Saturday, 08 August 2015 09:43

“...ደም መስጠት... በፈቃደኝነት...”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ (ከኢሶግ)
Rate this item
(1 Vote)

...የእኔ ደም አይነት O-RH ነው፡፡ ስለሆነም የእኔ ደም በሌላ የደም አይነት ሊተካ የማይችል ነው። በመውለድም ሆነ በተለያየ ምክንያት እንደዚህ ያለ የደም አይነት ያላቸው ሰዎች ደም ሊሰጣቸው  ቢፈለግ የግድ O-RH መሆን አለበት፡፡ ስለሆነም እኔ     ምንግዜም ችግር ለሚገጥማቸው ሰዎች ደም በመለገስ መድረስ ስለምፈልግ የደም ባንክ ደንበኛ ነኝ፡፡ ደም መስጠት የጀመርኩት በ2001/ዓ/ም ሲሆን እስከአሁን ድረስ ወደ ሰባት ጊዜ ሰጥቻለሁ፡፡ አሁን አቋርጫለሁ። ያቋረጥኩት ግን በመውለድ ምክንያት ነው፡፡ ሁኔታዬ ሲደላደል ደግሞ እንደገና እቀጥላለሁ፡፡
ሕይወት ታደለ
እናቶች ሕይወት ሲሰጡ ሕይወታቸውን ማጣት የለባቸውም፡፡
ማንኛዋም እናት በሰለጠነ ሰው የሙያ ድጋፍ ልጅዋን መውለድ ይገባታል፡፡
ደም ሲሰጡ በቀላሉ የሚተኩት ሲሆን ለተቀባዩ ግን መተኪያ የሌለውን ሕይወት ማትረፊያ ነው፡፡
ደም በፈቃደኝነት መስጠት ማህበራዊ ግዴታ ነው፡፡
ደም መስጠትን በሚመለከት ከአሁን ቀደም የታዘቡትን ያጫወቱን አቶ እሸቱ ኃይሌ ከፒያሳ ናቸው፡፡
“...ባለቤቴ በሕመም ምክንያት ወደ ሆስፒታል ገብታ የቀዶ ሕክምና እንደሚያስፈልጋት ተነገረኝ፡፡ ለዚህም አገልግሎት ከሚያስፈልጉት ነገሮች አንዱ ደም ማቅረብ ነበር፡፡ እኔ በተደረገልኝ ምርመራ ደም መስጠት የማልችል ሆንኩ፡፡ አንዳንድ ቤተሰቦች ደግሞ በተለያየ ምክንያት ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ስለዚህ ምን ይሻለኛል ብዬ ስጨነቅ... እንደኔው ደም ለመስጠት የቆመ ሰው ከምትቆም  ...ወጣ በልና አንድ ጎረምሳ ፈልግ አለኝ፡፡ እንዴት? የእኔ ጥያቄ ነበር፡፡ ትንሽ ገንዘብ ከሰጠሀቸው መጥተው ደም ይሰጡልሀል ነበር ያለኝ፡፡  ከዚያም አንዱን ይዤ ስሄድ... አንተማ በቅርብ ቀን ስለሰጠህ መስጠት አትችልም የሚል መልስ ተሰጠ፡፡ ከዚያም የተመለሰው ልጅ እራሱ አንዲት ሴት ልጅ ይዞልኝ መጣ፡፡ በዚህ መልክ የጠየቁኝን ገንዘብ ተደራድሬ ከፍዬ... የሁለት ሰው ደም ባንኩ ተክቶልኝ ለሆስፒታሉ አቀረብኩ፡፡ ይሄንን ገጠመኝ በፍጹም አልረሳውም። አሁን ግን እግዚአብሄር ይመስገን ሂዱና አምጡ የሚባለው ነገር ቀርቶአል አሉኝ...”
