Saturday, 08 August 2015 09:41

የዶፒንግ ፊሽካው አትሌቲክስን እየበጠበጠ ነው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

11 የኬንያ 8 የኢትዮጵያ ነው
                    
   ከሁለት ሳምንት በኋላ የሚጀመረው 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በዶፒንግ ዙርያ በተፈጠሩ አወዛጋቢ አጀንዳዎች መጥፎ ድባብ እያጠላበት ነው፡፡
በጀርመን ብሮድካስት ኩባንያ (ARD/WDR) እና በእንግሊዙ ሰንደይ ታይምስ ከሳምንት በፊት በዶፒንግ ማጭበርበር ዙሪያ የወጡ መረጃዎች ከመቶ በላይ አትሌቶችን በዶፒንግ ማጭበርበር ከስሰዋል፡፡ ሁኔታው የዓለም ሻምፒዮናውን የፉክክር ድምቀት ሊያደበዝዘው እንደሚችል ተሰግቷል፡፡ የዓለም አትሌቲክስን በሚመሩ ተቋማት በዶፒንግ ውንጀላው ዙሪያ የሚከተሉት አቅጣጫ ምን ሊሆን እንደሚችል በግልፅ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ክሱ ከ2001-2012  እኤአ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናና በኦሎምፒክ የተሸለሙ አንድ መቶ ሃያ ሜዳልያዎች ትክክለኛነት በዶፒንግ ማጭበርበር ጥያቄ እንደሚነሳቸው የሚዲያ ተቋማቱ ቢገልፁም የስፖርቱን ዓለም ያሳሰበው የአትሌቲክስ ተወዳጅነት አደጋ ላይ መውደቁ ነው፡፡ በተጨማሪም 144 የዓለም ሻምፒዮንና የኦሎምፒክ አሸናፊዎች በዶፒንግ ማጭበርበር መከሰሳቸው እና ከእነዚህ የሜዳልያ አሸናፊዎች 55 የወርቅ ሜዳልያ የተሸለሙ መሆናቸውን የሚዲያ ተቋማቱ ገልፀዋል፡፡ ይህ ሁሉ አወዛጋቢ አጀንዳ በ2016 እ.ኤ.አ በብራዚሏ ከተማ ሪዮ ዲጂኔሮ የሚካሄደው 31ኛው ኦሎምፒያድ አንድ ዓመት ሲቀረው መነሳቱ ደግሞ ለመላው ዓለም መደናገርን ፈጥሯል፡፡
በጀርመኑ የብሮድካስት ኩባንያና በእንግሊዙ ሰንደይ ታይምስ ጋዜጣ የዶፒንግ ማጭበርበር ፈጽመዋል በሚል የተከሰሱት የ57 አገራት አትሌቶች ናቸው፤ በተለይ ከራሽያ ሜዳልያ አሸናፊ አትሌቶች 80 በመቶ በዶፒንግ ማጭበርበሩ ተጠያቂ መደረጋቸው እና የኬንያ 18 ሜዳልያ አሸናፊ አትሌቶችም በጥፋተኛነት መነሳታቸው የሚዲያዎችን ትኩረት የሳበ ነገር ነው፡፡  በ30ኛው የለንደን ኦሎምፒክ እንኳን 10 የወርቅ ሜዳልያ ድሎች የዶፒንግ ችግር አለባቸው በሚል መፈረጁ አስደንጋጭ ነው፡፡ የጀርመኑ የብሮድካስት ኩባንያ እና የእንግሊዙ ሰንደይ ታይምስ ይፋ ባደረጉት ዝርዝር መሰረት 30 የራሺያ፤ 28 የዩክሬን፤ 27 የቱርክ፤ 26 የግሪክ፤ 24 የሞሮኮ፤ 22 የቡልጋሪያ፤ 20 የባሕሬን፤ 19 የቤለሩስ ፤16 የስሎቬኒያ፤ 13 የሮማንያና የኡጋንዳ ፤ 12 የብራዚል፤  11 የስፔን፣ የኬንያ፣ የሆላንድና የኮሎምቢያ፤ 9 የጃማይካ፤ 8 የፖርቱጋል፣ ስሎቫኪያ፣ ኳታር፣ የኢትዮጵያና የኩባ፤ 7 የስዊድን፣ የቼክ፣ የኤርትራ፣ የባህማስና የደቡብ ኮሪያ፤ 6 የላቲቪያ፣ የጀርመን፣ የቤልጄም፣ የጣሊያንና የሜክሲኮ፤ 5 የቻይና፣ የአሜሪካ፣ የሀንጋሪ፣ የኖርዌይ፣ የፈረንሳይ፣ የፖላንድ፣ የጃፓን፣ የአልጄሪያና ህንድ፤ 4 የሉታንያ፣ ሂስቶንያ፣ ስዊዘርላንድ፣ የኦስትሪያ፣ የፊላንድ፣ የብሪታንያና የደቡብ አፍሪካ፤ 3 የአውስትራሊያ፣ የካዛኪስታን፣ የትሪንዳንድና የቶቤጐ፣ የአየርላንድ የካናዳና የሰርቢያ እንዲሁም 2 የኒውዝላንድ አትሌቶች በዶፒንግ ማጭበርበር ተከሰዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ  ከሳምንታት በኋላ በሚካሄደው የዓለምአቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ በዶፒንግ ዙርያ የተፈጠሩ የውዝግብ አጀንዳዎች እየተወሳሰቡ መሄዳቸው ውጥረት እንደፈጠረ ነው፡፡
