬላዳ ተራ ሀብል ስለመሆኑ የእኔን ቃል እንደ ማረጋገጫ ይቀበል”
አንዳች ነገር ድንገት ሊፈጠር መሆኑ ተሰማኝ፤ ግን ምንም ለማለት አልቻልኩም፡፡ ራምሴ ከተቀመጠበት ተስፈንጥሮ ተነሳ፤“እኔ ራሴ ከአንገቷ ላይ አወልቀዋለሁ” አለ፡፡ በራሱ አጅ ከሚስቱ አንገት ላይ ያወለቀውን ሀብል ለሚስተር ኬላዳ አቀበለው፡፡ ተቀብሎ (በማጉያ መነጥር) በጥንቃቄ አየው …. ለመናገር አፉን ሲከፍት …. ድንገት የሚስቲቱን ፊት ተመለከተ፡፡
የሚሲስ ራምሴ ፊት በጣም ከመገርጣቱ የተነሳ ራሷን ስታ ልትወድቅ ትመስላለች፡፡ ሚስተር ኬላዳን በጣም በተበለጠጠ፣ በደነገጠ አይኗ አየችው፡፡ እይታዋ በውስጡ ልመና አለበት፡፡ በጣም ግልፅ ከመሆኑ የተነሳ የአይኗን መልዕክት እኛው ልብ ብለነዋል፡፡ ባሏ ብቻ ለምን እንዳልገባው አላውቅም፡፡
ሚስተር ኬላዳ ንግግሩን ገታ፡፡ አፉ እንደተከፈተ ቀርቷል፡፡ የቆዳው ቀለም ተለውጧል፡፡ በራሱ ላይ ያመጣው የስሜት ለውጥ እንዳይታይ በመጠንቀቅ፤
“በጣም ተሳስቻለሁ … በጣም ይቅርታ … ተመሳስሎ የተሰራ እንጂ ዋነኛው እንዳይደለ በመነፅሬ ስመለከተው አረጋገጥኩኝ … እንዳላችሁት ከአስራ ስምንት ዶላር የበለጠ ዋጋ አያወጣም …”
የኪስ ቦርሳውን አውጥቶ … ከውስጡ መቶ ዶላር መዘዘ፡፡ አንድም ቃል ሳይተነፍስ መቶ ዶላሩን ለሚስተር ራምሴ አቀበለው፡፡ “የማታውቀው ነገር ላይ አጉል ደፍረህ እንዳትፎክር ይሄ ጥሩ ትምህርት ይሆንሃል” አለው ሚስተር ራምሴ፤ ብሩን እየተቀበለ፡፡ የሚስተር ኬላዳ እጅ እየተንቀጠቀጠ እንደነበረ ልብ ማለት ችያለሁ፡፡ የተከሰተው ታሪክ በመርከቢቷ ላይ ዳር እስከ ዳር ናኘ፡፡ ሚስተር ኬላዳ ሰዎች ያን ምሽት በነገር ሲጎነትሉት ዝም ብሎ አሳለፈው። “ሁሉን አውቅ ባዩ” ምንም እንደማያውቅ ተጋለጠ ተባለ፡፡ ሚስስ ራምሴ ብቻ ራሷን በሀይል ስላመማት ወደ መኝታ ክፍሏ ገብታ ተደበቀች፡፡
በሚቀጥለው ማለዳ ተነስቼ ፂሜን መላጨት ጀመርኩ፡፡ ሚስተር ኬላዳ አልጋው ላይ ጋደም ብሎ ሲጋራውን እየሳበ ነበር፡፡ ድንገት በሩ አካባቢ አንዳች ድምፅ ሰማሁ… በበሩ ስር አንድ ፖስታ ተገፍቶ ወደ ክፍሉ ተወረወረ፡፡ በቶሎ በሩን ከፍቼ ግራና ቀኝ ተመለከትኩኝ፡፡ ማንም በአካባቢው የለም። ደብዳቤውን አንስቼ ሳስተውል የተላከው ለሚስተር ኬላዳ መሆኑን መገንዘብ ቻልኩኝ፡፡ ስሙ በትልልቅ ፊደሎች ሰፍሯል፡፡ ለኬላዳ ደብዳቤውን አቀበልኩት፡፡
“ከማን ነው የተላከልኝ?” … እያለ ከፈተው፡፡
“ኦ!” አለ፡፡ ኤንቨሎፑን ከፍቶ በውስጡ ደብዳቤ አለመኖሩን ሲመለከት፡፡ በደብዳቤ ፈንታ በውስጡ የመቶ ብር ኖት ይዟል፡፡ እኔን ቀና ብሎ ተመለከተኝና ፊቱ ከመቅፅበት ቀላ፡፡ ኤንቨሎፑን ወደ ብዙ ትናንሽ ቁርጥራጮች በጫጭቆ ለእኔ መልሶ አቀበለኝ፡፡
“በመርከቡ መስኮት ልትጥልልኝ ትችላለህ?” ሲል ጠየቀኝ፡፡ እንደጠየቀኝ አደረግሁ፡፡ ካደረግሁ በኋላ በፈገግታ ተመለከትኩት፡፡
“ማንም ሰው እንደ ሞኝ መቆጠርን አይወድም” አለኝ። “ሀብሉ ላይ ያሉት እንቁዎች እውነተኛ ነበሩ ወይ? … እኔ እንደሷ (ሚሲስ ራምሴ) አይነት ቆንጆ ሚስት ብትኖረኝ … እኔ ኮቤ ርቄ እየሰራሁ፣ እሷ አንድ አመት ሙሉ … ኒውዮርክ እንድትቀመጥ አልፈቅድላትም ነበር” አለ ሚስተር ኬላዳ፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህች ቅፅበት ሚስተር ኬላዳን ያን ያህል አጥብቄ እንደማልጠላው ተገነዘብኩኝ፡፡ ኬላዳ የኪስ ቦርሳውን አውጥቶ የመቶ ብር ኖቱን ትላንት ከወጣበት ስፍራ መለሰው፡፡

Read 3501 times