ከላይ ያነበባችሁት የሁለት ሰዎች አስተያየት የሚያሳየን ደምን በፈቃደኝነት መስጠት ለታማሚዎችም ይሁን ለአስታማሚዎች እንዲሁም ለሆስፒታሎቹ አሰራር በጣም ምቹ የሚሆን ከመሆንም በላይ ዜጎች ደም መስጠታቸው ደግሞ እንደ አንድ የውዴታ ግዴታ መወሰድ ያለበት ነገር መሆኑን ነው፡፡
እናቶች ከእርግዝና ጊዜ ጀምሮ እስከመውለድ ድረስ በሚኖራቸው ቆይታ በተለያየ ምክንያት የደም መፍሰስ ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ በተለይም በወሊድ ወቅት እስከ አስራ ሁለት ሰአት ድረስ ባለው ጊዜ በሚገጥም የደም መፍሰስ ምክንያት ህይወታቸው የሚያልፍ ብዙዎች ናቸው፡፡  ቀስ ብሎ ይደርሳል የማይባል... ጊዜ የማይሰጥ አጋጣሚ በምን ሊዳኝ ይችላል ቢባል የተዘጋጀ ደም መኖሩ የሚል መልስ የሚሰጠው ነው፡፡
የህክምና ባለሙያዎች ደም የሚያስፈልጋት ታካሚ ስትገጥማቸው ቤተሰቦቿን ደም አምጡ የሚል ትእዛዝ ከማስተላለፍ ባሻገር በተለይም ዛሬ ዛሬ እራሳቸው ተሳታፊ የሚሆኑበት ወይንም ደም የሚሰጡ መሆናቸው አበረታች ጅምር ነው ፡፡ ይህንን በሚመለከት የተወሰኑ ሐኪሞችን ለዚህ እትም አነጋግረናል፡፡
ዶ/ር ባልካቸው ንጋቱ በጳውሎስ ሆስፒታል ወይንም ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ረዳት ፕሮፌሰርና መምህር እንዲሁም የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡፡
 “...የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያ እንደመሆኔ መጠን የደም ችግር ምን ያህል እንደሆነ በትክክል እረዳለሁ፡፡ ሁልጊዜም ደም ሲያስፈልግ አምጡ ብሎ ከማዘዝ ይልቅ የሚሻለው ደም እየሰጡ ምሳሌ በመሆን ሌሎችም በዝግጅት እራሳቸው ፕሮግራማቸው አድርገው ወገናቸውን ለማትረፍ ደም እንዲሰጡ ማድረግ ይገባል፡፡ ስለዚህም ይህ የማንኛውም ሰው ግዴታ ተደርጎ ቢወሰድ ጥሩ ነው እላለሁ፡፡ የህክምና ባለሙያው ከሌላው ሰው የሚለይበት ምክንያት በስራው ላይ ስላለና ችግሩን ስለሚያየው ሲሆን ሌላው የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ የሚነግረው የሚያስ ተምረው ሰው ያስፈልጋል፡፡ በእኔ በኩል የሞራል ግዴታዬ ወይንም ማህበራዊ ግዴታዬ ነው ብዬ ስለማምን ለስድስተኛ ጊዜ ደም ለግሻለሁ፡፡”
ሌላው ያናገርናቸው ዶ/ር ሙስጠፋ ነጋሽ በእለቱ ደም ሰጥተው ወደ ቢሮአቸው ሲመለሱ ነበር ያገኘናቸው፡፡ ዶ/ር ሙስጠፋ በጳውሎስ ሆስፒታል ወይንም ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ረዳት ፕሮፌሰርና መምህር እንዲሁም የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡ እሳቸውም እንደሚሉት፡-
“...እኛ ስራችን ከደም ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ደም ከሌለ ስራችን ይቆማል ማለት ይቻላል፡፡ ስለሆነም እኛ ደም ሰጥተን ምሳሌ መሆን አለብን፡፡ ሐኪሙ እራሱ አምኖበት ደሙን ሲሰጥ የሚያይ ሰው ደም መስጠት ምንም ጉዳት እንደሌለው እና አስፈላጊ መሆኑን ይረዳል፡፡ ብሔራዊው የደም ባንክ ሰዎችን እያስተማረና እየቀሰቀሰ ደምን ከፈቃደኞች እና ከጤነኞች ሰዎች እየወሰደ ቢያከማች በችግር ጊዜ ያለምንም ችግር መውሰድ እና ታካሚዎችን ማዳን ይቻላል ማለት ነው። በችግር ጊዜ ደም ስጡ ሲባል ደም የሚሰጥ ከሆነ ሁሉም አገልግሎት ላይ ይውላል ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም በጤና እና በተለያዩ ምክንያቶች የተሰጠው ደም ከጥቅም ላይ ሳይውል ሊወገድ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ለእጥረት ይዳርጋል፡፡ ስለዚህ በጎ ፈቃደኞች ይህንን ማህራዊ ግዴታ አውቀውት ተግባራዊ ቢያደርጉት ጥሩ ነው፡፡