የእንግሊዙ ሰንደይ ታይምስ እና የጀርመኑ የብሮድካስት ኩባንያ ኤአርዲ ደብሊው ዲአር ከ2001 እስከ 2012 እኤአ 5ሺ አትሌቶች ያደረጓቸው 12ሺ የደም ምርመራዎች ዝርዝር መረጃ እንደደረሳቸው ካሳወቁ በኋላ ዓለም አቀፉ የዶፒንግ ተቋም ዋዳ ሁኔታውን በጣም እንዳስጨነቀው ገልፆ፤ መረጃዎች ትክክለኛ መሆናቸው ከተረጋገጠ የዓለም አትሌቲክስ ከስር መሰረቱ ሊናጋ እንደሚችልም እያሳሰበ ነው፡፡
በዓለም አቀፍ ግዙፍ የአትሌቲክስ የውድድር መድረኮች የዶፒንግ ማጭበርበር በከፋ ሁኔታ መቀጠሉን አረጋግጠናል የሚሉት የጀርመኑ የብሮድካስት ኩባንያ እና የእንግሊዙ ሰንደይ ታይምስ እንዳስገነዘቡት በኦሎምፒክ እና በዓለም ሻምፒዮና የውድድር መድረኮች ከተገኙ ሜዳልያዎች ሲሶው የተከለከለ መድሃኒት እና አበረታች ንጥረ ነገር በተጠቀሙ አትሌቶች የተመዘገቡ ናቸው በሚል ብጥበጣውን ቆስቁሰውታል፡፡ በሁለቱ የአውሮፓ ሚዲያዎች መረጃዎች መሰረት  በዶፒንግ ማጭበርበር የተጠቀሱት 800 አትሌቶች ያደረጓቸው የደም ምርመራዎች አጠራጣሪ እና የሚያደናግሩ መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡ የጀርመኑ ብሮድካካስት ተቋም ‹‹ታላቅ ምስጥር ጥላ የበዛበት የዓለም አትሌቲክስ›› በሚል የ55 ደቂቃዎች  ልዩ ዘጋቢ ፊልም የሰራ ሲሆን ዋዳ ይህን ፊልም በገለልተኛ ኮሚሽን ለማጣራት በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር በወጣው መረጃ ዙርያ ይፋ ባደረገው መግለጫ አንዳችም ማረጋገጫ እንዳላገኘበት አመልክቶ፤ ተከታይ ርምጃዎችን ከመውሰድ በፊት ማጣራት እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር በየዓመቱ ከዶፒንግ ጋር በተያያዘ  በአትሌቶች ላይ 35000 የደም ምርመራዎችን ያደርጋል፡፡ ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ በዶፒንግ ዙርያ የተሰሙ ክሶች ትክክለኛነታቸው ከተረጋገጠ የማያዳግም እርምጃ መውሰዳችን አይቀርም ብሏል፡፡
የኬንያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን የዶፒንግ ክሱ ለዓለም ሻምፒዮና አትሌቶቻችን በመረጥን ማግስት ይፋ መሆኑ የቡድን መንፈሳችን የረበሸ ብሎ አውግዞ፤ ክሶቹ ይፋ ከመሆን በፊት በዶፒንግ ችግር ዙርያ ለአትሌቶች በቂ ግንዛቤ በመፍጠር መሰራት ነበረበት በሚል ሁኔታውን አጣጥሎታል፡፡ ለዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ፕሬዝዳንትነት የሚወዳደረው አሁን ምክትል ፕሬዝዳንት የሆነው እንግሊዛዊው ሴባስቲያን ኮው በበኩሉ የዶፒንግ ክሱን በአትሌቲክስ ስፖርት ላይ የተከፈተ የጦርነት አዋጅ ብሎታል፡፡ የስፖርቱን ክብር እና ዝና ለመጠበቅ ሁላችንም በሃላፊነት የምንሰራበት ወቅት ብሎ ኮው ሲናገር፤ ለፕሬዝዳንትነት የሚፎካከረው ሰርጄይ ቡብካም የዶፒንግ ችግር በ21ኛው ክፍለዘመን በአትሌቲክስ ስፖርት ላይ የተጋረጠ አደጋ መሆኑን ገልፆ፤ የምርመራ እና የክትትሉን መንገድ ማጠናከር ቢሻል እንጂ አትሌቶችን መወንጀል ተገቢ አይደለም ብሏል፡፡
የወቅቱ የአይኤኤኤፍፕሬዝዳንት የሆኑት ሴኔጋላዊው ላሚን ዲያክ በበኩላቸው የአትሌቲክስ ስፖርትን በአስከፊ ቀውስ የከተተ ብለው ብዙ ሁኔታዎች በቂ ማረጋገጫ ሳይኖራቸው አትሌቶችን ለማዋረድ መሞከሩ የሚያሳፍር ብለውታል፡፡
የዶፒንግ ማጭበርበሩ በተለይ ፅናት በሚፈልጉ የአትሌቲክስ ውድድሮች ስፖርተኞች በደማቸው በቂ የኦክሲጅን ክምችት እንዲኖራቸው የሚያስችሉ መድሃኒቶችን ከመጠቀም ጋር ተያይዞ የተነሳ ነው፡፡ አይኤኤኤፍ ባለፉት 15 ዓመታት በዶፒንግ ዙርያ ከ19ሺ በላይ የደም ምርመራዎች በአትሌቶች ላይ ማድረጉን ለማወቅ የተቻለ ሲሆን እስከ 2.3 ሚሊዮን ዶላር በጀት በማንቀሳቀስ የሚያካሂደው ክትትል ነው፡፡
በተያያዘ 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በቻይናዋ ከተማ ቤጂንግ ከ2 ሳምንት በኋላ የሚጀመር ሲሆን ኢትዮጵያ እና ኬንያ የውድድሩ ድምቀት ከሚሆኑ ተሳታፊዎች ግንባር ቀደም ናቸው፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት ሞስኮ አስተናግዳ በነበረችው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ 46 አትሌቶችን ያሳተፈችው ኢትዮጵያ 3 የወርቅ፤3 የብር እና 4 የነሐስ  በድምሩ 10 ሜዳልያዎችን በማግኘት ከዓለም 6ኛ ደረጃ ይዛ አጠናቅቃለች፡፡ 3 የወርቅ ሜዳልያዎች በ800 ሜትር መሃመድ አማን፤ በ5000ሜትር መሰረት ደፋር እንዲሁም በ10ሺ ሜትር ጥሩነሽ ዲባባ የተመዘገቡ ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን የኮምኒኬሽን ክፍል እንደገለፀው 33 አትሌቶች የሚገኙበት ቡድን የዝግጅት ሂደት  እንደቀጠለ ነው፡፡ አትሌቶቹን  በወቅታዊ ብቃት፣ በሚኒማና በበርካታ የመምረጫ መስፈርቶች ተለይተው ጠንካራ ዝግጅት በማድረግ ላይ ናቸው ያለው አትሌቲክስ ፌደሬሽኑ፤ ከመካከለኛ እስከ ማራቶን ድረስ ባሉት ኢቨንቶች የሚካፈሉት እነዚህ አትሌቶች በአራራት ሆቴል ካምፕ አድርገው የቤጂንግን የአየር ንብረት መቋቋም ይችሉ ዘንድ ከፍተኛ ዝግጅት እያደረጉ ናቸው፡፡ ከቃሊቲ እስከ ሶደሬ ድረስ በሚገኙ ሞቃት አካባቢዎች ልምምዳቸውን በአግባቡ እንዲሰሩ መደረጉን ያመለከተው መግለጫው ቤጂንግ ላይ  ከአትሌቶቻችን  አስደናቂ ውጤት እንደሚጠበቅም ተስፋ አድርጓል፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የቅርብ ተቀናቃኝ የሆነችው ኬንያ በቤጂንግ 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 40 አትሌቶችን እንደምታሳትፍ ታውቋል፡፡ በዚሁ የኬንያ ቡድን የቀድሞና የአሁን የዓለም ሻምፒዮንና የኦሎምፒክ አሸናፊዎች የተካተቱበት ነው፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በሞስኮ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኬንያ አሥራ ሁለት ሜዳልያ በማግኘት ከራሽያ፣ ከአሜሪካና ከጃማይካ ቀጥላ በዓለም በአራተኛ ደረጃ ማጠናቀቋ ይታወሳል፡፡          

Read 3105 times