ዶ/ር ብርሀኑ ከበደ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ከአሁን ቀደም በነበረው አሰራር ሐኪሞች ባለባቸው የስራ መደራረብና ሌሎች ምክንያቶች እራሳቸው ደም እየሰጡ ምሳሌ የመሆናቸው ነገር ብዙም የሚታይ አልነበረም ይላሉ፡፡ ስለሆነም ሐኪሙ በአብዛኛው ደም አምጡ ይል ነበር፡፡ ነገር ግን በተለይም እናቶች በአጣዳፊ ሁኔታ በደም እጦት ሕይወታቸው ልታልፍ የምትችል በመሆኑ ከማንም በላይ ሐኪሙ ጉዳቱን ስለሚረዳ አሁን አሁን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጀመረው የሐኪሞች የደም መስጠት ልምድ እየዳበረ መጥቶአል፡፡ ስለዚህም እኛ ለተማሪዎቻችንም ይሁን ለህብረተሰቡ ምሳሌ ለመሆን የተቻለንን ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡ የእናቶችን ሕይወት ለማትረፍ ደም እየሰጠን እንገኛለን፡፡ ማንኛውም ሰውም በደም እጦት ሕይወቱ ማለፍ ስለሌለበት የምንሰጠው ደም ለመላው ተገልጋይ ይጠቅማል የሚል እምነት አለን፡፡
ደም የመለገስ ደንበኛ የሆነችው ሕይወት ታደለ እንደምትለው
“...በእርግጥ ለእኔ የደም መስጠት ምክንያት የሆኑኝ የሁለት ወላድ ሴቶች በደም መፍሰስ ምክንያት ሕይወታቸውን ማጣታቸው ነው፡፡ ነገር ግን እኔ ደም የምሰጠው ለእናቴ ወይንም ለአባቴ ለእህት ወንድሞቼ ወይንም ለእከሌ በማለት አይደለም፡፡ ደም የምሰጠው ለማንኛውም ሰው ነው፡፡ እኔ በምሰጠው ደም እናቶች ወይንም በመኪና አደጋ     የተጎዱ ወይንም ሌሎች ሰዎች ድነውበታል የሚል እምነት አለኝ። ልክ ደም ሰጥቼ ስወጣ አንድ ሕይወት እንዳዳንኩ ስለሚሰማኝ እጅግ ደስተኛ ነኝ፡፡”  
በኢትዮጵያ ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር በተያያዘ ወደ 85% የሚሆን የእናቶች ሞት ሲኖር ምክንያቶቹም ጽንስ በማቋረጥ ምክንያት 32% የተራዘመ ምጥ 22% ደም መፍሰስ 10% እና የደም ግፊት 9% ኢንፌክሽን 12% ናቸው፡፡ ይህንን ችግር ለመከላከልም በኢትዮጵያ የጤና ሽፋኑን ለማዳረስ ብዙ ስራዎች በመሰራት ላይ ናቸው። 3.500 /የሚሆኑ የጤና ጣቢያዎች 130/ የሚደርሱ ሆስፒታሎች ወደ 90/ ሚሊዮን የሚሆን የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማዳን ተገቢውን ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። ህ/ሰቡ ካለበት ድረስ ዘልቀው የጤና አገልግሎቱን የሚያደርሱ (38‚000) የሚሆኑ የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች በስራ ላይ ናቸው፡፡
ሕይወት ታደለ እንደምትለው፡-
“...የደም ባንክ ደንበኛ በመሆኔ እስከአሁን በግሌ ለአባቴ እና ለእህቴ ደም ባስፈለገ ጊዜ ባንክ እንደአስቀመጥኩት ገንዘብ መዘዝ እያደረግሁ ተጠቅሜበታለሁ፡፡ በእርግጥ ልክ ገንዘብ ሲጎድል እንደሚሞላው ሁሉ እኔም ወደ ደም ባንክ ያወጣሁዋቸውን መልሼ ተክቼአለሁ፡፡ ማንኛውም ሰው ደም መስጠት ከባድ ነው ብሎ ማሰብ የለበትም። አንድ ሰው ደም ሲሰጥ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ በትክክል ወደነበረበት ቦታ የሚመለስ እና የሚጎድል አለመሆኑን መረዳት ይገባዋል፡፡
ደም መስጠት ባህል ሊሆን ይገባል። ምክንያቱም የሰዎችን ሕይወት ማትረፍ ነውና። የእናቶችን ሕይወት ቀላል ስጦታ በማድረግ ከማትረፍ በላይ የሚያስደስት ነገር የለም። ደም ለሰጪው በቀላሉ ሊተካው የሚችለው ነገር ሲሆን ለተቀባዩ ደግሞ ከባዱን እና መተኪያ የሌለውን ሕይወት ማትረፊያ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡”

Read 3629 times